>

ስለ ጎሳ ፖለቲካ ሲወራ ፌዴራሊዝሙን አደጋ ላይ ልትጥሉት ነው አትበሉ! (ያሬድ ሀይለማርያም)

ስለ ጎሳ ፖለቲካ ሲወራ ፌዴራሊዝሙን አደጋ ላይ ልትጥሉት ነው አትበሉ!
ያሬድ ሀይለማርያም
በቤኒሻንጉል የሚኖር ኦሮሞ ወይም አማራ ወይም ትግሬ እዛው ክልል እንኳን ቢወለደ ከአንድ ጉሙዝ እኩል በክልሉ ውስጥ የዜግነት መብት የለውም። 
* በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ አንድ ጉራጌ ወይም ከንባታ ወይም ወላይታ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከአንድ ኦሮሞ እኩል የዜግነት መብት የለውም።  

ኢትዮጵያ በቋንቋ፣ በኃይማኖት፣ በባህል እና በሌሎች ማህበራዊ እሴቶች እጅግ የተሰበጣጠረ ሕዝብ ያለባት አገር እንደመሆኗ ሁሉንም ሕዝብ እኩል አከባብሮ እና አቻችሉ ሊያኖር የሚችል መንግስታዊ አወቃቀር ያስፈልጋታል። ለዚህም ፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር ተመራጭ እና ምቹ ስለመሆኑ ምንም የሚያከራክር አይደለም። ጥያቄው ያለው የፌደራሊዝም ሥርዓቱ በምን መሰረት ላይ ይዋቀር የሚለው ነው። ይህን ደግሞ በደመ ነፍስ እንዲህ ይሁን እንዲያ ከማለት አገሪቱ ያለችበትን ወቅታዊ እና ተጨባጭ እውነታዎች በቅጡ ያገናዘበ እና በደንብ በባለሙያዎች የተጠና ፌደራላዊ አወቃቀር እንዲኖር ማረግ ይቻላል። በዚህ ዘርፍ የተደረጉ በርካታ ጥናቶችም ስላሉ እነሱንም በቁጡ መፈተሽ ጊዜ እና አቅምንም ይቆጥባል።
እኔን እያሳሰበኝ ያለው በአገሪቱ ውስጥ እየተንሰራፋ የመጣው እና ለብዙ ዜጎች ህይወት ህልፈት እና መፈናቀል ምክንያት የሆነው ቋንቋን እና ጎሳን ያማከለው የመንግስት አወቃቀር ነው። ክልሎች በዚህ መልክ በመዋቀራቸው ብቻ ሳይሆን ላለፉት ሃያ ሰባት አመታትም በመንግስት እና አክራሪ በሆኑ ብሔረተኞች ሲቀነቀን እና ሲሰበክ የኖረው ዘር ተኮር ፖለቲካ ዛሬ ፍሬው ጎምርቶ በየክልሉ አደጋዎች እያስከተለ ነው። አንዱ ስፍራ ላይ አፈናቃይ እና ተሳዳጅ የሆነ የህብረተሰብ ክፍል ሌላው ክልል ላይ ተፈናቃይ እየሆነ አገር እየታመሰች ነው።
በሁሉም ክልልሎች የሚታዩት ዘር ተኮር ጥቃቶች ያልነኩት የህብረተሰብ ክፍል የለም። በግንባር ቀደምነት አማራው ከኖረበት ቅዮው ከወልቃይት እና እራያ አንስቶ በሁሉም ክልሎች ማለት ይቻላል የጥቃት ሰለባ ሆኗል። ኦሮሞውም እንዲሁ ከሶማሌ ክልል እና ከቤኒሻንጉል ጉምዝ እየተሳደደ ነው። በደቡብ ክልል አንዱ ጎሳ ሌላውን እያፈናቀለ ነው። ሌሎቹም ጎሳዎች ተመሳሳይ እጣ ፈንታ እየገጠማቸው ነው። ማቆሚያው የቱ ጋር እንደሆነ አይታወቅም።
ይህን አደጋ ያስከተለው ደግሞ አገሪቱ ስትከተል የኖረችው የጎሳ ፌደራሊዝም እንደሆነ ማሳያው የሁሉም ጥቃቶች ምንጭ አሳዳጅ የሆነው አካል ክልሌን ነው፣ የእኔ መሬት ነው፣ እናንተ ባዳዎች ናችሁ፣ በዚህ ስፍራ የመኖር ዋስትናችሁ በእኔ ፈቃድ የተወሰነ ነው ከሚል ስሜት የመነጨ መሆኑ ነው። ይህ ስሜት ደግሞ ዝም ብሎ ከየትም የመነጨ ሳይሆን የሕግ ድጋፍም ጭምር ያለው መሆኑ ነው። ከሕገ-መንግስቱ ጀምሮ የክልል ሕገ-መንግስቶች ለዜጎች እውቅና አይሰጡም። ዜጎች የአገራቸው ባለቤት አይደሉም። እያንዳንዱ ክልል ለብሄር፣ ብሄረሰቦች የተሰጠ ስለሆነ ሁለት አይነት ዜግነት እንዲኖር አድርጓል።
