>
5:13 pm - Monday April 18, 6067

ተረፈ-ወያኔዎቹ ራሳቸውን ለሕዝብ አጋለጡ (ከይኄይስ እውነቱ)

ተረፈ-ወያኔዎቹ ራሳቸውን ለሕዝብ አጋለጡ

 

ከይኄይስ እውነቱ

 

ቀደም ባሉ አስተያየቶቼ እንደገለጽኩት ተረፈ-ወያኔዎቹ የምላቸው ባጭሩ የወያኔ ትግሬን አሠረ ፍኖት የሚከተሉ የተደራጁ ኃይሎችና እና ግለሰቦች ናቸው፡፡ በኦሮሞ ነገድ ስም በፖለቲካ የተሰባሰቡት 5ት ድርጅቶች በውጭም (አብዛኞቹ በውጭ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ ናቸው) ሆነ ባገር ውስጥ እንቅስቃሴአቸው ተረፈ-ወያኔዎች የሚለው ቃል በሚገባ ይገልጻቸዋል፡፡ ወያኔ ጠላት ብሎ የፈረጃቸው በሙሉ ለተረፈ-ወያኔዎቹም ጠላት ናቸው፡፡ አምስቱ ድርጅቶች  ሸንጎ ሰብስበው ክፉ መክረው፣ በሐሰት ትርክት አጅበው የሰሞኑን መግለጫ በጋራ ያወጡት ኢትዮጵያዊነትን አንኳስሰው ዘረኝነት ለማነጋገሥ አስበው ነበር፡፡ ይሁን እንጂ የመግለጫቸው ውጤት አይደለም የሠለጠነው ዓለም ውስጥ የኖረና ዴሞክራሲን በተግባር ያያ፤ አይደለም ፊደል የቆጠረና በ21ኛው መቶ ክ/ዘመን የሚኖር ሰው፤ አይደለም ዕድሜና የሕይወት ተሞክሮ ያበሰለውና ጊዜን የዋጀ ፖለቲከኛ፤ የድርጅቶቹንና መግለጫ የሰጡትን ኃላፊዎች መንደርተኛ ተርመጥማጭነታቸውን ገሃድ አውጥቷል፡፡ እነዚህ ጉዶች በሩቅም ስናውቃቸው በቅርብም ስናስተውላቸው ተመዝነው እጅግ ቀልለው የተገኙ ናቸው፡፡ የኦሮሞ ሕዝብ ደግሞ ሚዛን በማይደፉ አድሮ ቃሪያ በሆኑ አስመሳይ ፖለቲከኞች አይወከልም፡፡

በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራውን የኦሮሞ ሕዝብ የማይመጥኑ ማፈሪያ ድርጅቶች መሆናቸውን ሕዝብ አስቀድሞ የሚያውቅ ቢሆንም አሁን በግላጭ ራሳቸው ላይ መስክረዋል፡፡ በጥባጭ ሳለ ማን ጥሩ ይጠጣል እንደሚባለው ለሽብሩ የግብር አባታቸው ወያኔ ትግሬ በቂ ነበር፡፡ ተጠራርተው አገር የገቡት የሎንዶኑን ሸንጎና ዱለት በተግባር ለመፈጸም ከሆነ እርማቸውን ያውጡ እንጂ የኢትዮጵያ ሕዝብ ባጠቃላይ ኢትዮጵያዊው ኦሮሞ በተለይ አይፈቅድላቸውም፡፡ በርግጥ ላም አለኝ በሰማይ የሆነ ጉም ዘገን ተስፋ እየሰጡ እዚህም እዚያም በስሜት የሚነዱት መንጋ ተከታዮች ሊኖራቸው ይችል ይሆናል፡፡

