>
9:26 pm - Tuesday August 16, 2022

ይድረስ ለወሊሶ፡- “ህሊናዬ እርቃኑን ከሚቀር ቤት-አልባ መሆን እመርጣለሁ!” (ስዩም ተሾመ)

ይድረስ ለወሊሶ፡- “ህሊናዬ እርቃኑን ከሚቀር ቤት-አልባ መሆን እመርጣለሁ!”

ስዩም ተሾመ

በቻይና የነበረኝን የ21 ቀናት ቆይታ አጠናቅቄ እንሆ ዛሬ ወደ ሀገሬ ተመልሼያለሁ። በቀጣይ ቀናት ወደ ወሊሶ እሄዳለሁ። ወሊሶ ከ1998 ዓ.ም ጀምሮ የኖርኩባት ቤቴ ናት። ብዙ ነገር የጀመርኩባት፣ ብዙ ነገር የሰራሁባት፣ ብዙ ነገር የሆንኩባት ከተማ ናት። ከሦሶት ሳምንት ቆይታ በኋላ ወደ ወሊሶ ለመሄድ በመዘጋጀት ላይ እያለሁ አንድ ወዳጄ የሚከተለውን መልዕክት አደረሰኝ፡-

“ስማ… እኔም ከ40 ቀን ዕረፍት በኃላ ወሊሶ ትላንት መጣሁ፡፡ አይሩ አይነፋም፡፡ በጣም በጣም በጣም …በጣም ብዙ ሰው ተቀይሞኃል፡፡ ‘እንዴት ያስፈታውን፣ ቻይና የለከውን፣ እንዲታወቅ ያረገውን፣… አብይን ውረድ ይላል’ ብለው፡፡ በጣም ብዙ ሰው በአንድ ቀን ውስጥ ጠየቁኝ፡፡ ስሜታቸው ደስ አይልም፡፡ ብዙ ሰው አዝኖብሃል፡፡ እንደ ጠላትም ተቆጥረሃል፡፡ እኔ ስለማቅህ የወዳጅነት ምክሬ፤ 1.ይቅርታ ጠይቅ፣ 2.ያልክበት አመክንዮ (ዝርዝር ምክንያት አስረዳ)፣ 3. ናና ሚሆነውን ተጋፈጥ…. 4.በዛው ጣልያን ላሽ በል፣…”

ይህ ወዳጄ የወሊሶን ያህል ያውቀኛል። ከወሊሶ ጋር ያለን ወዳጅነት ለ12 ዓመታት ያህል የዘለቀ ቢሆንም ልክ እንደ ወዳጄ አታውቀኝም። ስለማታውቀኝ በሙሉ ልብ አታምነኝም። በተለይ ከ2008 ዓ.ም ጀምሮ ስለ ወሊሶ ነዋሪዎች፣ ስለ ኦሮሞ ህዝብ መብትና ነፃነት በድፍረት ስሟገት የሃሳብ ነፃነቴን በጥርጣሬ ዓይን ትመለከተው ነበር። ለዚህ ደግሞ በ2009 ዓ.ም ከጦላይ ስወጣ ነው የተገነዘብኩት። ብዙ ሰዎች “እኛ እኮ የወያኔ ሰላይ ትመስለን ነበር” በማለት በፀፀት ነግረውኛል። ይህን በተመለከተ “ያልተዘጋ እስር ቤት ውስጥ ነፃነት ያስፈራል” በሚል ርዕስ አንድ ፅሁፍ አውጥቼ ነበር።

ጦላይ ውስጥ ያ… ሁሉ መከራ ሲደርስብኝ ኦቦ ለማ መገርሳ የኦሮሚያ ክልል ፕረዜዳንት ነበረ። ከዚያ ሁሉ መከራ በኋላ “ተሃድሶ” የሚባለው ቀልድ መጠናቀቁን ተከትሎ በተዘጋጀው “የምርቃ ስነ-ስርዓት” ላይ ኦቦ ለማ መገርሳ በአካል ተገኝቶ ነበር። ከጦላይ እንደወጣሁ እነ ቲም ለማን ደግፌ በየመድረኩ ሽንጤን ገትሬ ስከራከር ነበር። በዚህ ምክንያት በ2010 ዓ.ም በታወጀው የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ማዕከላዊ እስር ቤት ገባሁ። ከማዕከላዊ እስር ቤት እንደ ወጣሁ በኋላ ደግሞ የሰኔ 16ቱ የድጋፍ ሰልፍ አስተባባሪ ኮሚቴ አባል እንደ ነበርኩ ይታወሳል።

