>
2:48 am - Wednesday May 18, 2022

አስቸኳይ ጥሪ ለፖለቲከኞቻችን! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

አስቸኳይ ጥሪ ለፖለቲከኞቻችን!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው 
እባካቹህን እናንት ኖራቹህ የማትጠቅሙ ቀርታችሁም የማትጎዱ ፖለቲከኞቻችን ሆይ!  “ይሄ ጉዳይ በአስቸኳይ በገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን ተጣርቶ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ እንዲቀርቡ አድርጉ !” 
እባካቹህ ፖለቲካ (እምነተ አሥተዳደር) እናውቃለን ብለው “ፖለቲከኞች (እምነተ አሥተዳደራውያን) ነን!” ለሚሉና ፓርቲ (ቡድን) መሥርተው ለሚንቀሰቀሱ ነገር ግን ምን እንደሚሠሩ እንኳ ለማያውቁ ፖለቲከኞቻችን ይህችን መልእክት አድርሱልኝ???
ከኦነግ አመራሮች አቀባበል ጋር በተያያዘ በአዲስ አበባ፣ በቡራዩ፣ በአሸዋ ሜዳና በአዲስ አበባ ዙሪያ ባሉ ሌሎች ስፍራዎች ዘግናኝ አረመኔያዊ ጭፍጨፋና ሌሎች ችግሮች ተከስተው እንደነበረ ይታወሳል፡፡
ይሄንን ችግር ተከትሎም ፖሊስ (ጸጥታ አስከባሪ) “ፈቃድ ባልተሰጠው ሰልፍ ተሳትፋቹሃል!” በሚል ሕጋዊ ያልሆነ ምክንያት ሕገወጥ በሆነ መንገድ የአዲስ አበባን ወጣቶች በዘፈቀደ በጅምላ እያፈሰ ማሰሩ ይታወቃል፡፡
ይሄንን ሕገወጥ እርምጃ ተከትሎም ዓለም አቀፉ የሰብአዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ፖሊስ (የጸጥታ አስከባሪ) “መሣሪያ ሊነጥቁ ሲሉ እርምጃ ወሰድኩባቸው!” በማለት በጠራራ ፀሐይ አደባባይ ላይ የረሸናቸውን አምስት ንጹሐን የግፍ ሰለባ ወጣቶችን ጉዳይ ጨምሮ የቡራዩውን ፍጅት መንሥኤና ተያይዘው ያሉ ጉዳዮችን የሚያጣራ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን (ጀማ) በአስቸኳይ ተቋቁሞ እንዲያጣራው መጠየቁና ጥሪ ማድረጉ ይታወሳል፡፡
ይሁንና የዐቢይ አሥተዳደር ግን ጉዳዩ በገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን (ጀማ) እንዲጣራ ፈጽሞ ባለመፈለጉ የአምነስቲ ኢንተርናሽናልን ጥሪና ጥያቄ ሰምቶ እንዳልሰማ ዓይቶ እንዳላየ በመሆን ምንም ዓይነት ምላሽ  ሳይሰጥ አልፎታል፡፡ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን (ጀማ) ለማቋቋምም ያደረገው እንቅስቃሴ የለም፡፡
ያሳዘነኝና የገረመኝ ነገር ባዕዳኑ የእኛ ደኅንነት አስጨንቋቸውና የአገዛዙ እጅግ አደገኛ ሸፍጥና የፖለቲካ ቁማር በእጅጉ አሳስቧቸው እንዲህ ዓይነቱ አደገኛ የፖለቲካ ቁማር እንዲቆምና ተጠያቂ የሆኑ አካላት ተጠያቂ እንዲሆኑ ትኩረት ሰጥተው ሲሠሩ “ፖለቲካ እናውቃለን፣ የሕዝብና የሀገር ደኅንነትና ህልውና ጉዳይ ያሳስበናል!” ብለው የፖለቲካ ፓርቲ (የእምነተ አሥተዳደር ቡድን) መሥርተው ፖለቲካን ሥራቸው አድርገው የሚንቀሳቀሱት ወገኖቻችን ግን ይህ አገዛዙ ለራሱ የፖለቲካ ጥቅም ሲል ማለትም፦
* ሕዝቡ “ለውጥ መጥቷል ነጻነት አለ!” ብሎ ለመብቱ መከበርና መጠበቅ የሚያደርገውን ትግል ያለአንዳች ሥጋትና ፍርሐት በያገባኛል ስሜት በሙሉ የነጻነት ስሜት በንቃት እንዳይሳተፍ ለማቀብ፣
* ሕዝቡ “አሁንም የአገዛዙ ፈጽሞ ተጠያቂነት የሌለበትና ከሕግ በላይ የሆነ የግፍ ተግባሩ አለ ማለት ነው!” ብሎ እንዲያስብ በማድረግ ከቀደመው ፍርሐት ሳይወጣ እራሱን ከፖለቲካ እንዳገለለ እንዲቆይ ለማድረግና ከጥቂት ወራት በኋላ የሚደረገውን የአዲስ አበባ የምክር ቤትና ከንቲባ ምርጫን ሕዝቡ በፍርሐት እንደተሸበበ በፈለገው መልኩ መርቶ እራሱን አሸናፊ አድርጎ ለማውጣት ሲል በሕዝብ ላይ ሲፈጽመው የቆየውና አሁንም እየፈጸመ ያለው የተለመደ አረመኔያዊ ውንብድናንና የፖለቲካ ቁማርን እንደ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ሁሉ ፖለቲከኞቻችን በገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን (ጀማ) እንዲጣራ ሊጠይቁና ይህ እንዲሆን በተባበረ ድምፅ ጫና ሊያሳድሩ አልቻሉም፡፡
