>

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ መንግስት የአሥተዳደር ሥርዓት ለውጥ እንደማያደርግ ጠቆሙ! (ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው) 

ጠ/ሚ ዶ/ር ዐቢይ መንግስት የአሥተዳደር ሥርዓት ለውጥ እንደማያደርግ ጠቆሙ!
ሠዓሊ አምሳሉ ገ/ኪዳን አርጋው
ይሄ ዜና በዐቢይ ላይ ተስፋ ለጣለ የዋህ ወገን ሁሉ ታላቅ መርዶ ነው!!!
ወያኔ/ኢሕአዴግ ግራው ግብት ብሎታል!!! መውጫ ቀዳዳው ጠፍቶበታል፡፡ ቀውሱን መፍታት ይፈልጋል በሌላ በኩል ደግሞ ከቀውሱ መንሥኤ መውጣት አይፈልግም፡፡ እንዲህ እንዳይተወው ልጅ እንዳይልሰው እሳት ሆነበትና መላው ቸገረው፡፡ በራሱ ላይ በር ቆልፎ እሪ የሚል ጅል አይታቹህ ታውቃላቹህ??? እንዲያ ማለት ነው ወያኔ/ኢሕአዴግ ማለት፡፡
ዐቢይ ባለፉት የትወና ጊዜያቱ የአንድነት ፖለቲካን አቀንቃኝ መስሎ ታይቶ ነበር፡፡ በዚሁ ትወናውም ብዙዎችን ከምሁር እስከ ያልተማረ ያለውን ማጃጃል ማታለልና ከጎኑ ማሰለፍ ችሏል፡፡
ይህ አገዛዝ የጎሳ ፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) ሥርዓትን በመከተል ኢትዮጵያን በጣጥሶ “አንተ እከሌ የምትባል ጎሳ ወይም ብሔረሰብ ነህ፡፡ ይሄ ክልል ያንተ እከሌ የተባልከው ክልል ነው እንጅ የሌሎቹ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አይደለም፡፡ የክልልህ ድንበር እዚህ ድረስ ነው፡፡ በዚህ ክልልህ ውስጥ ሁሉንም ነገር የማድረግ መብቱና ሥልጣኑ ያንተና ያንተ ብቻ ነው እንጅ የሌሎቹ ብሔር ብሔረሰቦችና ሕዝቦች አይደለም!”
በማለት ሸንሽኖ ሀገርን በጎሳና ብሔረሰብ ካቃረጠና ከፋፍሎ ከሰጠ በኋላ ጎሳዎችና ብሔረሰቦች ይህ የጎሳ ፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) የአሥተዳደር ሥርዓት በሰጣቸው መብትና ሥልጣን መሠረት መኖር፣ መሥራት፣ መንቀሳቀስ፣ ማግለልና መንፈግ ሲጀምሩ ቀውስ አስከትሎ ቀውሱ ቀውስን እየወለደና እየተስፋፋ እየተወሳሰበም አገሪቱን የቀውስ ማጥ ውስጥ ከቶ ስንት ኪሳራ ካስታቀፈን ከዚህ ሁሉ ጊዜ በኋላም “ከቀውሱ ትምህርት ተወስዶ አገዛዙ የአሥተዳደር ሥርዓት ለውጥ አድርጎ እርማት ወይም ማስተካከያ ያደረጋል!” ተብሎ ሲጠበቅ ጭራሽ እንደገና ወደኋላ ተመልሶ ይሄንኑ ጠንቀኛ የጎሳ ፌዴራሊዝምን አሁንም ሙጥኝ ማለታቸውን ጠ/ሚ ዐቢይ በዛሬው የአዋሳ የኢሕአዴግ ጉባኤ ላይ፦
“እንደ ኢትዮጵያ ላለችና ፈርጀ ብዙ ብዝኃነትን ለተላበሰች ሀገር ፌዴራሊዝም የተሻለ የአሥተዳደር ሥርዓት ነው፡፡ የፌዴራል መንግሥት አወቃቀር ደግሞ የሀገሪቱን ታሪካዊና ነባራዊ ሁኔታ ማገናዘብ ይኖርበታል፡፡ ክልላዊ አሥተዳደርን ከብሔር ማንነት ጋር ሳናምታታ ማስተናገድ ከቻልን እንደኛ ሀገር ላለ ነባራዊ ሁኔታ ፌዴራሊዝም ተመራጭ የአሥተዳደር ሥርዓት መሆኑ አያጠያይቅም!” በማለት አረጋግጠዋል፡፡ ይሄ ምን ማለት ነው???
