>

ያልተገራዉ ፈረስ ሽምጥ ግልቢያ ወዴት ያደርሰን ይሆን? (ያሬድ ደምሴ መኮንን)

ያልተገራዉ ፈረስ ሽምጥ ግልቢያ ወዴት ያደርሰን ይሆን?

ያሬድ ደምሴ መኮንን

ጃዋር መሃመድ ለናሁ ቱሌቪዥን የሰጠዉን ቃለ ምልልስ ደጋግሜ ባዳመጥኩት ቁጥር የልጁ ወፈፌነት ቁልጭ ብሎ ይታዬኝ በዚህ ቃለ ምልልስ ወቅት የተነሱ ሃሳቦች (ቀረርቶዎችና ፉከራዎች በለጠ ይገልጸዋል) ትንሽ ተፍታተዉ ቢጻፉ የጃዋርን የወፈፌነትና የቅዠት ጉዞ ልቅም አድርገዉ ያሳያሉ ብዬ በማመኔ ጃዋርና የጃዋር ቀረርቶዎች ዙሪያ ለሁለተኛ ጊዜ ለመጻፍ ተነሳሁ፡፡ ምክንያቱም ጃዋርን አለቅጥ አግዝፎም ሆነ አኮስሶ ማየቱ የኢትዮጵያን ሰላምና አንድነት ለምንሻ ወገኖች ብዙ ዋጋ ማስከፈሉ አይቀርም፡፡ስለዚህ ይህ አደገኛ ሰዉ ተገቢ ቦታዉን ያገኝ ዘንድ የዚህን ሰዉ ማንነትና ዓላማ ለኦሮሞ ብሎም ለመላዉ ኢትዮጵያዊ ወጣቱ ትዉልድ በሚገባ ማሳወቅ ይኖርብናል፡፡

(ዲጄ እስኪ የጃዋርን ቀረርቶ እንደገና ከፍ አድርገህ ክፈተዉ!!ምን ይላል?)

“እኔ እንደ ነጻ ፈረስ የፈለኩትን እየተናገርኩ የፈለገኝን እየሰራሁ በፓርቲ ፕሪሲፕል በምናምን ምናምን ሳልታሰር ይህችን ሃገር  መርዳት ነዉ”

ይህ የጃዋር አባባል እንዲሁ እንደቀልድ ሊታለፍ የሚገባዉ ስላልሆነ ዛሬም ነገም ደግሜ ደጋግሜ አነሳዋለሁ፡፡ካያያዝ ይቀደዳል ካነጋገር ይፈረዳል ነዉ ነገሩ፡፡ ጃዋር ነጻ ፈረስ ሲል ግን ምን ማለቱ ነዉ?

ያዉ እንግዲህ እኛ መሃይሞቹ እስከሚገባን ድረስ ፈረስ ነጻ የሚሆነዉ ሳይገራ ሲቀር ብቻ ነዉ፡፡ ያልተገራ ፈረስ ነጻ ነዉ፡፡ በፈለገበት ይሰግራል፡፡መነሻም ሆነ መድረሻ የለዉም፡፡ጉዞ የሚያስጀምረዉም ሆነ ከጉዞዉ የሚያስቆመዉ ወይም መንገዱን ስቶ ወደገደል ቢነጉድ አቅጣጫ ለማስቀየር የሚያስችል ለባለቤቱ የሚታዘዝ ልጓም የለዉም፡፡ቢዝገይ ዘገየህ ብሎ በአለንጋ የሚሸነቁጠዉ ባለቤት የለዉም፡፡

እንግዲህ ከዚህ አንጻር ጃዋር በህዝብ ፍላጎት የማይጋለብ፣ መንገድ ስቶ ወደ ገደል ቢሰግር እንኳ በህዝብ ልጓም አቅጣጫ የማይዝ፣ግልቢያዉ ቢንቀራፈፍ በህዝብ አለንጋ ተሸንቁጦ የማይፈጥን ያልተገራ በሱ አባባል ነጻ ፈረስ ነዉ!!

