>

የተጋመድንበት ፈትል (ከፋሲካ መለሠ ተሾመ)

የተጋመድንበት ፈትል

ፋሲካ መለሠ ተሾመ

 

አባታችን ወደ አስራ ሶስት ልጆች ነበሩት፡፡ ከተለያዩ ሴቶች፡፡  ዘር ቆጠራ ባልችልበትም፣ የአባቴ ሚስቶች ስብጥር ከአማራ፣ ከኦሮሞ፣ ከጉራጌ፣ ከትግራይ እና ከኤርትራ ነው፡፡ እድለኛ ስለኾንኩ ከአንዷ በስተቀር ከኹሉም ከአባቴ ሚስቶቼ ጋር አብሬ ኖሬአለኹ፡፡ እናቴ ከአማርኛ ተናጋሪ ቤተሰብ ነው የመጣችው፡፡ ኾኖም በህጻንነቷ ወለጋ እና ኢሉባቦር አድጋለች፤ ስለዚህ ኦሮምኛ አቀላጥፋ ትናገራለች፡፡ በጣም ተናዳ ሰው መገሰጽ ስትፈልግ ወይም ንግግሯን በተረት ማሳለጥ ሲያሰኛት የምትጠቀመው በኦሮምኛ ነው፡፡ አኹን ሳስበው ኦሮምኛ የሚናፍቃት ይመስለኛል፡፡ አማራኛ እና ኦሮምኛ የሚናገር ሰው ካገኘች ኦሮምኛውን ትመርጣለች፡፡ በአኹኑ ዘመን አራዳዎች አነጋገር ኦሮምኛ ውስጧ ነው፡፡ ልጆቿን ያሳደገችን የአማራን ባህልና ስነልቦና ከኦሮሞው ጋር አጋምዳ እና ፈትላ ነው፡፡

ሌላዋ ያባቴ ሚስት ጉራግኛ ተናጋሪ የሆነችው ነጋዴዋ እትየ ዘነቡ ነች፡፡ ካባቴ ጋር ከተፈታችም በኋላ ቢኾን ከቤቷ አልጠፋም ነበር፡፡ በኹለት ምክንያት፤ በመጀመሪያ ኹለት ወንድሞቼን እና አንዷን እህቴን የወለደችው ካባቴ ስለሆነ፣ ኹለተኛው ደሞ የምንኖረው ባንድ ቀበሌ ነበር-የመርካቶው መሳለሚያ እና ኳስ ሜዳ፡፡  አባቴ ያንን ሰፈር እስከለቀቀ ድረስ በተለይ ቅዳሜ እና እሁድ የምውለው እና የማድረው እዛው እሷ ቤት ነበር፡፡ የጉራጌዎችን ባህል እና ስነልቦና እስኪበቃኝ ያላበሰችኝ እትዬ ዘነቡ ናት፡፡

ሌላዋ እናቴ ትእግስት ናት፡፡ ትውልዷ ትግራይ ስለነበረ አማርኛ አትችልም ነበር፡፡ አባቴ ትግርኛ ቋንቋ ስለሚችል ችግር አልነበረበተም፡፡ ኾኖም ከኔ ጋር ስታወራ፣ እሷ በትግርኛ እኔ በአማርኛ እየተነጋገርን እናወራለን፣ እንግባባለን፡፡ ገበያ ይዣት የምሄደው እኔ ነኝ፡፡ ያን ግዜ እድሜዋ ካስራ ስምንት አይበልጥም፡፡ ትእግስት የትግራዋይን ባህል እና ስነልቦና አስተዋውቃኝ ለኤርትራዊቷ እናቴ አስረክባኝ ሄደች፡፡

ሸዋዬ ኤርትራ ተወልዳ ያደገች የዘመናዊ የሹራብ መስሪያ ባለቤት እና ባለሙያም ነበረች፡፡ ያን ግዜ የአስመራ ሹራብ ከኢትዮጽያ አልፎ በጎረቤት ሀገሮችም የታወቀ ነበር፡፡ ሸዋዬ አማርኛ ብትችልም በእናት ቋንቋዋ ትግርኛ መናገር ይቀላታል፡፡ እሷ በትግርኛ እኔ በአማርኛ፡፡ ዘግየት ብሎ ከአስመራ የመጣው ታናሽ ወንድሟ ሙሴ እና የወንድሟ ልጆች እነ አማኑኤል ወንድሞቼም ጓደኞቼም ናቸው፣ አንድ ላይ ነው የኖርነው፡፡ እናም የአዲስ አበባ ስብእናየ ከኤርትራውያን ስብእና ጋር ተጋምዶ አደግኹ፡፡

