>

የማንን ግዛት ማን ያስተዳድር? (በፈቃዱ ዘ ኃይሉ)

ነገሮችን አቃልሎ እና ሸንሽኖ ለመረዳት መሞከር ጠቃሚ የሚሆንበት አጋጣሚ ቢኖርም፥ ሁሌም ትክክለኛ ውጤት አያስገኝም። አገርን የሚያክል ትልቅ ፅንሰ-ሐሳብ በግለሰብ ርስት ዓይን  ለመረዳት መሞከርም ከዚህ ዓይነቱ አደገኛ ስህተቶች አንዱ ነው። በኢትዮጵያ ‘እከሌ የተባለው ግዛት የማን ነው?’ እና ‘እከሌ የተባለውን ግዛት ማን ያስተዳድር?’ የሚሉት ጥያቄዎች ዐውድ በጣም አሳፋሪ እና ‘ገና በዚህ ጉዳይ እንኳ መግባባት አልቻልንም እንዴ?’ በሚል ራሳችንን እንድንታዘብ የሚያደርግ የዘወትር ገጠመኝ ነው።
‘አዲስ አበባ የማነች?’ የሚለውን ጥያቄ ደጋግሞ መስማት አስደናቂ አይደለም። የቡድን ሥም እየጠሩ፣ ታሪክ እየደረደሩ የባለቤትነት ማስረጃ ለማምጣት የሚሞክሩትን ሰዎች መከራከሪያ ማድመጥም የከተማዋን ኅልውና ያክል አዲስ ነገር አይደለም። የዚህ ጽሑፍ መነሻም የምክትል ከንቲባዋን ሹመት ተከትሎ የዚህ ክርክር እንዳዲስ ማገርሸት ነው። አዲስ አበባ የማን ነች? እነማን ናቸው ሊያስተዳድሯት የሚገባቸው? መጀመሪያ ግን ኢትዮጵያ ራሷስ የማነች?
ኢትዮጵያ የማነች?
ቢያንስ ለዚህ ጽሑፍ ሲባል ኢትዮጵያ የምንላት ሕዝቧን፣ ግዛቷን፣ መንግሥቷን እና ሌሎች የዓለም መንግሥታት የሚቀበሉትን ሉዓላዊነቷን ነው። ሉዓላዊነት የአገር ፅንሰ-ሐሳብነት መገለጫ ነው። በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ላይ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች “የኢትዮጵያ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች፣ ሕዝቦች” ናቸው (አንቀፅ 8)። ይህ ማለት ‘ኢትዮጵያ የኦሮሞ፣ አማራ፣ ሶማሌ፣ ትግራዋይ፣ ወዘተ የጋራ ንብረት ናት’ የሚል ትርጉም ይሰጣል። ከላይ ሲታይ ‘ኢትዮጵያ የሁሉም ናት’ የሚል ጭብጥ ያለው ይመስላል። ነገር ግን በዚህ ብያኔ እያንዳንዱ ዜጋ የኢትዮጵያ ሉዓላዊ ሥልጣን ባለድርሻ መሆን አይችልም። ‘የኢትዮጵያ’ የሚባሉት ብሔሮች፣ ብሔረሰቦች እና ሕዝቦች አባል ያልሆነ የኢትዮጵያ ዜጋ የሉዓላዊ ሥልጣኑ ባለቤት መሆን አይችልም።
ነገሩን በቀላል ምሳሌ ለማስረዳት ያክል፥ ሕገ መንግሥቱ “የውጭ አገር ዜጎች የኢትዮጵያ ዜግነት ሊያገኙ ይችላሉ” ይላል(አንቀፅ 6)። እነዚህ የኢትዮጵያ ዜግነት የተሰጣቸው የሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤት ናቸው ወይስ አይደሉም? ባለቤት እንዲሆኑ አንዱ የኢትዮጵያ ብሔረሰብ አባል ሆነው ዜግነት መቀበል አለባቸው ማለት ነው። ይህ ደግሞ አያስኬድም፤ ምክንያቱም ሰዎች የኢትዮጵያ ዜግነትን ለመቀበል፥ የራሳቸውን የዘውግ ማንነት እንዲክዱ እና አዲስ እንዲቀበሉ ማስገደድ አይቻልም። በጥቅሉ ይህ ድክመቱ የኢትዮጵያን ሕገ መንግሥት ዜጎች ሁሉ የአገር ሉዓላዊ ባለቤትነት ዕኩል ድርሻ የሌላቸው በማድረግ አስገራሚ ገጽታ ያላብሰዋል። ይህ ችግር የተከሰተው ኢትዮጵያዊ ዜግነት የተመሠረተው በዜግነት መብቶች ሳይሆን በቡድን ማንነት መብቶች በመሆኑ ነው። ለዚህ ነው በዜግነት-ብሔርተኝነት (civic nationalism) የሚመራ ‘ኢትዮጵያዊነት’ መመሥረት ያልተቻለው። የሁሉም የተባለ ነገር የእያንዳንዱ የመሆን ዕድሉ አናሳ ነው። የእያንዳንዱ የሆነ ነገር ግን የሁሉም መሆን ይችላል።
‘ኢትዮጵያ የማናት?’ የሚለው ጥያቄ ‘የእንዳንዱ/ዷ ዜጎቿ’ የሚል መልስ እስከሚያገኝ ድረስ፥ የክልሎች፣ የክፍለ ክልሎች የማንነት ጥያቄም እንዲሁ አጥጋቢ መልስ አያገኝም። ምክንያቱም የአስተሳሰብ ናሙናው አንድ ዓይነት ነው። ችግሩ አንድ አገር ባለቤት ለመሆን የሚገባቸው እና የሚመጥኑ ጥቂት የማሕበረሰብ ክፍሎች ብቻ ናቸው ብሎ ከማሰብ የሚመነጭ ነው። በርግጥ አገራት የተገነቡት በረዥም የፖለቲካ ሒደት፣ በፍጭት እና ማመቻመች ነው። ይሁን እንጂ በተለይ በዚህ ትውልድ ላይ የሚገኙ ሰዎች አገሮቻቸውን በምርጫ አላገኙም፥ በአገረ መንግሥት ግንባታው ላይም አልተሳተፉም (እንደኤርትራ ያሉትን አዳዲስ አገራት ለጊዜው እንዘንጋቸው)። እናም በዓለም የተከፋፈሉት ድንበሮች ለሠላም እና ስርዓት (order) ሲባል ዕውቅና ተሰጥቷቸው ይኖራሉ እንጂ የአንድ አገር ዜግነት ለመሆን ዘር አይመረጥም፤ ይህ በየትኛውም ዓለም ዐቀፍ ሕግ ተቀባይነት የለውም። በሕግ አግባብ ዜጋ የሆኑ ሁሉ ደግሞ የአገር ሉዓላዊ ሥልጣን ባለቤቶች ናቸው። ይህ በኢትዮጵያ አልተከበረም፤ በሕግም፣ በአስተሳሰብም። ስለዚህ፣ በኢትዮጵያ ውስጥ በተከፋፈሉት አስተዳደራዊ ክልሎች እና ክልላዊ ሕገ መንግሥታትም ተመሳሳይ ችግሮች ይስተዋላሉ።
የክልል ሕገ መንግሥታት የክልሉ ‘መሥራቾች’ እና ‘ባለቤቶች’ የሚሏቸው ፅንሰ-ሐሳቦች አሏቸው። በሚያሳዝን ሁኔታ፣ ክልሎቹ ሲመሠረቱ እና ፌዴራል ስርዓቱ ሲዘረጋ ነዋሪ የነበሩ ዜጎች ሳይቀሩ የክልሎቹ ‘መሥራቾች’ ተብለው ባለመቆጠራቸው ምክንያት የዜግነት መብቶቻቸው እንኳን አልተከበሩላቸውም። ይልቁንም ‘መጤ’ በሚል ቃል እና ‘እንግዳ’ በሚል መጠሪያ ማሸማቀቅ እና ማሳደድ እንደሞያ ተይዟል። በየቦታው በርስት እና የተፈጥሮ ሀብት ግጭት የበረከተው ግጭት፣ ዜጎችን በሕጋዊ መንገድ ከሚኖሩበት ቀዬ የማፈናቀል ደዌ የተባባሰው፥ በከፊል ዜጎች የባለቤትነት ስሜት እና በከፊሎቹ የባይተዋርነት ስሜት ነው። አገርን ወይም ክፍለ አገርን የተወሰኑ ዜጎች ርስት አድርጎ የመቁጠር አባዜ ነው፥ እኔ ከእከሌ የበለጠ ባለቤት ነኝ የሚለው አስተሳሰብ በኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት እና በየክልሉ ሕገ መንግሥታት እንዲሁም በየግለሰቡ አእምሮ ውስጥ ተዘርቶ የበቀለው።
አዲስ አበባን እነማን ያስተዳድሯት? 
