ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች- እንኳን ለብርሃነ መስቀሉ በሰላም አደረሳችሁ፤ አደረሰን!
ለዘመናት ተቀብሮ የኖረው የኢየሱስ ክርስቶስ መስቀል ከተጫነው ተራራ- ከተደበቀበት ስውር ስፍራ እና በክፋት ከተተወበት ምሽግ ጎራ ይወጣ ዘንድ በአማናዊ ደመራ- ሰማያዊ ምልክት የታየበትን ቀን ለምናከብርበት ለዚህ በዓል ለመላ የክርስትና እምነት ተከታይ ወገኖቼ የእንኳን አደረሳችሁ መልእክት ለማስተላለፍ በመቻሌ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ ስገልጽ ከተለየ አክብሮት እና ፍቅር ጋር ነው፡፡
ይህ ታላቅ እና ግሩም በአል በአልነቱ የክርስትያን ወገኖቻችን ቢሆንም ቅሉ ክብሩ እና ሀብትነቱ ግን የመላ ኢትዮጵያውያን ጸጋ ነው፡፡ በአለ መስቀል ከሀይማኖታዊ አስተምህሮቱ እና ከመንፈሳዊ እውነትነቱም ባሻገር የሚያስተምረን እና በውል እንድናስተውል የሚያስገድደን ሌላም ቁም ነገር ነገር አለው፡፡
እውነት የቱንም ያህል ዘመን፣ በምንም ያህል ውሸትና ቅጥፈት- ተንኮልና ሤራ፣ በየትኛውም ስልጣን እና ክፋት ብትሸፈንም በዘላቂነት ልትቀበር እንደማትችል አይነተኛ ማሳያ ነው፡፡ ለጥቂት ጊዜ ፀሐይን እንደሚሸፍን ደመና እውነትን ለተወሰነ ጊዜ መከለል፣ ውሸትንም እውነት ማስመሰል ይቻል ይሆናል፡፡ በመጨረሻ ግን እውነት እንደምታሸንፍና ከተቀበረችበትም ወጥታ ቀባሪዎቿን እንደምታሳፍር ለማስረዳት የክርስቶስ መስቀል ታሪክ ግሩም ማስረገጫ ነው፡፡
ይህንን የከበራ ሥርዓት የሠሩልን ቀደምት አበውና እመውም እምር በሆነው የበአል ስርአታችን የመስቀሉን አስተርእዮ ሁለንተናዊ መልክ በቀጥታ የተረኩልን እና በጥበብም ያቆዩልን ቢሆንም በተራዛሚው ግን የማይታወቅ የተሰወረ፤ የማይገለጥ የተከደነ ነገር ለዘለአለም ሊኖር ያለመቻሉን መንፈሳዊ እና ሰዋዊ እውነት በድንቅ የበአል ክዋኔ ሂደት አቆይተውልናል፡፡
በዚህ ፍጹም አስገራሚ የከበራ ስርአት ውስጥም ለእውነት ብቻ እንድንቆም፡፡ ለጊዜያዊ ጥቅም ስንል እውነትን እንዳንቀብር፤ ሥልጣን አለን- ብንናገር እንሰማለን- ጊዜው የኛ ነው- ወዘተ በሚል ቀባሪ እና አደናጋሪ አተያይ እውነትን ብንቀብራት እንኳን እውነት ግን ያው እውነት ናትና ጊዜዋን ጠብቃ እንደምትወጣ ብቻ ሳይሆን በተለየ ክብር እና በድንቅ የመገለጥ ሚስጥር እንደምትነሳ እንድናስብ የሚያደርገንን ይሄንን ታሪክ በመሳጭ የከበራ ጥበብ አደረጅተው እዚህ አድርሰውልናል፡፡