እንደ ግለሰብ ያለፕሪስፕል መኖር ቀላል ሊሆን ይችላል፡፡ያለ ፕሪስፕል ባሻዉ መንገድ የሚጋልብ ግለሰብ ግን ሃገርን መጉዳት እንጂ ሃገርን መርዳት ፈጽሞ አይቻለዉም፡፡ እንግዲህ አሁን በአገሪቱ በተለይም በቡራዩ የተፈጸመዉን ጭፍጨፋ ይሄ የፈለገኝን እየሰራሁ እኖራለሁ የሚለዉ ያልተገራዉ ፈረስ ጃዋር አላስፈጸመዉም ብሎ ለማመን የሚከብደዉ ሰዉ አለን?

ተፈጥሮዉ ሆኖ በፕሪሲፕል መታሰር የማይወደዉ ጃዋር መሃመድ ዛሬ ደግሞ 360 ድግሪ ተገለባብጦ ከህወሃት ጋር እጅና ጓንት ሆኖ ላለመስራቱ እርግጠኛ መሆን ይቻላልን?ጃዋር ስሙ ከማንም በላይ ከፍ ብሎ እንዲጠራ ያድርገዉ እንጂ አይደለም ከህወሃት ጋር ቀርቶ ከሠይጣንም ጋር እንኳ ቢሆን ለመስራ የሚያቅማማበት ሞራል ያለዉ አይመስልም፡፡ ከጃዋር ፍልስፍናና ያለፈ ድርጊት የምንረዳዉ ይሄንኑ እዉነት ብቻ ነዉ!!

(እስኪ ዲጄ ቀጥል…….ጃዋር ሌላ ምን አለ?)

“5000 ወጣቶችን ወደ እሳት ልከን አስጨፍጭፈናቸዉ ነዉ በነሱ ደም ነዉ ዛሬ ኢትዮጵያ ዉስጥ የምታየዉ ለዉጥ የመጣዉ፡፡በቀልድ አይደለም፡፡በጾለት አይደለም”

ከዚህ ንግግር 3 አበይት ጉዳችን እንረዳለን፡-

  1. ለዚህ ለዉጥ መምጣት የህይወት መስዋእትነት የከፈሉት ኢትዮጵያዉያን ቁጥር 5000 ብቻ ነዉ፣
  2. ይህ አንጻራዊ ለዉጥ እዉን የሆነዉ በቄሮ ደም ብቻ ነዉ፣
  3. ለዚህ አንጻራዊ ለዉጥ መገኘት ጾለት ምንም አይነት ድርሻ የለዉም፡፡

የጃዋር ጭንቅላት ቁልጭ ብሎ ይታየን ዘንድ ከዚህ በላይ የጠቀስናቸዉ ሶስት ጉዳዮችን እስኪ ትንሽ አፍታተን ለመመልከት እንሞክር፡፡

ጃዋር አሁን ለመጣዉ አንጻራዊ ለዉጥ መስዋዕትነት የከፈሉ ኢትዮጵያዉያን ቁጥር በአምስት ሽህ ቀንብቦ ያሳንሰዋል፡፡ያዉም የኦሮሞ ወጣቶች ብቻ ናቸዉ መስዋዕትነት የከፈሉት፡፡ የኦሮሞ ደም የኛ ደም ነዉ እያለ ጎንደር ላይ ለነጻነቱ ሲል በጥይት የተቆላዉ የአማራ ወጣት ጃዋር መጣ ላለዉ ለዉጥ ምንም አስተዋጽኦ የለዉም፡፡ የጃዋር የዕወቀት ልክ እንግዲህ እስከዚህ ድረስ ነዉ፡፡ለለዉጥና ለነጻነት የተደረገዉን ተጋድሎ በኢህአዴግ ዕድሜ ብንወስነዉ እንኳ፣ ከ1983 ጀምሮ የስርአቱን አፋኝነት በመቃወምና ለዉጥ በመሻት  ስንትና ስንት ኢትጵያዉያን መስዋዕትነት እንደከፈሉ ለልበ ድፍኑና ወፈፌዉ ጃዋር ማስረዳት ማገዶ መፍጀት ነዉ፡፡

