>

ሀሳብ ታጥቆ የተነሳን ለማሸነፍ ሀሳብ እንጂ ሰይፍ መወርወር አያዋጣም!!! (መሳይ መኮንን)

ሀሳብ ታጥቆ የተነሳን ለማሸነፍ ሀሳብ እንጂ ሰይፍ መወርወር አያዋጣም!!!
መሳይ መኮንን
እነዚህ ኢትዮጵያን በምጸአቷ ቀን ደርሰው ከገደል አፋፍ የመለሷትና ተስፋን የሰጧት መሪዎች የብሄር ፖለቲካን አስታመው ወደ መቃብሩ እየሸኙት ነው!!!
የብሄር ፖለቲካ እያቃሰተ ይመስላል። ትንፋሹ ቁርጥ ..ቁርጥ ሲል ይሰማኛል:: በሞት መልዕክተኞች ተከቦ ወደመቃብሩ እያዘገመ ይታየኛል:: ከአዲስ አበባ እየተመለሱ ያሉ ሰዎች እንደሚነግሩኝ መሬት ላይ ያለው ዕውነት በዚህ መንደር ከሚናፈሰው የተለየ ነው። የብሄር ቡድኖች ጉልበታቸውን የሚያሳዩት በአብዛኛው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ ለመሆኑ የተለያዩ አስረጂ ምሳሌዎችን እየጠቀሱ አጫውተውኛል። መሬት ላይ ያለው ሀቅ በእጅጉን ይለያል። መሬት ላይ የብሄር ቡድኖች ሜዳ እየጠበበና እየኮሰመነ በአንጻሩ የዜግነት ፖለቲካ ስጋ ለብሶ በአሸናፊ ግርማ ሞገስ ብድግ ብሎ እየተነሳ ነው። የሰሞኑ የመግለጫ ጋጋታ፡ የጽንፈኛ አክቲቪስቶች እርግጫ የበረከተው ያለምክንያት አልነበረም። የብሄር ፖለቲካ አይንህ ለአፈር እየተባለ በመሆኑ ነው።
በእርግጥም የብሄር ፖለቲካ እንደዳይኖሰር ከምድር ገጽ ላይ መጥፋት የሚገባው ነው። እንደጋና ያሉ ሀገራት በህገመንግስታቸው ገደብ እስኪጥሉ የደረሱት መዘዙን ጠንቅቀው ስለተረዱት ነው። የብሄር ፖለቲካ ዩጎዝላቪያን ወደ ትንንሽ ሀገራት ለውጧታል። የብሄር ፖለቲካ አፍሪካን የሰው ልጅ የስቃይ ምድር ትሆን ዘንድ ፈርዶባታል። ምንም እንኳን አብዛኞቹ የአፍሪካ ሀገራት የብሄር ፖለቲካን እያጠፉ ቢሆንም የቅኝ ግዛት ዘመን ማክተምን ተከትሎ የአፍሪካ ነቀርሳ ሆኖ ከአንድ ክፍለዘመን በላይ ቆይቷል። በአፍሪካ የብሄር ፖለቲካ እየገነገነ ሊወጣት የደረሰው ኢትዮጵያን ብቻ መሆኑን የተለያዩ መረጃዎች ያመለክታሉ። በኢትዮጵያም ይሀው ኋላ ቀር የፖለቲካ መስመር የቁልቁለት ጉዞውን መጀመሩን ምልክቶችን ማየት ጀምረናል። እሰየው ነው።
የኦሮሞ ውድ ልጆች የሆኑት ለማ መገርሳና አብይ አህመድ ከኢትዮጵያ የተሻገረ፡ ፓን አፍሪካኒዝምን ያለመ ራዕይ ይዘው መነሳታቸው ለብሄር ፖለቲካ አቀንቃኞች ምቾት የሚሰጥ አልሆነም። እነዚህ ኢትዮጵያን በምጸአቷ ቀን ደርሰው ከገደል አፋፍ የመለሷትና ተስፋን የሰጧት መሪዎች የብሄር ፖለቲካን አስታመው ወደ መቃብሩ እየሸኙት ናቸው። በዜግነት ፖለቲካ ውስጥ የተየለያዩ ቡድኖችን መብት ማስጠበቅ እንደሚቻል የተረዱት የቲም ለማ አመራሮች ለኢትዮጵያ በትክክለኛው ዘመን ፈዋሽ የሆነውን መድሃኒት ቀምመው በፍቅርና ይቅርታ መርፌ መውጋት መጀመራቸውን ቀጥለዋል።
