>
11:02 pm - Tuesday August 16, 2022

ብአዴን ከተንበርካኪነት ወደ ተራማጅነት!!! (ሀይለገብርኤል አያሌው)

ብአዴን ከተንበርካኪነት ወደ ተራማጅነት!!!
ሀይለገብርኤል አያሌው
ብአዴን (አዴፓ) በሕወሃት ሳንባ እየተነፈሰ የባርነት ጉዞውን እንዲቀጥል በፊትም በሗላም አመራሩንን ይዘውሩ የነበሩት ጸረ ሕዝቦቹ እነ በረከት ስሞንና ጀሌዎቹ ከድርጅቱ ተመንጥረው እንዲወገዱ የተካሄደው ሕዝባዊ ግፊትና የድርጅቱ አመራር ቁርጠኝነት ወደ ላቀ የታሪክ ምዕራፍ አሸጋግሮታል::
የቀድሞ ብአዴን የአሁኑ (አዴፖ) ከተቸነከረበት የሕወሃት የቁም እስር በሕዝብ ትግል ተላቆ ወደ ሕዝብ እቅፍ ለመግባት ተቃርቧል:: ያለፈው ዘመን የድርጅቱን ታሪክ ለታሪክ ትተነው በሃገሪቷ ውስጥ ለሚካሄደው ለውጥ እያስቀመጠ ያለውን አሻራ በማጉላት ልንደግፈው ይገባል::
የሕወሃት የሴራ ፖለቲካ ከሽፎ ከጨዋታው ሜዳ እንዲገለል (በኦዴፓና በአዴፓ)በአብይና በለማ በደመቀና በገዱ የተቀየሰው ስትራቴጂና የተወሰደው እርምጃ ዛሬ ላለንበት የለውጥ ሁኔታ አድርሶናል:: የለውጡ መሪ ዶር አብይ ቢሆንም አቶ ደመቀ እራሱን ከጠቅላይ ሚንስትርነት በማቀብ አብይ እንዲመረጥ በማድረጉ በፖለቲካ ታሪካችን አዲስ ምዕራፍ ከማስመዝገቡም በላይ የለውጡ ቀያሽ መሃንዲስ በመሆን ታላቅ ገድልም ፈጽሟል::
የሳይበር ጀብራሬዎችና ጮርቃ ብሄረተኞች የኛ ያሉት መንጋ ያለ እነዚህ  መሪዎች ተሳትፎና ቅንጅት ባይታገዝ ኖሮ ዛሬም ከሕወሃት አፈና ባልወጣን ነበር::
ብአዴን አዲሱ መጠሪያው አዴፓ በተጀመረው የለውጥ ጉዞ ውስጥ የበለጠ ተጠናክሮ ሃገር የማረጋጋት አቅም እንዲፈጥር  በውሃ ቀጠነ በትችት ከመጎንተል ይልቅ ከጎን ሆኖ ሂሳዊና ሞራላዊ ድጋፍ መስጠቱ የተሻለ እንዲሰራ ያግዘዋል::
ብአዴን (አዴፓ) በሕወሃት ሳንባ እየተነፈሰ የባርነት ጉዞውን እንዲቀጥል በፊትም በሗላም አመራሩንን ይዘውሩ የነበሩት ጸረ ሕዝቦቹ እነ በረከት ስሞንና ጀሌዎቹ ከድርጅቱ ተመንጥረው እንዲወገዱ የተካሄደው ሕዝባዊ ግፊትና የድርጅቱ አመራር ቁርጠኝነት ወደ ላቀ የታሪክ ምዕራፍ አሸጋግሮታል::
ከማንም በፊት ብአዴን እንዲሞረድ እንዲስተካከልና ከሕወሃት እስር ቤት እንዲላቀቀ ለአመታት በስውር ከቅርብ ግዜ ወዲህ ደግሞ በይፋ የምንችለውን ስንጥር የቆየን ጥቂት ወገኖች አለን::