የመግለጫዎቹ ነጥቦች ላይ ሌሎች ኢትዮጵያውያን ከውጭም ካገር ውስጥም ተችተዋል፤አስተያየት አቅርበውበታል፡፡ በጥቅሉ ለማለት የምፈልገው መግለጫው ሥጋት የወለደው ነው፡፡ ሥጋቱም በእነ አቶ ለማ ቡድን የሚቀነቀነው ኢትዮጵያዊነት፣ የዘር ፖለቲካ አጥፊነት እና ሕዝቡም በኢትዮጵያዊነትና አንድነት ዙሪያ መሰባሰቡ ነው፡፡ የፖለቲካ አመንዝራነት/የሥልጣን ሴሰኝነት እንዲህ ዕርቃንን ሲያስቀር እጅግ ያሳፍራል፡፡ የዘረኝነት ደዌ ፊደልን ደጋግመን ቆጥረናል ያሉትን ጭርሱኑ ሲያደድብ ከዕውቀትና አስተውሎት ሲያርቅ መመልከት በጣሙን ያማል፡፡ ለሕዝብና ለአገር መወሰድ ያለበትን ኃላፊነትን ሲያስዘነጋ፣ በማንአለብኝነት ሲያስፎክርና ሲያስዝት፣ በእኛ ፈቃድ ነው የምታድሩት ሲያስብል፣ ወክለናል ላሉት ሕዝብ በተለይም ለቅርብ ቤተሰቦቻቸው የሚያሸማቅቅ መግለጫ ነው፡፡ የመግለጫው ይዘት በራሱ ትላልቆቹን ነገዶች የማጋጨት ውጤት ያለው ሆኖ ሳለ፣ ይህንን አጥፊ ተግባር ለሌላ አሳልፎ መስጠት አዛኝ ቅቤ አንጓችነት ነው፡፡ በዚህ የተወላገደና አጥፊ ሃሳብ እንኳን ሕዝብና አገርን የራስን ድርጅት በአግባቡ መምራት ይቻላል? እነዚህ ወገኖች ኢትዮጵያን ብዙ ነገዶች በአንድነት እንደሚኖሩባት አገር፣ እነዚህም ነገዶች/ጎሣዎች በወል ስም ኢትዮጵያውያን ተብለው እንደሚጠሩ አምነው ከሆነ የመጡት፣ ወያኔ ትግሬ በቅርቡ የፈጠረውን ‹ኦሮሚያ› የሚባል ግዛት ብቸኛ ባለቤት ከመሆን አልፈው የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ ላይ ማን አዛዥ ናዛዥ እንዳደረጋቸው ፈጣሪ ይወቀው፡፡ ቅንነቱና ሆደ ሰፊነቱ ቢኖር፣ ኢትዮጵያ ለሁላችን የምትበቃ ግዛቶቿም የእገሌና የእገሌ ነገድ የግል ንብረት ሳይባሉ ሁላችንም እኩል ባለቤቶች መሆናችንን ባስተዋሉት ነበር፡፡ ማነው ባለአገር? ማነው መፃተኛው? ማነው ሠፋሪ? ማነው መጤ? እውነቱን ለመናገር የጊዜ ጉዳይ ካልሆነ በቀር ‹ሠፋሪ› ወይም ‹መጤ› ያልሆነ ማነው? ከዛሬ 500/600 ዓመታት በፊት ዛሬ ኦሮሚያ በሚባለው ግዛት የትኞቹ ነገዶች ይኖሩ ነበር? በአዲስ አበባስ? ዘመናቱን በሺዎች አድርገን እናስበው፡፡ ሙግቱ የቱ ጋር ያቆማል? ኧረ እያስተዋልን፡፡ ኧረ ለመጪው ትውልድ ለልጆቻችሁና ለልጅ ልጆቻችሁ አስቡ፡፡