አንዲት የነገሌ ቦረና ሴት ካባቴ አንድ ልጅ ወልዳለች፡፡ ከርሷ ጋር አልኖርኩም፡፡ በ1968 ዓ.ም መጨረሻ አባቴ ለስራ ነገሌ ሲሄድ ይዞኝ ይሄዳል፡፡ ሴትዮዋ በወቅቱ ነገሌ ቦረና ከተማ ውስጥ ከነበሩት ጥቂት ምግብ ቤቶች የአንደኛው ባለቤት ነበረች፡፡  እዚያ ስንደርስ ወንድ ልጅ ወልዳ አራስ ቤት ነበረች፡፡ ወንድምህ ነው አለኝ አባቴ፡፡ ነገሌ ለአንድ ሳምንት ያህል ብቻ ቆይተን ወደ አዲስ አበባችን ተመለስን፡፡ ያችን ያባቴን ወዳጅ ብቻ ሳይኾን ያንን ጨቅላ ወንድሜን ከዚያ ጊዜ በኋላ አይቻቸው አላውቅም፡፡ ከጊዜ ብዛት የተነሳ የሴትዮዋን ስም ረስቼዋለኹ፡፡  ያ- የኢጆሌ-ቦረና ወንድሜ በህይወት ካለ አኹን አርባ አመት አካባቢ ይሆነዋል፡፡ ስሙንም ስለማላውቀው አብቹ ብዬ ልጥራው፡፡ አደራህን አብቹ! የኦሮሚፋ ተናጋሪ ማህበረሰብን ለመገንጠል ከሚጥሩ ቡድኖች ጋር እንዳትገጥም፡፡ ያባት ሀገር ግንድ ነው አይገነጠልም፡፡

የመጀመሪያ ደረጃ ትምህርት ቤት እያለኹ የነበሩኝ የጓደኞቼ የብሄር ስብጥር ብዙም ትዝ አይለኝ፡፡ ኾኖም ከተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ቤተሰቦች ሊመጡ እንደሚችሉ አልጠራጠርም፡፡  በወጣትነቴ የኢሕአፓ አባል የኾንኩት ገና የአስረኛ ክፍል ተማሪ እያለኹ ነው፡፡ ኢሕአፓ ደግሞ በዘር የሚሸነሽን ፓርቲ አልነበረም፡፡ ኢሕአፓ ከምስራቅ እስከ ምእራብ፣ ከደቡብ እስከ ሰሜን  የምንገኘውን የኢትዮጵያን ልጆች በአንድ ድስት ውስጥ ከታ ነበር ክሽን አድርጋ የሰራችን፡፡ ኢሕአፓ ከነስሙም የኢትዮጵያ ሕዝባዊ አብዮታዊ ፓርቲ ስለነበር እና የሀገራችን ዋነኘው ችግር የመደብ እንጅ የብሄር አይደለም ብሎ የተነሳ ፓርቲ ስለነበር ኹላችንም በጊዜያዊ ሕዝባዊ መንግስት  ገመድ ገምዶ አታገለን፡፡ በጣም ትዝ የሚሉኝ፣ በኢሕአፓ ውስጥ አብሬአቸው የሰራኹት፣ እኒያ ልጆችን ልጥቀስ፡፡ ሀጎስ እና ቴዎድሮስ ጸጋዬ ከትግራይ እና ከኤርትራ ቤተሰቦች፤ ጌታነህ ታደሰ፣ አበበ ማሞ እና አባይነሕ ኹነኛው ከአማራ፤ መሰረት ድሪባ፣ በቀለ ቶላ እና የትናየት ደቻሳ ከኦሮሞ ቤተሰቦች፤ መሀመድ ኢድሪስ ከጉራጌ፤ በኮድ ስሙ ሙላቱ እና ነጋሽ በቀለ ከደቡብ ቤተሰቦች ነበሩ፡፡ እስር ቤት ውስጥ የነበረንበትማ የሚደንቅ ነው፡፡ ወደ ሰማንያ ከሚደርሰው ብሄር በሉት ብሄረሰብ ልጆች ጋር አብረን መታሰር ብቻ  ሳይኾን አንድ ላይ ኖርን፤ ከጎረቤቶቻችን ከሱዳን እና ሶማሌዎች ጋር ሳይቀር፡፡

  • ኦሮምኛ ተናጋሪ ኦነግ፣ ኦሮምኛ ተናጋሪ ኢሕአፓ፣  ኦሮምኛ ተናጋሪ መኢሶን፣ ኦሮምኛ ተናጋሪ የኢሰፓ አባል፤
  • ትግርኛ ተናጋሪ ሻእቢያ፣ ትግርኛ ተናጋሪ ህውሀት፣ ትግርኛ ተናጋሪ ኢሕአፓ፣ ትግርኛ ተናጋሪ መኢሶን፣  ትግርኛ ተናጋሪ የኢሰፓ አባል፤
  • አማርኛ ተናጋሪ   ኢሕአፓ፣ አማርኛ ተናጋሪ መኢሶን፣  አማርኛ ተናጋሪ የኢሰፓ አባል፤
  • ጉራግኛ ተናጋሪ ኢሕአፓ፣  ጉራግኛ ተናጋሪ መኢሶን፣ ጉራግኛ ተናጋሪ የኢሰፓ አባል፤  
  • ሲዳምኛ/ወላይታ ተናጋሪ  ኢሕአፓ፣ ሲዳምኛ/ወላይታ ተናጋሪ መኢሶን፣ ሲዳምኛ/ወላይታ ተናጋሪ የኢሰፓ አባል፣ ወዘተ ወዘተ፤