ቄሮዎችም ፋኖዎችም ዘርማዎችም ለዚህ ለዉጥ እዉን መሆን ለከፈሉት መስዋእትነት ተገቢዉን ክብርና ቦታ እየሰጠን የሌሎች ግለሰቦችንና ቡድኖች የላቀ አስተዋጽኦ ደግሞ በትንሹም ቢሆን ለወፈፌዉ ጃዋር ልናስታዉስዉ ግድ ይለናል፡፡እስኪ አባይን በጭልፋ……

የአሁኑ ለዉጥ እዉን እስኪሆን ድረስ ጋዜጠኞች የህወሀት ኢህአዴግን የጭቆና አገዛዝ ለመቃወም ብእራቸዉን ስላተጉ ብቻ ወህኒ የተወረወሩት ይህ ለውጥ እዉን እንዲሆን እንጂ የጋዜጣቸዉ ወይም የመጽሄታቸዉ ህትመት ቁጥር እንዲጨምር ብለዉ አልነበረም፡፡ እነእስክንድር ነጋ፣ ርዕዮት ዓለሙ፣ ተመስገን ደሳለኝ….. ሌሎች እዚህ ላይ ስማቸዉን ዘርዝሬ መጨረስ የማልችለዉ በርካት ብዕረኞች የምቾት ኑሯቸዉንና ቤተሰባቸዉን ተሰናብተዉ ወህኒ የተወረወሩት ለምን ነበር? ፖለቲከኞቻችን እነ አንዱአለም አራጌ፣ መረራ ጉዲና ብርቱካን ሚዴቅሳ ወዘተ ለምን ነበር የፖሊስ ካቴና እጃቸዉ ላይ አጥልቀዉ ወደ ዘብጥያ የወረዱት? እነሱ ነበሩ እኮ የእኛን እስራት የታሰሩልን፤የእኛን ቁስል የቆሰሉልን፡፡

ከ1983 ዓ.ም ወዲህ ለህትመት ሲበቁ የነበሩትን የግል ሚዲያዉ መጽሄቶችና ጋዜጦች ለዚህ ለዉጥ መሳካት ስንትና ስንት አሰተዋጽኦ እንዳበረከቱ ማን ያዉቃል? ለዚህ ለዉጥ እዉን መሆን የቪኦኤ፣ የዶቼ ቬሌና የኢሳትን አሰተዋጽኦ በየትኛዉ መለኪያ ተሰፍሮ ይታወቃል? ኢሳት ላለፉት 8 ዓመታት በማፊያዉ መንግስት ለ 28 ጊዜያት ያህል ጃም እየተደረገ ያለምንም ተሰፋ መቁረጥ በአገዛዙ እየተፈጸመ ያለዉን ግፍና ጭቆና ለኢትዮጵያዉያን ብሎም ለዓለም ህዝብ ሲያሳዉቅ መኖሩ የዚህ ለዉጥ አንዱ አካል አያደርገዉምን? ከ2008 ጀምሮ በኦሮሚያና በጎንደር የነበረዉን አመጽ እግርበግር በመዘገብ ለህዝብ አድርሶ ለዚህ ያበቃን አንዱ ነጻ ሚዲያ ኢሳት አልነበረምን?

