>
4:42 pm - Wednesday January 16, 9247

ተአምር ካልተከሰተ የሀዋሳውን ጉባዔ የሚቀለብስ ምንም ነገር አይኖርም!!! (መሳይ መኮንን)

ተአምር ካልተከሰተ የሀዋሳውን ጉባዔ የሚቀለብስ ምንም ነገር አይኖርም!!!
መሳይ መኮንን
* መቀሌ ላይ ጥዕሎ ተጋብዞ፡ ለስብሃት ነጋ ባንዲራውን አስታቅፎ ወደ ሀገር ቤት የገባው ኦነግ ከህወሀት ጋር የድብቅ ጫጉላ ጊዜ ላይ እንዳለ የሰኔ 16ቱ የግድያ ሙከራና የቤንሻንጉል ጉምዙ ጥቃት ከማስረጃም በላይ ናቸው።
ረቡዕ በሀዋሳ የሚጀመረው የኢህአዴግ አባል ድርጅቶች ጉባዔ የኢትዮጵያን ፖለቲካ የመወሰን ሁነኛ ተጽዕኖ አለው። ሶስቱ አባል ድርጅቶች በተናጠል ያደረጉትን ጉባዔ አጠናቀው ለሀዋሳው የሚወክሏቸውን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላትን መርጠዋል። ብአዴን እየተጠበቀ ነው። ከህወሀት በቀር ሶስቱ ድርጅቶች ከስያሜ ጀምሮ የተለያዩ ለውጦችን አድርገዋል። ከብሄር ጥብቆ ተላቀው ሀገራዊ የፖለቲካ ፓርቲ ለመሆን ዳርዳርታውን ጀምረውታል። ህወሀት ግን እዚያው ተቸንክሮ መቅረትን መርጧል። ደደቢት ላይ የአማራውን ህዝብ ጠላት ብሎ የሰየመበትን ማኒፌስቶ እንደታቀፈ፡ የነጻ አውጪ ካባውን እንደደረበ አረጀበት። ዘንድሮም እዚያው ነው።
የሀዋሳው ጉባዔ የኢህአዴግን ሊቀመንበር ለመምረጥ የሚሰየም እንደሚሆን ተነግሯል። የኢትዮጵያ ህዝብ ከዳር እስከዳር የተቀበላቸውና ተስፋም ያደረገባቸው ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ሊቀመንበር ሆነው የመመረጣቸው ነገር ያለቀለት ይመስላል። በኦዴፓ(የቀድሞው ኦህዴድ) እና በብአዴን(ብአዴንም ስሙን ወደ አዴፓ ቀይሮታል የሚል መረጃ ሰምቼአለሁ) መሀል ያለው የመናበብና የትስስር ገመድ የጠበቀ በመሆኑ የሀዋሳው ጉባዔ የተለየ የአመራር ለውጥ እንደማያሳይ ይነገራል። በደኢህዴንም በኩል አብዛኛው ከለውጡ ጋር የተሰለፈ አመራር በመሆኑ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ቦታቸውን ይዘው እንዲቀጥሉ ያደርጋቸዋል የሚለው ተስፋ የብዙዎች ነው።
ይሁንና ግን በትንሹም ቢሆን የህወሀትንና የዘር ፖለቲካ አቀንቃኝ የሆኑ የተቃዋሚ ፓርቲዎችና አክቲቪስቶችን ተጽዕኖም አሳንሶ መመልከት የሚገባ አይደለም። ህወሀቶች ዶ/ር አብይን ከኢህአዴግ ሊቀመንበርነት እንዲነሱ የመጨረሻ እድላቸውን እየሞከሩ ነው። የኢህ አዴግ ጽ/ቤት ሃላፊና የህወሀት ም/ሊቀመንበር ወ/ሮ ፈትለወርቅ(ሞንጆሪኖ) በቅርቡ በሰጡት መግለጫ አዲስ ሊቀመንበር የመመረጥ መብት አለን ያሉበት አገላለጽና የድምጻቸው ቅላጼ የህወሀትን የመጨረሻ ፍላጎት ያሳዩበት ነበር። ህወሀቶች አንድ ላይ ተሰልፈዋል። ዳግም ቤተመንግስት የመግባት እድላቸው እንደጠበበ ቢያውቁም የእነሱን ጥቅምና ፍላጎት የማይነካ፡ ኢትዮጵያ እያለ የማይዘምር፡ በብሄር ፖለቲካ ባህታዊ የሆነ ሊቀመንበር እንዲመረጥ የሚችሉትን ሁሉ እያደረጉ መሆኑን ከውስጥ የሚወጡ መረጃዎች ያመለክታሉ።
