>
5:14 pm - Sunday April 20, 5332

ስርአቱ እንከን አልባ ዲሞክራሲ እንዲገነባለን የምናልም ከሆነ ህልማችንን እንመርምር!!! (ፋሲል የኔአለም)

ስርአቱ እንከን አልባ ዲሞክራሲ እንዲገነባለን የምናልም ከሆነ ህልማችንን እንመርምር!!!
ፋሲል የኔአለም
ዲሞክራሲ ህጻናት  እንደሚሰሩት የአሸዋ ቤት በአንድ ቀን ተገንብቶ የሚያልቅ ነገር አይደለም።  ዲሞክራሲን  ቀድማ የጀመረችው እንግሊዝ እንኳን ዛሬ ከደረሰችበት ደረጃ ለመድረስ  ከ200 ዓመት በላይ ወስዶባታል፤ አሜሪካም ተመሳሳይ አመታትን አሳልፋለች። የአብይ መንግስት እንከን አልባ ዲሞክራሲ (perfect democracy) እንዲገነባለን የምናልም ከሆነ ህልማችንን እንመርምር፤ ለነገሩ እንከን አልባ የሚባል ዲሞክራሲ የለም፣ አይኖርምም። የአብይ መንግስት ለዲሞክራሲ መዳበር የሚጠቅሙ መሰረታዊ የሚባሉትን ተቋማት ከገነባልን ታሪክ ከሰሩ ታላላቅ የኢትዮጵያ መሪዎች ተርታ ይመደባል። የተቋማት ግንባታ እንደ መጻፍና መናገር ቀላል አይደለም፤ ብዙ ትዕግስት፣ እውቀትና ጥበብ የሚጠይቅ ፈታኝ ስራ ነው።  አሁን በየቦታው የምናያቸው መንገራገጮች የዲሞክራሲ ግንባታ ምን ያክል ፈታኝ እንደሆነ የሚያሳዩ ናቸው። እነዚህን ችግሮች አልፈን ለውጤት ከበቃን የዚህ ትውልድ ታሪክ በደማቅ ቀለም ተጽፎ ይቀመጣል። እየተደማማጡ መነጋገር ካልተቻለ ወይም ሁሉም በራሱ ሙዚቃ ብቻ መደነስ የሚፈልግ ከሆነ የዲሞክራሲ ግንባታ ህልም ሆኖ ይቀራል።  ከሁሉም በላይ የዲሞክራሲ ግንባታውን እናግዛለን ብለው ወደ አገር ቤት የገቡ የፖለቲካ ድርጅቶች ይህንን ጉዳይ ጠንቅቀው ማወቅ አለባቸው። በተለይ ከያቅጣጫው ድንጋዮች የሚወረወርበት የአርበኞች ግንቦት7 ከማንም በላይ ስክነትን፣ ትዕግስትንና ጥበብን በማሳየት አርአያ መሆን አለበት። ድርጅቱ ከቀኝ ከግራ በሚወረወሩ ፍላጻዎች ሳይደናገጥ፣ ከአብይ መንግስት ጋር እየተመካከረ፣ ዲሞክራሲን በማዋለዱ ስራ ላይ መተባባር አለበት። ድርጅቱ አሁን ካጋጠመው በላይ ትዕግስት የሚፈታተኑ ፈተናዎች ሊያጋጥሙት ይችላሉ። እነዚህን ፈተናዎች መወጣት የሚቻለው ዜጎችን በማንቃትና በማደራጀት እንዲሁም ተመሳሳይ ራዕይ ከያዙት ከእነ አብይ ጋር እየተመካከረ መስራት ሲችል ነው።
