>
10:24 am - Sunday May 22, 2022

የህላዌ እና የበረከት 'ክሊክ' የሆነችን ሴት የአ.ዴ.ፓ ማ.ኮ አባል ማድረጉ ሴትዮዋን አለማወቅ? ወይስ..? (ውብሸት ሙላት)

የህላዌ እና የበረከት ‘ክሊክ’ የሆነችን ሴት የአ.ዴ.ፓ ማ.ኮ አባል ማድረጉ ሴትዮዋን አለማወቅ? ወይስ..?
ውብሸት ሙላት
ስለ እናትዓለም መለሰ፦ ሁሉን ነገር ለማጥራት!
እናትዓለም መለሰ ኦሮሞ መሆኗ ለተቃውሞዬ ምክንያት አይደለም፤ ሊሆንም አይችልም!
 
1. እናትዓለም መለሰን የአዴፓ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል መሆኗን የምቃወመው ኦሮሞ በመሆኗ አይደለም። ኦሮሞ ሆነው የብአዴን አመራርም ማእከላዊ ኮሚቴም አሉና። ኦሮሞ በመሆናቸው ብቃወምማ ሌሎች ሦስት ሲጠቆሙ እቃወም ነበር። ማእከላዊ ኮሚቴም ሲሆኑ እቃወም ነበር። እንዴት አድርጌ እነ ሙሀመድ አብዱን እቃወማለሁ?  የዶክትሬት ድግሪውን እንዲማር ቀደም ብሎ የሄደውን እና በዚሁ ምክንያት አሁን ላይ በእጩነት አልቅረብ ያለውን ለገሱ ቱሉን (ቢቀርብ ኖሮ) እንደት እቃወማለሁ? ኦሮሞ በመሆኗ በጭራሽ አልተቃወምኩም። የምቃወምበትን ምክንያት ላስረዳ!
2.   እናትዓለም መለሰ የእነ ህላዌ ዮሴፍ እና የእነ በረከት ‘ክሊክ’ እንደሆነች እንጂ “ኦነግ” (ይህም በቅን ልቦና ይተርጎምልኝ) ናት የሚል መረጃ የለኝም። ህላዌ ዮሴፍ የኢቲቪ/ኢቢሲ ስራ አስኪያጅ እያለ ከሪፖርተርነት ምክትል ዳይሬክተር (የአንድ ዘርፍ) ያደረጋት ልጅ ነች። ህላዌ ዮሴፍ አሁንም ከእናትዓለም ጋር ከፍተኛ ቀረቤታ አላቸው። ህላዌ የአማራን ህዝብ እስካጥንቱ ድረስ ከጎዱት እንዲሁም አሁን ላይ ያለውንም ለውጥ የማይደግፍ ሰው መሆኑ ይታወቃል። የጠቆመቻትም (በመረጃ አለመኖር ተቃውሞ ባይቀርብባትም) የዋፋ ማርኬቲንግ የትዕምት (ኤፈርት) ድርጅት ሃላፊ  የሆነች ሌላዋ የእነ በረከት እና ሕላዌ ወዳጅና ክሊክ ሴት ነች፡፡ ጉባኤያተኛውም ከአዲስ አበባ ስለሄደች እንዲሁም መረጃ ስለሌለው እንደሌሎች እጩዎች የቀረበባት ተቃውሞ አልቀረበባትም፡፡ ማንም ሰው ሊገነዘበው እንደሚችለው እነ በረከትና ህላዌ ዮሴፍን ብአዴን/አዴፓ ለማስወጣት ምን ያህል እንደታገልን ስንት ሕዝብ እንዳለቀ ስንት ሰው እንደታሠረ ወዘተ ሁላችንም እንገነዘባለን ብየ አስባለሁ፡፡
