>
11:03 pm - Tuesday August 16, 2022

የኦሮሞ ፖለቲካን እንዴት እንየው? አፍታትተን ስንመለከተው!!! (ናሁሰናይ በላይ)

የኦሮሞ ፖለቲካን እንዴት እንየው? አፍታትተን ስንመለከተው!!!
ናሁሰናይ በላይ
አሁን ፌዴራላዊ መንግስቱን መቆጣጠር የቻለዉ የኦሮሞ ኤሊት፡ የአጀንዳ ቀረፃና አካሄድ ስልት በቅድመ ድርጊት ታግዞ በመከወን የሚገለፅ “መሪነት” ነው፡፡ ሊደረግ የታሠበዉን ድርጊት ትንሽ ነው ለማስባል ከፍ ያለ አስደንጋጭ አጀንዳ ቀድሞ በመልቀቅ የተፈለገውን ሃሳብ ቅቡል የማድረግ ስልት ነው፡፡ ይህ አካሄድ ጥሩ መገለጫው “ለሠማዩ ወርውር፡ ጣሪያዉን እንድትመታ” አይነት ነው፡፡ለፌዴራላዊ መንግስት ቁጥጥሩ ከዚህ ቀደምቶቹ የኢትዮጵያ የፓለቲካ ኃይሎች አንፃር የተለየ ዉጣዉረድ ነበረበት ለማለት አይቻልም ፡፡ ስልጣኑን ለመቆጣጠር “ደም አፋሰንበታል” ቢሉም ስልጣን በደም ቅብብል በተለመደበት አገር የኦሮሞ ልሒቃን ሂደት ወጣትን አደራጅቶ ከማሳመፅ አልፎ እዚህ ግባ የሚባል አስተዋፅኦ አድርገናል ለማለት እሚያስችል ድፍረት አይኖራቸዉም።
በዋናነት ጉዳዩ በ17 ወታደራዊ ትግል ማዕከላዊ መንግስት የያዘዉን ህወሓት የመታገል በመሆኑ፡ የህወሓት ባላንጣዎችን የማሰባሰብ ወዳጅና ደጋፊን የማስወገድ ስልት ተግባራዊ የማድረግ ሂደት ነው ያለው፡፡ ከዚህ አኳያ ማዕከላዊ መንግስቱን ለመቆጣጠር የሚጠቀሙባቸው መንገዶች ብዙ ናቸዉ፡፡
#1) ብዐዴን የኃይል ሚዛን ፊትአዉራሪ
ይህ ብዐዴንን ተጠቅሞ (ህወሓትን የጋራ ባላንጣ በማድረግ) የስልጣን ዓላማን ማሳካት የዓላማዉ ቀዳሚ ስትራቴጂ ነው!
የኦህዴድና ብዐዴን ትብብር የመርህና ርዕዮተዓለምን መሠረት ያደረገ አጋርነት ሳይሆን በድፍን “የጋራ ጠላትን የመፋለም” ቁርኝት ነው፡፡ በዚህም ህወሓትን ከፌዴራላዊ መንግስት ቁጥጥር ውጭ የማድረግ ሂደቱን ማሳካት ነው፡፡ ከሞላ ጎደል ተሳክቷል ብለው ያስባሉ! እዚህ ላይ የእነ አብይ ግብ መንግስት መያዝ ነው የእነ ደመቀ ግን ህወሓትን ዞር ማድረግ ነዉ፡፡ የኦህዴድ ረጅም ግብ ነው፡ የብዐዴን አጭር ነዉ፡፡ይህ አጋርነት እንዲፀናም “ኦሮማራ” የሚል ፕሮጀክት ይፋ ሆነ፡፡ ብአዴን ከራሱ ስኬት ይልቅ የህወሓት ዉድቀት የሚያስደስተው ሳዲስት ፓርቲ እንዲሆን የለፉም አልጠፉም።
#ሀ, ‘ኦሮማራ’ የኃይል ሚዛን ማሳመሪያ 
በኦህዴድ የተያዘዉ የማዕከላዊ መንግሥት ስልጣን እስኪረጋና ሙሉ ቁጥጥር እስኪረጋገጥ ደግሞ ኦሮማራን መጠበቅና መንከባከብ ደግሞ በዋናነት የሰሜን አቢሲኒያ ጥንታዊ አጋር ህዝቦችን ‘ለመለያየት’ የሚረዳ እንዲሆን ተደርጎ ይቀነቀናል፡፡ ዳርዊን እንደሚለው ግዝያዊ ፀብ የሚበረታው በቅርብ ዘመዶች መሃከል ነው፤ ይህን የተረዳ ሰው በግዜው ባይኖርም። ጅምሩ ‘በጣና ኬኛ’ እንደገናም በለማ መገርሳ የባህርዳር ጉዞ ይፋ የሆነ ነው፡፡ ይህ ሞቶ ላጀበዉ አጋርነት ደግሞ ቀድሞ የተገነባው የፀረ ትግራይ ቅራኔ ትልቅ ድጋፍ ሆነ፡፡ ይህንን አጋርነት የሚገዳደር ምልክት የታየበት የአማራና ትግራይ የአገር ሽማግሌዎች ስብሰባን ተከትሎ የተሠጠዉ ምላሽ፡ ‘የኦሮማራን’ ተፈላጊነት ያሳየ ነበር፡፡
