>
5:38 pm - Wednesday November 30, 2022

በሀዋሳው ጉባኤ ህወሀት በቁሙ ተስካሩን መብላት ይጀምራል!!! (መሳይ መኮንን)

በሀዋሳው ጉባኤ ህወሀት በቁሙ ተስካሩን መብላት ይጀምራል!!!
መሳይ መኮንን
የሰሞኑ ወሬዎች
 –  መፈናቀል 

– የኢህአዴግ ጉባዔ

– የአቶ ጌታቸው አሰፋ ነገር
 
ኢትዮጵያ በሀገር ውስጥ ተፈናቃዮች ብዛት የዚህን ዓመት ሪከርድ መያዟ እየተገለጸ ነው። ጦርነት ከበጣጠሳት ሶሪያና ማብቂያ ባጣው ግጭት ከምትታመሰው የዲሞክራቲክ ኮንጎ በልጣ በውስጣዊ መፈናቀል ብዙ ሚሊዮን ዜጎች ያላት ሀገር በመሆን ኢትዮጵያ በቀዳሚነት እየተነሳች ነው። በኢትዮጵያ መፈናቀል ያልተከሰተበት አከባቢ ማግኘት ይቸግራል። ባለፉት አምስት ወራት ብቻ ከ1ሚልየን በላይ ዜጎች ተፈናቅዋል። ሰሞኑን ቤንሻንጉል ጉምዝ በተከሰተው ግጭት የተፈናቀሉ ዜጎች ቁጥር 70ሺህ ደርሷል። ዛሬ ከወልቃይት እንደሰማነውም በህወሀት ታጣቂዎች ጥቃት የደረሰባቸው በመቶዎች የሚቆጠሩ የአማራ ተወላጆች ወደ አጎራባች አከባቢዎች ተሰደዋል።
መፈናቀል ብርቱ ፈተና ሆኖ ከፊታችን ተደቅኗል። አሁን ባለው አሀዝ ከ2ሚሊየን በላይ ዜጎቻችን ከቤት ንብረታቸው ተፈናቅለው በተለያዩ አከባቢዎች ተጠልለዋል። መረጃዎች እንደሚያመለክቱትም በአንዳንድ የሀገሪቱ ክፍሎች የሚታየው የግጭት አዝማሚያ ተጨማሪ ዜጎች ይሀው እጣ ፈንታ ይገጥማቸዋል። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ እንዲሉ የተፈናቀሉትን ማቋቋም ሳንችል ተጨማሪ ዜጎች ከተፈናቀሉ ሁኔታውን ከባድድ ያደርገዋል። ለእነዚህ ዜጎች ለመድረስ ኢትዮጵያውያን የሚችሉትን እንዲያደርጉ ይጠበቃል። ኢትዮጵያ ከፍተኛ ማህበራዊና ፖለቲካዊ ቀውስ ውስጥ ለመግባቷ እንደምልክት የሚታየው መፈናቀል ከረሃብ ቀጥሎ መገለጫችን እንዳይሆን ያሰጋል።
የመፈናቀሉ መንስዔ የጎሳ ፖለቲካ ያመጣው መዘዝ መሆኑ አሻሚ አይደለም። ለ27 ዓመት ተኮትኩቶ ያደገውና በጥላቻ ፍግ የደለበው የጎሳ ፖለቲካ ዋጋ እያስከፈለን ነው። ይህ ቀውስ ትርፍ የሚያስገኝላቸው የፖለቲካ ነጋዴዎች ገበያው ደርቶላቸዋል። የፈነዱት ቀውሶች እንዲቀጣጠሉና አዳዲስ የግጭት አከባቢዎች እንዲፈጠሩ በማድረጉ ስውር እንቅስቃሴ እጃቸው የተነከረባቸው አክቲቪስቶችና የፖለቲካ ድርጅቶች የበለጠ ቀውስ ከመፍጠር አርፈው የሚተኙ አይደሉም። በተለይ ህወሀት የሚባል በክፋትና ተንኮል የቆመ ፋሽስታዊ ድርጅት በፊት ለፊትና በጀርባ ሆኖ ቁማሩን እየተጫወተ ነው። መፍትሄው አንድ ነው። አሁን የሚደረገው ቁስልን የማጠብ እርምጃ ዘለቄታዊ መፍትሄ አያመጣም። የጎሳ ፖለቲካን ለአንዴና ለመጨረሻ ጊዜ በማጥፋት ኢትዮጵያን ከተደቀኑባት ፈተናዎች መታደግ ብቸኛው መንገድ ነው።
የኢህአዴግ ጉባዔ