የህወሀቶች ፍላጎት በግልጽ ይታወቃል። በአደባባይም ገልጸዋል። በኦዴፓ ጉባዔ ላይ ተወክለው የተገኙት የህወሀት አመራር በግልጽ ”ኦህዴድ አዲስና ጠንካራ አመራር እንደሚመርጥ ተስፋ አደርጋለሁ” ብለው ተናግረዋል። ኦህዴድ በድጋሚ ዶ/ር አብይን ሊቀመንበር አድርጎ በመምረጥ ተስፋቸውን ጉም አለበሰባቸው እንጂ። ከሀገር ውስጥ እስከባህር ማዶ የህወሀት አክቲቪስቶች፡ ምሁራን፡ ደጋፊዎች በሰልፍ የዶ/ር አብይ መንግስት እንዲወርድ ቅስቀሳ ላይ ተጠምደዋል። የ27 ዓመት ንግስናቸውን ወደ መቃብር የሸኘባቸውን የዶ/ር አብይን አስተዳደር ለመበቀል የማይፈነቅሉት ድንጋይ እንደማይኖር እየነገሩን ነው።
ትግራይ ኦን ላይን የተሰኘ የህወሀት አራጋቢ ድረገጽ በይፋ ጠ/ሚር አብይ አህመድ ስልጣን እንዲለቁ ጠይቋል። የህወሀቱ የአደባባይ ምሁር ፕ/ር ተኮላ ሀጎስ የመከላከያ ሰራዊት መፈንቅለ መንግስት አድርጎ ሀገሪቱን እንዲቆጣጠር ጥሪ አድርገዋል። ከቡራዩ እስከ ቤንሻንጉል፡ ከወልቃይት እስከ ሀረር እዚህም እዚያም የተበራከተው ግጭት በህውሀቶች የተጠነሰሰ፡ ፋይናንስ የተደረገ መሆኑን መዘንጋት አይገባም። ይህም የጠ/ሚር አብይን መንግስት በማዳከም በአቋራጭ የቤተመንግስት መንገድ ከተገኘ ለመሞከር እንደሆነ ተረድተናል።
ህወሀቶች ብቻቸውን አይደሉም። የሰኔ 16ቱ የመስቀል አደባባይ የግድያ ሙከራን በተመለከተ የአቃቤ ህግ የክስ መዝገብ እንደሚያሳየው ዶ/ር አብይ በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ ተቀባይነት የሌለው በመሆኑ የኢትዮጵያ መንግስት መሆን የሚገባው ኦነግ ነው የሚል ዓላማ ይዘው በተነሱ የኦነግ ሰዎች የተፈጸመ ነው። ከኦነግ ጋር ታክቲካል ግንኙነት የፈጠሩ አንዳንድ አክራሪ የኦሮሞ ብሄርተኞችም ከዚህ የግድያ ሙከራ ጀርባ ስለመኖራቸው ከጥርጣሬ በላይ መግለጽ የሚቻል ነው። ጠ/ሚር አብይ አህመድ ወደ ቤተመንግስት ከመግባታቸው በፊት፡ እንደውም የኦህዴድ ሊቀመንበር ሆነው ከመመረጣቸው አስቀድሞ በአደባባይ ሲወንጅሏቸውና እንዲባበሩ ጭምር ግፊት ሲያደርጉ የነበሩ አክራሪ ብሄርተኞች እንደነበሩ አይዘነጋም። ወደ ሀገር ውስጥ በክብር ተጠርተው ከገቡ በኋላም ጠ/ሚር አብይ አህመድ በፍቅር የሰበሰቡትን ህዝብ በጥላቻ ስብከት ሲበትኑት እያየን እየሰማን ነው። ሁለት መንግስት ኢትዮጵያ ውስጥ እንዳለ አድርጎ ሃላፊነት የጎደለው መግለጫ መስጠትም ዋናው ዓላማ የጠ/ምር አብይን መንግስት ዕውቅና ለመንፈግ ነው።