 በድርጅቱ ላይ ከያቅጣጫው የሚወረወረው ፍላጻ ዋና አላማ በአብይ መንግስትና በግንቦት7ት መካከል ስንጥር መክተት ነው። ግንቦት7ን በመምታት የ አብይን መንግስት መምታት ወይም የአብይን መንግስት በመምታት ግንቦት7ትን መምታት የሚል ስትራቴጂ የሚከተሉ ሃይሎች እንዳሉ ገሃድ እየወጣ ነው። በትዕግስት፣ በጥበብና በብልጠት ከተሰራ የእነዚህ ሃይሎች እድሜ ከጠዋት ጤዛ እድሜ አያልፍም። የድርጅቱ አመራሮች ከዚህ በፊት ሲከተሉት እንደነበረው በጎን የሚሰነዘሩ ትችቶችን በመመለስ ጊዜን ባለማጥፋት አባሎቻቸውን በማንቃትና በማደራጀት እንዲሁም ለአብይ መንግስት የሃሳብና ሌሎችንም ድጋፎች በማድረግ በአገራችን የምንመኘው የዲሞክራሲ ተቋማት ግንባታ እውን እንዲሆን መጣር አለባቸው።
አንዳንድ የድርጅት አመራር ነን የሚሉ ሰዎችም ከእንግዲህ ወዲያ እስከዛሬ በመጡበት መንገድ እንዲጓዙ መፍቀድ ተገቢ አይደለም። የሚናገሩትና የሚጽፉት በድርጅቱ ላይ ለሚወርደው ናዳ ምክንያት እየሆነ ስለሆነ ድርጅቱ በትዕግስት የሚያይበት ጊዜ ማብቃት አለበት።  ድርጅቱ ማንኛውም መግለጫ በህዝብ ግንኙነት በኩል መሰጠት አለበት የሚል መመሪያ ካወጣ በሁዋላ፣ መመሪያውን እየጣሱ  አስተያየት አይሉት መረጃ የሚሰጡ አባሎቻቸው ተው ሊባሉ ይገባዋል።  እነዚህ ከውጭ ወደ አገር ቤት የገቡ “መሪዎች”  ይህንን ድርጅት የሚጠቅሙ አይደሉምና ቶሎ ወደ መጠቡት ቦታ ቢመለሱ ድርጅቱ ያተርፋል እንጅ አይከስርም። በግንቦት7 ዙሪያ እንድጽፍ ያደረገኝ ድርጅቱ የያዘው ራዕይ ለኢትዮጵያ እጅግ ጠቃሚ ነው ብዬ ስለማስብ ብቻ ነው። አብይንም የምደግፈው በራዕዩ ነው።  የሁለቱ ድርጅቶች ራዕይ እውን የሚሆንባቸው ተቋማት ቢገነቡ ለኢትዮጵያ ትልቅ ጸጋን ይዞ እንደሚመጣ ስለማምንና ይህ ራዕይ የሚጨናገፍ መስሎ ሲታየኝ ዝም ማለት አልችልም። እውነት ለመናገር በተቃዋሚው ጎራ ያለው በሽታ በኢህአዴግ ጎራ ካለው በሽታ የሚተናነስ አይደለም፤ እንዲያውም አንዳንዴ ለውጡን እየመሩ ያሉ የኢህአዴግ መሪዎች በተቃዋሚው ጎራ ከተሰለፉት አንዳንድ “ራስ ወዳዶች” ተሽለው የተገኙበትን አጋጣሚ አስተውያለሁ።  እስካሁን በአካልም ሆነ በስልክ አግኝቼ ያነጋገርኳቸው የኢህአዴግ መሪዎች፣ በተለይ የብአዴን ከፍተኛ አመራሮች፣ ቃላቸውን አክብረው ዲሞክራሲ በክልሉ እውን እንዲሆን የሚያደርጉት ጥረት ለእነዚህ ሰዎች ያለኝ አክብሮት እንዲጨምር አድርጎታል። በተቃዋሚ ጎራ የተሰለፉ የተወሰኑ ራስ ወዳዶች በእነዚህ ሰዎች ቦታ ቢሆኑ ኑሮ ከእነሱ የተሻለ ስራ እንደማይሰሩ በጣም በእርግጠኝነት መናገር እችላለሁ። “ዲሞክራሲ ዲሞክራሲ” የሚለው ሁሉ የዲሞክራሲ ጠበቃ ይሆናል ማለት አይደለም፤ የዲሞክራሲን ንድፈ ሃሳብ በትምህርት ታገኘው ይሆናል ነገር ግን ዲሞክራሲን በኑሮህ ካላሳየኸው በትረካ ብቻ እውን አታደርገውም።
Filed in: Amharic