>

“እርካብና መንበር” - ሙሴ እና ዐብይ* (ክንፉ አሰፋ)

“እርካብና መንበር” – ሙሴ እና ዐብይ*

ክንፉ አሰፋ

         ሳይታሰብ ብልጭ ብላ እንደገና ድርግም ያለችው የለውጥ ጭላንጭል፣ በእያንዳንዱ ልብ ውስጥ ተቋጥራ የነበረች የተስፋ ስንቅንም ይዛ ጭልጥ ያለች ይመስላል። አዕምሯችን ይህንን  ቅጽበታዊ ለውጥ ለመቀበል ቢቸግረውም፣ በሌላኛው መነጽር ስንመለከተው ግን ይህ ሊሆን ግድ ይላል። በተዓምር የቆመች የዚህች የደም ምድር እጣ ፈንታን መጽሃፉ በአንዲት ምዕራፍ ውስጥ እንደቋጫት እንገነዘባለን። አይናችንን በደንብ ካልገለጥን ግን ነገሩን ላናየው እንችላለን። ስለዚህ መፅሐፉን ማንበብ ብቻ በቂ አይደለም። መረዳትንም ይጠይቃል። በደንብ የተረዳው ሰው፣ በለሆሳስ የተላለፈ መልዕክቱን ያገኘዋል።

         መልዕክቱም ግልጽ ነው። የነጻነት ተጋድሎ። በዚህ ፍልሚያ ውስጥ ሶስት ተዋንያን ይኖራሉ።  ተሻጋሪ ሕዝብ፣ አሻጋሪ ሰው እና አሳዳጅ ሃይል። ከብዙ ትንቅንቅ እና ተጋድሎ በኋላ የአሳዳጁ ገቢር ከትዕይንቱ ይወጣና ሁለቱ ይቀራሉ። ተሻጋሪ እና አሻጋሪ በተራቸው መድረኩን ተቆጣጥረው የሚከውኑበት አሳዛኝ ትዕይንት ውስጥ እንገባለን። ሙሴ፣ የእስራኤል ሕዝብ እና ፈርኦን። ፈርኦን ቀይ ባህር ላይ ሰጥሞ ቀርቷል። ሙሴ ያንን እጅግ አስቸጋሪ ሕዝብ እየመራ በረሃውን ያቋርጣል..

         ዐብይ፣ ሕዝቡ እና ህወሃት። የአሳዳጁ ገቢር ገና ከትዕይንት ጨርሶ አልወጣም። ይህ ገቢር በትዕይንቱ ውስጥ እስካለ ድረስ፤ “ሕዝቤን ልቀቅ” የሚለው ምእራፍ ገና አልተዘጋም። በዚህ መሃል የተወረወረ አንድ ውብ ጥቅስ የሁሉንም ቀልብ ይስባል።  “ባርነትን ችሎ የነበረ ሕዝብ፣ ነጻነትን መሸከም አቅቶታል!”። (ለማ መገርሳ)

         የ“እርካንብ እና መንበር” ደራሲ ስለ በትረ-ሙሴ እና ጀነራል ፓርክ በዚህ መጽሃፍ አንስቶ በስፋት ሄዶበታል። ጸሃፊው ይህንን ጉዳይ ያነሳው ያለ አንዳች ምክንያት አልነበረም። ይህ ታሪክ መለኮታዊ ነው። ታሪኩ ትንግርታዊ ነው። ታሪኩ መንፈሳዊም ነው። ጉዳዩን ከአሁንዋ ቅጽበት ጋር እያጣቀስኩ፤ ጠለቅ ብዬ ከማየቴ በፊት የመጽሃፉን ይዘት በወፍ በረር ልቃኝ።