ለዚህ ለዉጥ ደራሲያንና የታሪክ ሰዎች ያበረከቱት አስተዋጽኦ ማነዉ ለማራከስ የሚደፍረዉ? በዉቀቱ ስዩም ከአሚን ባሻገርና የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጅግሳ እዉነተኛ የኦሮሞና የአማራ የዘር ምንጭ የሚሉት መጻህፍት ለኦሮሞና አማራ የአብሮነት ትግል ያበረከቱትን አስተዋጽኦ ማን ጀግና ነዉ በቁጥር ሰፍሮ ሊነግረን የሚችለዉ?  

ለዚህ ለዉጥ እዉን መሆን የቴዲ አፍሮን ያህል መስዋዕትነት የከፈለ ጀግና ይኖራልን? አዝማሪዉ ሁሉ ሳሚን ልሳምሽ እያለ የመሸታ ቤት ዘፈን ሲዘፍን፣ቴዲ አፍሮ አልነበረም እንዴ የስርአቱን ሰዎች እስራት፣ጭቆና፣ ስድብና ዛቻ ሳያስፈራዉ አገዛዙን ፊትለፊት ቆሞ በመቃወም የአብዛኛዉን ኢትዮጵዊ ልብ ለለዉጥ የቀሰቀሰዉና ወኔዉ እንዲበረታ ያደረገዉ?የፋሲል ደመወዝ አረሱት ሁመራን…. የሚለዉ ዜማ የስንቱን ጎንደሬ ልብ ለአመጽ እንዲያነሳሳ አላደረገም ብሎ ሊሞግት የሚነሳ ማነዉ?

ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት ላንቃዉ እስኪላቀቅ ሲጮህና ሲቃወም የነበረዉ ኢትዮጵያዊ ዲያስፖራ ለዚህ ለዉጥ እዉን መሆን ድርሻ አልነበረዉም ወይ?የ1997 ምርጫን ተከትሎ አማራ ኦሮሞ ሳይል ለነጻነቱ አደባባይ በመዉጣት ህይወቱን ለጨካኙ መንግስት ወታደሮች አሳልፎ የሰጠዉ ወጣት ከዚህ ለዉጥ ባለቤትነት ገፍትሮ የሚያስወጣዉ የትኛዉ ደፋር ነዉ?

የትግራይ ተወላጆቹ አብረሃም ያየህና ገብረመድህን አርአያ ኢህአዴግ አገሪቷን ከመቆጠጠሩ በፊት ጀምሮ ባገኙት ሚዲያ ሁሉ ተጠቅመዉ ስርአቱን ለማጋለጥ ያደረጉት ርብርብ ለዚህ ለዉጥ ያበረከተዉ አስተዋጽኦ ስለምን ይዘነጋል? የኤርሚያስ ለገሰ የአገዛዙን ገበና ፍንትዉ አርጎ የሚያሳየዉ የመለስ ልቃቂት የተሰኘ መጸሃፍስ ስፍራስ የት ላይ ነዉ?ለዚህ ለዉጥ የጋምቤላዉ ኦባንግና የአፋሩ ያሲን የሱፍ ያበረከቱት አስተዋጽኦ ማነዉ ለማራከስ የሚደፍረዉ?የነ አበበ ገላዉ፣ ሲሳይ አጌናና የታማኝ በየነ ሚና በምን ይገመታል?  

ኧረ የቱን ጠቅሰን የቱን እንተወዋለን? ለዚህ ለዉጥ መምጣት ሁሉም ኢትዮጵያዊ የየራሱን ድርሻ አበርክቷል ብለን በደምሳሳዉ እንለፈዉ፡፡ሁሉም ኢትዮጵያዊ ኦሮሞ፣አማራ፣ትግሬ፣ ጋምቤላ፣አፋር………ሁሉም እዚህ ለዉጥ ላይ የራሱን አሻራ አስቀምጧል፡፡እናም ይህ ለዉጥ የብዕር፣የጩኸት፣የዜማ፣የሚዲያ፣የጾለት፣ የድንጋይ ዉርወራና….. የሌሎችም የብዙ ብዙ ነገሮች ድምር ዉጤት መሆኑ ሊታወቅ ይገባል፡፡  ይ–ሰ-ማ-ል ጃዋር?