ኦነግና አክራሪ ብሄርተኞቹ በበርካታ ጉዳዮች ላይ የማይስማሙ፡ እርስ በእርስ ሲወነጃጀሉና አንዱ አንዱን ለማጥፋት እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩ እንደነበሩ እናስታውሳለን። ሆኖም አሁን ላይ አንድ የሚያደርጋቸው አንድ አጀንዳ አግኝተዋል። ኢትዮጵያዊነትን አንግበው እሰከአፍሪካ የተዘረጋ ህልም አለመው የተነሱትን ጠ/ሚር አብይ አህመድንና በጥቅሉም የቲም ለማ አባላትን በኦሮሞ ህዝብ ዘንድ የተጠሉ እንዲሆኑ ማድረግ፡ በሂደትም ይህን አመራር ከስልጣን በማስወገድ የአራት ኪሎ ቤተመንግስትን መቆጣጠር ላይ ያነጣጠረ የጋራ የትግል መስመር ቀርጸው እየተንቀሳቀሱ ነው። የሚያስቡት ነገር ቅዥት መሆኑን ቢያውቁትም ማለቂያ የሌለውን አጀንዳቸውን እየሰጡ በትርምስ ውስጥ መቆየት የፖለቲካ ንግዳቸው ምሶሶ አድርገውታል።
በቅርቡ መግለጫ በጋራ ያወጡትና ”ተገደን ነው የብሄር ፖለቲካን የመረጥነው” የምትል ነጠላ ዜማ ከሰሞኑ እያሰሙ ያሉ ድርጅቶችም የጠ/ሚር አብይ አህመድን መንግስት ለማዳከም እጃቸውን ስለማስገባታቸው መረጃዎች ይጠቁማሉ። እነዚህ ሃይሎችን ህውሀቶች በተዘዋዋሪ ሊጠቀሙባቸው እንደሚችሉ ይታመናል። መቀሌ ላይ ጥዕሎ ተጋብዞ፡ ለስብሃት ነጋ ባንዲራውን አስታቅፎ ወደ ሀገር ቤት የገባው ኦነግ ከህወሀት ጋር የድብቅ ጫጉላ ጊዜ ላይ እንዳለ የሰኔ 16ቱ የግድያ ሙከራና የቤንሻንጉል ጉምዙ ጥቃት ከማስረጃም በላይ ናቸው።
ህወሀቶች ከአክራሪ የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶችና አክቲቪስቶች እንዲሁም ከአንዳንድ ኢህ አዴግ ውስጥ ከሰገሰጓቸው አፍቃሪ አመራሮች ጋር በመሆን የሀዋሳውን ጉባዔ በእነሱ ፍላጎትና መስመር ለመቀልበስ ተግተው እየሰሩ ናቸው። ከፍተኛ ገንዘብ መመደባቸውም ይነገራል። ኢህአዴግ ውስጥ ያሉና አሁንም በህወሀት ፍቅር የተለከፉ አመራሮችን ተጠቅመው ሌሎችንም በገንዘብ ደልለው የምርጫውን ውጤት ለመቀየር እንችላለን ብለው ተነስተዋል። እንግዲህ ረቡዕ ዕለት የሚጀመረው የሀዋሳው ጉባዔ ሁሉን ነገር ይለይለታል።
ህወሀቶች ያልተረዱት ነገር ጠ/ሚር አብይ አህመድ የኢህአዴግ ሊቀመንበር በመሆናቸው አይደለም የኢትዮጵያ ህዝብ ድጋፉን የሰጣቸው። እንደውም እኔን ጨምሮ አብዛኛው ደጋፊያቸው ዶ/ር አብይ ከኢህአዴግ ጋር ስማቸው ሲነሳ ሰውነታቸን ይቆጣል። ይቀፈናል። ደስ አይለንም። ዶ/ር አብይ በምርጫ ኮሮጆ ድምጽ ሳይሰጣቸው በህዝብ ይሁንታ መሪነታቸው ተቀባይነትን ያገኙ ሰው ናቸው። ለኢትዮጵያ በጣሯ ጊዜ የተገኙላት፡ በምጧ ወቅት የመጡላት፡ ከገደል አፋፍ ሊመልሱ በቁርጠኝነት የተነሱላት መሪ በመሆናቸው እንጂ ኢህአዴግንማ አንቅሮ የተፋ ህዝብ ነው የኢትዮጵያ ህዝብ።
