>

ጥንታዊዋን አገር ወደ ጥንታዊ ስርአት መመለስ (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

ጥንታዊዋን አገር ወደ ጥንታዊ ስርአት መመለስ

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ

(ኮተቤ  ሜትሮፖሊታን  ዩኒቨርስቲ)

አምስት የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ሰሞኑን የሰጡት መግለጫ በተለያዪ የመገናኛ ብዙኃን እንደተዘገበ ይታወቃል፡፡ በቀረበው መግለጫ ላይ አምስት መሰረታዊ ጉዳዮች የቀረቡ ሲሆን በኦሮሞ ብሄር ላይ የጥቃት ድርጊት ሊፈፀም እንደሆነ፤ አዲስ አበባ የኦሮምያ እነደሆነች፤ ኢሳት ፀረ-ኦሮሞ እነደ ሆነ፤ ለውጡን/የሽግግር ሂደቱን እና በቋንቋ ላይ የተመሰረተው የፊዴራል ስርአት ተገቢ እነደሆነ የሚዘረዝሩ ናቸው፡፡ የመጀመሪያዎቹ አራቱ ጉዳዮች መሰረተ-ቢስ(ተራ ውንጀላ) ሲሆኑ፤ ከእነረሱ ይልቅ ግን ለዛሬ ትኩረት የምሰጠው በመጨረሻው ጉዳይ ላይ ነው፡፡ የዘር ፖለቲካ ከህወሕት ስርአት ጋር አብሮ መክሰም አለበት ብየ ስለማምን በዚህ ጉዳይ ላይ የተሰነዘረው ሀሳብ ከሌሎች ጉዳዮች በላይ ገርሞኛል፡፡

ይህ መግለጫ በዚህ ስአት ለምን እንደተሰጠ ባይገባኝም፤ የተሰጠው መግለጫ በኢትዮጲያ ፖለቲካ ውስጥ ስም በላቸው ሰውች መሰጠቱ እጅጉን ገርሞኛል፡፡ የዘር ፖለቲካ በርካታ ችግሮች እንዳሉበት ከእኛ በላይ አስረጅ ያለ አይመስለኝም፡፡ ዳሩ ግን ለሀያ ሰባት አመት የኖርንበትን ችግር መረዳት ካልቻልን  በርካታ ተመራማሪዎች ያቀረቡትን የጥናት ውጤት ከብዙ በጥቂቱ የሚከተሉትን መቃኘት እንችላለን፡፡

የዘር ፖለቲካ (ethnic federalism) የውስጥ እና የውጭ፣ እኛ እና እነሱ፣ መጤ እና ነባር ነዋሪ፣ የሚሉትን አባባሎችን ስለሚያቀነቅን ተቀባይነት የለውም፤ የዘር ፖለቲካን የምታቀነቅን ብቸኛዋ አገርም ኢትዮጲያ ናት፡፡ እናንተን የሚያህል የፖለቲካ ተዋናኛ እንዴት ይህን የዘር ፖለቲካ ለማራመድ ታስባላችሁ፡፡ ከፈራረሰችው ዩጎዝላቨያ የተወረሰው የዘር ፖለቲካ ዜጎቸን ከመከፋፈል እና በጎሪጥ እንድንተያይ ከማድረግ ውጭ ምንም አልፈየደም፤ ሁኖም ግን ለህወሐት እድሜ ማራዘሚያ ታስቦ እንጅ የዘር ፖለቲካ አገር አንደሚያፈርስ ድሮውንም ይታወቅ ነበር፡፡ የዘር ፖለቲካ በብሄሮች መካከል ግጭትን እንደሚጋብዝ በበርካታ ተመራማሪዎች ተጠቅሳል፤ ለምሳሌ የሚከተሉትን ጥናቶች እንዳስረጅነት መመልከት ይቻላል (ለገሰ 2015፣ አብኪን 2006፣ ላንካስተር 2012፣ በቃሉ 2017፣ አሰፋ 2006፣ ኦክላነድ ኢንስቲትየት 2014፣ ኪያሚልክ 2014፣ ቪስታል 1999)፡፡