         በተለይ ስለ አመራር ጥበብ ዳጎስ ያሉ ማለፍያ መልዕክቶችን ይዟል።  ከግዜ በኋላ የጸሃፊው ማንነት ሲገለጽ፣ መጽሃፉ ለምን የአመራር ፍልስፍና እና ጥበብ ላይ እንዳተኮረ እንገነዘባለን። “ዲራአዝ” በሚል የብዕር ስም የወጣው የዚህ መድብለ ሃሳብ ደራሲ ዶ/ር ዐብይ አህመድ መሆናቸው አሁን ይፋ ሆኗል።  ጠቅላይ ሚኒስትር ዐብይ “እርካብ እና መንበር”ን ራሳቸው ስለመድረሳቸው በይፋ ባይነገሩም መጽሃፉ መታሰቢያነቱ ለ”ትዝታ እና ዝናዬ” (እናት እና ባለቤታቸው) ማድረጋቸው ድርሰቱ የሳቸው አሻራ ስለመሆኑ አንዱ ምስክር ነው። በሰኔ 20 ቀን 2010 ዓ.ም በጽ/ቤታቸው አዳራሽ ለተሰበሰቡ የኪነ ጥበብ ባለሞያዎች፤ የመጽሃፉ ደራሲ ራሳቸው መሆናቸውን ስለመናገራቸውም ተዘግቧል። በዕለቱ የተወሰኑ ኮፒዎች ላይ እየፈረሙ ለአርቲስቶቹ አድለዋል።

         “እርካንብ እና መንበር” ኢ- ልቦለድ መጻህፍ ይሁን እንጂ የአጻጻፍ ስልቱም ሆነ ይዘቱ ከለመድነው ደረቅ የፖለቲካ ሃተታ ወጣ ያለ ነው። በውስጡ የያዘው መሰረታዊ መልዕክት ስለ መሪነት ጥበብ ይሁን እንጂ ተምሳሌታዊ እሳቤን የቋጠሩ ቁልፍ ምዕራፎችም አሉበት። የታዋቂ ሰዎች ጥቅሶች፣ ግጥሞች እና አባባሎች፣ ተረት እና ምሳሌያዊ አነጋገሮች ታክለውባታል። በአንበሳ የሚመሰለው የጀግንነት እና የጀብደኝነት ባህል፤ ሃይል እና ጭካኔ የበዛበት የኢትዮጵያ ስልጣን ስርዓት ትኩረት ተሰጥቶበታል።

         ጸሃፊው በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ያላቸው ጥልቅ ግንዛቤ ድንቅ ነው። ሚዛናዊም ነው።  ከአብዛኞቹ የኦሮሞ ልሂቃን የሚተረከው የበዳይነት እና የተበዳይነት፣ የከሳሽ እና የተከሳሽነት ስሜት የወጣ አተያይ በመሆኑ ሚዛናዊነቱ ምስካሬ አያሻም። በተለይ ደግሞ ስለ አጼዎቹ ዘመነ መንግስት እና በትረ-ስልጣን የነጠሩ ሀሳቦችን እያፈለቀ ግንዛቤ ያስጨብጣል። እያንዳንዱ መሪ ወደላይ የወጣበት እርካብ እና የተቀመጠበት ዙፋን፣ በጎም ይሁን መጥፎ፣ ግን የራሱ የሆነ የታሪክ አሻራ ጥሎ አልፏል። መሪውን ዝቅ እና ከፍ የሚያደርገው የሄደበት መንገድ፣ የከወናቸው ተግባራት እና የነበረው ራዕይ እንጂ ዘውጋዊ ማንነቱ አለመሆኑን ያስረግጣል። በአንበሳ እየተመሰለ የሚቀርበው የጀብድነትን አተያይ እና ዘውዳዊ ጭካኔን በአሉታዊ መልኩ ይጠቅሳል።

         መጽሃፉ ስለ ትላንታችን በስሱ ይዳስሳል። ከአጼ ቴዎድሮስ ዘመነ መንግስት ጀምሮ በኢትዮጵያ የተከሰቱት መንግስታትን የአገዛዝ ዘይቤ ይቃኛል። የገዢዎቹን ስልተ-አመራር እያነሳ ፣ ርዕዮታቸውን በበጎም ሆነ በክፉም ይገልጻቸዋል። የሚኮነነውንም በነጠሩ ሃሳቦች ይኮንናል፤ የሚመሰገነውን ደግሞ ያመሰግናል እንጂ እንደሌሎቹ ሁሉንም በዜሮ አያባዛውም።

