>

የኦሮማራ ዘመነ መንግስት! (ስዩም ተሾመ)

የኦሮማራ ዘመነ መንግስት!
ስዩም ተሾመ
የኦሮማራ ዘመነ መንግስት የተጀመረው በዚህ ዓመት ከመሰላችሁ ተሳስታችኋል። ስለ ኦሮማራ ስርዖ መንግስት ባለማወቃችሁ አይፈረድባችሁም። ምክንያቱም እዚህ ሀገር ትላንትን ዘልለን ዛሬ መኖር የጀመርን ይመስል የጋራ ታሪክ የለንም። ከበጎ ይልቅ አስከፊ የታሪክ ገፅታ በሰረፀበት ማህብረሰብ ዘንድ “ኦሮማራ” የሚባል የሁለት ብሔሮች ጥምር መንግስት መኖሩን ማወቅ በጣም ከባድ ነው። ከአክሱም ስርዖ መንግስት ቀጥሎ የዛግዌ ዘመነ መንግስት፣ ከዚያ ቀጥሎ ደግሞ የአማራ ሰለሞናዊ ስርዖ መንግስት እንደመጣ ይታወቃል። ብዙዎቻችን የአማራ ሰለሞናዊ ስርዖ መንግስት ማዕከል ከሸዋ ወደ ጎንደር ከዞረ በኋላም የአማራ ዘመነ መንግስት እንደቀጠለ ሰምተናል፥ ተምረናል ወይም ይመስለናል። እውነታው ግን ከዚህ የተለየ ነው።
የአክሱም ዘመነ መንግስት የወደቀው በዛግዌ ስርዖ መንግስት ተሸንፎ ነው። የዛግዌ ዘመነ መንግስት የወደቀው በአማራ ስርዖ መንግስት ተሸንፎ ነው። የኦሮማራ ዘመነ መንግስት ግን የመጣው በማሸነፍና በመሸነፍ አይደለም። ይህ ማለት ግን በኦሮሞና አማራ መካከል ጦርነትና ግጭት የለም ማለት አይደለም። ከዚያ ይልቅ በሁለቱ መካከል በተካሄዱት ጦርነቶች አንዱ ወገን አሸናፊ ሆኖ የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት ለመቆጣጠር አልቻለም። በመሆኑም የአማራ ሰለሞናዊ ሰርዖ መንግስት ማዕከሉን ከሸዋ ወደ ጎንደር ካዞረ በኋላ ቢያንስ ለአራት ክፍለ ዘመናት ሀገሪቱን በጥምረት አስተዳድረዋል። ከ17ኛው ክፍለ ዘመን እስከ 19ኛው ክፍለ ዘመን መጨረሻ ድረስ ማዕከሉን ጎንደርና ወሎ በማድረግ ኢትዮጵያን ያስተዳደሩት በዋናነት የጎንደር አማራና የወሎ የጁ ኦሮሞዎች ናቸው። ከ19ኛው ክ/ዘመን መጨረሻ ጀምሮ እስከ 20ኛው ክፍል ዘመን መጨረሻ ማዕከሉን ሸዋ በማድረግ ኢትዮጵያን ያስተዳደረው ደግሞ በዋናነት የሸዋ አማራዎች እና ኦሮሞዎች ናቸው። ከአፄ ባካፋ እስከ እዮኣስ፣ ከትልቁ ራስ አሊ እስከ ትንሹ ራስ አሊ፣ ከአፄ ሚኒሊክ እስከ ልጅ እያሱ፣ ከአፄ ሃይለስላሴ እስከ አብይ አህመድ፣… ወዘተ ሙሉ በሙሉ፥ በግማሽ፥ በከፊል ኦሮሞና አማራ ናቸው።
ይሁን እንጂ የኦሮማራ ዘመነ መንግስት በሁለቱ ሕዝቦች ትብብርና አንድነት ላይ ብቻ የተመሰረተ አይደለም። ኦሮሞና አማራ የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት ለመቆጣጠር በተደጋጋሚ የኃይል ፍጥጫና ሽኩቻ ውስጥ ገብተዋል። በዚህ ምክንያት በተለያየ ግዜና ቦታ በሁለቱ ሕዝቦች መካከል ግጭትና ጦርነት ተቀስቅሷል። ሆኖም ግን አንዳቸውም ሌላው በዘላቂነት ማሸነፍ አልቻሉም። ባለፉት አራት መቶ አመታት በአማራና ኦሮሞ መካከል የሚደረግ የኃይል ሽኩቻ በሀገሪቱ ላይ “የሽብር ዘመን” (Reign of Terror) አስከትሏል። ይህ የሽብር ዘመን ደግሞ ከኦሮሞና አማራ ይልቅ ሌላ ሦስተኛ ኃይል የፖለቲካ ስልጣኑን በበላይነት እንዲቆጣጠር ያስችለዋል። በኦሮሞና አማራ የኃይል ሽኩቻ በፈጠረው ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን የሚቆጣጠረው የትግራይ ገዢ መደብ ነው።
የኦሮሞና አማራ ሽኩቻን ተከትሎ የሚከሰተው የሽብር ዘመን በሀገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ ክፍተት ይፈጥራል። ይህን ክፍተት በመጠቀም የትግራይ ገዢ መደብ ለአንድና ሁለት አስርት አመታት የኢትዮጵያን የፖለቲካ ስልጣን በበላይነት ይቆጣጠራል። በመጨረሻ ግን የኦሮሞና አማራ ልሂቃን በመካከላቸውን ያለውን የኃይል ሽኩቻ ወደ ጎን በመተው የጋራ ጥምረት ይመሰረታሉ። በዚህ መሰረት የትግራዩን ገዢ መደብ ተባብረው ከስልጣን ያስወግዳሉ። በዚህ መሰረት የኢትዮጵያ የፖለቲካ ኃይል ሚዛን የሚወሰነው በኦሮማራ ጥምረት መጥበቅና መላላት ነው።
Filed in: Amharic