እስር ቤት ውስጥ የኖርኩት ከላይ ከጠቀስኳቸው ከተለያየ ቋንቋ ተናጋሪ ቤተሰብ ከመጡ የኢትዮጵያ ዜጎች  ጋር ነው፡፡ ብንኳረፍ ወደን በመረጥነው የአላማ ልዩነት፤ ብንታኮስ ወደን በመረጥነው የአላማ ልዩነት ነው፤ ያ-ደሞ ያባት ነው፣ የሚጠበቅም ነበር፡፡ ሳንፈልግ በተወለድንበት ብሄራችን ሳቢያ አልተኳረፍንም፣ አልተቧቀስንም፣ አልተታኮስንም፡፡ አብዛኛው የዚያ ትውልድ አባላት በዋነኝነት ያቀነቅኑ የነበረው በመሬት፣ በዴሞክራሲ እና በህዝባዊ መንግስት ጥያቄ ላይ ነበር፡፡ ያን ተመርኩዞ ያ-ኹሉ ወጣት መጀመሪያ የንጉሱን ስርአት፣ ቀጥሎም የወታደራዊውን ስርአት በሕዝባዊ መንግስት ለመተካት ተናነቀ፡፡

የዚያ ትውልድ ልጆች  የተሰባሰቡት በዋነኝነት በኢሕአፓ፣ አንዲያም ካለ ደሞ በመኢሶን ውስጥ ነበር፡፡ የኹለቱም ፓርቲዎች ቁልፍ የስትራቴጂክ ጥያቄ ደግሞ የመሬት፣ የዲሞክራሲ እና ከፍ ሲልም የመደብ ጥያቄ ነበር፡፡ በእርግጥ የብሄር ጥያቄ አንዱ የሀገራችን ችግር ነው ብለው በፕሮግራማቸው ላይ አስፍረው ታግለውለታል፡፡ ኾኖም ጥያቄው የሚፈታው በሀገር ደረጃ በሚፈጠር የዴሞክራሲ ስርአት ነው የሚል እምነት ነበራቸው፡፡ ስለዚህ ያ-ትውልድ በነዚህ ኹለት ፓርቲዎች ውስጥ ኾኖ የታገለው ለሕዝባዊ መንግስት ነበር፡፡ አብዛኛው የዚያ ትውልድ አባላትም በቀይሽብር ያለቀው የህዝባዊ መንግስት ምስረታን ቀዳሚ በማድረግ በመታገሉ ብቻ ነበር፡፡

የቀይ ሽብር እልቂት ለጥቂቶቹ ጎጠኞች ተመቻቸው፡፡ የጎሳ ፖለቲካ አራማጆች የኾኑት የዚያ ትውልድ አባላት አንድ፣ ኹለት፣ ሶስት ተብለው የሚቆጠሩ ብቻ ሳይኾኑ፣ ቁጥራቸው ከአርባ እና ከሃምሳ የማይዘል፣ በስም የሚታወቁ የትውልዱ ቅራሪዎች ናቸው፡፡ እኒያ የትውልዱ እሪያዎች፣ የኤርትራን ማህበረሰብ እንወክላለን በማለት ሰባት እና ስምንት ኾነው ቀደም ብለው ድርጅት መሰረቱ፡፡ ሌሎች ሰባት እና ስምንት የሚኾኑ ወጣቶች ደሞ የትግራይን ህዝብ እንወክላለን ብለው ነፍጥ አነሱ፡፡ ኦሮሞ ነን የሚሉ በተመሳሳይ ሰባት እና ስምንት ኾነው ነጻ ሀገር እንመስርት ብለው ትግል ጀመሩ፡፡ ፋሽን ይመስል ሌሎች ሰባት-ስምንት የሚሆኑ የሶማሌ ወጣቶችም ሶማሌን/ኦጋዴን ለመገንጠል አመጹ፡፡ እንግዲህ እነዚህ ሰባት ስምንቶች የኢትዮጵያ ዋነኛው ችግር  የብሄር ጥያቄ ነው በማለት በየአቅጣጫው በረሃ ገቡ፡፡ ‹የኛን ቋንቋ ይናገራሉ› የሚሏቸውን በሺ የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን ሰብስበው ‹ደሀ እንድትኾን ያደረገኽ የአማራ ቋንቋ ተናጋሪ ነው› አሉት (የሻእቢያን፣ የህወሀትን እና የኦነግን የድርጅቶቻቸውን መመስረቻ ሰነድ ይመለከቷል)፡፡ ስንኩል እና ጎዶሎ ታሪክ እያጣቀሱ የገበሬውን ጦር ጋቱት፤ በኢትዮጵያዊ ዜግነት ላይ እንዲዘምትም አደረጉት፡፡ ያሰቡት የጦር ሜዳ ድል ለሁሉም ባይኾን ለኹለቱ ድርጅቶች ተሳካላቸው፤ ኤርትራም ተገነጠለች፣ ህወሀትም ቀሪውን የሀገራችንን አገር ገዛ፡፡