ግ7 እና ኦነግ ከጉዳዩ ጋር ስማቸው ስለተነሣ ብቻ ድርጊቱን አውግዘው “መንግሥት” ሲሉ የጠሩት አካል ጥቃቱን ባደረሱት አካላት ላይ እርምጃ እንዲወስድ ጠይቀዋል፡፡ ነገር ግን አገዛዙ እራሱ የችግሩ አካል መሆኑ በግልጽ ዕየታየ ባለበት ሁኔታ አገዛዙ እርምጃ እንዲወስድ መጠየቅ ማለት ምን ማለት ነው??? የአሸባሪው ኦነግ ነገር አይደለም የሚገርመኝ የግ7 ነኝ ባዩ ቡድን እንጅ፡፡
ሌሎቹ የተቀሩት “ለሕዝብ የቆምን የሕዝብ አገልጋይ ፖለቲከኛና የፖለቲካ ፓርቲ ነን!” ባይ ግለሰቦችና ቡድኖች ግን ይሄንን ያህል እጅግ አደገኛ ግፍና ሴራ በሕዝብ ላይ ተፈጽሞ በዓይናቸው በብረቱ ዕያዩና እየሰሙ አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጥሪውንና ማሳሰቢያውን ካቀረበ በኋላም ቢሆን እንኳ ጥሪውንና ማሳሰቢያውን በመደገፍ በአስቸኳይ ገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን (ጀማ) ተቋቁሞ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ሕግ ፊት እንዲቀርቡ አልጠየቁም፡፡ እንደዚህ ፈዘውና ደንዝዘው እንኳን ለሀገርና ለሕዝብ እንዴት ብለው ለራሳቸው እንኳ እንዴት እንደሚበቁ አላውቅም፡፡
በእውነት በእጅጉ አሳዛኝና ትዝብት ላይ የሚጥል ነገር ነው፡፡ ወያኔ ተገዶ ወይም ጫና ተደርጎበት ይሄንን እንዲያደርግ መደረጉ ምን ጥቅም እንዳለውና አለማድረጉ ደግሞ ምን ጉዳትና አደጋ እንዳለው በመዘናጋት ሳያስቡት ቀርተው ካልሆነ በስተቀር ወያኔ ጫና ተደርጎበት ይሄንን አለማድረጉ ቀጣዩን ጉዞ ዋስትና አልባ እንደሚያደርገውና አገዛዙ በቀጣይ ጊዜያትም ተመሳሳይ የውንብድና ተግባር እየፈጸመ፣ በሕዝብ ላይ አደጋና ግፍ እያደረሰ ፖለቲካዊ ጥቅሙን እንዲያስጠብቅ ዕድል መስጠትና ምቹ ሁኔታ መፍጠር ማለት እንደሆነ ሳይገባቸውና ሳይረዱ ስለቀሩ ከሆነ ጥሪውን ያላሰሙትና ጥያቄውን ያላቀረቡት በዚህ ደካማ የማሰብና የማገናዘብ ብቃታቸው ብዙ ኪሳራ በሀገርና ሕዝብ ላይ ከማድረሳቸው በፊት ሁሉንም ነገር ጣል እርግፍ አድርገው ፖለቲከኛ ነን ማለታቸውን ትተው አርፈው እቤታቸው ቢቀመጡልን መልካም ነው፡፡
እባካቹህን እናንት ኖራቹህ የማትጠቅሙ ባትኖሩ የማትጎዱ ፖለቲከኞቻችን ሆይ! አሁንም ቢሆን አልረፈደምና እባካቹህ “ይሄ ጉዳይ በአስቸኳይ በገለልተኛ አጣሪ ኮሚሽን ተጣርቶ ተጠያቂ የሆኑ አካላት ለፍርድ ሳይቀርቡ ከአገዛዙ  ጋር አብረን የምንሠራው ምንም ዓይነት ጉዳይ አይኖረንም!” የሚል የጸና አቋም በመያዝ ተረባርባቹህ ጥሪውን አቅርባቹህ በማስፈጸም ቀጣዩ ጊዜ አንጻራዊ የሆነ ዋስትና እንዲኖረው አስችሉ??? የዐቢይ አሥተዳደር “ይሄንን አላደርግም!” ካለ ደግሞ “አላደርግም!” በማለቱ አወናባጅነቱና የትወና ተግባሩ በአደባባይ እንዲጋለጥ አድርጉ???
ካልሆነ ግን የአገዛዙን ማንነት እያወቃቹህት እንዴት ብላቹህ ነው አገዛዙ እንደለመደው ያለተጠያቂነት እንደፈለገ የፖለቲካ ጥቅሙን የሚያስጠብቅበትን የውንብድና ተግባር እየፈጸመ፣ የፈለገውን እያደረገ ደኅንነታቹህ ተጠብቆ ከእሱ ጋር ተፎካክራቹህ አሸናፊ ልትሆኑ የምትችሉት??? እንዴት ነው ግን የምታስቡት??? ካልሆነላቹህ ምናለ ቦታውን ብትለቁና የሚችል ቢገባበት???
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic