>

የምሕላ ጥሪ (ከይኄይስ እውነቱ)

ምሕላ ጥሪ

ከይኄይስ እውነቱ

ታላቁ ሊቅ አለቃ ኪዳነ ወልድ ክፍሌ ‹‹መጽሐፈ ሰዋስው ወግስ ወመዝገበ ቃላት ሐዲስ›› በተባለው መጽሐፋቸው ‹‹ምሕላ›› ልመና፤ ምልጃ፤ የማኅበር፣ የሕዝብ ጸሎት፤ እግዚኦታ፡፡ በማለት ፍቺ ሰጥተውታል፡፡ (ገጽ 583)

እንደ ኢትዮጵያ ኦርቶዶስ ተዋሕዶ ቤ/ክርስቲያን ሥርዓት ምሕላ የሚደረግባቸው ጊዜያት የተደነገጉ ቢሆንም ባገር ላይ መዐት፣ መቅሠፍት፣ አባር ቸነፈር፣ የሰላም እጦትና አለመረጋጋት የመሳሰሉት የተፈጥሮም ሆኑ ሰው ሠራሽ ጥፋቶች ሲኖሩ በቤ/ክርስቲያኒቱ የበላይ አካል እየታወጀ መድኅን የተገኘበት መሆኑ ለምእምናን እንግዳ ጉዳይ አይደለም፡፡ ይኽች ቤ/ክርስቲያን ሉዐላዊ በምትለው የቅዳሴ ጸሎቷ፤ ‹‹መቅድመ ኅሡ ሰላማ ለብሔር፡፡›› ከሁሉ አስቀድማችሁ ለብሔር (ለሀገር) ሰላም ጸልዩ ትላለች፡፡

በእስልምናውም ቢሆን ለአገር ዱዐ ማድረግ የተለመደ ነው፡፡ በጁምአ ሰላተ ቊኑት ማድረግ እንግዳ አይደለም፡፡

በእስልምናውም ሆነ በክርስትናው የጸሎት ግዳጅ ፈጻሚነትን መሠረት በማድረግ እና አገራችን ኢትዮጵያ የምትገኝበትን ወቅታዊ ሁኔታ ግምት ውስጥ በማስገባት የእምነት ተቋማት በሙሉ ቢቻል ከመጪው ማክሰኞ ወይም ረቡዕ ጀምሮ ለሦስት ቀናት የሚቆይ ከጾም ጋር የተባበረ ምሕላ በመላው ኢትዮጵያ ቢደረግ ፈጣሪ ባገራችን ያንዣበበውን የጥፋት ደመና በምሕረቱና ይቅርታው ይገፍልናል የሚል እምነት ስላለኝ የእስልምናውም ሆነ የክርስትናው ሃይማኖቶች አመራር ላይ የምትገኙ አባቶች በጥብቅ እንድታስቡበት ወንድማዊ ጥሪዬን በታላቅ አክብሮት አቀርባለሁ፡፡

እንደየእምነታችን በብሔራዊ መልኩ ቢደረግ ፋይዳው ታላቅ ነው፡፡ ለበጎ ካሰብነው ለመፈጸም አይከብደንም፡፡ እንደየእምነታችን በነፃነት ሥርዓተ አምልኮአችንን መፈጸም የምንችለው እኮ የኹላችን የጋራ ማምለኪያ ዓፀድ የሆነች አገራችን ኢትዮጵያ በሰላም ባንድነት ህልው ስትሆን አይደለም?  

Filed in: Amharic