ከዚያ በኋላ እዳው ገብስ ነው እንዲሉ፣ ኢትዮጵያ የተጋመደችበትን ቋጠሮ ለመፍታት፣ ከ1983 ዓ፣ም በኋላ የነበረውን ትውልድ በዚያ ስንኩል እና ጎዶሎ ታሪክ ለሃያ ሰባት አመት ጠመቁት፡፡ ‹ነጻ የወጡትም፣ ነጻ ያወጡትም፣ ነጻ ያልወጡትም› አንድ ላይ ኾነው የኢትዮጵያዊነትን ፈትል በደነዘ ቢላ ገዘገዙት፡፡ ኢትዮጵያዊነትን ያቆራኙ እሴቶች  የሉም ብለው ካዱ፡፡ የጎጥ ክልል አስምረው፣ የጎጥ ፓስፖርት አደሉ፡፡ አማራ የሚሉትን ከኦሮሞ፤ ኦሮሞ የሚሉትን ከሶማሌ፤ ወላይታ የሚሉትን ከሲዳማ፤ ጉራጌ የሚሉትን ከጉራጌ ወዘተ ወዘተ መጤ-ሰፋሪ ብለው አፈናቀሉ፣ አዘረፉ፣ አሰገደሉ፡፡ በግልብ ትንታኔአቸውም ኢትዮጵያውያን የተጋመዱበትን ፈትል በጣጠስነው ብለው ፎከሩ፡፡ ቢሆንም፣ ቢኾንም ‹ተቻችላችኹ ኑሩ› እያሉ አሾፉብን፡፡

ያም ኾኖ፣ እኛ ኢትዮያውያን የተጋመድንበት የስነልቦና ቋጠሮ ውሉን ስላላገኙት ገዘገዙት እንጅ አልበጠሱትም፡፡ ኢትዮጵያዊነት አንደ ቀስተ-ደመና ህብረቀለማት የተሰናሳለ አልባሳት ይመስላል-ባለ ቀለማት ጥለት፡፡ ቀዩን ሲመዙት አረንጓዴው ይጠነክራል፤ አረንጓዴውን ሲስቡት ቢጫው ይበረታል፡፡ ከንቱ ድካም፡፡ ኢትዮጵያ የተቋጠረችበትን ውል እንፈታለን ብለው ደክመው አደከሙን፣ ቧጠው አስቧጠጡን፣ ጠልሽተው አጠለሹን፡፡ የጋራ አገር ብቻ ሳይኾን የጋራ ከተማ እና የጋራ ባንዲራ እንኳን እንዳይኖረን ዳከሩ፡፡              

የኢትዮጵያ ህዝብ በጣም የተሳሰረ ነው ሲባል፣ ለማለት ብቻ የሚነገር ይመስላል፡፡ ብዙዎቻችን ከምናስበው በላይ የኢትዮጵያ ዜጎች የተጋመድንበት ውሉ እጅግ ውስብስብ ከመኾኑም በላይ ቋጠሮው የትላይ እንደኾነ መለየት  ያስቸግራል፡፡ ለዚህም ነው ኢትዮጵያን ለመበታተን የተደረገው ተከታታይ ሙከራ ሲከሽፍ የምናየው፡፡ ኢትዮጵያን ለማፈራረስ ከተፈለገ ኢትዮጵያያውያን ተጋምደው የተቋጠሩበትን ውል ማግኘት ያስፈልጋል፡፡ ችግሩ የዚያን የቋጠሮ  ውል ማንም አያውቀውም፡፡

አማራው፣ ኦሮሞው፣ ጉራጌው፣  ትግሬው፣ ሶማሌው፣ ወላታይው ፣ሲዳማው፣ አፋሩ፣  ቤንሻንጉሉ ወዘተ በከፍተኛ ደረጃ የተጋመደ ነው፡፡ ይህ መጋመድ ግን በተለያዩ ብሄሮች መሀከል ያለውን የቋንቋ እና ሌሎች የማንነት መገለጫዎችን ደምስሶ እንደ ኮንዶሚኒየም ፎቆች አንድ ወጥ አላደረጋቸውም፡፡ ኢትዮያዊነት ልክ በሀበሻ ቀሚስ ላይ እንደምናየው  ባለ ቀለማት ጥበብ አንድ መደብ ላይ የተጠለፈ ነው፡፡ ጥበቡን ጥበብ የሚያደርገው የሁሉም ቀለማት ሰበዞች ተዋህደው ሲገኙ ብቻ ነው፤ አንዷን ክር ከመዘዝናት ጥልፉ ይበተናል፡፡ኢትዮጵያዊነትም እንዲኹ-አንዱን ብሄር ከኢትዮጵያዊነት ስናወጣው ምስቅልቅላችን ይወጣል፡፡ የኤርትራ የ30 አመት ጦርነት፣ የህወሀት እና የኦነግ የማይገነጠለውን ለመገንጠል እና ከኢትዮጵያ ተለይቶ መኖር የተደረገ ትግል  ያስከተለው ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ ቀውስ ለዚህ ምስክር ነው፡፡

የኢትዮጵያ ህዝብ የተጋመደበትን ፈትል ለመግለጽ የራሴን ታሪክ እንደምሳሌ ወስጃለኹ፡፡ ኾኖም ይኽ በቂ አይደለም፡፡ ምናልባት የኢትዮጵያን ብሄሮች እንዴት እንደተጋመዱ ባክልበት ምሉእ ያደርገው ይኾናል፡፡ በዚህ አጭር ጽኹፍ የኹሉንም ብሄሮች ታሪክ መግለጽ አይቻልም፡፡ ልክ እንደሎተሪ እጣ ኹለት ብሄረሰቦችን ብቻ አንስቼ በጣም ባጭሩ ልግለጽ-ወላይታ እና ጉራጌ፡፡ መጀመሪያ ከወላይታ ልጀምር፡፡