በመጀመሪያ በጎንደር ይካሄዳል የተባለ “የትግራይ እና አማራ ጉባኤ” ይፋ ሲደረግ በከፍተኛ ፍጥነት (በሶስት ቀን የድንገት ዝግጅት) “ለማ ባህርዳር ይጓዛል” የሚል ፕሮግራም ይፋ ሆነ፡፡ በ3 ቀን ጥናት ተሠራ ተብሎ ከአማራና ትግራይ ጉባኤ ቀድሞ “ኦሮማራ” ተቀነቀነ፡፡ ሳምንት ዘግይቶ የአማራና ትግራይ የአገር ሽማግሌዎች ጉባኤ በሚካሄድበት ቀን ደግሞ “የኦዳ አዉቶብስ ምረቃ ዝግጅት” በማቅረብ፡ ዶ/ር ነጋሶን ተጋባዥ በማድረግ ከአመራሩ ጋር በማሳየት ትኩረት ከጎንደር መድረክ ይልቅ በነነጋሶ መታደም እንዲሳብ ለማድረግ ተሠራ፡፡ ይህ ቁማር ኦሮምያ ኢኮኖሚክ ሪቮሊሽን ተብሎ የተወራለት ስሙም ጭምር ቶሎ የከሰመ ፓኬጅ አንድ አካል ነው።
ከዚያ ወዲህ በሚፈጠሩ አሳዛኝ ክስተቶች ሁሉ ተጠያቂነትን ለመሸሽ “የአማራና የኦሮሞን ህዝብ ለማጋጨት የፈለጉ ኃይሎች የፈጠሩት ነው” የሚል አሰልቺ ፕሮፖጋንዳ ይለቃሉ፡፡ አሁን በኢትዮጵያ ከዝናብ ወቅት በላይ ለማና አብይ የሚሰጡት መልስ በጣም ተገማች ከመሆኑ የተነሳ ህዝቡ በሆነ ጉዳይ ሊሉት የሚፈልጉት ነገር ቀድሞ እየገመተ ተቸግሯል። በተገኘዉ አጋጣሚ ሁሉ ይህ አግላይና ጊዜያዊ “የኦሮማራ” ጥበቃ ጠንክሮ የሚሠራበት ነው:: ለዚህ ሲባል የአንድ ወቅቱ የናረ አጀንዳ “የኦሮሚያ ከአዲስአበባ ልዩ ጥቅም” ከአጀንነት እንዲዘገይም ተደርጓል፡፡
#ለ, የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም አጀንዳን ማቆየት
አዲስአበባ በኦሮሚያ ክልል መሀል የምትገኝ ከመሆኗ ጋር በተያያዘ ከክልሉ ጋር ቁርኝት ይኖራታል፡፡ በተለይም ክልሉ ከከተማዉ የሚጠቀመዉ ጉዳይ መኖሩ እንዳለ ሆኖ ከተማው ግን ከክልሉ የሚጠቀመው የተፈጥሮ ሃብት መኖሩን የህገመንግስቱ ድንጋጌ ተገንዝቧል፡፡ ይህም በዋናነት በገበያ ዋጋ የሚመራው እንዳለ ሆኖ ከገበያም ውጭ የውሃ አቅርቦትና መሠል የተፈጥሮ ሃብቶች ምንጭ ኦሮሚያ ነው፡፡ ህገመንግስቱም ይህን ታሳቢ አድርጎ “..ከተፈጥሮ ሃብት አጠቃቀም ጋር በተያያዘ የኦሮሚያ ልዩ ጥቅም ይጠበቃል..ዝርዝሩም በህግ ይወሰናል” ይላል:: የኦሮሚያ ልሒቃን ግን ጉዳዩን ከተፈጥሮ ሃብትና ህገመንግስታዊ መንፈሱ በወጣ መንገድ የከተማውን ሉዓላዊ ስልጣን በሚጋፋ የማንነትና የባለቤትነት ጉዳይ አድርገው ረቂቅ አቀረቡ፡፡ ይህ በከተማው ሰፊ ህዝብ ያለዉን የአማራና ሌሎች ልሂቃንን አስቆጥቷል፡፡ ብአዴን ለኦሮማራ ሲል ባላየ ባልሰማ አልፎታል፤ ለዚህም ነው ከአማርው ሊህቅ ከሃዲ የሚል ስም የተለጠፈለት።
እናም በዚህ አጀንዳ ቸኩሎ መግፋት “የኦሮማራ” ትብብርን ስለሚያደናቅፍ የማቆየት ስልት ተነደፈ፡፡ ምክንያቱም ህወሓትን እስከመጨረሻው “ገድለህ” ስጋት የሌለበት ቁጥጥር እስኪረጋገጥ የኦሮማራ ትብብር የግድ መሠንበት አለበት፡፡ ለዚያ ነው ለማ “አውሬውን አቆሰልነው እንጂ ገና አልገደልነውም” ያለው ÷ አብይም ፅፎታል በሚባለዉ መፅሐፍ “ጠላትን እስከመጨረሻው እስክታሰናብተው ድረስ በብልሃት መንቀሳቀስ አለብህ” የሚለው። አሁን የትናንቱን የአማራና ትግራይ የምክክር መድረክ መጀመር፡ የአማራና ትግራይ የፖለቲካ ኃይሎች መቀራረብ መፍጠር ለኦሮሚያ ልሒቃን የጠራራ ፀሐይ መብረቅ ነው፡፡ ስለዚህም የኤርትራ ምክረሃሳብ ታክሎበት ትግራይና አማራ የትጥቅ ግጭት ውስጥ እንዲሞካከሩም ይፈለጋል፡፡ “የህወሓት ፍፃሜ እስኪረጋገጥ” ይቀጥላል፡፡ የኦህዴድ መንግስታዊ ቁጥጥሩን የሚያደናቅፈው የትግራይ እና የአማራ ፖለቲካ ኃይል ትብብር በመሆኑ ይህ እንዲፈጠር በፍፁም አይፈለግም፡፡ የዚህ ስጋት ምንጭ የሚሆን ተቆርቋሪነት ምናልባትም ከአማራው ወገን እንዳይመጣም ብሔርተኝነቱን ማለዘብ ይፈለጋል፡፡