        የተሳካ መሪ ሊኖረው የሚገባው የመሪነት መስፈርቶችን መጽሃፉ ይዘረዝራል። ስልጣንና ሃይልን ለመጠቀም መሪ መሆን እንደሚያስፈልግ ይነግረንና እንዴት መሪ መሆን እንደሚቻል፤ ብቁ ለመሆን ምንና ምን እንደሚያስፈልጉም ይጠቅሳል። መሪ መሆን የሚሻ ወይንም የሚችል ሰው  የመምራት ሥራቸውን የሚጀምሩት ዛሬውኑ መሆኑን ሲገልጽ፤

“ከዕለታት በዚህ ቀን መሪ እሆናለሁ”  ከሚል የቅዠት እስር ቤት መውጣት አለበት። ምክንያቱም ከዕለታት አንድ ቀን የሚባል ቀን የለም። በህይወት ውስጥ የተሰጠችን እምር ዕድሜ ዛሬ፣ ነገ ወይም ከነገ ወዲያ እንጂ ከዕለታት አንድ ቀን አይደለም።” (ገጽ 79)

አንድ ሰው ፍላጎት ወይንም ችሎታ ስላለው ብቻ የአገር መሪ ሊሆን እንደማይችል የሚያብራራው ክፍል፤ ኃላፊነት ለመቀበል የተዘጋጀ ጽኑ ልብ መኖር እና ለመሪነት መጠራትን እንደ አይነተኛ መስፈርቶች ይውስደዋል።

         በምዕራፍ ስድስት ላይ የምናገኘው ረቂቅ ሃሳብ ቀልብ ይስባል። ሙሴ እስራኤላውያንን በፈርዖን ግዛት ከነበሩበት ባርነት አላቅቆ ወደ ተስፋይቱ የከነዓን ምድር እየመራ ሲያሻግራቸው የገባባትን ፈተና በዚህ ምዕራፍ እናያለን። ሙሴ እስራኤላውያንን እየመራ ከግብጽ ባርነት ነጻ አውጥቷቸዋል፤ የቃል ኪዳኑ ሕግጋትን ሲቀበል፤  ከፈጣሪ እና በሕዝቡ መካከለኛ ሰው በመሆን አገልግሏል፤ እንዲሁም እስራኤልን እስከ ተስፋይቱ ምድር መዳረሻ መርቷል። የከነዓንን ምድድር ግን ሳይረግጥ ነው ያለፈው። የእስራአኤል ሕዝብ ወደ ተስፋይቱ ምድር የገባው በተነገረለት በ40 ቀናት ሳይሆን፣ ይልቁንም በአርባ አመታት እንደነበር ታላቁ መጽሃፍ ይነግረናል። ከመአተ-መአታት በኋላ ከድንቁርና እና ከፈርኦናዊ ባርነት የወጣው ሕዝብ ግን መቋጫ የሌለው ጥያቄ እየደረደረ ሙሴን በእጅጉ ይፈታተነው ነበር። በመጨረሻ ሙሴ በበረሃው ውስጥ ከዋተተ በኋላ ወደ ተስፋይቱ ምድር ወደ ከነዓን ሳይደርስ ሕይወቱ አልፋለች።

         ወገኑን ከፈርኦን ግፍ እና ባርነት አላቅቆ ወደ ተስፋይቱ ምድር ሲያሻግር፤ ሙሴ የተደቀነበትን የማያቋርጥ እና እልህ አስጨራሽ ትንቅንቅ በስፋት ተሂዶበታል። እስራኤላውያን በግብጽ ምድር የዘላለም ባርያ ነበሩ።  የፍትሕ መንገዳቸውን ሁሉ ዘግቶ፣ ሁለመናቸው ከእጁ መዳፍ እንዳይወጣ፣ ወደ ነጻነት የሚሻገሩበትን መንገድ በእሾህ አጥር ያጠረ፣… ልበ ደንዳናው ፈርኦን በመጨራሻ ጉልበቱ ተፈታ። ሙሴ ሕዝበ እስራኤልን ቀይ ባህርን ቢያሻግራቸውም ማርና ወተት ወደምታፈልቀው ወደ ተሰፋይቱ የከነዓን ምድር ግን አልገባም። ከግብጽ ሳይሆን ከጉያው የበቀሉ ጠላቶች በጉዞው ላይ ክፉኛ ተነሱበት። “ነብይ በሃገሩ አይከበርም፤ ታላቅ መሪም ሁል ግዜ በህዝብ አይወደድም” የሚለው የመጽሃፉ ምዕራፍ ስድስት ስለዚህ ታሪክ ይነግረናል።

