>

ገራፊ እና ተገራፊ - አሳሪ እና ታሳሪ ከየፓርቲያቸው ለማእከላዊ ኮሚቴ ተመርጠዋል!!

ገራፊ እና ተገራፊ – አሳሪ እና ታሳሪ ከየፓርቲያቸው ለማእከላዊ ኮሚቴ ተመርጠዋል!!

ቢ.ቢ.ሲ አማርኛ

ከወራት በፊት ከእስር የተፈቱት አቶ መላኩ ፈንታ እና ጀነራል አሳምነው ፅጌ ጨምሮ ያልተጠበቁ ግለሰቦች የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ሆነው ተመረጡ።

አዴፓ ለቀናት ድርጅታዊ ጉባኤውን ባህርዳር ውስጥ ሲያካሂድ ቆይቶ ዛሬ ይፋ እንዳደረገው ለዕጩነት ከቀረቡት መካከል በፈቃዳቸው ለመልቀቅ ጥያቄ አቅርበው የነበሩት ምክትል ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ደመቀ መኮንንና የክልሉ ፕሬዚዳንት አቶ ገዱ አንዳርጋቸው ይገኙበታል።

ፓርቲው በተጨማሪም አቶ ደመቀ መኮንንን የፓርቲው ሊቀመንበር አድርጎ ሲመርጥ አቶ ገዱ አንዳርጋቸውን ደግሞ ምክትል ሊቀመንበር አድርጎ ሰይሟል። አዴፓ ለፓርቲውና ለኢህአዴግ ስራ አስፈፃሚ አባልነት አስራ ሶስት ሰዎችን አሳውቋል።

ለማዕከላዊ ኮሚቴ አባልነት ከተሰየሙት ውስጥ የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባዋ ወ/ሮ ዳግማዊት፣ የአማራ ክልል ኮሚኒኬሽን ቢሮ ኃላፊ አቶ ንጉሱ ጥላሁን፣ የብሔራዊ ባንክ ገዢ ዶክተር ይናገር ደሴ፣ በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ መምህር የሆኑት ዶክተር ስዩም መስፍን እና የአዲስ አበባ መገናኛ ብዙሃን ውስጥ የሥራ ኃላፊ የሆኑት ወይዘሮ እናታለም መለሰ ይገኙበታል።

ለጉባኤው የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል እንዲሆኑ የቀረቡት 75 ግለሰቦች የነበሩ ሲሆን ከእነዚህም መካከል አስሮቹ ሲቀሩ 65ቱ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባል ሆነው ተመርጠዋል።

ከድርጅቱ ነባር አመራሮች መካከል አቶ ከበደ ጫኔ፣ አቶ መኮንን ወሰንየለህ፣ ወ/ሮ ፍሬህይወት አያሌው፣ ወ/ሮ ብስራት ጋሻው ጠና፣ አቶ ጌታቸው አምባዬ፣ ወ/ሮ ዘነቡ ታደሰ፣ አምባሳደር ካሳ ተክለብርሃን ከድርጅቱ እንዲሰናበቱ ተወስኗል።

በሌላ በኩል የደቡብ ኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲያዊ ንቅናቄ (ደኢህዴን) የቀድሞውን ጠቅላይ ሚንስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝን ጨምሮ 23 የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላቱን አሰናብቷል።

በሀዋሳ ከተማ እያተካሄደ ባለው ጉባኤ ከተሰናበቱት ነባር አመራሮች መካከል አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ፣ ሽፈራው ሽጉጤ፣ አምባሳደር ተሾመ ቶጋ፣ ሲራጅ ፈጌሳ፣ አምባሳደር ሬድዋን ሁሴን እና መኩሪያ ኃይሌ ይገኙበታል።

ማእከላዊ ኮሚቴ እስከ 10ኛው ድርጅታዊ ጉባዔ በእግድ እንዲቆዩ አድርጓቸው የነበረውን አቶ ሳሙኤል ደምሴ፣ ከሰተብርሃን አድማሱ (ዶ/ር) እና ወ/ሮ አማረች ኤርሚያስን ከድርጅቱ አሰናብቷል።

ከባለፈው ረቡዕ ጀምሮ በመቀሌ ሲካሄድ የቆየው 13ኛ የህዝባዊ ወያነ ሃርነት ትግራይ (ህወሃት)ድርጅታዊ ጉባኤም ዛሬ ተጠናቋል።

ሕወሓት ዶ/ር ደብረፅዮንና ወ/ሮ ፈትለወርቅ ሊቀ-መንበርና ምክትል ሊቀ-መንበር አድርጎ መርጧል።

ከዚህ በተጨማሪም ድርጅቱ አቶ ጌታቸው ረዳ፣ አቶ ጌታቸው አሰፋ፣ ወ/ሮ ኬሪያ ኢብራሂም እና አዲስዓለም ቤለማ (ዶ/ር) ጨምሮ 11 አባላትን ለኢህአዴግና ለሕወሓት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴዎች አባላትን መርጧል።

ነገር ግን ከአስራ አንዱ ሥራ አስፈጻሚዎች ሁሉም ነባር የድርጅቱ ታጋዮች ሲሆኑ አንድም አዲስና ወጣት አባል አለማካተታቸው ታውቋል።

ሕወሓት ቀደም ሲል የነበረውን የድርጅቱን የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ቁጥርን ከ45 ወደ 55 ያሰደገ ሲሆን ከእነዚህ ውስጥም 15 የሚሆኑት ወጣትና አዳዲስ የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ናቸው።

የድርጅቱ ሊቀመንበር ደብረጽዮን ገ/ሚካኤል በጉባኤው ማጠናቀቂያ ላይ ባደረጉት ንግግር ጉባኤው ዴሞክራሲያዊ ትግል የተደረገበት እና ታሪካዊ ነበር ብለዋል።

Filed in: Amharic