#ሐ, የአማራ ብሔርተኝነትን ማለዘብ
ከምንግዜውም በላይ ገኖ የወጣው የአማራነት ሚናን ያነገበዉ የአማራ ብሔርተኝነት ከሞላጎደል የኦሮሞ ኤሊት የስጋት ምንጭ ነው፡፡ ኣብይ ኣህመድም ስጋቱን በይፋ ገልጿል፡፡ ከዚህ ኣንፃር ልሒቃኑን በማቀፍ ትብብር ያለው ብሔርተኝነት እንዳይሆንና “ለዉጡን” እንዳያደናቅፍ ብዐዴን የቤት ስራ ወስዷል፡፡ እንደነ ታማኝ ያሉ ግለሰቦችም “አማራው የሚያምርበት ኢትዮጵያዊነት ነው” የሚል ማደንዘዣ መርፌ ይዘው እንዲቀሰቅሱ የቤት ስራ ወስደዋል፡፡ ታማኝ ከግንቦት ሰባት እኩል ለኩል የአብይን ፀረ የአማራ ብሄርተኝነት አጀንዳ ለማራገብ ሽር ጉድ እያለ ነው።
 
2) ሌሎች አጋሮችን ማደራጀት
ፌዴራላዊ መንግስት ቁጥጥር ህወሓትን የሚቃወሙትን የማደራጀትና የመጠቀም ስራው እንዳለ ሆኖ በወዳጅነት የተፈረጁትን መለወጥና ማንሳት አንዱ ስልት ነው፡፡ ለዚህም የህወሓት ወዳጆች አንድ በአንድ ተነቅለዋል፡፡
#ሀ, ሶማሌ
በወሠን ደም አፋሳሽ ግጭት ከኦዴፓ ጋር ቅራኔ ውስጥ የነበረዉ የሶማሌ ክልል ከፍተኛ አመራር በወታደራዊ ጣልቃ ገብነት ጭምር በመብት ጥሰት ተከሶ እስር ቤት ገብቷል፡፡ ሙሉ ለሙሉ አፍቃሬ ኦህዴድ የሆነ፡ ህወሓትን በማብጠልጠል የሚታወቅ ኃይል ይዞታል፡፡ለአብይ ያለው ታማኝነት ያሳየዉም በመለስ ዜናዊ ስም ተሰይሞ የነበረው የክልሉ ሪፈራል ሆስፒታል ስም መቀየር፣ የክልሉ መዝሙር ሞቓዲሹ ነክ ወደሆነው የድሮ መዝሙር መቀየር እንዲሁም ታላቋን ሱማልያ ታሳቢ ወዳደረገው ባንዲራ መቀየር ነው። አብይ ሕገ መንግስትን ጥሶ በመፈንቅለ መንግስት የሾመው ሙስጠፋ ዑመር ሶማሊዎች “ብቸኛ ፀረ ትግራይ ዉለታ ቢስ ሶማሌ” ብለው ይጠሩታል።
#ለ, ደኢህዴን
በአፍቃሬ ህወሓትነት የተጠረጠረው የደኢህዴን አመራርም  ራሱ አብይ ጣልቃ ገብቶ በግጭት ለሰው እልቂት ምክንያት በመሆናችሁ ስልጣን ልቀቁ በማለቱ የድርጅቱና የክልሉ አመራር በሙሉ ተወግዷል ፡፡ በምትኩም የአብይ አህመድ ትዉልድ አካባቢ ጅማ ተወልዳለች፡ ካድሬነትም በኦህዴድ ዉስጥ የጀመረች ናት የምትባለው ሙፈሪያት ካሚል ተመርጣ “የቲም ለማ አባል” ተደረገች፡፡ የጅማዋ ልጅ ዙርያ አሁን የማናነሳው መዓት ጣጣ አለ። ስንት ደም የፈሰሰበትና የተፈናቀሉበት የኦሮሚያ አመራር ግን “በለውጥ አመራርነት” ይሞካሻል፡፡
#ሐ, ቀጣዮቹ ተረኞች
ቀጣዩ ሂደት በአፋር ፡ ቤኒሻንጉል እና ጋምቤላ “በህወሓት ነፃነታችንን አግኝተናል” የሚሉ ደጋፊዎች ፈንታ የአብይ ታዛዥ ለማስቀመጥ እየተሠራ ነው፡፡ አመራር ዝግጅትና ማፍረሻ እየተሠራ ነው፡፡
ሐ.1 አፋር
