>

ሳይቃጠል በቅጠል! (ፋሲል የኔአለም)

ሳይቃጠል በቅጠል!
ፋሲል የኔአለም
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል በተፈጠረው ግጭት ከአንድ መቶ በላይ ሰዎች ሙት እና ቁስለኛ ሲሆኑ ከ70 ሺህ በላይ ህዝብ ተፈናቅሏል!
በቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል ላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ በማወጅ፣  ክልሉን ከፖሊስ፣ ከመከላከያና ሲቪል አስተዳደር በተውጣጣ ቡድን ለተወሰነ ጊዜ መምራት ይገባል።  ክልሉ የተለያዩ ታጣቂዎች መፈንጫ ሆኗል። ለውጡን ለማወክ የሚፈልጉ ሃይሎች ትኩረታቸውን ከሶማሊ ወደ ቤንሻልጉል ጉሙዝ አዙረዋል። በተለይ የአማራና  የኦሮምያ  ክልል መሪዎች ግንባር ቀደም ተጠቂዎች በእነዚህ ክልሎች የሚኖሩ ዜጎች በመሆናቸው በእጅጉ ሊያስቡበት ይገባል።
 በክልሉ በተፈጠረው ግጭት የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከ70 ሺህ በላይ መድረሱን የመንግስታቱ ድርጅት የሰብዓዊ ጉዳዮች ቢሮ አስታውቋል። ችግሩ ተባብሶ ይቀጥላል የሚል ስጋት አለ።
አስቸኳይ የሰብዓዊ ድጋፍ ያስፈልጋል ተብሏል። አምነስቲ ከ40 በላይ ሰዎች መሞታቸውን ሲናገር ነዋሪዎች ግን የሟቾች ቁጥር ከአንድ መቶ በላይ ነው፣ በመቶዎች የሚቆጠሩ ቤቶችም ተቃጥለዋል ብለዋል።
ኦነግ በግጭቱ ውስጥ እንዳለበት በርካታ መረጃዎች እየወጡ ነው። ድርጅቱ ግን የግጭቱ ተሳታፊ አለመሆኑን ተናግሯል። ግጭቱ የተጀመረው አራት የቤንሻንጉል ክልል ባለስልጣናት አጎራባች ኦሮሚያ ውስጥ ባልታወቁ ታጣቂዎች መገደላቸው ነው። በርከት ያለ ቁጥር ያላቸው ኦሮምኛና አማርኛ ተናጋሪ ኢትዮጵያውያን “መጤ” ተብለው የጥቃት ዒላማ ተደርገዋል።
በክልሉ እየተፈጸመ ባለው ወንጀል ህወሃት፣ የኦነግን ስም የሚጠቀሙ ተጣቂዎች ( ከዳውድ ኢብሳው ኦነግ ጋር ግንኙነት ይኑራቸው አይኑራቸው ስለማላውቅ ነው) ፣ ሱዳን( ግብጽ) እጃቸው የለበትም ለማለት አልደፈርም።  ሳይቃጠል በቅጠል።
Filed in: Amharic