ዛሬ ከምንም ነገር በላይ ለእውነት የምንቆምበት ጊዜ ላይ ነን፡፡ በዙሪያችን ብዙ የተሳሳቱ መረጃዎች፣ ስም ማጥፋቶች፣ የሐሰት ወሬዎች፣ አሳሳች አሉባልታዎች እና በስሜት የሚነዱ ማስመሰሎች በገፍ አሉ፡፡ እነዚህ ሁሉ ጊዜያዊ ግርግሮች ለጊዜያዊ መሸንገል እንጂ ለዘላቂ ድል መሰረት ሊሆኑ እንደማይችሉ የመስቀሉ ታሪክ ሁነኛ ምሳሌ ነው፡፡
ምንም ያህል ቢያብረቀርቁ በፍጹም ወርቅ እንዳልሆኑ መገንዘብ እና እውነተኛው ወርቅ ግን ጊዜውን ጠብቆ እንደሚወጣ ከመስቀሉ ታሪክ እንማር ዘንድ ይገባናል፡፡ እኛ ከጸናን፣ ካልተከፋፈልን፣ መድረሻችንን ካወቅን፣ ከበደል ሳይሆን ከፍትህ ካበርን እና ለሐሰተኞች ጆሮ ልቦናችንን ከነፈግን እውነት ብትቀበር እንኳን እንደ ታላቁ መስቀል ሁሉ ቢዘገይም ነጻ እናወጣታለን፤ነጻ ማውጣትም ብቻ ሳይሆን ሰማየ ሰማያት ደርሶ የመገኛ አቅጣጫ ብስራት ይዞ የተመለሰ ጭስ እንዳስገኘው ደመራ በአለም ፊት እናበራታለን- እናደምቃታለን፡፡
ይህ በዓል የደመራ በዓል ነው፡፡ የመደመር በዓል ነው ልንለውም እንችላለን፡፡ እያንዳንዱ እንጨት ተደምሮ ችቦ ይሠራል፡፡ እያንዳንዱ እንጨት ባንድ ሆኖ በታላቁ ደመራ ህልው መሆን ውስጥ የራሱን ድርሻ ይወጣል፡፡
እየተጨፈለቀ ሳይሆን ህብር በራሱ ብርሀን እየደመቀ፡፡ እየተዋጠ ሳይሆን የራሱን ብርሀን እየሰጠ፤ እየተጠፋፋ ሳይሆን አንዱ በአንዱ ውስጥ እየሰፋ፡፡ እየተደመረ- እየተጨመረ ታላቁን ደመራ በክብር ይደምራል፡፡
ደመራ ደመራ እንዲሆን አያንዳንዱ እንጨት- እያንዳንዱ ችቦ አንድ ላይ ሆኖ ለአንድ ዓላማ በጥበብ፣ በውበት እና በአንድነት መቆም አለበት፡፡ አንድ ሆኖ ተደምሮ እንዲቆምም አንዱ ከሌላው መያያዙ ግዴታ እንጂ ሲሻ ብቻ የሚሆን ውዴታ አይደለም፤ መያያዝ፣ ህብር መፍጠር አብሮ መቆም እና አብሮ ማብራት ለደመራ ባህሪው ሳይሆን ተፈጥሮው ነው፤ እኛም እንዲያ ነን- ደመራነት ነው የሚያምርብን- መደመራችን ነው የሚያበረታ የሚያቆመን፤ የሚያበራን፣ የሚያደምቀን እና የሚያሞቀን፡፡
የሺ ፍልጥ ማሠሪያው ልጥ እንደሚባለው እንጨቶቹ በልጥ እየተያያዙ አንድ ችቦ ሆነው ጸንተው ይቆማሉ፡፡ ይህ ማያያዣ ልጥ ሕጋችን፣ ሥርዓታችን፣ እሴቶቻችን፣ ለውጥ ፈላጊነታችን፣ መፈቃቀዳችንና መተባበራችን ናቸው፡፡