ስለሆነም በግሌ ለእነዚህ ሰዎች ክሊክ በመሆን አዴፓን ለመከፋፈል የተጠቀሙበት ስልት አድርጌ ነው የምወስደዉ፡፡  አማራንም ሆነ ኦሮሞን ለዚህ ሁሉ በደል የዳረጉትን የቀድሞዉን ጠቅላይ ሚኒስትር “ታላቁ መሪ ብላችሁ ጥሩ!” በማለት ትእዛዝ የሰጠችዉ በድርጅቱ (በኢቢሲ) ሥራ አስኪያጅነቷ አይደለም፡፡ ሥራ አስኪያጅ ስላልሆነች፡፡ ወገንተኝነቷ ለኦሮሞም ለአማራም ሕዝብም ነው ብየ አላስብም፡፡ በመሆኑም እናትዓለም መለሰን ኦሮሞ ስለሆነች አልተቃወምኩም፡፡
3. እናትዓለም መለሰ ወደ ፓርቲ ሕይወት ትቀላቀል ዘንድ አስቀድሞ ጥያቄ የቀረበላት በኦህዴድ ነበር፡፡ አልፈልግም ኦህዴድ አልሆንም አለች፡፡ ይሔ ጥያቄ የቀረበላት እዚሑ የአሁኑ ኢቪሲ እያለች ነው፡፡ እሷም ኦህዴድን በመተው ለብአዴን አመለከተች፤ነገር ግን በሕዋስም በመሠረታዊ ድርጀትም ተቀባይነት አጣች፡፡ ልብ አርጉልኝ ኦህዴድን አልፈልግም አለች፡፡ ብአዴንን ብትፈልግም የአባልነት ሥነምግባር  መሠፈርቱን ስላላሟላች ሳይቀበላት ቀረ፡፡ በአቶ ሕላዌ ዮሴፍ ሥር (ዘርዓይ የኢቲቪ ዳይሬክተር፣ሕላዌ ምክትል እንደነበሩ ያስታውሷል፡፡ በእነ ሕላዌና ዘርዓይም ጊዜ የአንድ ዘርፍ ኃላፊ ነበረች፡፡ የእነ ዘርዓይና የሕላዌ ቀኝ እጅ ሆና ሰው ስታምስና ስታሳምስ ነበር፡፡
4. እነ ዘርዓይና ሕላዌ ከለቀቁ በኋላ ደግሞ እናትዓለም መለሰ የአቶ ዘርዓይ አስገዶምን በመተው ግልብጥ ብላ  የብርሃነ ኪዳነማርያም ወዳጅ ሆነች፡፡ ከዚያ በእነ ዘርዓይና በብርሃነ ኪዳነ ማርያም መካከል በነበረው ፍትጊያ (ሁለቱም ህወሃት ናቸው) አቶ ብርሃነ ኪዳነ ማርያምን በመደገፍ ዘርዓይን በየዐደባባዩ በየስበሰባው መውቀስናመክሰስ ትቀጥላለች፡፡ ለአቶ ብርሃነ በለስ ቀናው፡፡
ከዚያም ድብደባው ተጀመረ፡፡ ተመስገን ገብረሂወት (በብሔሩ ኦሮሞ የሆነው ጋዜጠኛ) ገና ከተሾመ ሦስት ወር የሆነውን ቦታ እንዲባረር አስደርጋ ቦታውን ያዘች፡፡ ተመስገን ገብረሂወት ከኢቲቪ/ኢቢሲ ሲባረር ኦቢኤን  ቀጠረው፡፡ አሁን ላይ ፋና መሠለኝ የሚሠራው! አሮሞውን ተመስገንን እንዲባረር አድርጋለች፡፡ መቼም ተመስገን በየነ ሳይባረር ተመስገን ገብረ እግዚአብሔርን ማባረር ምን የሚሉት ነው?