አዲሱን የአዲስ አበባ ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ (በሙሉ የከንቲባ ሥልጣን) መሾም ተከትሎ የአዲስ አበባ ባለቤት እና አስተዳዳሪ ጉዳይ የተለመደ ሙግት አገርሽቷል። በሚያሳዝን ሁኔታ ከጥቂት የሕጋዊ አግባብነት እና የቅቡልነት ጥያቄ ካነሱት ተቺዎች በስተቀር፥ ሹመቱን የተቃወሙትም ይሁኑ የደገፉት ከላይ በተጠቀሰው የአስተሳሰብ ደዌ ተነድተው ነው ማለት ይቻላል። በተለይም ደግሞ ምክትል ከንቲባው ‘ኦሮሞ ስለሆኑ ይገባቸዋል’ እና ‘ኦሮሞ ስለሆኑ አይገባቸውም’ የሚሉት ሁለቱም አንድ ዓይነት ስህተት ሠርተዋል።
በዚህ በኩል የአዲስ አበባን ነዋሪዎች ቁጥር በብሔር ሸንሽነው ‘አማራዎች ብዙ ነን፤ መምራት ያለብንም እኛው ነን’ ይላሉ። በወዲያ በኩል ደግሞ ‘የታሪክ ባለቤትነቱ የኦሮሞ ስለሆነ አስተዳደሩ የእኛ መሆን አለበት’ ይላሉ። እንደገና በዚያ በኩል ደግሞ ‘በታሪክ ከተባለማ ወደኋላ በተጓዝን ቁጥር የእኛ ነበር’ ይላሉ። በወዲያ በኩል ደግሞ ‘በሕገ መንግሥቱ እና በጂኦግራፊያዊ አቀማመጥ የእኛ ባለቤትነት ተረጋግጧል’ የሚል ክርክር ይመጣል። በዚህ ብቻ አይወሰንም፤ ‘አዲስ አበባ ተወልደው ባደጉ ‘ልጆቿ’ መመራት አለበት’ የሚሉ አሉ። በባለቤትነት እና በአስተዳዳሪነት ይገባኛል ሽሚያ ውስጥ ሙያዊ ብቃት፣ የነዋሪው ምርጫ እና ይሁንታ ከቁብ አልተጻፈም፤ ብቸኛው ቁምነገር መወለድ ብቻ ይመስላል።
‘አዲስ አበባን እነማን ያስተዳድሯት?’ በሚለው ጥያቄ ውስጥ ቁም ነገሩ መወለድ ብቻ ተደርጎ መታሰብ ካልቀረ በቀር፥ የአዲስ አበባ ባለቤትነት ጥያቄም ማጨቃጨቁ አይቆምም። አዲስ አበባን የአዲስ አበባ ነዋሪ እስከሆኑ፣ የነዋሪዎቿን ቅቡልነት ባገኘ ምርጫ እስከተመረጡ ድረስ የቻይና ዘር ያለው የኢትዮጵያ ዜጋም ቢሆን፣ ቤንሻንጉል ጉሙዝ ወይም ሱማሊ ክልል ተወልዳ ያደገችና በኋላ የአዲስ አበባ ነዋሪም የሆነችም ብትሆን መምራት ትችላለች። በመወለድ የሚገኝ የማስተዳደር መብት የለም። እንዲህ ከሆነ የአዲስ አበባ ግዜያዊ ባለቤቶች በወቅቱ ነዋሪዎቿ ይሆናሉ።
‘ልዩ ጥቅም’ vs. ‘ባለቤትነት’
የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት አንቀፅ 49/5 «የኦሮምያ ክልል፤ የአገልግሎት አቅርቦት ወይም የተፈጥሮ ሀብትን አጠቃቀምንና የመሳሰሉት ጉዳዮችን በተመለከተ እንዲሁም አዲስ አበባ በኦሮሚያ ክልል መሐል የሚገኝ በመሆኑ የሚነሱ ሁለቱን የሚያስተሳስሩ አስተዳደራዊ ጉዳዮችን በተመለከተ ያለው ልዩ ጥቅም ይጠበቅለታል» ይላል። ይህንን በተሳሳተ መንገድ የሚረዱት ብዙ ናቸው።
ልዩ ጥቅሙ አዲስ አበባ በአንድ በኩል የመጠጥ ውኃ እና ሌሎችም ከአጎራባቿ የኦሮምያ ክልል አስተዳደራዊ አካባቢዎች የምታገኝ በመሆኑ፤ በሌላ በኩል ቆሻሻዎቿን የምታራግፍበት እና የበከለችውን ወንዝ የምታስወግድበት እና ሌሎችንም ጫናዎች የምታሳድርበት በመሆኑ ለጥቅሟና ጉዳቷ እንደክፍያ የሚሰጥ ጥቅም ነው እንጂ የልዩ ባለቤትነት ዐዋጅ አይደለም። ይህ ጉዳይ አዲስ አበባ የየትኛውም ክልላዊ አስተዳደር መሐል ብትገኝ ኖሮ ማድረግ የሚገባት ጉዳይ ነው። በርግጥ ልዩ ተጠቃሚዎቹ በአዲስ አበባ ዙሪያ ያሉት አካባቢዎች ናቸው መሆን የሚኖርባቸው። የሆነ ሆኖ ያ የሚደረገው በክልሉ አማካይነት ነው። ነገር ግን ኦሮምያ የኢትዮጵያ አካል መሆኗ ቀርቶ ነፃ መንግሥት ብትሆን እንኳን የአዲስ አበባ ጊዜያዊ ባለቤቶች ነዋሪዎቿ፣ አስተዳደሮቿም የነዋሪዎቿ ምርጫዎች ናቸው የሚሆኑት። ከዚያ ውጪ ያለው ሁሉ ሕጋዊ ቅቡልነት የለውም። በሕግ ቢደነገግም ፍትሐዊ ስለማይሆን ተቀባይነት አይኖረውም።
Filed in: Amharic