ከሁለት ሳምንት በፊት በአዲስ አበባ ከተማና በዙሪያዋ የተከሰተውን ችግር አስመልክቶ “ዶ/ር አብይ ወይ ፍረድ ወይም ውረድ!” የሚል ፅሁፍ በመለጠፌ ምክንያት እንደ ጓደኛዬ አገላለፅ ወሊሶ ውስጥ “በጣም በጣም በጣም …በጣም ብዙ ሰው ተቀይሞኛል”። ከዚህ በተጨማሪ “እንዴት ከእስር ያስፈታውን፣ ቻይና የላከውን፣ እንዲታወቅ ያረገውን… አብይን ውረድ ይላል” በማለት ውለታ ቆጥረዋል። እኔ ግን በፍፁም ውለታ አልቆጥርም። ምክንያቱም ከላይ የተጠቀሱትን ነገሮች ያደረኩት የራሴን መብትና ነፃነት ለማስከበር ነው።

“የዜጎች መብትና ነፃነት ይከበር!” እያከልኩ የተሟገትኩት እኩልነትና ፍትህ እንዲረጋገጥ ነው። ይህም ቢሆን ከማንም በፊት ለእኔና ስለ እኔ ነው። በመጀመሪያ ደረጃ “የዜጎች መብትና ነፃነት ይከበር!” ማለት የሃሳብና አመለካከት ነፃነቴን በተግባር ማረጋገጥ ነው፣ ሲቀጥል የዜግነትና የሞራል ግዴታዬ ነው። የዜጎች እኩልነትና ፍትህ ካልተረጋገጠ ደግሞ የእኔ መብትና ነፃነት ትርጉም አልባ እና ፋይዳ-ቢስ ነው።

ስለዚህ የእኔ ዓላማና ግብ የእኔ መብትና ነፃነት ማስከበር፣ የዜጎች እኩልነትና ፍትህ እንዲረጋገጥ አስተዋፅዖ ማበርከት ነው። ጠ/ሚ አብይ አህመድን ሆነ ፕ/ት ለማ መገርሳን የምደግፈው የዜጎችን መብትና ነፃነት እንዲያስከብሩ፣ እኩልነትና ፍትህን እንዲያረጋግጡ ነው። ባለፈው በቡራዩ ከተማ በተፈጠረው ችግር ምክንያት የዜጎች ህይወት ጠፍቷል። ይህን ተከትሎ በተለያዩ የአዲስ አበባ አከባቢዎች በተካሄደው የተቃውሞ ሰልፍ ላይ ዳግሞ የዜጎች ህይወት ጠፍቷል።

በዜጎች ህይወትና ንብረት ላይ ጉዳት ያደረሰው አካል ማንም ይሁን ማን ጠ/ሚ አብይ አህመድ ይህን የመከላከል ወይም በአስቸኳይ የማስቆም ግዴታና ኃላፊነት አለበት። ይህ ባለመሆኑ ምክንያት በዜጎች ህይወትና ንብረት ጉዳት ደርሷል። ይህ ሲሆን ደግሞ እኔ “ዶ/ር አብይ ወይ ፍረድ ወይም ውረድ!” የሚል ፅኁፍ በፌስቡክ ገፄ ላይ አውጥቼያለሁ። ምክንያቱም ዶ/ር አብይን የምደግፈው ዜጎችን በእኩል ዓይን አይቶ እንዲፈርድ ነው። ይህን ማድረግ የተሳነው ዕለት ከብዙዎች ቀድሜ እንደደገፍኩት ሁሉ ከብዙዎች ቀድሜ “ወይ ፍረድ አሊያም ውረድ” እለዋለሁ። በዚህ ምክንያት ወሊሶ ተቀይማኛለች!!

እውነት ለመናገር ወሊሶ ከተቀየመችኝ ብዙ እጥፍ ተቀይሜያታለሁ። የ12 አመት ቤቴ ከተቀየመችኝ በላይ እኔን አስቀይማኛለች!!! የታገልኩለት የሃሳብና አመለካከት ነፃነት ጥፋት ሆኖ ይቅርታ እንድጠይቅ ትሻለች። “ዜጎች በእኩል ዓይን ይታዩ፣ ፍትህ ይረጋገጥ!” ማለቴን ዶ/ር አብይን ከመጥላት ጋር አያይዛዋለች። በራሴ የሆንኩት፣ በግሌ ያደረኩት ሁሉ “አብይ ወይ ፍረድ ወይም ውረድ” በሚለው ሰርዛዋለች። የሆንኩትን ትታ እንዳስመስል ትሻለች። ከእኔነቴ ይልቅ አስመሳይ እንድሆን ትፈልጋለች። እኔነቴን ከማጣት የመኖሪያ ቤቴን መልቀቅ እመርጣለሁ። የሞራል ሰብዕናዬ ተገፍፎ ህሊናዬ እርቃኑን ከሚቀር ቤት አልባ መሆን እመርጣለሁ!! በማስመሰል ቤተኛ ከመሆን ሃቅን ይዤ ስደተኛ መሆን እመርጣለሁ!!!

Seyoum Teshome | September 25, 2018
Filed in: Amharic