ማጣቀሻዬ የወላይታው ተወላጅ፣ ዋና ዋጌሾ፣ በ-1990 ዓ.ም. በጻፉት የወላይታ ህዝብ ታሪክ ከሚለው መጽሀፍ ነው፡፡     እስከቅርብ ግዜ ድረስ በወላይታ አካባቢ በየዋሻው ውስጥ ተደብቀው የሚገኙት ጥንታዊ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ንዋየ ቅድሳት መቼ እና እንዴት እንደመጡ በትክክል አይታወቅም፡፡ እንዳንድ ጸሀፊዎች  በግራኝ ወረራ ወቅት ንዋየ ቅድሳቱ ወደ ተለያዩ የሀገራችን ክፍሎች ሄደዋል፤ አንዱ እና ዋነኛው ወላይታ ነበር የሚሉ አሉ፡፡ ይህ ግምት እውነት የመኾን እድል ቢኖረውም፣ እኔ ግን ከዚያም በላይ በነበረ የኢትዮጵያውያን የመጋመድ ምክንያት ነው እላለኹ፡፡ ለዚህ ደግሞ ማስረጃ የሚኾነን  የሚከተለው ነው፡፡

የወላይታ ህዝብ 110 ከሚደርሱ የተለያዩ ጎሳዎች በመጡ ሰዎች የተመሰረተ ብሄረሰብ ነው፡፡ እነዚህ ማህበረሰቦች ለረጅም ክፍለዘመን አብረው ከኖሩ በኋላ ማላ እና ዶጋላ በመባል ሁለት ትላልቅ የወላይታ ነገዶችን ፈጥረዋል፡፡ የጥንቱ የወላይታ ንጉስ መቶሎሜ የአኹኑን ሰላሌ እና ፍቼን አልፎ ሰሜን ሸዋን ጭምር ያስተዳደር ነበር፡፡ እንደውም አንደኛዋ የሞቶሎሜ ሚስት፣ ከቡልጋ የማረካት (እግዚእሐርያ በመባል የምትጠራ የአቡነ ተክለኃይማኖት እናት) እንደነበረች ይታወቃል፡፡ እግዚእሐርያን ተከትለው የመጡ በርካታ አማሮች በወላይታ ሰፍረው ቀርተዋል፡፡ ዳሞቴዎች ከጎጃም ቡሬ የመጡ ጎጃሜዎች ናቸው፡፡ ካህናቱ ደግሞ የክህነት ስራቸውን ያለማቋረጥ በመስራት ከወላይታ ህዝብ ጋር ተቀላቅለው ኖረዋል፡፡ ቃልቻዎች  ከወሎ፣ ቡቡላ የሚባሉ ከቡልጋ፣ ጎንደሬዎች ከጎንደር፣ ኦሮሞዎች ከአርሲ እና ከጅማ፣ ትገሬዎች ከትግራይ፣ ሀዲያዎች ከሀዲያ፣ ማረቆ ተብለው የሚጠሩት እና ከወንጂ እና ከአካባቢው ወደ ወላይታ በብዛት ኼደዋል፡፡ አንዳንዶቹ የራሳቸውን እምነትን ይዘው ቢኖሩም ቀሪዎቹ የወላይታን ባህልና እምነት ሙሉ በሙሉ ወስደዋል፡፡ ያም አለ-ያ ኹሉም ወላይታነታቸውን ተቀብለው ነው የሚኖሩት፡፡

ታላቁ የወላይታ ንጉስ ካዎ ጦና፣ የትግሬ ዝርያ ቢኖርበትም፣ ህዝቡም ኾነ የታሪክ ጸሀፊዎች የሚያውቁት በወላይታነቱ ነው፡፡ ጋይም ሚካኤል የሚባለው የትግሬ ባላባት እህቱን ለወላይታው ንጉስ ለሊቼ ከዳረ በኋላ እዚያው ወላይታ ውስጥ ከነሰራዊቱ እስከመጨረሻው ኖሯል፡፡ የትገሬ ሰራዊት ከወለይታዎች ጋር ተደባልቆ የወላይታን ጦር እስከ አስራ-ሁለት ትውልድ ድረስ መርቷል፡፡ የካዎ ጦና መሰረትም ከዚያ ይመዘዛል፡፡  ካዎ ጎቤ ተብለው  የሚጠሩት ዝነኛው የወላይታ መሪ በወቅቱ የጂማ ኦሮሞ ንጉስ የነበሩትን ሴት ልጅ (አቤንቶ ዲጊቲ) አግብተዋል፡፡ በዚያን ጊዜ የንጉሱን ልጅ ተከትለው በርካታ የኦሮሞ ተወላጆች ወላይታ ውስጥ የመጡ ሲኾን፣  እስከመጨረሻው ከወላይታ ህዝብ ጋር በመጋባታቸው እና በመዋለዳቸው ወላይታ ኾነው ቀርተዋል፡፡ እንግዲህ ይህን መጋመድ ነው፣ ሰሚ ካገኘን፣ ኢትዮጵያዊነት የምንለው፡፡