         ደራሲው የኮርያዊው ጀነራል ፓርክ ቹንግ ሂን ታሪክ  ከሙሴ ታሪክ ጋር እያዛመደ ይጠቅሰዋል። በ1960ዎቹ በርስ-በርስ ጦርነት ስትታመስ የነበረችው ደቡብ ኮርያ፤ ከነበረችበት እጅግ የከፋ ጭቆና እና ሙስና ለማላቀቅ በመፈንቅለ መንግስት መደረጉ ግድ ነበር። ጀነራል ፓርክ በዚያ መፈንቅለ መንግስት በትረ-ስልጣኑን ያዙና ሃገሪቷን ወገባቸውን ታጥቀው ሃገሪቷን ለመቀየር ተነሱ። ብዙ ቢጥሩም ግን ስፍራቸው ላይ አልቆዩም። በራሳቸው ደህንነት ሃይል ተገደሉ።

ሙሴ ሕዝቡን ቀይ ባህርን አሻግሮ ከነዓን ምድርን ሳያያት አለፈ።   ጀነራል ፓርክ ቹንግ ደቡብ ኮርያ አሁን የደረሰችበትን አስገራሚ እድገት ደረጃ ሳያይ ቢያልፍም ለዛሬዩቱ ኮሪያ ስኬት አሻራውን አሳርፏል።

          በእርካብና መንበር ውስጥ የምናገኘው ተምሳሌት መጪው መሪ የሙሴን ገጸ ባህርይ  ተላብሶ ሕዝቡን ከባርነት ወደ ነጻነት የሚያሻግር ይመስላል። ሙሴ በንጉሱ፣ በፈርዖን ቤት ውስጥ ሲያድግ የወገኖቹን ባርነት እና ስቃይ በቁጭት ይመለከት ነበር። ጮክ ብሎ የሚያስብ መልዕክቱ ይገባዋል።  ዶ/ር አብይም በኢህአዴግ ውስጥ ሆነው ሲሰሩ ፣ በሕዝቡ ይፈጸም የነበረውን በደል ውጭ ከሚሰማው በላቀ መንገድ ያውቁታል። ህወሃት የራሱን በደል በነሱ ጫንቃ ላይ ጭኖ ለአመታት ሲጋልብባቸው እንደነበርም አስተውለዋል።

በመጨረሻ የተነሳውን የለውጥ ማዕበል እንደ እርካብ ተጠቅመው መንበሩ ላይ ወጥተዋል። እዚህ ለመድረስ የሄዱበት መንገድ  አስሸጋሪ ይሁን እንጂ ከፊት የሚጠብቃቸው ጉዳይ ደሞ እጅግ ውስብስብ ነው። ቀይ ባህርን አሻግሮ ወደ ከነዓን ምድር ማድረስ! እሳቸው አንድ፤ እንቅፋቶቹ ግን ብዙ ናቸው።

 የፈርዖን ቅሪቶች አንድ ቦታ ላይ መሽገው የለውጡ ራስ ምታት ሆነዋል።  ለዘመናት ሲሰራበት የነበረው የዘር ቁርሾም ቢሆን እንዲህ እንደዋዛ የሚቆም አይነት አይደለም።  ከሰማይ መና እየወረደለትም የሚያጉረመርም ሕዝብን ለማሻገር የሚወስደውን ግዜ እና ጉልበት በውል ሊረዳ የሚችለው ሙሴ ብቻ ነው።  ፈተናው በየፈርጁ ቢደረደርም፤ አብይ ይህንን ሕዝብ ከነ ሙሉ ችግሩ ለመምራት ከ 7 ዓመታቸው ጀምሮ ያሰቡበት ይመስላል። “እኔ አሻግራችኋለው” የሚል ቃል ሲናገሩ፤ የራስ መተማመናቸው ምን ያህል እንደሆነ ለመረዳት አያዳግትም።