ለመሆኑ እነ አቶ ዳውድ ወደአገር ቤት በገቡበት ዕለት ባደረጉት ንግግር ያነሷት ኢትዮጵያ ጋሼ መሥፍን ከኵተት እስከ ሽበት በአገር የ‹ኔታነት› በዕውቀት÷በማስተማር÷በመገሠፅ የማሰኑላት፣የሚበጃትን በማመልክት ወቀሳ÷ ከሰሳና ዘለፋ የተቀበሉላትን ኢትዮጵያ ነው? እነ አቶ ለማ እና ዶ/ር ዐቢይ ከፍ ከፍ ያደረጓትን፣ ከምንም በላይ ያከበሯትን፣ የኩራት ምንጭ ያደረጓትን፣ የብዙ ኅብረ ነገዶች አንድነት ማሠሪያ ማተብ ያደረጓትን፣ በመወለድ/በሕይወት አንቀልባ÷ በሞት/በኅልፈት ከፈን መግነዝ የሆነችውን ኢትዮጵያ ነው? ታማኝ የታመነላትን÷ አለኝታነቱን ያስመሰከረላትንና የሚያነባላትን ኢትዮጵያ ነው? ቴዲ አፍሮ ብትከሳ ብትጠቁር÷ብታጣ ብትነጣ ምትክ የሌላት ዘላለማዊ እናት ብሎ የዘመረላትን ኢትዮጵያ ነው? ህልውናዋ ጥፋቷ÷ ድህነት ጕስቁልናዋ÷ልማት ብልጽግናዋ÷ ውሎ አዳሯ ዕለት ዕለት የሚያሳሳቸው/የሚያሳስባቸው ኢትዮጵያውያን የሚያነሷትን ኢትዮጵያ ነው? ለስደተኛው ዘላለማዊ ስንቅ የሆነችውን ኢትዮጵያ ነው?  በፍጹም አይደለም፡፡

የዘር ፖለቲካ እንዲህ ቆሻሻና አዋራጅ ነው፡፡ ከሰውነት ተራ አውርዶ ጎሣ/ነገድ ለተባለ ግዑዝ ጣዖት ማደሪያ የሚያደርግ፣ ፊደል የቆጠሩትን ዓይነ ልቡና የሚያሳውር፣ ደናቁርትና ድንክዬ የሚያደርግ፡፡ ይህ ውርደት በሌሎች ነገዶች ስም የሚነግዱትን የዘር ፖለቲከኞች ኹሉ ይመለከታል፡፡ የአሁኑም ሆነ የመጪው ትውልድ ማፈሪያዎች ናቸው፡፡

በኢትዮጵያዊነቱ የሚኮራው ኦሮሞ ከቀረው ኢትዮጵያዊ ወንድሞቹና እህቶቹ ጋር በጋራ መሥዋዕትነት የከፈለው የጥላቻና መለያየት÷ ዓለም ኹሉ አንክሮ ለተፋው የዘረኝነት ፖለቲካ የሚሰብኩና የወያኔ ትግሬ  የግብር ባሪያዎች ለሆኑ ተረፈ-ወያኔዎች ለመገበር አይደለም፡፡

የኦሮሞ ሕዝብ ከሌሎች ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋር የወያኔ ትግሬ አገዛዝን ሲታገል የቆየው በስሙ በሚነግዱና በሥልጣን ፍትወት በሰከሩ ዘረኞች ተረኛ ጨቋኝና ዘራፊ ለመሆን ወይም ‹የኦሮሞ ወያኔ› ለመፍጠር አይደለም፡፡ ይልቁንም ከቀረው ኢትዮጵያዊ ወገኖቹ ጋር ቋንቋው÷ባህሉና ታሪኩ ተከብሮለት ለሁሉም እኩል የምትሆን፣ ዜጎች ኹሉ በፈለጉትና በመረጡት የኢትዮጵያ ክፍል በባለቤትነት÷ በነፃነት በመንቀሳቀስ ኑሮአቸውን መሥርተው በሰላምና በፍቅር ተሳስበው የሚኖሩባት ኢትዮጵያን በማይናወጽ የዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት መሠረት ላይ ለማቆም ነው፡፡