ሌላው ብሄር ጉራጌ ነው፡፡ የጉራጌዎች ምንጭ ደግሞ ከወላይታውም የበለጠ የሚገርም ነው፡፡ ስለ ጉራጌ ህዝብ ታሪካዊ ምንጭ የተለያዩ ጸሀፍት የተለያየ ሃሳብ ሰንዝረዋል፡፡ ፖል ሔንዝ እንደሚለው የጉራጌ ህዝብ በአክሱም ዘመነ መንግስት የኢትዮጵያ አካል የነበረ ሲኾን የአክሱማውያን ሀይል እየተዳከመ ሲመጣ የጉራጌ ህዝብ ተነጥሎ በመቅረቱ ከግዜ ብዛት ቋንቋውና ባህሉ እየተለየ መጣ ይለዋል፡፡ ብራውክ ሃመፕር የተባለው የታሪክ ሰው ደሞ ክርሰቲያን የኾኑት የጉራጌ ማህበረሰብ አባላት የኢትዮጵያው ንጉስ የአምደጽዮን ወታደሮች ነበሩ፡፡ ምንጫቸውም  በዋነኝነት ጉራእ ከሚባለው የኤርትራ ክፍል ሲኾን፣ በኋላም በግራኝ ወረራ ወቅት ከጎጃም እና ጎንደር አካባቢ በመነሳት ወደ አኹኑ የጉራጌ ግዛት ለተወሰነ ወታደራዊ ተልእኮ ሄደው በዚያው ሰፍረው የቀሩ ናቸው፡፡  የሙስሊሞቹ ጉራጌዎች ምንጭ ደግሞ ከሃረር አካባቢ እና ማህበረሰብ (ሃርላ)   ተነስተው በአኹኑ የምስራቅ ጉራጌ ክልል የኖሩ ናቸው በማለት ጽፏል፡፡ እንግዲህ የጉራጌ ህዝብ ምንጭ ከኤርትራ ይሁን ከጎጃም፣ ወይም ከጎንደር ፣ ወይም ደግሞ ከሀረር  የዚህ ጽኹፍ የመከራከሪያ ነጥብ አይደለም፡፡ ቁም ነገሩ የጉራጌ ማህበረሰብ ከኢትዮጵያዊነት ጋር እንዴት አድርጎ እንደተጋመደ ለማሳየት ብቻ ነው፡፡

 የኦሮሞ እና የአማራ ማህበረሰብ ቁርኝት ደግሞ ልክ እንደ ወላይታው እና ጉራጌው ፍጹም አንድ አይነት እና ተመሳሳይ ነው፡፡ ጎጃሜዎች ከኦሮሞዎች ጋር፣ ጎንደሬዎች ከኤርትራ እና ከትግራይ ሰዎች ጋር፤ ሰሜን ሸዋዎች ከኦሮሞ፣ ከጉራጌ  ከሀዲያ እና ከሌሎች ብሄረሰቦች ጋር ተዋህደው እና ሊለዩ በማይቻልበት ደረጃ ተጋምደው ነው ኢትዮጵያን የሰሯት፡፡ በየትኛውም ዘመን የነበረ  የኢትዮጵያ ንጉስ ንፁህ ብሄር የለውም፡፡  ከመቶ አመታት በፊት ኢትዮጵያን ከገዙት ከንጉስ ሱስንዮስ እንኳን ብንጀምር፣ ንጉሱ የአንድ ብሄር ተወላጅ አልነበሩም፡፡ ጎንደርን ማእከል አድርገው በተከታታይ ከሰባ አመታት በላይ ኢትዮጵያን የመሩት  ኦሮሞች ምን ያህል ከጎንደሬዎች፣ ከኤርትራውያን ከትግራውያን እና ከጎጃሜዎች ጋር እንደተጋመዱ ማን ይኾን የሚያውቀው? እውን አጼ ቴዎድሮስ ጥርት ያሉ ጎንደሬ ናቸው? ቢያንስ ስልጣን ከመያዛቸው በፊት ጀምሮ ያገቧቸው ሴት የኦሮሞው የታላቁ ራስ አሊ ልጅ አልነበሩምን? እኝህስ ሴት ከባለቤታቸው ከአጼ ቴዎድሮስ ጋር በመኾን የኦሮሞውን ያባታቸውን ዙፋን ነጥቀው እራሳቸውን እቴጌ አላደረጉም?