 ቀድሞውኑ የተፈወሱ ከእነዚህ መሪዎች ጎን ሆነው እያገዟቸው ነው። በሽታውና ልክፍቱ በደማቸው የሚዘዋወርባቸው በረድፍ  ተሰልፈው መርፌውን ይወጉ ዘንድ እድሉ ተሰጥቷቸዋል። የሚፈራገጥ አይጠፋም። መርፌው መርዝ የሚሆንበትም የትየለሌ ሊሆን ይችላል። ግን ምርጫ የለውም። ከነልክፍቱና በሽታው አብረው ተያይዘው ይጠፏታል እንጂ ከዚያ ያለፈ የሚያመጣው አንዳች ነገር የለም።
ዓለም ወደ አንድ መንደር እየገባች፡ በየሀገራት መሀል ያለው ድንበር እየደበዘዘ፡ አንድ የጋራ የመገበያያ ገንዘብ በየክፍለ አህጉሩ እየተፈጠረ፡ ከምስራቅ ጫፍ እስከ ምዕራብ ጸሀይ መጥለቂያ፡ ከሰሜን ዋልታ፡ እስከ ደቡብ የመሬት ንጣፍ ድረስ የዓለም ህዝብ ቤተሰብ እየሆነ በመጣበት 21ኛው ክፍለዘመን በብሄር ፖለቲካ የሰከሩ፡ ከመንደራቸው ጋጥ የዘለቀ ራዕይ ማየት የተሳናቸው፡ ሰፊዋን ዓለም በጠባቡ የጎጣቸው መሬት ልክ መመልከትን የመረጡ የፖለቲካ ነጋዴዎች ኢትዮጵያ ውስጥ በርክተው ይታያሉ።
ጥላቻን መፈክራቸው፡ ጽንፈኝነትን መስመራቸው፡ መበታተንን ግባቸው ያደረጉት እነዚህ የብሄር ፖለቲካ አቀንቃኞች የሚጋልቡትን ያህል ከኋላ አሰልፈው የሚችሉትን እየሞከሩ ለመሆናቸው ከሰሞኑ እየታዘብ ነው። የማህበራዊ ሚዲያዎች ደግሞ እንደፈለጋቸው የሚፈነጩበት ሰፊ ሜዳ በመሆኑ ጉልበት አቅማቸውን በማሳየት የመሬት ላይ ኪሳራቸውን ለመሸፈን በትጋት እየሰሩበት ነው። ከዚህ መደረክ ወርዶ መሬት ላይ ያለውን ሀቅ ለመረመረ ሰው እነዚህ በብዙ የሚጮሁት የብሄር አቀንቃኞች፡ ደካማ፡ አቅመ ቢስ፡ ትንንሽ ፍጡሮች ሆነው ይታዩታል። አይ ፌስቡክ?! ስንቱን ኮሳሳ አገዘፈብን ባካችሁ?!
ለማንኛውም የብሄር ፖለቲካ በገበያው ፈላጊ እያጣ ነው። አቀንቃኞቹ ከዚህም በላይ አብዝተው ቢጮሁ አትፍረዱባቸው። ውድቀትን በጩሀት ማስቀረት አይቻልም። ኢትዮጵያ ለሁሉም ትሆን ዘንድ ቤተመንግስት የገቡት መሪዎች ስራቸውን እየሰሩ ነው። በኢሳትም ሆነ በሌሎች የዜግነትን ፖለቲካ በሚያቀነቅኑ ሃይሎች ላይ ሰሞኑን የበረከተው እርግማንና የሰይፍ መዓት ያነጣጠረው አራት ኪሎ ቤተመንግስት በተቀመጡትና አፍሪካ ድረስ ራዕይ አንግበው በተነሱት ቁርጠኛ የህዝብ መሪዎች ላይ ነው።
የሰኔ 16ቱ ጥቃት የዚሁ የቀበጺ ተስፋ እርምጃቸው አንዱ አካል ነው። ከእንግዲህም ሊሞክሩ ይችላሉ። ግን አያሸንፉም። ሀሳብ ታጥቆ የተነሳን ለማሸነፍ ሀሳብ እንጂ ሰይፍ መወርወር አያዋጣም። ጊዜያዊ መንገጫገጭ ቢኖር እንኳን በዘላቂነት የአሸናፊነት አክሊሉን የሚደፋው የዜግነት ፖለቲካ መሆኑን ለመናገር ነቢይ መሆን አይጠይቅም።
Filed in: Amharic