እነ ፍቅር ይልቃልና አሸብር ጌትነትን ጭምሮ ሌሎች በርካታ ብሔራቸው አማራ የሆኑ ጋዜጠኞችንም እንዲባረሩ አደረገችም፤አስደረገችም፡፡ ምክንያቱም ተመስገን ገብረ እግዚአብሔር ከነበረበት ቦታም በአንድ ጊዜ ተስፈንጥራ የኢቲቪ/ኢቢሲ ዋና ሥራ አስኪያጅ የአቶ ብርሃነ ኪዳነማርያም ምክትል ሆነች፡፡ በዚህን ጊዜ የግድ የፓርቲ አባል መሆን አስፈለጋት፡፡ ቦታው ለፓርቲ አባል ብቻ የተተወ ነው፡፡ ኦህዴድን አልፈለግም ብላ ስለነበር ወደ ኦህዴድ መግባት አልተመቻትም፡፡
እንደውም ለአቶ ብርሃነ ራስ ምታት የሆነ የፓርቲ አባላት እና በየግምገማው የሚያስቸግሩት የነበሩት ብአዴን ውስጥ ስለነበሩ እነሱን ለማጥቃትም ስለሚመች የብአዴን አባል እንድትሆን ተስማሙ፡፡ ችግሩ የብአዴን በመሠረታዊና በሕዋስ ደረጃ እንቀበልም ብለዋታል፡፡ እነ ብርሃነ እና እናትዓለም ተመካክረው ከሁለቱ መዋቅሮች በላይ ባለው የብአዴን የወረዳ አመራር እንደትሆን አደረጉ፡፡ ከዚያ ብርሃነን ሲያስቸግሩት የነበሩት በመሥሪያ ቤትም በድርጅትም አለቃቸው በመሆን እንዲባረሩ አደረገች፡፡ አደረጉ፡፡
አሁንም ልብ በሉ! ለሕወሃቱ ብርሃነ ኪዳነ ማርያም በማገዝ የብአዴንንና የኦህዴድ አባላትን እንዲባረሩ አደረገች፡፡ ሌላው ልብ ሊባል የሚገባው የዘርዓይ እና የብርሃነ ጭቅጭቅ እና ኔትወርክ ሕወሃት ዉስጥ የነበረውን የእነ አቦይ ስብሃትና የእነ አባይ ወልዱ ቡድንን መሠረት ያደረገ እንጂ ከኦሮሞም ለአማራም ጋር ትሥሥር የሌለው መሆኑ ነው፡፡
እንግዲህ አንድኛውን ዝሆን በመደገፍ (ምናልባትም ለግላዊ ጥቅም) በርካታ ብቃት ያላቸውን ጋዜጠኞች እንዲባረሩ የሠራች መሆኗን ልብ አድርጉልኝ፡፡ ወቅቱን ሁኔታውን እየመዘነች ወደ የት እንደምታዘንብል፣ integrity እንደሌላት መገንዘብ ያስፈልጋል፡፡
5. የእናትዓለም በኢቢሲ የነበራት ታሪክ ብዙ ነው፡፡ ከተቋሙ ሃምሳኛ ዓመት በዓል ጋር የተገናኙትን ሁለቱን ብቻ ልጥቀስ፡፡ የሕሊና ፍርድ ስጡ ከዚያ፡፡ አንድኛው ሪፖርተርና ፎርቹን ጋዜጣም ላይ መውጣቱን አስታውሳለሁ፡፡ ሃምሳኛ ዓመቱ ሲያከብር ወደ ሃያ ሚሊዮን ብር የሚጠጋ ገቢ ማመንጨት ያቅዳል-ኢቢሲ፡፡ እነ ብርሃነና እናትዓለም ዋናና ምክትሎቹ ለእነ ሰራዊት ፍቅሬና ሳምሶን አስራ አንድ ሚሊዮን ወስደው ዘጠኙን እንዲስገቡ ይስማማሉ፡፡
ይህንን ህገ ወጥ ድርጊት የግዥና ንብረት ክፍል ሃላፊው ድርጊቱ ሕጋዊ አይደለም አልፈርምም ይላል፡፡ ከዚያ ዘጠኝ ሚሊዮን እንዲወስዱ ተስማሙ፡፡ የግዥና ንብረት ክፍል ሃላፊው (የብአዴን አባል የሆነ ብርሃኑ ታረቀኝ የሚባል) ድጋሜ አልስማማ አለ፡፡ ወደ ሰባት ሚሊዮን ወረደ፡፡ አሁንም አልስማማ ይላል፡፡ ብርሃነና እና እናትዓለም ይህንን ሰው አባረሩት፡፡ እሱም ወደ ጸረ ሙስና ወሰደው፡፡ በአጠቃላይ ከእነ ሰራዊት እና ሳምሶን ጋር የነበረው ውል ቀረ፡፡ ጸረ-ሙስና ሲይዘው፡፡