ለመፍትሄዎቹም ለየት ያለ ስትራቴጂ ቀይሰዋል።

“እርካንብ እና መንበር” ችግሮችን ስለመፍታት የሚለን ነገር አለ።  አዲስ አስተሳሰብ እና አዲስ መንገድ። ከአልበርት አንስቴይን እስከ ኒኮሎ ማኪያቬሊ።  ብዙ ጸሃፍትን ይጠቅሳሉ። ችግሮችን በውይይት መፍታትን በጽኑ ያምኑበታል። ለዚህም ተፎካካሪን የማሳመን ብቃት እና ችሎታን ስለማዳበር ይመክራሉ። ይህ ካልሆነ ግን ሌላ እጅግ በረቀቀ መንገድ እንዳለም ይነግሩናል። አንድን ተቀናቃኝ  በሃሳብ ረትቶ ማሸነፍ ካልተቻለ ለዚህ አዲስ ስትራቴጂ አለ ይለናል ደራሲው…

 “እንደ ውሻ ጠላት ላይ በመጮህ ማምለጫን ማመቻቸት ዘላቂ መፍትሄ ባይሆንም ለግዜው ይጠቅማል። ምክንያቱም እንዳይመለስ ሆኖ ያልተሸኘ ጠላት ግዜ ጠብቆ ዳግም ለማጥቃት እንደሚመጣ ምንም ጥርጥር የለውምና። ታዲያ ግዜው ሲደርስ ልክ እንደ ነብር ኮቴን ሳያሰሙ ከጀርባ ቀብ ማድረግና ህልሙን በአንድ ጀንበር ማምከን መረሳት የለበትም፤ ወይንም ስውር የሆነ ወጥመድ ማዘጋጀት ይበጃል። ሰዎች ራስ ወዳድ ናቸውና በጥቅም ሂድባቸው። የሚፈልጉትን ነገር እያሳየህ የምትፈልገው ስፍራ ውሰዳቸውና ጣላቸው። ከዚያም ‘በሬ ሆይ ሳሩን አይተህ  ገደሉን ስታይ’ በልና ተርትባቸው። ይህን መሰሉ ለዘብተኛ የሃይል አጠቃቀም ዘዴ ሰላም ሳይበጠበጥ ሕዝቡም ሳያጉረመርም የተደላደለ የስልጣን ባለቤት ለመሆን ያግዛል።” (እርካንብ እና መንበር ገጽ 37-38)

ከዚህ የምንገነዘበው ደራሲው ሆደ ሰፊ ብቻ ያለመሆናቸውን ነው። አስፈላጊ ሆኖ ሲገኝ በዚህ አይነቱ “ጠላትን” ድምጽ በማያሰማ ሳይለንሰር የመምታት ጥበብም ተክነዋል። “ሆ ብዬ መጣለሁ”ን እያንጎራጎሩ በድል አድራጊነት ስሜት ሸገር የገቡት ወገኖች ይህ እጣ ሳይደርሳቸው አልቀረም።  እነሱም ዘንድ ችግር አለ። ድምጽ አጥፍተው የድሉ ተቋዳሽ ከመሆን ይልቅ መሪ ተዋናይ መሆን አማራቸው። ምህረት እየተደረገላቸው ገብተው የአንበሳውን ድርሻ መጠየቅ ጀመሩ….

አሁን ላይ ሆነን ብዙ ማለት አንችልም። ተስፋ እና ስጋት ተደማምረው ግርግር የበዛበት ሽግግር እንደሆነ ግን በግልጽ እናያለን።

*ከኢትዮጲስ ጋዜጣ እትም ላይ የተወሰደ

https://youtu.be/YEwJAxxzQVs

Filed in: Amharic