>
4:46 pm - Wednesday January 26, 2022

የዶ/ር አብይ ፈተና...ፕሮፌሽናሊዝም የጎደለው የፀጥታ መዋቅር (ኢያስፔድ ተስፋዬ)

የዶ/ር አብይ ፈተና…ፕሮፌሽናሊዝም የጎደለው የፀጥታ መዋቅር
ኢያስፔድ ተስፋዬ
ወደፊት የአብይ መንግስትም ይመረጥ ወይም ሌላ አካልም ይመረጥ፤ ለሚመጣው ሁሉ ፈተና የሚሆነው የሃገሪቱ security apparatus ፕሮፌሽናል አለመሆን ነው።
የፈለገ ከፓለቲካ ወገንተኝነት ነፃ ቢሆን፤ በመርህ እና በህግ የሚመራ የህዝብ አገልጋይ ቢሆን ሊሰራ የተቀመጠበት ቦታ ላይ በወጉ ለመስራት የሚያስችል ትምህርት፣ እውቀት እና ልምድ ከሌለው አደጋ ነው።
ፓለቲካ ነክ በሆኑ የወንጀል ጉዳዮች ሰዎች ተጠርጥረው ሲታሰሩ እና ፓሊስ አሳማኝ ማስረጃ ማቅረብ ሳይችል ሲቀር ነገሩ ገኖ ይወጣል እንጂ ከተራ የስርቆት ወንጀል አንስቶ እስከ ነፍስ የማጥፋት ወንጀሎችን የሚፈፅሙ ወንጀለኞች ላይ የፓሊስ የመረጃ አሰባሰብ ስራ ብዙ አሳፋሪ ገመናዎች አሉት።
ይህን ሃሳብ የበለጠ እንዲያስረዳልኝ በ2007 ዓ.ም በአ.አ ፓሊስ ኮሚሽን ለተወሰኑ ቀናት ታስሬ በነበረበት ወቅት ያጋጠመኝን ገጠመኝ ላካፍላችሁ።
በቤት ሰብሮ ዘረፋ ተጠርጥሮ የታሰረ አንድ ወጣት እኔ ከነበርኩበት ክፍል ጅርባ ታስሮ ነበር። በፓሊስ በኩለ ዘርፈሃልና እመን የተባለባቸውን ወንጀሎች ባለማመኑ ከፍተኛ ድብደባ ይፈፀምበት ነበር…ድብደባው የመረረው ተጠርጣሪም ለምርመራ ከሄደበት ቢሮ ስለት ይዞ በመመለስ ሌሊቱን የእጁን ደም ስሮች እና አንገቱን ገዝግዞ ያድራል። በነጋታው ከክፍላችን ስንወጣ እሱ አልወጣም። ፓሊሶቹ እንዲወጣ ሊነግሩት ወደ ውስጥ ሲገቡ ክፍሉ ደም በደም ሆኖ ተጠርጣሪው ተዘርሯል። አምቡላንስ ተጠርቶ ተጠርጣሪው ወደ ሆስፒታል ከተወሰደ በኋላ የታሰርንባቸው ክፍሎች እያንዳንዳቸው ካሜራ የተገጠመላቸው ስለነበር ራሱ ላይ ነው ጉዳት ያደረሰው ወይስ ሌላ ሰው ነው የጎዳው የሚለውን ለማወቅ በቦታው የነበሩት ፓሊሶች የተቀረፀውን ቪዲዮ ወደ ኋላ አጠንጥነው ማየት ስላቃታቸው ካሜራውን ኢንስቶል ያደረጉት ቻይኖች ተጠርተው ወደኋላ እንዲያጠነጥኑላቸው አድርገዋል። እንግዲህ ወደ ኋላ ማጠንጠን የማይችል የፀጥታ ሃይል ተይዞ እንዴት ታላላቅ የሽብር ውጥኖች ሊመረመሩ እንደሆነ ይታያችሁ።
ታሪኩ በዚህ አያበቃም። ተጠርጣሪው ከተመለሰ በኋላም ድብደባው ተጠናክሮ ስለቀጠለበት በፓሊስ ከቀረቡለት ወንጀሎች መካከል 40ዎቹን መርጦ ያምናል።
ያልሰራውን ወንጀል ሲያምንላቸው ግን ፓሊሶቹ ያላስተዋሉት እሱ ስራዬ ብሎ ያደረገው ነገር ነበር። ተጠርጣሪው ለማመን የመረጣቸው ወንጀሎች በሙሉ የተፈፀሙት ከዚህ በፊት ተጠርጣሪው በሌላ ወንጀል ተፈርዶበት በማረሚያ ቤት በነበረበት ወራት የተፈፀሙ ናቸው። 🙂 እንግዲህ ጉዳዩ ፍርድቤት ሲደርስ የሚሆነውን አስቡት…..