የአፋሩ ፕሬዚዳንት ሓጂ ስዩም ልክ እንደሌሎች በርካታ ብሄር ብሄረሰቦች የአፋር ህዝብ በህወሓት ትግል ለመጣው ለዉጥ ከፈተኛ አክብሮት ያለዉና በመርህ ደረጃ ከህወሓት ጋር የሚሰለፍ መሆኑ ግልፅ ነው። አብይ ሶማሊ ላይ በቀላሉ ያሳካው ወታደራዊ መፈንቅለ መንግስት አፋር ላይ ሊያደርገው አልቻለም። ባለፈው ወር አብይ እና የአፋር መንግስት ከፈተኛ ቅራኔ ዉስጥ ገብተዋል። አብይ ሓጂ ስዮምን “ሪፎርም አድርግ” ሲለው፣ ሓጂ ስዩምም “ሪፎርም ሁሌም ስናደርግ ነበር፣ አሁንም እያደረግን ነው፣ ማወቅ ከፈለግክ ግን ይሄው” ብሎ ክልሉ ለሁኔታው የሚሆነዉን ያካሄደውን ሪፎርም በማሳወቅ መልክ ላክ። ሆኖም አብይ የፈለገው የበራሕሌው ሓጂ ስዮም ትግራይን ስለሚያከብር በሌላ ፀረ ትግራይ መቀየር አለበት የሚለው ፍላጎት ነበርና እንደ ታማኝ ምንጮቼ አብይ ሓጂ ስዩምን “አሁኑኑ ብትወርድስ?” እንዳለዉና ሓጂ ስዩምም “የምሾመዉም የምወርደዉም በአፋር ህዝብና በፓርቲየ ዉሳኔ ነው፣ ስርዓቱ ፌዴራላዊ መሆኑ አትርሳ” እንዳለው ተገንዝብያለሁ። አሁን አብይ ወደ ኦሮምያ ከተጠጉ የአፋር አከባቢዎች ወጣቶችን በማነሳሳት ክልላዊ መፈንቅለ መንግስት ለማድረግ ከፍተኛ ኢንቨስትመንት እያደረገ ነው። አሁንም ዓላማው ትግራይ ያለ ወዳጅ ማስቀረትና ህወሓትን ማምበርከክ ነው።
ሐ.2 ቤንሻንጉል
መስከረም አስራ ስድስት አራት ከፍተኛ የክልሉ አመራሮች ተገድለዋል። እነዚህ ከፈተኛ አመራሮች በፌዴራላዊ ስርዓቱ የማይደራደሩና በአብይ እየተደረገ ያለው የጉልበት ጣልቃ ገብነት በግልፅና በጥብቅ የሚቃወሙ ሰዎች ነበሩ። የአብይ ምስል እንዳይሰቀል ያደረጉና አቋማቸዉን ለአብይ ጭምር በግልፅ ያሳወቁ፣ አብይ ፀረ ብዝሃነት ነው የሚል የጋራ አቋም የነበራቸው ሰዎች ናቸው፤ ልክ እንደ ፕሬዝዳንቱ። የክልሉ ፕሬዚዳንት ቀኝ እጅ የሚባሉ አራት አመራሮች “በኦነግ ሰራዊት በተደራጀ ሃይል ተገደሉ” ተባለ እንጂ ኦነግ እነዚህን የሚገድልበት ምክንያት የለዉም። ኦህዴድ በኦነግ ላይ ከወጠነው የስም ማጥፋት ዘመቻ አካል ነው። በተለመደ መንገድ የቤንሻንጉል ክልል መንግስት ለሕገ መንግስቱ ጠበቃና ለፌዴራል ስርዓቱ ዘብ መሆኑ ለአብይ አልተመቸም፤ የህወሓት አጋር ተደርጎ ስለታየ ከሚወገዱ ዝርዝር ዉስጥ የገባው ከ 4 ወራት በፊት ነው። አሁን በሆይሆይታና በሚድያ ግፊት አብይ ለራሱ የሚመች አሻንጉሊት ለማስቀመጥ ከጫፍ ደርሷል። የቤንሻንጉል ህዝብና ከፈተኛ አመራር ግን አራቱ የክልሉ ሟች አመራር ማን ሊገድለው እንደሚችል አዉቋል።
#3. ዋና አማካሪዎች: ኤርትራ and et al
የድህንነቱ ሰራተኛ የነበሩት ለማ እና አብይ በየሳምንቱ ከሻዕብያ ይሰነዘር የነበረው የሽብር ጥቃት እነሱን ጨምሮ የኢትዮጵያ የፀጥታ ክፍል ምን ያህል ዋጋ እንደከፈለ ያዉቁታል። አቶ ለማም ኤርትራ እየሰለጠነ ይመጣ የነበረዉን የኦነግ ሃይል ሳይሰለቻቸው በማሰር በአስር ሺዎች እስር ቤት በመዳጎን ይታወቃሉ። አሁን ነገር ሁሉ ተገልብጦ፣ ኢትዮጵያን ከሽብር አደጋ ሲከላከል የነበረው የፀጥታ አካል ወንጀለኛ፣ ፖሊስ በዳይ የሻዕብያ መንግስት ቁንጮ ኢሳያስ ካባ የሚደረብለት ጀግና ለመሆን በቃ። እዚህም ሌላ ስልት አልተጠቀሙም፤ ህወሓትን የሚጠላ ወዳጅ ሲሆን ህወሓትን የሚወድ ደግሞ ጠላት በሚል መርህ ነው ሂወታቸዉን ላገራቸው የሰጡ ተሳዳጅ፣ ፀረ ኢትዮጵያ ተወዳጅ የሆነው። ኢሳያስ “ወያኔ እኔ ነኝ የማዉቀው፣ ተንኮለኞች ናቸው። በትንሹ ለሃምሳ አመት ነው የሚያሰሉት። እናንተ ከምትረዱት በላይ ወያነ ዉስብስብ ነው፤ እኛን ያደቀቀን ወያነ ነው፤ ስለዚ እንዴት እንደምትይዝዋቸው ልምከራቹህ” እንዳለ ሙሉ ማስረጃ አለኝ። ኢሳያስ ቀጥታ ትእዛዝ እየሰጠ ዉሳኔዎች እያስወሰነ ስለመሆኑ አንዳንድ የምዕራባዉያን ዲፕሎማቶችን ራሱ ማስደንገጡ ይታወቃል። ኢሳያስ ከርቀት ሊበትናት ያልቻላትን ኢትዮጵያ በቅርብ ርቀት እየመራት ስለመሆኑ የሚጠራጠር የቅርብ ታዛቢ አይኖርም። ኤርትራ ዋነኛዋ የኢትዮጵያ ፖለቲካ መዘዉር ማእከል ሆናለች። ምናልባትም ከአራት ኪሎ በላይ።
 
4) ኢትዮጵያዊነትን በማቀንቀን መጠርጠርን መፋቅ
በቅርብ ጊዜ የኢትዮጵያ ታሪክ እነ ለማ በሄዱበት አሃዳዊነትና ህብረ ብሄራዊ ኢትዮጵያዊነትን አጀንዳ ያደረገ የኦሮሞ ኤሊት ወይንም ድርጅት አይታወቅም፡፡ ኦሮሞነትን በማቀንቀን የተሳከለትም የለም፡፡ እናም የለማና አብይ ቡድን ዛሬም ኦሮሞነትን ለብቻው በማቀንቀን ስህተትን አልደገሙም፡፡ እሱ የጓዳ አጀንዳ ነው፡፡
ይልቁንም “ኢትዮጵያዊነትን” በመስበክ ወትሮም በህወሓት ቅራኔ ውስጥ እንዳለ የሚሰማዉን “የዜጋ ብሔርተኛዉን” ስሜትና ቀልብ መቆጣጠር ነው፡፡ በዚህም በስደት የኖሩ ሁሉም ድርጅቶች፡ አንዳንዶች ከመቃብር ተቀስቅሰው አገራቸው መግባት ቻሉ፡፡ ማረፍያ (constituency) የሌለው የብሔር ፖለቲካ ተቃዋሚ ኃይል አብይ አህመድና ለማ መገርሳን “የኢትዮጵያ አምላክ” ያወረዳቸዉ ሙሴዎች አድርጎ ተመለከተ፡፡ ከ “ኢትዮጵያዊነት” አስተሳሰብ አኳያ እንደነሱ ጥብቅ “የዜጋ ብሔርተኛ” ከኦሮሞው ወገን በሌለበት፡ ሁለቱን የኦሮሞ መሪዎች አነገሰ፡፡ ለሰማዩ ወርዉር እንዲልም “ምስራቅ አፍሪካ አንድ ይሆናልም” አሉት፡፡ ሚስኪኑም ዋለለ።
እነሱም ይህን ስስ ብልት ቀድመው በመረዳት: የኖሩበትን አገር “ኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው” አሉ፡፡ አዳሜ ልቡ ተሠቀለ፡፡ ለአንዳንድ የብሔር ፖለቲካ ተቃዋሚዎችማ አብይና ለማ እልም ያሉ ብሔርተኞች ሆነው ሳለ የብሔር ፌደራሊዝሙን የሚያፈርሱበትን ቀን በመጠባበቅ አነገሳቸው፡፡ የጎጃም ሰው አልተገናኝቶም የሚለው አይነት ያለመናበብ ተፈጠረ።
“የዜጋ ብሔርተኛው” እነ አብይና ለማን የኢህአዴግ አባልነታቸው እስኪጠፋ ድረስ፡ የፌዴራል ስርዓቱ የፈረሰ እስኪመስል በህሊናው የሳለዉን አግላይ “ኢትዮጵያዊነትን” ተጋተ፡፡ ለዚህም የሠላምና የፍቅር አምባሳደር አደረጋቸው፡፡ ባልዋሉበት የአሃዳዊነት ወይንም ኢትዮጵያዊነት ሰባኪ መስለው ቀረቡ፡፡ የስልጣን ይገባናል መነሻዉ “ብዙ ነን: ኦሮሞ በልኩ ተጠቃሚ አልሆነም፡ ወዘተ..” እንዳልነበር “የኢትዮጵያዊነት” ጠበቃ ነን ትረካ ታወጀ፡፡ “ኦሮሞ አቃፊ ነው፡ እኛም የኢትዮጵያ ጠበቃ” ስለተባለ ምንም ቢከሰት ህወሓት ይወገድ እንጂ  ማንንም አያስወቅስም የሚል ያተፃፈ ህግ ነገሰ።
ስለዚህ ለ “አንድነት” ኃይሉ ኦሮሚያም ሆነ ኢትዮጵያ ላይ የፈለገው በደል ቢፈፀም እነ አብይን አይመለከትም፡ ኦሮሞን አይመለከትም ሆነ፡፡ “ቲም ለማም” ህቡዕ ማንነቱ የማይታወቅ ኃይልን ደጋግሞ በመዉቀስ ከደሙ ንፁህ ነን ማለትን ተለማመደው፡፡ አሻሚ ትርጉም በሚሰጡ ዉንጀላዎች ራሱን ለመደበቅ ብዙም ግዜና ገንዘብ አልፈጀበትም።
#ሀ) ኦሮሞን የሚመለከተዉ ምን ሲሆን ነው?