ከዚህ በተጨማሪም የዘር ፖለቲካ የአገርን አንድነት ያዳክማል፡፡ የህወሐት ስርአት አላማው በማኪያቬሌ የከፋፍለህ ግዛ ፖሊሲ  ታላቂቱን አገር መበታተን እንደነበር አሁንም የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ (ኢንተርናስሽናል ክራይስስ ግሩፕ 2009፣ መሃሪ ታደሰ 2004፣ ዊልያም 2004፣ ያንግ 2006፣ አላን 2002)፡፡ በዘር ፖለቲካ ውስጥ አንዱን እየደገፉ፣ አንዱን እያገለሉ መጓዝ አገሪቱን የጦርነት እና የግጭት ቀጠና ሊያደርጋት እንደሚችል ተመራማሪዎች አሁንም ገልፀዋል(ያንግ 2006)፡፡

የዘር ፖለቲካ ጥላቻን፣ መቃቃርን፣ አለመተማመንን፣ አለመረጋጋትን ያስከትላል፡፡ በናይጀሪያ ውስጥ ሰሜን ለሰሜኖች፣ ደቡብ ለደቡቦች የሚለው እሳቤ፤ እንዲሁም በህንድ ቦንቤ ውስጥ በስሜኖች እና በአናሳ ደቡቦች መካከል የነበረው ቅራኔ እና ግጭት የእኛ እና የእነርሱ ወይም መጤ እና ነባር ነዋሪ በሚለው አስተሳሰብ ዘየ ስለተቃኘ ነበር (አለማንተ 2003፣ በርማን 2010፣ ኪዩሚላካ 2006)፡፡

ከዚህ በተጨማሪ የዘር ፖለቲካ አስቸጋሪ የሚሆንበት በርካታ ምክንያቶች መካከል በኢትዮጲያ ውስጥ ለዘመናት በነበረው ነፃ የዜጎች እንቅስቃሴ ምክንያት የአንድ ብሄር ተናጋሪ በአንድ ቦታ የተገደበ እይደልም፡፡ በርካታ ቁጥር ያለው ኢትዮጲያውያን የራሱን ቋንቋ ከሚናገረው ማህበረሰብ ርቀው ነው የሚኖሩት፡፡ የዜጎችን  የብሄር ስብጥር ሳይሆን ተመሳሳይ ብሄርተኝነትን ስለሚያራምድ ዜግች የራሳቸው ቋንቋ ከሚነገርብት ማህበረሰብ በራቁ ቁጥር ዋስትና እንዳይሰማቸው ያደርጋል፡፡

የዘር ፖለቲካ እኛ እና እነሱ የሚለውን አመለካከት ስለሚያራምድ በዜጎች መካከል የተቃርኖ ስሜትን ስለሚያጭር የማህበረሰቡን ትስስር ያዛባል(ሂውስ 2010)፡፡ ከቀድሞዋ የሶቪዮት ህብረት፣ ከዮጎዝላቪያ፣ ከችጎዝላቫኪያ እንደምንማረው የሚቃረኑ ማህበረሰቦች በአንድ ላይ ሊኖሩ አይችሉም፡፡ ጥላቻን የሚያነሳሳ የጎሳ ፖለቲካ ደግሞ ለዘር ማፅዳት እና ለዘር ፍጅት በር እንደሚከፍት የዘርፉ ባለሙያዎች ያስረዳሉ(ሆልደር እና ባልደረቦቹ 2006)፡፡

የዘር ፖለቲካ  የራስ ብሄርተኝነትን ፍላጎት ብቻ  ስለሚያራምድ በዜጎች ላይ ምክንያታዊ አስተሳሰባቸውን ይጋርደዋል፡፡  ከዚህ በተጨማሪም የዘር ፖለቲካ ሰብአዊ አይደለም፤ ሰዎች በሚናገሩት ቋንቋ አማካኝነት አድልኦ ማድረግ ሰብአዊነት የጎደለው ተግባር ነው፡፡ አንድ የሚያደርገንን ሰብአዊነታችን/ሰው መሆናችን/ ትተን ሰው በሚናገረው ቋንቋ መሰረት መፈረጅ የሰው የመጨረሻው የውድቀት ምልክት ነው፡፡

አብዛኛውን ጊዜ የዘር ፖለቲካን የሚያቀነቅኑ ዜጎች ያነገቡት ሀሳብ የበላይነቱን ማሳየት  ሲሳናቸው የሚደበቁበት ምሸግ ይፈልጋሉ፤ ተስበውም በዘር ፖለቲካ ውስጥ ይገባሉ፡፡ አቅም አላባ የሆኑ እና በራሳቸው የማይተማመኑ ሰዎች የሚደገፉበት ምርኩዝ ነው፡፡ ስለዚህ በፖለቲካው ሜዳ ከተፎካካሪዎቸ ጋር በሀሳብ ተከራክሮ  የበላይነት ከማሳየት ይልቅ በዘር ፖለቲካ ውስጥ መሸሸግን ይፈልጋሉ፡፡