.
የዛሬ 3 ሳምንት አካባቢ የኢትዮጵያን መንግስት ወክለው በአሜሪካ ሴኔት ውስጥ ንግግር ያደረጉት ልኡክ
“ባለፉት 27 አመታት ስልጣን ላይ የነበረው ገዢው ፓርቲ የሃገሪቱን ሴኪውሪቲ አፓራተስ የራሱ አገልጋዮች አድርጓቸው ስለነበር አሁን ያሉበት ሁኔታ እጅግ የተዳከመ እና በሃገሪቱ የተለያዩ ቦታዎች የሚነሱትን ሁከቶች ማስቀረት የሚችል ስላልሆነ የአሜሪካን እርዳታ ያስፈልገናል” ማለታቸውን በተለያዩ ሚዲያዎች ሰምተናል።
.
እውነታው ይኸው ነው…. በቤንሻንጉል በሻሸመኔ በወልዲያ በአዋሳ በወልቂጤ በአ.አ ሰኔ 16 …..ወዘተረፈ የተፈጠሩትን ሁኔታዎች ቀድሞ ማክሸፍ ይቅርና የተከሰተውን ነገር በቅጡ ማጣራት እና መመርመር እንኳን አልተቻለም።
.
ለሃጥአን ሊመጣ የሚገባው ዱላ ላፃድቃን ሲተርፍ ወንጀለኛው በነፃ ሲንሸራሸር ንፁሁ ሲታሰር ህዝብ ከመንግስት ጋር ያለው ልዩነት እየሰፋ ይሄዳል።
8 ወር በቀረው የአዲስ አበባ ምክርቤት የሟሟያ ምርጫንም የአብይ ድርጅት በፀጥታ ሃይሉ መዋቅር ጥፋት ብቻ በዝረራ ሊሸነፍ የሚችልበት እድል ሰፊ ነው።
ችግሩ በቀላሉ እና በቅርቡ የሚፈታም አይመስልም…. ለ2012ቱ ምርጫም የአብይ ስስ ብልት የሚሆነው ይኸው ፕሮፌሽናሊዝም የሚጎድለው የፀጥታ መዋቅር ነው።
.
በአ.አ  20ምናምን ሰው ሲገደል በቡራዩ በአንድ ሌሊት ያ ሁሉ ዘግናኝ ወንጀል ሲፈፀም የፀጥታ ሃይሉ ሊሳተፍ የቻለው በግድያና በእስሩ እንጂ ወንጀሉን ቀድሞ ሊደርስበት አልቻለም። ስህተትን በሌላ ስህተት እንዲሉ ወንጀለኞቹን ለመያዝ የተኬደበት መንገድ ደግሞ ራሱን ችሎ ወንጀል ሆኗል።
.
ዶ/ር አብይ የሃዋሳውን የኢህአዴግ ጉባኤ በድል ተወጥተው ከተመለሱ በቅድሚያ ሊያስተካክሉት የሚገባው ጉዳይ ይኸው ነው።
Filed in: Amharic