-የኦሮሚያ አመራር እየመራ በዚህ አገር ሰፊ የአደባባይ ግፍ ተፈፅሟል፡፡ ግፍ እናወግዛለን ባሉበት፡ የግፍ ምድር ማስተዳደር ጀመሩ ግን ሁሌም ባለቤቱ የማይታወቅ ኃይል ነው የሚወቀሰው፡፡ አመራሩን ይቅርና በቃ ኦሮሞን አይመለከትም እየተባለ የንፁሃን ደም ፈሰሰ፡፡ “የተደመረ” ነዉና እንደ አብዲ ኤሌ አይታሰርም ወይም እንደ ደሴ ዳልኬ አይባረርም፤ ዋናው “መደመር” ነው።
– በነቀምት በጠራራ ፀሐይ ሰው በሞላበት አደባባይ ሰው በድንጋይ ተቀጥቅጠቀ ሲገደል፡ ኦሮሞን አይመለከትም ። የወሊሶ ከንቲባ በልጁና በሚስቱ ፊት በሂወት እያለ ሲቃጠል እንኳን በክህደት ሌላ ጥፋተኛ ይፈለግለታል።
– በአወዳይ የሶማሊ ተወላጆች በአደባባይ ሲታረዱ ኦሮሞን አይመለከትም
– ምዕራብ ሐረርጌ ከፖሊስ ጣቢያ የተጠለሉ ከ60 በላይ ሶማሌዎች ታርደው ተቃጥለው ጉድጓድ ተጥለዉም ኦሮሞን አይመለከትም
– በሻሸመኔ በሰው ልጅታሪክ ሆኖ የማያዉቅ ህዝብ ተሰብሰቦ ለፍቶ አዳሪ ተዘቅዝቆ ተሰቅሎ እየተገደለ ኦሮሞን አይመለከትም
– በጉጂ ከ800ሺህ በላይ ጌዲዮ ተፈናቅሎ፡ ኦሮሞን  አይመለከትም
– በቡራዩ ንፁሀን የገጀራ እራት ሆነው ፡ ሺህዎች ዋና ከተማዉ አፍንጫ ላይ ተፈናቅለው  አሮሞን ወይንም ቄሮን አይመለከትም ፡፡ ግን ደግሞ የይቅርታ ቡድን ወደ ጋሞ ይላካል፡፡
– በአጭር ጊዜ ውስጥ ከነሶርያ ጋር የሚያስጠራ የውስጥ መፈናቀል ተከስቶ፡ የሚወራው ስላለፈው “የ27 ዓመት የጨለማ ጊዜ” እንጂ የነኣብይን አመራር አይመለከትም ፡፡
– በርካታ የትግራይ ልዋጭ እና መወልወያና መጥረግያ ሻጮች፣ የጉልትና የአነስተኛና የሆቴል ባለቤቶች፣ የመስኖ እርሻ ባለቤቶች ሲዘረፉ “የወምበዴ ድርጊት እንጂ ኦሮሞን አይወክልም” ተባለ።
– ስንት የአማራ አርሶአደሮች ሰብላቸው ተቃጥሎ ተፈናቅለው ጉዳዩ “ኦሮማራን ለማፈረስ የሚሰሩ ናቸው” እንጂ ኦሮሞን አይመለከትም፡፡ብአዴንም ከአማራው ደህንነት ይልቅ ስልጣን ይበልጥባታል እና ዝምታን መረጠች።
5) “ኦሮሞነት ከፖለቲካ አስተሳሰብ በላይ ነዉ!”
ልክ ነው ይበልጣል፡፡ የኦሮሞ ልሒቃን ከላይ እንዳልነው ከሞላ ጎደል ባለፈዉ መቶ ዓመታት ውስጥ “የኢትዮጵያዊነት” አቀንቃኝ ተብለው የሚፈረጁ አይደለም፡፡ ኦሮሞነት የፖለቲካ ኣስተሳሰባቸው ምሰሶ ነዉ ፡፡ የአንዳንዶች ትዝብት ግን እንዳዉም ከማንነት የተነሳ “ኦሮሞዉ ሁሉ ልክ ነው” በሚል የሚያንፀባርቁ እንዳሉ ይጠቅሳሉ፡፡ እናም ከፖለቲካ አስተሳሰብና ርዕዮተ ዓለም ይልቅ ብሔራዊ ማንነት መለኪያ ሆኖ ይስተዋላል፡፡ የፖለቲካ ድርጅቶቹ ልዩነቱም የአስተሳሰብ አይደለም፡፡
ለአብነትም ራሱ አቶ ለማ መገርሳ በፀጥታ አስተዳደር ኃላፊነት በነበረበት ወቅት በኦነግነት ሲያስራቸው የነበሩና ድርጅታዊ አባልነት ያልነበራቸዉን ለኦህዴድ በከፍተኛ አመራርነት መሾሙ፡ ድርጅቱም ወደ ከፍተኛ አመራርነት ያመጣቸው በፖለቲካ አስተሳሰብ መለኪያ ሳይሆን በኦሮሞነት መሆኑ ነዉ፡፡ አሁን ደግሞ በተለያየ ሁኔታ በውጭ አገር የነበረ የኦሮሞ የፖለቲካ ልሒቃን ወደ አገራቸው መጥተው ለመሰብሰብ ችለዋል፡፡ ሁሉንም ኦሮሞነት ያግባባቸዋል፡፡ ለነ ለማና አብይ ግን ጠንካራ የኦሮሞ አክራሪ ጠበቃዎች ወደ ህዝባቸው የተሰባሰቡበት ብቻ ሳይሆን ከእንግዲህ ወዲያ የየትኛውም ወገን ኤሊት የኦሮሞ አጀንዳ ዘዋሪ እንደማይሆን ማረጋገጫ ነው፡፡ አብይም ” ለኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች የስልጣን ወንበር ማካፈል፡ ሲያስፈልግም እስከመልቀቅ እንሄዳለን፡፡ ከጠላቶች ስር የሚርመጠመጡት ግን ከጠላት ለይተን አናያቸውም ::” በማለት በትግራይ የኦነግ አቀባበልን ትኩረት ያደረገ መልዕክት ሰጠ፡፡ ጠላት ሳይሆን ተፎካካሪ ብለን እንጥራቸው ያለዉን ሃሳብ በዜሮ አባዛው።  እናም “ሰብሰብ በሉ” ተብለው ከሁለትና ሶስት በላይ ፓርቲ መኖሩ እንደማይጠቅም “ተግባብተው” የነ በቀለ ገርባዉ ኦፌኮ ከኦነግ ለመቀላቀል ንግግር ጀምሯል፡፡ በፀብ ከኦነግ የተለየው የነሌንጮ ODF ፀቡን ትቶ በጋራ መግለጫ እስከመስጠት ሄዷል፡፡ አብይም በአንድ ወቅት በኦሮሞ ትግል የሚያደንቀው ኦነግን እንደሆነ ገልጿል ይባላል፡፡ ምክንያቱም ጉዳዩ ከፖለቲካ ሰልፍ በላይ ነው፡፡ Colonization የሰበከዉ ኦነግም ዛሬ መገንጠል ኣላልኩም ሲል ክዷል፡፡