ዛሬ ሃገር ቤት ገብተው እጅ የመስጠት ያህል የተንበረከኩት ትግሉን መኖሪያ ያደረጉ ጡረተኞችና ማንነታቸውን በቅርብ ያወቁ እርጥብ ብሄረተኞች ያለ የሌለ ውግዘት ሲያደርጉብን ነበር:: አሁንም እነዚሁ ሃሳብ አልቦ መንጋዎች የለውጡን ሂደት ለማወሳሰብ አላስፈላጊ ውዥንብር ለመፍጠር አይሳካም እንጂ ጥረት እያደረጉ ነው::
ወቅቱ የድርጅትና የቡድንን ስብዕና የመገንቢያ የፖለቲካ ውድድር ግዜ ሳይሆን በሃገርና በሕዝብ ሕልውና ላይ የተከፈተውን የጥፋት ዘመቻ ለመመከት እጅ ለእጅ ተደጋግፈን የምንቆምበት ሁኔታ ውስጥ ነን:: የአንድነት ፖለቲካ ይሁን የብሄር አደረጃጀት በአንዲት ኢትዮጵያ ሃገራዊ ሉአላዊነት ላይ እስከተስማማን ድረስ ሃገር ለማዳን በጋራ የማንቆምበት ምንም ምክንያት አይኖረንም ::
ትላንት አምርረን  የታገልነውን ብአዴንን(አዴፓን) ዛሬ ልንደግፈውና ከጎኑ ለመቆም ስንነሳ የሕዝብን ጥያቄ በመቀበሉና እራሱን ለማስተካከል በመሞከሩ ነው::
ከእንግዲህም አዲሱ የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ አመራር በክልሉ ጸጥታና ልማት ባሻገር ጠንካራ ሃገራዊ ትስስር የሚፈጠርበት አቅጣጫና የሕዝብ ለህዝብ ግንኙነትን በማጠናከር ሃገሪቷን ሊያፈነዳት ያበጠውን ጠባብ ብሄረተኝነት ለማስተንፈስ ከአጋር ፓርቲዎች ጋር በመተባበር በኢትዮጵያዊነት ፕሮጀክት ላይ ትኩረት አድርጎ እንዲሰራ ግፊት ሊደረግበት ይገባል::
አማራው በታሪኩ ሰውን በሰውነቱ የሚቀበል አኩሪ ባህል ያለው በመሆኑ በክልሉ የሚኖሩ የሌሎች ብሄረሰቦችን መብት በሕግ የተከበረ እንዲሆን ከአድሎና ከቡድን የጸዳ የህግ ጠገግ ሊያበጅ ይገባል::
ከሕወሃት ነጻ መውጣት ማለት ያደፈውን የልዩነት ፖለቲካ ማርገብ ማለት ነው:: ወያኔ የዘራውን የጥላቻ መርዝ ነቃቅሎ አብሮነት እንዲያቆጠቁ ማድረግ ሲቻል ነው ለውጡ ለውጥ የሚሆነው::
ትንሹ ሕወሃት ትልቁን ሕዝብ እረግጣ ለመግዛት ያስቻላት የጥላቻ ትርክቷና የከፋፍለህ ግዛው እስትራቴጂዋ ነው:: ሕወሃትን የሚገልና የሚቀብራት የኢትዮጵያውያን አንድነት ሲረጋገጥ ነው:: ይህው ገና በአብይ የመደመር ጅማሮ መላላጥ ጀምራለች::
ስለሆነም የሕዝብና የሃገር ጠላቶችን ዘራፊና ገዳዮችን የሚያዳክማቸው አንድነት  ከሆነ እሱን ማጠናከሩ የቅድሚ ትኩረት ሊደረግበት ይገባል::
የአጭርና የረጅም ግዜ መርሃ ግብር ዘርግቶ በሂደት ኢትዮጵያዊነትን በጠንካራ መሰረት ላይ ለማነጽና የልዩነት ድንበሩን ለማጥበብ ተግቶ በመስራት የአማራ ዲሞክራሲያዊ ፖርቲ ታሪክ ያስመዘግባል የሚል እምነት አለኝ::
እግዚአብሄር ይርዳን!!!
Filed in: Amharic