የየአባል ፓርቲዎቹ ተወካዮች ሀዋሳ እየገቡ ነው። ነገ ወሳኙ ጉባዔ ይጀመራል። ባለፉት ሁለት ሳምንት ከህወሀት በቀር ሌሎቹ አባል ፓርቲዎቹ በተናጠል ባደረጓቸው ጉባዔዎች መሰረታዊ የሚባል የፖለቲካ መስመርና የአመራር ለውጥ በማድረግ ለሀዋሳው ጉባዔ ተዘጋጅተዋል። በተለይም ኦዴፓ(ኦህዴድ) ና አዴፓ(ብአዴን) የኢህ አዴግን ቀኖና ሰብረው፡ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን ምስሶ ገንድሰው፡ አፍቃሪ ህወሀት የሆኑ አመራሮችን አራግፈው ወደ ሀዋሳ ማምራታቸው ጉባዔውን ተራ ጉባዔ እንዳይሆን ያደርገዋል።
አዴፓ(ብአዴን) የወሰደው እርምጃ በህወሀት መንደር ጫጫታን መፍጠሩን እየሰማን ነው። በይፋ የአብዮታዊ ዴሞክራሲን መስመር ማስወገዱን ያስታወቀው አዴፓ በምትኩ ልማታዊ ዴሞክራሲን እንደሚከተል አስታውቋል። ኤርሚያስ ለገሰ እንዳጫወተኝ የአዴፓ አካሄድ ኢህ ዴግን የሚያፈርስ ነው። የድርጅቱ መተዳደሪያ ደንብ ላይ በግልጽ እንደተቀመጠው የአብዮታዊ ዴሞክራሲን መንገድ መከተል የአባል ድርጅቶች ግዴታና ምርጫ የሌለው ጉዳይ ነው። አዴፓ ወይ ከኢህ አዴግ መውጣት አለበት አልያም ኢህአዴግ የሚባለው የህወሀት ፈረስ ሞቶ መቀበር ይገባዋል። ለነገሩ ኦዴፓ(ኦህዴድ) ተመሳሳይ የማፈንገጥ እርምጃ በመውሰድ ቀዳሚው ሆኗል። ኦዴፓ የኢህአዴግን የህልውና መሰረት የሆነውን የብሄር ጭቆና ትርክት በመቀየር የጀመረው አዲስ አቅጣጫ በህወሀት ላይ የተተኮሰ የመጀመሪያው ጥይት መሆኑ የሚዘነጋ አይደለም። አዴፓ(ብአዴን) የመጨረሻውን ቡጢ ሰነዘረና አረፈው። አብዮታዊ ዲሞክራሲ የሚለውን አፍና ጭራ የሌለውን ኮተት ህወሀት ብቻውን ታቅፎት ቀርቷል።
የህወህት መሪዎች አብዮታዊ ዲሞክራሲን የመጽሀፍ ቅዱስ ቃል አድርገውታል። በቅርቡ መግለጫ የሰጡት የህወሀት ም/ሊቀመንበር ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገ/እግዚያብሄር አሁን በሀገሪቱ የሚታየው ቀውስ ምክንያቱ አብዮታዊ ዲሞክራሲን በመተዋችን የመጣ ነው ብለዋል። መፍትሄውም ወደነበርንበት መመለስ ነው ሲሉ ገልጸዋል። በህወሀት መንደር ”አብዮታዊ ዲሞክራሲ ወይም ሞት!” መፈክር ጎልቶ እየተሰማ ነው። እንግዲህ ሌሎቹ አባል ፓርቲዎች ቆርጠው የጣሉትን መስመር ህወሀት ብቻውን ይዞ መዝለቁ ኢህ አዴግን ያፈራርሰዋል የሚለውን አስተያየት የሚያጠናክር ሆኗል። ባለው አሰላለፍና የሃይል ሚዛን ከሆነ ኦዴፓና አዴፓ የበላይነቱን ይዘዋል። በዚህም መሰረት ህወሀት ወይ ይደመራል አልያም ብቻውን ኢህአዴግን ታቅፎ ወደ መቀሌ ይገባል። ምርጫ የለውም። የቀድሞ የኢንሳ ዳይሬክተር ጀኔራል ተክለብርሃን ወልደአረጋይ አዴፓና ኦዴፓ ህወሀትን ሊያጠፉት ነው ብለው ሰሞኑን በትግራይ ቴሌቪዥን አሟርተዋል። እንደአፋቸው ያድርገው።
የአቶ ጌታቸው አሰፋ ነገር