አዎ  በቤኒሻንጉል የሚኖር ኦሮሞ ወይም አማራ ወይም ትግሬ እዛው ክልል እንኳን ቢወለደ ከአንድ ጉሙዝ እኩል በክልሉ ውስጥ የዜግነት መብት የለውም። በተመሳሳይ ሁኔታ አንድ አንድ ጉራጌ ወይም ከንባታ ወይም ወላይታ በኦሮሚያ ክልል ውስጥ ከአንድ ኦሮሞ እኩል የዜግነት መብት የለውም።
እነዚህ ነገሮች ከጥላቻ ፖለቲካ ጋር ተቀላቅለው የፈጠሩት ነገር ይሄው ዛሬ የምናየው እርስ በእርስ መጠፋፋት እና አንዱ ሌላውን ማሳደድ ነው። ይህ አይነቱ ጎሳን ያማከለ፣ ዜጎችን ያበላለጠ፣ አንዱን ተሳዳጅ ሌላውን አሳዳጅ ያደረገ ዘር ተኮር የመንግስት ፖሊሲ ሊቀየር ይገባል። የሚያሳዝነው ይህ ሁሉ አደጋ እየታየ እና ህዝብ በገዛ አገሩ እየተፈናቀለም ፌደራሊዝሙ የተዋቀረበት መንገድ ይፈተሽና ይስተካከል ሲባል አክራሪ ጎሰኞቹ ብቻ ሳይሆኑ በዘር ፖሊቲካ የቆረቡ ሰዎችም ፌደራሊዝሙን ልታጠፉብን ነው የተነሳችሁን እያሉ ሲያላዝኑ እና እንቧ ከረዩ ሲሉ መስማታችን ነው። ፌደራሊዝሙን ከጎሰኝነት አጽዱት ሲባል በአንድነት ስም ልትውጡን ነው የሚል ስጋትም ነው ደጋግሞ ሲገለጽ የሚሰማ።
በአገሪቱ ውስጥ ጎጠኝነት ተንሰራፍቶ ከቁጥጥር ውጭ እየወጣ ነው። ሰዎች በጎጥ ከረጢት ውስጥ ሆነው ነው አገራቸውን የሚያስቡት። ያ ደግሞ የጋራ አገራዊ እራይም ሆነ እንደ አንድ አገር ሕዝብ በጋራ እንዳንቆም ብቻ ሳይሆን አብረን እንዳንኖርም እያደረገ ነው። ችግሩ የዘር ፖለቲካውን የሚያጦዘው ሊሂቃኑ የጥቃሉ ሰለባ አይደለም። በዘር ግጭት የሚሞተው ያው በየመንደሩ ያለው ደሃው ሕዝብ እና የዚህ መሰሪ ፖለቲካ ግራ ቀኙ ያልገባው ምስኪን ሕዝብ ነው። ፖለቲከኛው ከሚሱ አዲስ አበባ፤ ቀሪውም አውሮፓ እና አሜሪካ ተቀምጦ ነው እሳትና ነዳጅ ወደ ድሃው መንደር የሚወረውረው። በጎሳ ፖለቲካ መዘዝ ሟቹ እና ተፈናቃዩ ግን ደሃው ሕዝብ ነው። በእኛ ዝቅጠት ይህ ድሃ ህዝብ እስከ መቼ ነው ባገሩ ተሳዳጅ የሚሆነው።
ይህ ነገር በጊዜ ተመክሮበት እልባት ያግኝ የሚል ጥሪ ከመብት ተሟጋቾች ሲቀርብ ፌደራሊዝሙን ልታፈርሱ ነው እያሉ የሚያንቧርቁ ጎሰኞች ቆመው ሊያስቡ ይገባል። አሁንም በግልጽ ቋንቋ ለማስቀመጥ ‘አዎ! ኢትዮጵያ  ፌደራላዊ የመንግስት አወቃቀር ነው የሚበጃት’። እዚህ ላይ ጥያቄም ሆነ ጥርጥር የለም። ጥያቄው ዘርን ያማከለ አይሁን ነው። የዘር ፖለቲካው እያስከተለ ያለውን አደጋ ባሳሰብን ቁጥር ጸረ ፌደራሊዝም አድርጎ ማቅረብ አንድም ዝም ለማሰኘት አለያም በዘር ፖለቲካው እያተረፍን ስለሆነ ለእኛ ተመችቶናል እና ማንም ቢሞት እና ቢፈናቀል አይመለከተንም ነው የሚሆነው።
እግረ መንገዴን አንድ ጥያቄ ላንሳ፤ ዛሬ ጠቅላላ ጉባዔውን በአዋሳ ከተማ በማካሄድ ላይ ከሚገኘው ኢህአዴግ ምን እንጠብቅ?