ከኢትዮጵያ የአንድነትና ፍቅር ስብከቱ በፊት የነበረዉን ቅስቀሳና ንግግር ላስታወሰ ግን ዋናው አጀንዳ ኦሮሞን በልኩ የስልጣንና ጥቅም ባለቤት ማድረግ እንደሆነ ግልፅ ነው፡፡ የዚህ ማሳረጊያ የአዲስአበባ ባለቤትነት ማረጋገጥ መሆኑ ግን ግልፅ ነው፡፡ የዘገየዉ የልዩ ጥቅም አጀንዳም መደላድል ሲበጅለት የቆየ ነው፡፡
6. ሰፈራና ቤት ግንባታ
የአዲስአበባ ልዩ ጥቅም አጀንዳ ውይይት ፊት ከመምጣቱ በፊት እንዲዘገይ የተደረገው ኦሮማራን ለመጠበቅ ኣንዱ ጉዳይ ሆኖ፡ በቂ ዝግጅት ማድረግም ዋናው ስልት ነው፡፡ለዚህም በዋናነት የአዲስ አበባን ዲሞግራፊ ማናጋት ዋናው ስራ ነው፡፡ የኦሮሞ ከተማ የሚሆነው በኦሮሞ ቁጥጥር ስር መሆኑን በህዝቡ ሚናና ድርሻ ማረጋገጥ ሲቻል ነው፡፡ “ኦሮሞን በማፈናቀል በሌሎች ተይዛለች” ለምትባለው ከተማ የቁጭት መወጫው ኦሮሞው የላቀ ድርሻ መያዙ ሲረጋገጥ ነው፡፡ ለዚህ ነው የተቀናጀ ማስተር ፕላን ተቃውሞ የገጠመው፡፡ አቶ ኩማ እንዳለው ግን “ፕላኑ የሚመለስበት ወቅት አለ”፡፡ ለዚህ አንዱ ስራም በከተማው ዙሪያ ሰዎችን ማስፈር ነው፡፡ እናም በሶማሌ አዋሳኝ በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ 1 ሚሊዮን ኦሮሞዎች አሉ በሚል (በርግጥ ሶማሊ ውስጥ የሚኖረው ኦሮሞ በ 1999 ዓ.ም 20 ሺ 263 ሰው ነበር፣አሁን ተፈናቀለ የተባለው ቁጥር 1 ሚልየን ነው:: እንግዲህ በዚህ ዓመት እና መፈናቀል ደረሰ በተባለበት ግዜ ያለው አስራ አንድ አመት ነው። እናም ሃያ ሺ የነበረው የኦሮሞ ቁጥር በዓለም ታይቶ በማያዉቅ ሁኔታ በአስራ አንድ ዓመት ወደ አንድ ሚልየን ተጠጋ ማለት ነው።)  የተሰራው ስራ የማስፈር ፕሮግራም ነው፡፡
ይህ ከምስራቅ ኢትዮጵያ የተፈናቀሉትን በፊንፊኔ ዙሪያ የማስፈር ፕሮግራም ዓላማው የዲሞግራፊ ባላንስ ነው፡፡ ከምስራቅ ኦሮሚያ አንስቶ ፊንፊኔ ዙሪያ ማምጣት ግቡ መርዳት ብቻ አይደለም፡፡ በቢሊዮን ገንዘብ ተሰብስቦ (አሁንም ድረስ ቀጥሏል): በ12 ከተሞች በመቶ ሺህ ሰዎች ከምስራቅ ኦሮሚያ ቀያቸው ለቀዉ በልዩ ዞን ማስፈር ተችሏል ፡፡ ለፕሮጀክቱ የባንክ ብድር ያንገራገሩ የመንግስት ባንኮች ኃላፊዎችም ተነስተዋል (የንግድ ባንክ ከፈተኛ አመራር ጨምሮ) ፡፡ አሁን የትኬት ሽያጩም የባንክ ብድሩም ቀጥሏል ፡፡ የቤት ግንባታዉንና ገንዘብ ማሰባሰቡንም የሙስሊም ኮሚቴ ነን የሚሉ አካላት በኮሚቴነት የሚፈፅሙት መሆኑ ሌላም ጥያቄ እንዲመጣ ይጋብዛል፡፡ በአዲስ አበባ ዙርያ እየተሰራ ያለዉን ሸፍጥ በሌላ ፁሁፍ እመለስበታለሁ። በየዋህ ተመልካች ፊት አለም አቀፍ ሃይማኖትና ብሄር ነክ ሴራ እየተሰራ ነው።