ህወሀቶች ሙከራችሁ ከንቱ ነው። ሴራችሁ የትም አያደርሳችሁም። 27 ዓመት ባገኛችሁት እድል ያልማረካችሁትን ህዝብ ከእንግዲህ ከእንደገና ብትፈጠሩም ልታገኙት የምትችሉት አይደለም። ተሳክቶላችሁ የሀዋሳውን ጉባዔ መቀልበስ ብትችሉ እንኳን የኢትዮጵያ ህዝብ አይቀበላችሁም። ከህወሀቶች ጋር እጅና ጓንት ሆናችሁ እየሰራችሁ ያላችሁም አክራሪ ብሄርተኞችም የህዝብን ልብ በጥላቻ አታሸንፉትም። የጀመራችሁት የጥፋት መንገድ የሚያደርሳችሁ ከገደል ነው። ስትሰርቁ ልትስማሙ ትችላላችሁ። መከፋፈሉ ላይ ግን ቀድማችሁ የምትገዳደሉት እናንተው ናችሁ። ጥሪ ተደርጎላችሁ በሰላም ወደ ሀገር ቤት ገብታችሁ የሰላም እጅ የዘረጋላችሁን መሪ እጅ ለመቁረጥ እያደረጋችሁ ያለው እንቅስቃሴ ጊዜያዊ ድል ሊያስገኝላችሁ ይችላል። መጨረሻችሁ ግን አጉል አወዳደቅ መሆኑን አትዘንጉት። ከህዝብ ጋር የሆነ ሁሌም አሸናፊ ነውና።
 በያዝነው ሳምንት አይንና ጆሮአችን ወደ ሀዋሳ ይሆናሉ። ትኩረታችን ከኢህ አዴግ ጉባኤ ላይ መሆን ይገባዋል። ኦዴፓ(ኦህዴድ) የቤት ስራውን አጠናቋል። ብአዴን በታቀደለት መልኩ አጠናቋል። ደኢህዴንም በአብዛኛው የለውጡ አካል መሆኑ ተረጋግጧል። ህወሀቶች ኩርፊያቸውን ይዘው ድምጻቸውን ለእኩይ ዓላማ ሊያውሉት ተዘጋጅተዋል። ሂሳቡ ሲሰላ ህወሀት ከወዲሁ ምኞቱ ተጨናግፏል ማለት ይቻላል። ከ180ዎቹ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ድምጽ ጠ/ሚር አብይ ከ120 በላይ እንደሚያገኙ የተለያዩ መረጃዎችን እማኝ በማድረግ መተንበይ ይቻላል። ተአምር ካልመጣ፡ ከሰማይ ዱብ እዳ ካልወረደ በስተቀር የሀዋሳውን ጉባዔ የሚቀለብስ ምንም ነገር አይኖርም።
ባይመረጡስ? የህውሀቶችና የአክራሪ ብሄርተኞች ሴራ ቢሳካስ? ከባድ ነው። የለውጡ ሂደት ወደኋላ በመመለስ ብቻ አይቆምም። ኢትዮጵያ ወደ ትርምስ ትገባለች። ህወሀት የቤተመንግስት መንገዱን ይጀመራል። አክራሪ ብሄርተኞች በየመንደራቸው ግልገል መንግስታትን በማቋቋም እንደሶማሊያ የጎበዝ አለቆች ሰፈራቸውን የሚያስተዳድሩበት የተበጣጠቀች ሀገር ትሆናለች። አዲዮስ ኢትዮጵያ!
አዎን! ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ ከኢህአዴግም በላይ ናቸው። የእሳቸውን መልካም ነገሮች በኢህአዴግ ቅርጫት ውስጥ አሳንሶ መመልከት ተገቢ አይደለም። ኢህአዴጎች የኢትዮጵያ ህዝብ ለዘመናት ለፈጸሟችሁት ሃጢያት ይቅር እንዲላችሁ ከፈለጋችሁ እኚህን የለውጥ ሃዋሪያ፡ ሊቀመንበራችሁ አድርጋችሁ በሙሉ ድምጽ ምረጧቸው!!!
Filed in: Amharic