አስተያየቴን ከርእሴ ጋር ባልተያያዘ ለጠ/ሚር ዶ/ር ዐቢይ አንድ መልእክት በማስተላለፍ እቋጫለሁ፡፡

ጠ/ሚር ዐቢይ፤ የርስዎ የምርጫ መሠረት/አካባቢ (constituency) አንድ የተወሰነ የኢትዮጵያ ግዛት ሳይሆን መላዋ ኢትዮጵያ መሆኑን ዐውቀው አመራርዎን በዚህ መንፈስ ይቀጥሉ፡፡ እርስዎ የአንድ ነገድ ተወካይ አይደሉም፡፡ የአንድ ጎሣ ድርጅት ሊቀመንበርም አይደሉም፡፡ የማይምኑበትን ጉዳይ በስልታዊ ምክንያትም ቢሆን አያስታምሙ፡፡ ደጋግሞ እንደተነገረው የፖለቲካችን ሳንካዎች መካከል አንዱና ዋናው ቅንነት ማጣት ነው፡፡ የርስዎ ተቀባይነት አንዱ ምሥጢር ደግሞ  ቅንነት ነው፡፡ ይህንን መልካም ጠባይ ይዘው ይዝለቁ፡፡ በሁለት ልብ ከሚያነክሱ ጋር ሕዝብም ፈጣሪም አይተባበርም፡፡ የፍትሕ አስተዳደር የመንግሥት ዋናው ዓምድ መሆኑን አይዘንጉ፡፡ ያገርና ሕዝብ ህልውን የሚገዳደሩ አጥፊዎች ላይ የሥልጣን ሰይፍ ባግባቡ መምዘዝ ያለና የሚኖር ነው፡፡ ያለ ሕግ የፀና መንግሥት የለም፤ አይኖርምም፡፡ አገር ከማረጋጋቱ የቅድሚያ ተግባር ጎን ለጎን በፖሊሲ፣ በሕግ፣ በተቋማት፣ በመዋቅር ወዘተ የሚደረጉ መሠረታዊ ለውጦች ላይ ከምር በመሥራት ዴሞክራሲን ሕጋዊና ተቋማዊ መሠረት እንዲኖረው ማድረግ ያስፈልጋል፡፡ ስለሆነም በሕዝብዎ አምነውና ለሕዝቦ ታምነው ጅምር ለውጡን ከለውጡ ደጋፊ ኃይሎች ጋር ባንድነት ወደሚፈለገው ግብ ለማድረስ ይትጉ፡፡

ዓለም አቀፍ የፍትሕ ተምሳሌት የሆነችውን ‹‹እመቤት ፍትሕ›› (Lady Justice) አስተውለዋታል? ሴት የመሆኗ ምክንያት የመለኮታዊ ሕግና ሥርዓት፣ የተፈጥሮና ልማዳዊ ሕግ ሰዋዊ መገለጫ የነበረችው የሮማ አማልክት ጀስቲሻ (justitia) መነሻዋ ስለሆነች ነው፡፡ ከአድልዎ ነፃ ለመሆኗ (በሀብታም በደሀ፣ ጠንካራ ደካማ፣ ቅን ጠማማ መካከል ልዩነት ሳይደረግ) ምልክት ዓይኗ በመሐረብ ተሸፍኗል፤ ለሚዛናዊ ፍርድ (የከሳሽና የተከሳሽን ወይም በሙግት ተካፋይ የሆኑ ወገኖችን ታሪክ እኩል የመስማት) ተምሳሌትነት የሆኑትን የፍትሕ ሚዛኖች በአንድ እጇ፤ የሥልጣን (የምክንያታዊነት ሥልጣን፤ ሕግን የማስፈጸም ሥልጣን/ ሕግ የተላለፉትን የመቅጫ) ተምሳሌት የሆነውን በሀሉት በኩል የተሳለ ሰይፍ/ጎራዴ ደግሞ በሌላ እጇ ይዛለች፡፡ ሰይፉ ከፍትሕ በታች ሆኖ ሕግን ለማስከበር አስፈላጊ ነው፡፡

ስለሆነም ከፍትሕ በታች የሆነውን የሥልጣንን ሰይፍ በተገቢው ጊዜና ቦታ ሚዛናዊ በሆነ መልኩ መጠቀም አስፈላጊ ነው፡፡ ያም ጊዜ አሁን ይመስለኛል፡፡

 

Filed in: Amharic