‹ለየብቻ እንወድቃለን፣ በጋራ እንቆማለን› ብለን ተደምረን አብረን መቆም አለብን፡፡ ችቦዎቹ ብቻቸውን ደመራን አይመሠርቱም፡፡ አንድ ላይ ሆነው በአንድ ዋልታ ዙሪያ መቆም አለባቸው፡፡ ይህ ዋልታ ኢትዮጵያዊነታችን ነው፡፡ ሁላችንም የምንቆምበትና የምንቆምለት ሀገራዊ እሴትና ማንነት፣ ሀገራዊ አንድነትና ሀገራዊ መንግሥት አለን፡፡ ያንን ለመፍጠር ነው ሁላችንም አንድ ላይ ተደምረን የምንቆመው፡፡
ሀገራችን ደመራ ናት፡፡ ሁላችንም አንድ ላይ ተደምረን የምንቆምላትና የምንቆምባት፡፡ ለአንድ ሀገራዊ ዓላማ የምንሰለፍባት፡፡ በየሠፈራችሁና በየአካባቢያችሁ ደመራውን ስትመለከቱ ሀገራችሁን አስቡ፡፡ ራሳችሁንም ከችቦዎች ውስጥ ፈልጉ፡፡ ችቦው እንዲቆም፣ ደመራውም እንዲጸና እኔ ምን አድርጌያለሁ ብላችሁም አስቡ፡፡ለአፍታም ራሳችሁን ጠይቁ፡፡
በባሕላችን ከመስቀል ወዲያ ክረምት፣ ረሐብና ችጋር የለም ይባላል፡፡ ክረምት የሚያመጣው ፈተና ከደመራ በኋላ ያልፋል ተብሎ ይታመናል፡፡ እኛ መከራን፣ ችጋርን፣ ጦርነትንና ግጭትን በበቂ ሁኔታ ቀምሰናቸዋል፡፡
አይናፍቁንም፤ አንመኛቸውም፡፡ አሁን እኛ ኢትዮጵያውያን እንደ ደመራው ሁሉ አንድ ሆነን ተደምረናልና ከዚህ በኋላ እነዚያ የእንባ ሰበቦቻችን አይቀጥሉም፡፡ እንዲቀጥሉም አንፈቅድም፡፡ አልሞት ባይ ተጋዳይ ሆነው ሊፍጨረጨሩ ይችላሉ፡፡ ይህም ከመስቀል በኋላ እንደሚመጣ ዝናብ ነው፡፡ ዝናቡም እያለቀ፤ ችግሩም እየነጠፈ ይሄዳል እንጂ እድሜ አይኖራቸውም፡፡ ይህ እውን እንዲሆን ግን ደመራውን በምንለኩሰበት ቅጽበት እንደ ሀገር እንደመር ዘንድ ሁላችንም የበኩላችንን ለማድረግ ቃልኪዳናችን እናጸና ዘንድ በፍጹም ትህትና እና አክብሮት ጥሪዬን አቀርባለሁ፡፡
መስቀል የአዲሱ እህል እሸት የሚበላበት ጊዜ ነው፡፡ ይህም ለአርሶ አደሩ ተሥፋ ነው፡፡ እናም አርሶ አደሩ ይህንን ተሥፋውን ማማ ሠርቶ ከአውሬ ይጠብቀዋል፡፡ እኛም የዴሞክራሲን፣ የፍቅርን፣ ይቅርታን፣ የመደመርንና የለውጥን ተሥፋ እየቀመስን ነውና ይህንን ተሥፋችንን የአንድነት ማማ ሠርተን ከአውሬዎች- ከአጥፊዎች ልንጠብቅ ይገባናል፡፡
እንደ ደመራው ተደምረን እንድናበራና ጨለማውን እንድንገፈው ጥሪዬን እያቀረብኩ፤ በድጋሚ መልካም የመስቀል በዓል እንዲሆንልን ከልብ እመኛለሁ፡፡ መልካም በአል!
ኢትዮጵያ በልጆቿ ጥረት ታፍራ፣ ተከብራና በልጽጋ ለዘላለም ትኑር!
ፈጣሪ ኢትዮጵያንና ህዝቦቿን አብዝቶ ይባርክ!
አመሰግናለሁ፡፡