የዘር ፖለቲካ  የሰውን እና የካፒታልን እንቅስቃሴ ይገድባል፡፡ አክራሪ ብሄርተኝነት በሚቀነቀንበት አገር ዜጎች መዋለ ነዋያቸውን ለልማት እና ለአገር ግንባታ አያፈሱም፡፡ ከሁሉም በላይ ደግሞ በዘመነ  ግሎባላይዜሽን ይህን እሳቤ ማንገብ አግባብነት ያለው አይመስለኝም፡፡ የምንኖርበት አለም አንድ መንደር እየሆነች በመጣችበት ጊዜ ጥንታዊዋን አገር ወደ ጥንታዊ ስርአት መመለስ ዘመኑን የዋጀ አስተሳሰብ አይመስለኝም፡፡

References

Aalen, L. 2002. “Ethnic Federalism in a Dominant Party State: The Ethiopian Experience 1991-2000’’, Norway,  Michelsen Institute, Bergen,  2002.

Abbink, J. (2006). ‘’Ethnicity and conflict generation in Ethiopia: some problems and prospects of ethno-regional federalism’’ Journal of Contemporary African Studies 24,3:389 – 414.

Alemante, G. 2003. “Ethnic Federalism: Its Promise and Pitfalls for Africa”, Yale Journal of International Law, 28:51–107.

Assefa, F. 2006. ‘’Theory versus Practice in the Implementation of Ethiopia’s Ethnic Federalism’’, In Turton, D. (ed.)  Ethnic Federalism: The Ethiopian Experience in Comparative Perspective. Oxford,  Eastern African Studies,  James Currey Ltd 73Botley Road.

Bekalu Atnafu Taye (2017) Ethnic federalism and conflict in Ethiopia. African Journal on Conflict Resolution. Volume 17, Number 2, 2017

Berman, B. 2010. ‘’Ethnicity and Democracy in Africa. Ethnic Diversity and Economic Instability in Africa: Policies for Harmonious Development’’ Japan International Cooperation Agency Research Institute, 2010.

Holder, C.  Zeba Huq, Mary Catherine Ryan 2006. ‘’Early Warning in Ethiopia: Anaysis’’. In Rosenberg, S. and Miller, M.(eds.)  Human Rights & Genocide,  Clinic Cardozo School of Law International Crisis Group 2009. Ethiopia: Ethnic Federalism and its discontents, Africa Report N°153 – 4 September.

Legesse, T. 2015.Ethnic Federalism and Conflict in Ethiopia: What Lessons Can Other Jurisdictions Draw?’ Africa journal of International and Comparative Law. 23, 3 (, pp 462-475.

Kymlicka, W. 2006. ‘’Emerging Western Models of Multination Federation: Are they relevant for Africa’’? In Turton, D. (ed.) Ethnic Federalism: The Ethiopian Experience in Comparative Perspective. Oxford. Eastern African Studies. James Currey Ltd 73 Botley Road,

Lancaster, R. 2012. Federalism and Civil Conflict: The Missing Link? University of North Texas, unpublished MA thesis, 2012.

Mehari, T. 2004. Paper submitted in partial fulfillment of the requirements for the Degree of Master of Science by Coursework in Forced Migration at the University of Oxford. Refugee Studies Centre Queen Elizabeth House University of Oxford

Oakland Institute  2014. ‘Engineering Ethnic Conflict: the Toll of Ethiopia’s Plantation Development on the Suri People’< www.oaklandinstitute.org info@oaklandinstitute.org> (2014).

Vestal, T. 1999. Ethiopia: A post-cold war African State. Westport: Greenwood publishing Group Praeger.

William, I. 2004. ‘’Ethnicity, Ethnicism and Citizenship: A Philosophical Reflection on the African Experience’’, Journal of Social Science 8, 1, 45-58.  

Young, J. 2006. Peasant revolution in Ethiopia: The Tigray People’s Liberation Front, 1975-1991 Cambridge University Press, 2006.

Filed in: Amharic