ህወሀት ለማዕከላዊ መንግስቱ አሻፈረኝ ማለት ከጀመረ ሰንብቷል። ባለፉት 27 ዓመታት በህዝብና ሀገር ላይ በፈፀሟቸው ከባድ ወንጀሎች የሚፈለጉ የህወህት ሰዎችን በመደበቅ ለህግ ተገዢ አለመሆኑን በተደጋጋሚ አስመስክሯል። የኢንሳውን ሃላፊ ጨምሮ በርካታ ወንጀለኞችን አሳልፎ ላለመስጠት የወሰነው ህወሀት ይህን ግትር አቋሙን አቶ ጌታቸው አሰፋን ዳግም ለህወሀት ስራ አስፈፃሚ ኮሚቴ አባልነት በመምረጥ ያበጠው ይፈንዳ ብሏል።
የአቶ ጌታቸው አሰፋን የሰሞኑ ወሬ ኢሳት ላይ እርግማን እያሰሙ ላሉ ሰዎች ጮማ መረጃ ሆኖ ቀርቦላቸዋል። ኢሳት አቶ ጌታቸው አሰፋን በተመለከተ የእስር ማዘዣ እንደተቆረጠባቸውና ወደ ሱዳን ሳይሸሹ እንደማይቀር በመግለጽ ዜና ማቅረቡ የሚታወስ ነው። ሰሞኑ ህወሀት እኚህን ሰው የስራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል አድርጎ መምረጡን ሲገልጽ ከወዳጆቻችን ሳይቀር በእኛ ዜና ላይ ጥያቄዎች መነሳታቸውን ታዝበናል። ከኢሳት ላይ ስህተት ፍለጋ እንቅልፍ አጥተው የሚያድሩት ደግሞ ጥሩ የማጥቂያ ዱላ አገኘን ብለው የጭቃ ጅራፋቸውን መወርወር ጀምረዋል።
በእርግጥ ኢሳት አልተሳሳተም። ያስተላለፈው መረጃ ትክክለኛ ነው። የኢትዮጵያን ፖለቲካ ላይ ላዩን የሚመለከቱ፡ በተለይም የህወሀትን መሰሪ ባህሪ ያልተረዱ ሰዎች የሚሰነዝሩት አስተያየትና የሚሰጡት ድምዳሜ ነጥብ ሲያስጥል እያየን ነው። ህወሀት በወቅቱ የክስ ዋራንት የተቆረጠላቸውን አቶ ጌታቸው አሰፋን ወደ ሱዳን ለጊዜው እንዲሄዱ ማድረጉን ሰምተናል። በፌደራል መንግስቱ ሲጠየቁ የመለሱትም ወደ ሱዳን ሄዷል የሚል ነበር። አቶ ጌታቸው አሰፋን አሳልፎ መስጠት የህወሀትን አንድነት ያናጋል የሚል አቋም ላይ የደረሱት ህወሀቶች የክስ ዋራንት የተቆረጠባቸውንና ወደፊትም የማይቀርላቸውን አመራሮች ላለመስጠት ወስነዋል። ይበልጥም ይህን አቋማቸውን ለማሳየት በወንጀል የሚፈለጉትን ሰዎች ወደ ላይ በማምጣት የህወሀት ደጋፊዎችን ስነልቦና ለመጠገንንና በመሃላቸውም መተማመንን ለመፍጠር መወሰናቸውን ነው የሰማነው።
አቶ ጌታቸው አሰፋ ለምን የአዲስ አበባውን ስብሰባ ቀሩ? ወ/ሮ ፈትለወርቅ በወቅቱ ተጠይቀው አቶ ጌታቸውን ካየሁት ሁለት ሳምንት አለፈኝ ያሉት ለምን ይሆን? አንድ የህወሀት ሰው በዚያ ሰሞን አቶ ጌታቸው ለህክምና ሱዳን ይመላለሳል ሲሉ የተናገሩት የአጋጣሚ ነውን? የብሄራዊ መረጃና ደህንነት መስሪያ ቤት የጸረ ሽብር ግብረሃይል አዛዥ አቶ ተስፋዬ ኡርጌ ከሰኔ16ቱ የመስቀል አደባባይ ፍንዳታ ጋር በተያያዘ በተደረገባቸው ምርመራ የሳቸው የበላዮችም እጃቸው መኖሩ ምን ያመክታል? እውን አቶ ጌታቸው አሰፋ በሀዋሳው ጉባዔ ላይ ይገኙ ይሆን?
ህወሀት በቁሙ ተስካሩን መብላት ይጀምራል
ወደ ሀዋሳው ጉባዔ ልመለስ። ህወሀት ከአዴፓና ኦዴፓ ጋር ይፈታተሻል። አቅሙን ያውቃል። ደኢህዴን ሚናውን ለይቷል። የህወሀት አሽከርነት ከደኢህዴን ላይም ተገፎ ተጥሏል።
Filed in: Amharic