ሌላኛዉ ስለሰዉዬዉ ብዙ ነገር የሚያሳዉቀን ጃዋር ለዚህ አንጻራዊ ለዉጥ መገኘት ጾለት ምንም አይነት ድርሻ የለዉም ብሎ በድፍረት የተናገረዉ ነገር ነዉ፡፡ይሄን አባባል እንዲሁ በቀላሉ የምናየዉ ጉዳይ አይሆንም፡፡፡፡ይሄን የሚለን በእዉቀቱ ስዩም ቢሆን ኖሮ ጉዳዩን እዚህ ላይ አንስተን ባልተከራከርንበት ነበር፡፡ነገር ግን ይህን እያለን ያለዉ በቅርቡ ሃጂ አድርጌ መጣሁ የሚለዉ ኃማኖተኛዉ ጃዋር መሃመድ ነዉ፡፡

ልብ በል! ፆለት በእስልምና አስተምህሮ ትልቅ ቦታ ቢኖረዉም፣ ሃጂ አድርጎ ለመጣዉ ጃዋር ግን ቦታ የለዉም፡፡ ለአመታት በየመስጊዱና በየአብያተ-ክርስቲያናቱ ፈጣሪ ለዚች ሀገር የሚበጅ መሪ እንዲሰጣት ቀን ከሌሊት በጾም በጾለት ተግተዉ ሲለምኑ የኖሩ እናቶችና አባቶች በጃዋር ዘንድ ቦታ የላቸዉም፡፡ለዚህም ነዉ ጃዋር ይህ ለዉጥ የመጣዉ በጾለት አይደለም የሚልህ፡፡እንደ ፖለቲካል ሳይንቲስቱ እምነት ትግል እንጂ ፆለት ምንም ነገር ሊለዉጥም ሆነ ሊቀይር አይችልም፡፡

ፈጣሪን የማይፈራን ሰዉ ፍራ ነዉ ነገሩ፡፡ ጃዋር ስለአምላኩ ያለዉ ግንዛቤ ይህ ነዉ፡፡

እንግዲህ እዚህ ያልተገራ ልጓም አልባ ፈረስ ላይ ነዉ በሚሊዮን የሚቆጠሩ የኦሮሚያ ወጣቶች የተፈናጠጡት፡፡ ከዚህ በላይ ለዚች ሃገር ስጋት ኬት ይመጣል?

ላለፉት ሃያ ሰባት ዓመታት የኦነግንና የህወሃትን ተረት ተረት እየሰማ ያደገዉ አዲሱ ትዉልድ ቄሮ በጃዋር የዘረኝነት ሃሳብ ልቡ መማረኩ ግልጽ ነዉ፡፡ በዚህም የተነሳ የጃዋርን ትእዛዝ እንደ መለኮት ቃል አምነዉ ለመተግበር ዝግጁ የሆኑ ቄሮዎች ዶ/ር አብይ ለሚመራዉ መንግስት ትልቅ ተግዳሮት ሊሆኑ እንደሚችሉ አያጠራጥርም፡፡

ዶ/ር አብይና ለማ መገርሳ ከፊት ለፊታቸዉ አንድ አፋጣኝ ስራ ይጠብቃቸዋል፡፡ ያልተገራዉ ፈረስ ላይ የተፈናጠጡትን ቄሮዎች ከፈረሱ ላይ በፍጥነት እንዲወርዱ ማድረግ የዶ/ር አብይ መንግስት ከሁሉ በፊት መሰራት ያለበት የቤት ስራ ነዉ፡፡ እስከዚያዉ ግን ያልተገራዉ ፈረስ ግልቢያ የት ያደርሰን ይሆን እያልን መቆዘማችንን አናቆምም! እንቀጥላለን!!

ቸር ያሰማን!!

Filed in: Amharic