ለመኾኑ ኢትዮጵያውያን የተቋጠሩበት ውሉ ያለው የት ላይ ይኾን? የፈረደበት የአማርኛ ቋንቋ ለበርካታ አመታት የቤተመንግስት ቋንቋ ሆነና (በጎንደር ቤተመንግሰት የኦሮሞ እና የትግሪኛ ቋንቋ መነገሩ ተረስቶ)  አማራ ገዛን የሚል ድቤ ይጎስማል፡፡ የኔ ቢጤ ተላላ አማራ ነኝ ባይ ደግሞ ኢትዮጽያን የሰራት አማራ ብቻ ነው ለማለት ይዳዳዋል-ሚስኪን፡፡ ሌላው ሚስኪን ‹ያልተቀላቀልኩ ንጹህ› ኦሮሞ ነኝ ባይ ደግሞ፣ ሶስት አራተኛው የኢትዮጵያ ግዛት በአማራ የተወረረ የኦሮሞ ግዛት ነው ይለናል፡፡ እነዚኹ ወገኖች በመላው ደቡብ፣ ምስራቅ ምእራብና ሰሜን በመስፋፋት ሌላው ብሄር አግብቶ፣ ወልዶ፣ ተዋልዶ እና ሰፍሮ እንዲያም ሲል ቋንቋውን አሰተምሮ የኖረውን የኦሮሞን ህዝብ፣ የቀይ መስመር ድንበር አበጅተው ያ ስፍራ የኦሮሞ ክልል ብቻ ነው  ይሉናል፡፡ ሌላው ተላላ ትግሬ ደሞ አማራው ሚኒሊክ ስልጣናችንን ነጥቆ ገዛን ይላል፡፡ የሚያወሩት በሬ ወለደ ውሸት እውነት እንኳን ቢኾን ለእኛ የ21ኛው ክፍለዘመን ኢትዮጵያውያን የሚመጥን መረጃ አይደለም፡ ይህች ጎንበስ ጎንበስ እንዲሉ-የብሄር ጥጋጥግ ፍለጋ ዋነኛ መነሻዋ የኢኮኖሚ የበላይነትን ለማግኘት እንደኾነ ‹በቀደም እለት› የተጠናቀቀው የህወሀት የ27 አመት የግዛት ታሪክ ምስክር ነው::

ለመኾኑ የአማርኛ ቋንቋ እና ባህልን ለአማራ ብቻ፣ የኦሮምኛን  ቋንቋ እና ባህልን ለኦሮሞ ብቻ፣ የሲዳማን ቋንቋ እና ባህልን ለሲዳማ ብቻ፣ የወላይታን ቋንቋ እና ባህልን ለወላይታ ብቻ፣ የትግርኛን ቋንቋ እና ባህልን ለትግሬ ብቻ፣ የአፋርን ቋንቋ እና ባህልን ለአፋር ብቻ፣ የጉራጌን ቋንቋ እና ባህልን ለጉራጌ ብቻ ወዘተ ማን ነው የሰጠው? አንዱ የአንዱን ብሄር ተወላጅ (በጋብቻ፣ በጉዲፈቻ፣ በምርኮ፣ በሰፈራ እና በመስፋፋት) ከቀላቀለ እና ቋንቋውን ካስለመደ በኋላ ስለራሱ ጎጥ ብቻ የሚሰብክ የየትኛውም የብሄር አባል የሞራል ብቃት የለውም፡፡ ኹሉም  ቋንቋዎች እና ባህሎች የኹሉም ኢትዮጵያውያን ናቸው፡፡ ሰማንያ ይኹኑ ዘጠና ቋንቋዎቻችን እና ባህሎቻችን የኹላችንም ቅርሶች ናቸው-ቅርሶቻችንን ደሞ እንጠብቃለን እንጅ አናጠፋም፡፡

ለመኾኑ የወሎው ንጉስ ሚካኤል፣ የጎጃሙ ንጉስ ተክለይማኖት፣ የሸዋው ልጅ እያሱ እና የወላታው ንጉስ ጦና የአንድ ብሄር ሰዎች ናቸው? ሚኒሊክ እና ቀዳማዊ ኃይለሥላሴንስ ማነው ያንድ ብሄር ሰዎች ናቸው የሚለው?  መንግስቱ ይለማርያምን፣ መለስን፣ ኃይለማርያምን እና አብይን ማን ነው ያንድ ብሄር ሰዎች ያደረጋቸው? አዳሜ ስነ ልቦናው እና ባህሉ ተጋምዶ እና በጋብቻ ተዋልዶ የብሄር ‹ደሙ› ከተበረዘ በኋላ፣ ‹የዚህ ወርቅ እና ጀግና ብሄር ተወላጅ በመኾኔ እኮራለኹ› እያለ ሊያጃጅለን ይሞክራል፡፡ ይኼንን የመቀላቀል ነገር እንደገና ወደ ራሴ በመውሰድ ምሳሌ ልስጥ፡፡ ነፍሱን ይማረውና የስጋ ዘመዴ ጋሽ አርጋው አንድ ቀን ‹አበበ ቢቂላ እኮ የኛ ዘመድ ነው› አለኝ፡፡

ጋሽ አርጋው አንዳንዴ ስለሚቀለድ የምሩን ነው ብዬ አላሰብኩም፡፡ ‹እናንተ የጅሩ ሰዎች ነን ትላላችኹ፣ እንዴት ኾኖ የቢቂላ ልጅ የስጋ ዘመዳችን ሊኾን ይችላል;›› ብዬ ጠየቅኹት፡፡