– ለውጡን እየመሩ እዚህ ያደረሱትን ኃይሎች ሥልጣን ማጽደቅ፣
– ህውሃት ሰልፉን አሳምሮ ለውጡን በሙሉ ልብ እንዲቀላቀል ጫና ማሳደር፤ ካልሆነም በጊዜ እራሱን ችሎ እንደ አንድ ፖርቲ እንዲቀጥል መስማማትም፤
– የህውሃት ነገር አንድም አውራውን ፓርቲ ኢህአዴግን አለዛም እራሱን ህውሃትን ለሁለት ሊከፍለው ይችላል። ህውሃት አሁን ያለበት አቋም አንድ እግሩ ከለውጡ ጋር ሌላ እግሩ ደግሞ የቀድሞውን የደህንነት ሹም ጌታቸውን የመሰሉ የንጹሃን ደም በጃቸው ያለ ሰዎችን እና ሙሰኛ ጀነራሎቹን ይዞ የአፈንጋጮች ደሴት ላይ አሳርፏል። የዚህ ድርጅት ሁለቱም እግር ከሁለቱ በአንዱ ስፍራ ላይ ካላረፈ ኢትዮጵያም አታርፍም፤ ሰላምም አታገኝም። የህውሃት ነገር በዚህ ጉባዔ እልባት ሊያገኝ ይገባል።
– ከስም ለውጥ ባለፈ ድርጅቱ የፖለቲካ አስተሳሰብ መስመሩን መቀየር ይጠበቅበታል። ከርሞም ከዚህ ጉባዔ ማግስት ልማታዊ አብዮታዊ ዲሞክራሲ እያለ የሚያላዝን ከሆነ ድርጅቱ ለውጡን ለመምራትም ሆነ ለመሸከም አልተዘጋጀም ማለት ነው።
– አገሪቱ በምትከተለው የፌደራል አወቃቀር ላይ፣ የአገሪቱን የሕግ ምህዳር ማስተካከል እና ማሻሻል ላይ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን ለማስፋት የሚያስችል የዲሞክራሲ ፍኖተ ካርታ ለመቅረጽ መንገድ የሚከፍት ንድፈ ሃሳብ ይዞ ካልመጣ ለውጡን አዝጋሚ ያደርገዋል፤
– የድርጅት እና የመንግስት መዋቅርን በቅጡ እንዲለይ ካላደረገ እና ገለልተኛ ሊሆኑ የሚገባቸው የመንግስት ተቋማት ከድርጅቱ መዳፍ እንዲወጡ ካላደረገ ለውጡ የይስሙላ ይሆናል። ለዚህም የፍትህ ተቋሙ፣ የጸጥታው እና መከላከያ፣ የምርጫ ተቋማት፣ መገናኛ ብዙሃን፣ የሰብአዊ መብት ኮሚሽን፣ ጸረ – ሙስና ተቋም፣ ከፍተኛ የትምህርት ተቋማት፣ የጥናት እና ምርምር ተቋማት እና ሌሎች ከፓርቲው ጫና ነጻ ሊሆኑ የሚገባቸው ተቋማት ከካድሬዎች መፈንጫነት ወደ ባለሙያዎች የሥራ መስክነት እንዲቀየሩ የሚያስችል ውሳኔ ይዞ ካልመጣ ለውጥ ደና ሰንብች ይሆናል።
ለማንኛውም ለለውጥ ኃይሉ መልካሙን ሁሉ እየተመኘን የአገር ግንባታውም (nation building) ሆነ የመንግስት ግንባታው (state building) ትግል ከወዲሁ አሳታፊ፣ በጥናት ላይ የተመሰረተ፣ ግልጽነት የተሞላው እና ተጠጣቂነት የሚረጋገጥበት መሆኑን ማረጋገጥ ያስፈልጋል። መሰረቱ ያልጸና የአገርም ሆነ የመንግስት ግንባታ አሸዋ ላይ እንደ ተጣለ ድንኳን ነውና በነፈሰ ቁጥር መንገዳገድ ብቻ ሳይሆ ከስር መመንገልም ይኖራል።
ቸር ያሰማን!
Filed in: Amharic