አበጋዝ ወንድሙ
ቡራዩ የፈሰሰው የዜጎች ደምና ፣እንባ ሳይደርቅ ፣ በካማሽ ዞን የሚኖሩ በርካታ ዜጎች እንደተገደሉና እስከ 13ሺ የሚቆጠሩ አባወራዎች ወደ ምስራቅ ወለጋ ዞን መሰደዳቸውን እየሰማን ነው። ለዚህ እየለመድነው የመጣ ለሚመስለው የዜጎች በግፍ መገደልና ለስደት መዳረግ የአሁኑ ‘ገፊ ምክንያት‘ ደግሞ የአራት የካማሽ ዞን አመራር አባላት ላይ የደረሰው ግድያ ነው እየተባልን ነው።
የተለያዩ ዘገባዎች እንደዘገቡት፣የካማሽ ዞን አመራር አባላት በአሶሳ ከተማ፣ የቤንሻንጉልና የኦሮሚያ ክልሎች የጋራ ጸጥታ ጥምር ኮሚቴ ውይይት ላይ ተካፍለው ወደ ቀዬአቸው ሲመለሱ ፣ (የኦሮሚያ ክልል የኮሙኒኬሽን ኃላፊ አቶ አዲሱ እንደሚሉት ‘በኦነግ ስም በሚንቀሳቀሱ ታጣቂዎች ‘ ) ጊምቢ አካባቢ ተገድለዋል። ይሄንን ተከትሎ ነው እንግዲህ በካማሽ ዞን የተለየዩ ወረዳዎች ማንነት ላይ ያተኮረ ብጥብጥ ተነስቶ በርካቶች የተገደሉትና ሺዎች ቀዬአችወን ጥለው እንዲሰደዱ የተገደዱት።
በሀገራችን ባለፉት 27 አመታት ልዩነታችን ላይ እንጂ አንድነታችን ላይ ጠንክሮ ባለመሰራቱ (ምናልባትም ሆን ተብሎ) በተለያዩ አካባቢዎች የሚኖሩ ዜጎቻችን ማንነታቸውን መሰረት ያደረገ መጠነ ሰፊ ጥቃትና ስደት እንደደረሰባቸው ሁላችንም የምናውቀው እውነታ ነው።
ይሄ በሚሆንበትም ጊዜ መንግስት ሃላፊነት በተላበሰ መልኩ በመንቀሳቀስ ችግሩን ለመቅረፍ ያሳየው የነበረው ዳተኝነት፣ ተጠያቂነት የለም የሚል መንፈስ በሰዎች ላይና በአጠቃላይ በህብረተሰቡ ዘንድ በማሳደሩ፣ ችግሩ ይበልጥ ተባብሶ አንድ ሚሊዮን ፣ባብዛኛው የኦሮሞ ብሄረሰብ አባላትንና የሶማሌ ብሄረሰብ አባላትን ወዳፈናቀለ ሂደት እንዲሸጋገር መሄዱ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ከመሆኑም በላይ አሁንም ድረስ መፍትሄ ያልተገኘለት ጉዳይ ነው።
ወንበዴዎች አድፍጠው ሰው በገደሉ ወይንም በሌላ ምክንያት የኛ ወገን ተጎዳ በሚል፣ ወደ ህዝብ ለህዝብ ግጭት ተቀይሮ በጥቂት ሰዎች ሞት ሰበብ በርካቶች ሲሞቱና ሺዎች ሲሰደዱ ፣ የመንግስት ያለህ ፣ የህግ ያለህ ፣የወገን ያለህ ብለን ለመጮህ የምንገደደው ቢያንስ የህዝብን ጩሀት አደምጣለሁ የሚል የአመራር ቡድን ስልጣን በመያዙ ነውና ፣ከከዚህ ቀደሙ የተለየ ተግባራዊ እንቅስቃሴ እንጠብቃለን።እንዲህ ያለ ስደት በበዛበት፣ መረጋጋት በሌለበትና የዜጎች ህይወት እንደ ቅጠል እየተቀጠፈ ባለበት ወቅት ስለ ልማትና እድገት ወይንም ዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ማውራት የሚቻል አይደለምና ቅድሚያ ለሚሰጠው ቅድሚያ ይሰጥ።
በአሁኑ ሰዓት በሀገራችን በብዙ መቶ ሺ ከሚቆጠሩ የጎረቤት ሀገር ስደተኞች በተጨማሪ ፣ ከቀዬአቸው ተፈናቅለው በጊዜያዊ መጠለያ ኑሮአቸውን እንዲገፉ የተገደዱ ከ 1.5 ሚሊዮን በላይ ኢትዮጵያውያን መኖራቸውና ፣ ይሄ ቁጥር ደግሞ በየጊዜው አያሻቀበ መሄዱ ለሀገራችን ሰላምና መረጋጋት ትልቅ አደጋ ከመሆኑም በላይ የሀገር ህልውናንም ጥያቄ ውስጥ ሊያስገባ እንድሚችል በጊዜ ተገንዝበን መፍትሄ ልንፈልግለት የግድ ነው።
ከዚህ አንጻር ሁሉም ዜጋ ሃላፊነት ቢኖርበትም፣ ያንበሳው ድርሻ የመንግስት በመሆኑ፣ መንግስት ባጣዳፊና ያለምንም ማመንታት ቅድሚያ ሰጥቶ የጸጥታ ሃይሉን በማሰማራት ይሄንን የሚቆጣጠርበት ተግባር ውስጥ በግድ መግባት ይኖርበታል።
የዜጎች ሃላፊነት ደግሞ ጎራ ለይቶ መወነጃጀሉን በመተው ነገሮች ሊቀዛቀዙ የሚችሉበት ነገሮች ላይ በማተኮር ለወገን ደራሽነታቸውን ማሳየት ሊሆን ይገባል። ከየትኛውም ወገን ባሉ ሰዎች በንዴትም ሆነ በተበዳይነት ስሜት በመነሳት በየሶሻል ሚዲያው የሚጻፉ ጽሁፎች በመሬት ላይ ሲያስተጋቡ ሊያደርሱት የሚችሉት ጥፋት እጅግ ከፍተኛ መሆኑን በመገንዘብ ከእንዲህ ያለ አሉታዊ አቀጣጣይ ተግባር እንዲቆጠቡም ተማጽኖዬን አቀርባለሁ።