ሁለተኛው ድርጊት ደግሞ ጸረ-ሙስናና እና የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ጠንቅቆ የሚያውቀው ነው፡፡ ለስቱዲዮ ግንባታ የሚውል ቁሳቁስ ብርሃነና እሷ በ2.5 ሚሊዮን ዶላር እንዲገዛ ይስማማሉ፡፡ ጨረታ ሳይወጣ ነው፡፡ አሁንም ይሔው የግዥና ንብረት ክፍል ኃላፊው ብርሃኑ ታረቀኝ ሕጋዊ ስላልሆነ አልስማማም ይላል፡፡ ሁለት ወይም ሶስት (?) ጊዜ ጨረታ ወጥቶ በዚያው በ2.5 ሚሊዮን ይገዛ ይባላል፡፡ የመንግሥት ግዥና ንብረት አስተዳደር ደግሞ ተመሳሳይ ቁሳቁስ በ650 ሺህ ዶላር ይገዛል፡፡ ግዥው ተገቢ አይደለም ይላል፡፡ የሆነ ሆኖ ወደ 1.1. ሚሊዮን ዶላር ወጥቶ ተገዛ፡፡ ብርሃኑ ታረቀኝ ግዥው ሕጋዊ አይደለም፤ብዙ ገንዘብ ያስወጣል፤ አለ፡፡ የግዥ ሂደቱን አልጠበቀም ስላለ ከላይ የተገለጸው የእነ ሠራዊት ውል መቋረጥ ጋር ደምረው አባረሩት፡፡
ብርሃኑ ከስንት ክርክር በኋላ በአስተዳደር ፍርድ ቤት ውሳኔ ተመለሰ፡፡ የብርሃኑ ታረቀኝን ኃጢአት (የአብየን ወደ እምዬ እንዲሉ) በየስብሰባው ያላነሳችበት ጊዜ የለም፡፡ እሱ ግን ንጹህ ስለሆነ ተመለሰ፡፡ እንግዲህ እናትዓለም እንዲህ ዓይነቱን ድርጊት ስትፈጽም የኖረች ናት፡፡
6. እናትዓለም መለሰ የብርሃነ ኪዳነማርያም ቀኝ እጅ በመሆን ብቻ በፈጸመቻቸው ተግባራት፣የአመራር ብቃት አለመኖር ወዘተ ጋዜጠኞችም ሌሎች ሠራተኞችም ስለጠሏት፣ መምራት ስላልቻለች ኢቢሲ 2009 ዓ.ም. ነሐሴ (2010 መስከረም) ወር ጀምሮ ማሻሻያ መደረግ ሲጀምር ከነበረችበት ምክትል ሥራ አስኪያጅነት ተነሳች፡፡ በዚህን ጊዜ ዶ/ር ነገሪ ሌንጮ የመንግሥት ኮሚኒኬሽን ሚኒስትር ሆነው ስለነበር እናትዓለም መለሰ ሌላ ካርድ መዘዘች፡፡
እናትዓለም የተባረርኩት “ኦሮሞ ስለሆንኩ ነው” በማለት አቤቱታ ለዶ/ር ነገሬ እንዲሁም ለአቶ አባዱላ ገመዳ ተደጋጋሚ አቤቱታ አቀረበች፡፡ አሁንም ልብ አድርጉልኝ! የብአዴን አባል ለዚያዉም የወረዳ አመራር ደረጃ ያለች ናት፡፡ የኢቪሲ ሥራ አስኪያጅም የብአዴን አባል የሆነ ነገር ግን በብሔሩ አገው ነው፡፡ ኦህዴድን አልፈለግችም ነበር፡፡ ብአዴንም አልተቀበላትም ነበር፡፡ ኋላ ላይ የሆነችውን ከላይ ተመልከተናል፡፡ ሁሉ ነገሯ የግል ጥቅም እንጂ ፖለቲከኛ በመሆን አይደለም፡፡ ለህዝብ ጥቅም ቅድሚያ በመስጠት አይደለም፡፡
7. እናትዓለም መለሰ የብአዴን አባል ሆኖም ባላት የድርጅት ታሪክ የአማራ ሕዝብን መብትና ጥቅም ለማስከበር ያደረገችው ትግል የለም፡፡ የኦሮሞንም ጭምር! ይልቁንም በተቃራኒው ነዉ፡፡ መቼም አማራ ክልል ዉስጥ የሚኖር የኦሮሞ ተወላጅ እስከማውቃቸው ድረስ ቆራጥ እና ታጋይ ለኦሮሞም ለአማራም ሕዝብ ጥቅም ውለፍት አይሉም፡፡ አቶ ለገሰ ቱሉንና አቶ ሙሀመድ አብዱ ለዚህ ትልቅ ማሳያዎች ናቸው፡፡