የዚሁ የቅድመ ልዩ ጥቅም ዝግጅት አካል በአክራሪ ብሔርተኝነት የሚታወቅ ሰው ከተማዉን እንዲመራ ተመርጧል፡፡ በ1993 የAAU የተማሪዎች አመፅ በከተማዉ ጉዳይ ተባሮ የነበረ እንደሆነ የሚነገርለት በተቀናጀ ማስተር ፕላን እቅድ ዋና ተቃዋሚ የነበረ ሰው  የከተማዉን ምርጫ በማራዘም የከተማዉ ምክር ቤት አባል ሳይሆን የከተማ ቻርተሩ ተሻሽሎ እንዲሾም ተደርጓል፡፡ የሹመት ሂደቱን “.. እስከምርጫው የሚቆይ ጊዜያዊ አመራር ነው” መባሉም በሁለቱ ዓመት የፊንፊኔን ባለቤትነት የማረጋገጥ ዝግጅቱን ዳር የማድረስ ሚና ነው፡፡ አሁንም በከተማው ልማት ለተፈናቀሉ አርሶአደሮች በሚል የ56ሺህ ቤቶች ግንባታ ተጀምሯል፡፡ አሁንም የመሬት ኦዲት ተደርጓል ፡ የህንፃ ኦዲት ተደርጓል፡ የመንግስት ቤት ኦዲት ተደርጓል ፡፡ የድርሻና ባለቤትነት ዴታ ይገኝበታል፡ ለቀጣይ ማስተካከያ ምቹ ሆኗል፡፡ ቀጣይ ቤቶቹ ፡ መሬትና የግንባታ ቦታ እንዴትና ለማን ይሰጣል የሚለዉ የሚታይ ነዉ፡፡ በዚሁ መሃል የፍላጎት ጥቆማዎች ተከስተዋል ፡፡ ፋና እንደዘገበው ትላንት ም/ከንቲባ ታከለ ኡማ  6400 የኦሮሞን ወጣት በአዲስ አበባ ሰብስበው በሚያናግሩበት ሰዓት የተነሳው “የመሬት ይሰጠን” ጥያቄ የከተማው አስተዳደር መልስ ይሰጥበታል ብሏል። የሚገርመው ነገር ይህንን ዜና የከንቲባው ፌስቡክ ፔጅ ዉይይቱ “ከኢትዮጵያ ወጣቶች” ብሎ ነበር የዘገበው። ፋናም በትእዛዝ ኦሪጅናሉን ዜና ኤዲት አድርጎታል፤ እድሜ ለስክሪን ሾት ዋናዉን ይዘነዋል። በፍተሻና በአፍሳ የከተማው ነዋሪ የማሸማቀቅ ስራ ተጠናክሮ የቀጠለበት ግዜ መሆኑ አይረሳ።
7. የልዩ ጥቅም አጀንዳ ዋዜማ
የከተማውና የፖለቲካው ሂደት ቀጥሎ “የዜጋ ብሔርተኞችን” ፍላጎትና የወደፊት ነገር ጠቋሚ ነገር የኦነግ አቀባበል እና የቡራዩ ክስተትን ተከትሎ መጥቷል፡፡ይህ በአጭሩ እንበልተው።
#ሀ, የቡራዩ መልእክት 
ከቡራዩ ክስተት ጋር በተያያዘ የኦሮሞ ፖለቲከኞችን ፍላጎት የሚጋፋ “አደገኛ” ጥቆማ ታይቷል፡፡ ከሞቱት ሰዎች በላይ የተደቀነው ተግዳሮት ነገን ጠቋሚ ነዉ፡፡ “ኦህዴድ ከአዲስአበባ ይውጣ ፡ አዲስአበባ ለነዋሪዎቹ ” ተባለ፡፡ ከዚያም ወጣቱ ታፍሶ ተለቀመ፡፡ የከተማው ከንቲባ ኦዴፓ፣ ፌዴራል ኦዴፓ እንዲሁም ኦሮምያ ኦዴፓ ሆነው ምን ዓይነት ድርድር እንደሚኖር እግዚሄር ያሳያቹህ።
#ለ, አፈሳውና የአንድነት ፖለቲካ ቀርቃር
አዲስአበባ “የአንድነት” ኃይሉ ብቸኛ ማረፊያ ብትሆንም፡ ከቡራዩ ጋር ተያይዞ ንቁ ተሠላፊዎቹ ተለቅመው ታስረው በከተማው ጉዳይ በቀጣይ በሚደረገው ነገር ውስጥ ተቃውሞ “እንዳይደገማቸው” የሚያደርግ “እርምት” እየተወሠደ ነው፡፡ ይህም “የዜጋ ብሔርተኛዉን” ቅርቃር ውስጥ የሚከት ነው፡፡
#ሐ, የ 5ቱ ኦሮሞ ድርጅቶች ጥቆማ
ይህ በእንዲህ እያለም 5 የኦሮሞ ድርጅቶች “ለሰማዩ ወርዉር፡ ጣሪያውን እንድታገኝ” በሚለው ብሒል፡ የልዩ ጥቅም ይዘት ላይ ክርክርን የሚቀንስና የአጀንዳዉን ዋዜማ ጠቋሚ፡ “አዲስአበባ የኦሮሞ ነች” አዋጅ አወጡ፡፡ በኦሮሞ ጉዳይ ልዩነት ስለሌለ OLF እና የሌንጮ ODF ፀባቸዉን ትተው (የሌንጮ ቡድን ወለጋ ብሄድ ኦነግ ይገድለናል ብሎ ከሆቴል ባልወጣበት ሆኔታ) በአዲስ አበባ ጉዳይ የጋራ መግለጫ ሰጡ፡፡ ቀጥሎ በተለመደው የድራማ ክዋኔም ODP በኢህአዴግ መድረክ ይዞት ይመጣል፡፡ ይህ ከነአብይ እውቅና ውጭ የሆነ ባለመሆኑ፡ በቀጣይ ከስደት የተመለሠው ሊሂቅ በአጀንዳ ቀረፃ፡ እነ ለማ በማስፈፀም የሚኖራቸዉን ትብብር ጠቋሚ ነው፡፡ የአዲስ አበባ ጉዳይ ኦህዴድ ከልዩ ጥቅም ወደ ባለቤትነት አሳድጎታል። የታከለ ኡማ ዋና ተልእኮም ይሄ ይመስላል።
መዳረሻዉ ምንድን ነዉ? 
የሚተነበይ ቢሆንም የኦሮሞ  ሁለንተናዊተፅዕኖ ማረጋገጥ የቅርቡ ግቡ ነው፡፡ ክስተቶችን ገጣጥመን በመዋቅራዊ ይዘታቸው አንጥረን  ካላየን በማራኪ ንግግሮችና በስሜታዊ ገለፃዎች ታዉረን ከመወናበድ አንድንም፤ በዝርዝር ካላሰብን ሃገራችንም ነበር የመሆን እድልዋ የሰፋ ይሆናል። ህወሓትን በዚህ ሁሉ አሻጥር ማሸነፍ ካልቻልን “ህወሓትን ከኢህአደግ በማገድ” ሃገሪትዋን እንደፈለግን ማድረግ አለብን የሚለው አማራጭ በሰዎቹ ጠረጴዛ መኖሩ ግን ይገርማል።
በጨዋ ደምብ እንወያይ።
አመሰግናለሁ።
Filed in: Amharic