‹ቢቂላ እና ሚስቱ፣ አበበን ገና ከህጻንነቱ ጀምሮ በጉዲፈቻ ያሳደጉት ቤተሰቦች እንጅ በስጋ አይወልዱትም፡፡ ወላጆቹ የኛ የስጋ ዘመዶች የጅሩ ሰዎች ናቸው› አለኝ፡፡ ጋሽ አርጋውን አልተከራከርኩትም፡፡ ያም ኾኖ በፍጹም አላመንኩትም፡፡ ይሄንን ወሬ ነው ብዬም ለማንም አልተናገርኩም፡፡ ያም ኾኖ ውሸት እንዳይኾንብኝ፣ አንድ ቀን፣ የቅርብ ጓደኛዬ እና የስራ ባልደረባዬ የነበረው ኦሮሞው ዘካርያስ፣ ‹ምርጥ የሆኑት የኢትዮጵያ ሯጮች በሙሉ ኦሮሞዎች ናቸው› ካለኝ በኋላ፣ ከአበበ ቢቂላ ጀምሮ መቁጠር ጀመረ፡፡ ይኄን ጊዜ፣ ጣልቃ ገባኹና ‹እዚህ ላይ ታቆማለኽ፣ አበበ ቢቂላ አማራ እንጅ ኦሮሞ አይደለም› ብዬ ላበሽቀው ሞክሪያለኹ፡፡  ያን ቀን ጓደኛዬ ዘካርያስ፣ የቢቂላን ልጅ አማራ በማድረጌ፣ ከት ብሎ የሳቀብኝን እስከአኹን አልረሳውም፡፡

ወደ ነጥቤ ስመለስ፣ ከብዙ አመት በኋላ ነው፤ ሬዲዮ ሳዳምጥ የአበበ ቢቂላ በሮም ኦሎምፒክ የማራቶን ድል መታሰቢያ  ፕሮግራም ሲተረክ ሰማኹ፡፡ ጋዜጠኛው፣ አበበ ቢቂላ ከሮም እንደተመለሰ አየር መንገድ ላይ የሰጠውን ቃለመጠይቅ አሰማ፡፡ ቀጥሎም በቦታው ተገኝተው የነበሩት የአበበ ወላጆች ሰጥተውት የነበረውን የድምጽ ቅጅ አስከተለ፡፡ የአበበ ወላጅ አባት ናቸው ተብለው ቃለምልልስ ያደረጉት አቶ ቢቂላ ሳይኾኑ፣ የሰሜን ሸዋ የአማርኛ ቋንቋ ቅላጼ ያረበበባቸው ሌላ ሰው ነበሩ፡፡ እናቱ  የተባሉት ወይዘሮ ውድነሽም እንዲኹ፡፡ በጣም ገረመኝ፤ ጋሽ አርጋው ያጫወተኝ እውነት መኾኑ ገባኝ፡፡ ያም አለ-ያ፣ የአበበ ቢቂላን ኦሮሞነት ማንም ሊነጥቀው አይችልም፡፡ አበበ ማለት ማንም ይውለደው ማን፣ ቢቂላ ያሳደገው ኦሮሞ ነው፤ ከዚያ በላይ ግን አበበ ቢቂላ ኢትዮጵያዊ ነው፤ አራት ነጥብ፡፡ ይህን እውነተኛ ታሪክ እንደምሳሌ ያነሳኹት፣ የኢትዮጵያ ህዝብ የተጋመደበት ውሉ እና ቁርኝቱ እጅግ ውስብስብ መኾኑን ለማሳየት ብቻ ነው፡፡

   ያለመታደል ኾኖ የኛን ቋንቋ የማይናገር ጀግናን ጥላሸት መቀባት እንወዳለን፡፡ የሚገርመው ያ-የሌላ ብሄር ጀግና የተባለ ሰው ታሪኩ ሲጠና የራሳችን ኾኖ ያርፈዋል፡፡ የጋራ ጀግና እና አርበኛ ሞልቶን እና ተትረፍርፎን በጋራ እንዳንዘክረው የተደረገበት መንገድና ኹኔታ እርግማን ነው ያሰኛል፡፡ በመዲናችን በአዲስ አበባ ሀውልት የሰራንላቸውን ሰማእቱን አቡነ-ጴጥሮስን አማራ አይደሉም፤ የጎጃሙ ንጉስ፣ ንጉስ ተክለኃይማኖት አማራ አይደሉም፣ የወላይታው ንጉስ ጦና ወላይታ ብቻ አይደሉም ወዘተ ወዘተ ብዬ በመከራከሬ ስንቱ ጎጠኛ በዚያ 27 አመት ተቀይሞኛል!!!! ለነገሩ እኔ፣ ያኔም ኾነ አኹን አልተቀየምኩም፡፡

ከምእራብ፣ ከምስራቅ፣ ከደቡብ እና ከሰሜን በመነሳት አንዱ ብሄር ሌላውን፣ በንግድ፣ በጦርነት፣ በምርኮ፣ በጋብቻ፣ በጉዲፈቻ በሰፈራ እና በመሳሰሉት ምክንያቶች ለብዙ ክፍለዘመን ተቀላቅለን እና ተጋምደን ኢትዮጵያን ከመሰረትን በኋላ፣ የብሄርን ጥግ ለመታከክ መሞከር (ያውም በ 21ኛው ክፍለዘመን) የጤና አይመስለኝም፡፡ ለማንኛውም አኹን ብርሃን ይታየኛል፡፡ ብርሃንን ካየኽ ተከተለው እንዲል የጥንቱ ፈላስፋ፤ እኔም እንደ መላው የሃገራችን ዜጎች ብርሃን እየተከተልኩ በተስፋ ተሞልቻለኹ፡፡

 

በቃኝ!!!!!!

Filed in: Amharic