ብአዴን እናትዓለምን አባል ሲያደርጋት (በቅንነት አባል ሆናለች ብለን ካሰብን) አማራ ክልል ዉስጥ አለመወለዷን፣ ክልሉ ዉስጥ ያለች ሠራተኛ ወይም ኗሪ አለመሆኗን መሥፈርት አላደረገም፡፡ እንግዲህ ብሔርን መሠረት ያደረገ ለአንድ ብሔር የሚታገል ድርጅት የብሔር ዳራዋን መመልከትና ማጥናት ተፈጥሯዊ ቢሆንም ብአዴን ይህንን አላደረገም፡፡ በጣም ጥሩ ነው፡፡ በገቢር ድርጅቱ የተቋቋመለትን ሕዝብ ጥቅም የሚጻረር ተግባር የሚሠራን ሰው (ራሱ የብሔሩም አባል ቢሆን-አቶ አለምነው ምሳሌ ነው ለዚህ) አመራር ማድረግ የለበትም፡፡
እኔ አማራ ሆኜ የኦህዴድ/አዴፓ አባል እንደሆን ከተፈቀደልኝ (የክልሉ ተወላጅ እንኳን ሳልሆን ልክ እናትዓለም ለብአዴን/አዴፓ) እንደሆነችው፣ ኦዴፓ ለተቋቋመለት ለኦሮሞ ሕዝብ መሥራት አለብኝ፡፡ አባል ሆኜ፣ሾሞኝ ማለትም አምኖኝ ኦሮሞን የማይጠቅም በተለይ የሚጎዳ ነገር መፈጸም ፍጹም ክህደት ነው፡፡ ከሃዲ የሆነ ሰው ብቻ እንዲህ የሚያደርገው፡፡
ኦሮሞ (አማራ ሆኜ) ሳልሆን የኦዴፓ አባል ከሆንኩ እንደዉም የኦሮሞን ጥቅም የሚጻረር ድርጊት እየፈጸምኩ ስለምን አልተሾምኩም? ያልተሾምኩት አማራ ስለሆንኩ ነዉ ይባል እንዴ? እንዴት እንዲህ ላስብ እችላለሁ? ሳልሾም ከቀረሁስ እንደዉ ቅሬታ ማቅረብ ያለብኝ ወድዶ እና ፈቅዶ አባል ያደረገኝ ድርጅትና መሪዎች (ኦዴፓ እና መሪዎቹ ጋር እንጂ) እንዴት አድርጌ ብአዴን/አዴፓ እና አመራሮቹ ጋር እሔዳለሁ?
እናም የእናትዓለም መለሰም ባሕርይ  የፈለገችውን ካርድ እየመዘዘች የምትጫወት ፍጹም የኦሮሞን የአማራንም ሕዝብ የማትወክል ናት ብዬ ስለማምን ነው የማእከላዊ ኮሚቴ አባል እንዳትሆን (ከረፈደ በኋላም ቢሆን) የምፈልገው፡፡
8. በአጠቃላይ ካላት የሥራ ላይ ታሪክ አንጻር የአሁኑ ለውጥ ተሳታፊ ስለመሆኗ አይታወቅም፡፡ ለሕዝብም አርኣያ አትሆንም፡፡ በለዉጡ ሒደት የጎላ ድርሻ መኖርና ለሕዝብ አርኣያ መሆን የሚሉት ሁለት መለኪያዎች ለብአዴን/አዴፓ የማእከላዊ ኮሚቴ አባልነት ወሳኝ መሥፈርት መሆናቸው ሊቀመንበሩ አቶ ደመቀ መኮንን አስቀድመው ተናግረዋል፡፡ እናትዓለም መለሰ ግን ሁለቱንም አታሟላም፡፡
እናም እናትዓለም መለሰ የአዴፓ ማእከላዊ ኮሚቴ አባል ሆና መቀጠል የለባትም፡፡ ለአዴፓ ብቻ ሳይሆን ኦዴፓም ውስጥ ቢሆን ወይም ሌላ ላይ መቀጠል የለባትም፡፡ በፈጸመችዉ ድርጊት ተጸጽታ መልቀቅ አለባት፡፡ ይሔ አሁንም አቋሜ ነው፡፡ ኦሮሞና አማራን ከማጋጨት የዘለለ ፋይዳ የላትም፡፡ የእስካሁን ታሪኳ ለዚህ ምስክር ነው፡፡
ይሄን ታሪክ እያወቁ ስለ እናትዓለም ምንም ነገር ትንፍሽ ያላሉት አቶ ስዩም መኮንን እና በተወሰነ መልኩ አቶ ተፈራ ደርበውም አድርባይነት ባህርይ አሳይተዋልና ሊወቀሱ ይገባል፡፡
Filed in: Amharic