“ክልላዊ አሥተዳደርን ከብሔር ማንነት ጋር ሳናምታታ ማስተናገድ!” ማለት ምን ማለት ነው??? ሁሉም የሀገሪቱ ክፍል በዕኩል መብት ደረጃ የሁሉም ኢትዮጵያውያን ከሆነማ ታዲያ “ይሄ ክልል ያንተ ነው እንጅ የእነሱ አይደለም! በዚህ ክልል ውስጥ ሁሉንም የማድረግ መብቱ ያንተ ነው እንጅ የእነሱ አይደለም!” ብሎ ማለትን ምን አመጣው ታዲያ???
“ይሄ ክልል የእኛ ነው ውጡልን!” ማለት ወይም “የዚህን ክልል ሀብት የመጠቀም መብት ያለን እኛ የክልሉ ባለቤቶች ነን እንጅ እናንተ የሌላ ክልል ሰዎች አይደላቹህም!” በማለት “የክልሉ ባለቤቶች አይደላቹህም!” የተባሉትን ማግለል ወይም የክልሉን ሀብት በዕኩል ደረጃ እንዳይጠቀሙ ማድረግ፣ በክልሉ የሥልጣን እርከኖች ድርሽ እንዳይሉ ማድረግ (ከአማራ ክልል በስተቀር) የጎሳ ፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) ሥርዓቱ የሰጠው መብት አይደለም ወይ??? የጎሳ ፌዴራሊዝም ማለት ይሄንን ማለት ካልሆነ “ይሄ ክልል የእነ እከሌ ነው የእነ እከሌ አይደለም፡፡ የዚህ ክልል መንግሥትም የእነሱ ነው፡፡ ድንበሩ ይሄ ነው!” ማለትን ምን አመጣው???
“አይ እንደዚህ ማለት አይደለም!” ካላቹህ የጎሳ ፌዴራሊዝሙ የሚሰጠው መብትና ራሱ ርዕዮተዓለሙ ከእጃቹህ ላይ ከሽፏልና፣ ፈርሷልና፣ ነፍሶበታልና (ኤክስፓየርድ አድርጓልና) ይሄንን ጎሳንና ቋንቋን መሠረት ያደረገውን የጎሳ የፌዴራሊዝም አከላለልን ጣሉት ወይም አስወግዱትና እንደሠለጠነው ዓለም ከዚህ ውጭ ያለውን የፌዴራሊዝም ዓይነት ማለትም ሁሉንም የኢትዮጵያን ክፍል የሁሉም ኢትዮጵያዊ ሀብት የሚያደርገውን ታሪክን፣ መልክአ ምድራዊ አመችነትን፣ የአየር ንብረትን…. መሠረት ያደረገውን የፌዴራሊዝም (የራስ ገዝ) አከላለል ሥርዓትን ወይም ደግሞ ሌላኛውን የአሥተዳደር ሥርዓት ማለትም በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል ያለው ሕዝብ ራሱ በመረጠው ተመራጭና በራሱ ቋንቋ መተዳደር፣ መመራት፣ መዳኘት፣ መማር የሚችልበትን አሐዳዊ የአሥተዳደር ሥርዓትን በቦታው ተኩ??? ከሁለቱ አማራጮች አንደኛውን መምረጥ ይቻላል፡፡
ይሄንን ካደረጋቹህ በኋላ በነጻ፣ ፍትሐዊና ተአማኒ ምርጫ ተወዳድራቹህ ማሸነፍ ከቻላቹህ አሥተዳድሩ፡፡ መመረጥ ካልቻላቹህ ደግሞ ቢያንስ እናንተው እራሳቹህ ያመጣቹህብንንና የፈጠራቹህብንን ጠንቅ እናንተው እራሳቹህ ነቅላቹህልናልና አስወግዳቹህልናልና ይሄንን አድርጋቹህ መሔዳቹህም አንድ ነገር ነውና እባካቹህ ይሄንን አድርጉ???
ወገኖቸ የሚገርማቹህ ነገር ምን አለ መሰላቹህ እነኝህ ሰዎች ወያኔ/ኢሕአዴጎችን ማለቴ ነው ሕገ መንግሥታቸው የሚላቸውን ነገሮች እንኳ አንደኛውን ሐሳብ ከሌላኛው ጋር ማስማማት ያልቻሉ ሰዎች ናቸው፡፡ ሕገመንግሥት የሚሉት እርስ በእርሱ የሚጋጭ ሐሳብ ያለበት ተራ ሰነድ ነው፡፡ ምክንያቱም “ማንኛውም ዜጋ በየትኛውም የሀገሪቱ ክፍል በነጻ የመዘዋወር፣ ኑሮን የመመሥረትና ሀብት የማፍራት መብት አለው!” ብሎ ሲያበቃ በሌላ በኩል ደግሞ የሕገመንግሥቱን ሉዓላዊ ሥልጣንና ክልላዊ ሥልጣኑን ለየ ክልሉ ጎሳዎችና ለብሔረሰቦች ሰጥቶ የየክልላቸው ባለቤቶች፣ ጌቶች፣ አራጊ ፈጣሪዎች አድርጎ ሙሉ መብትና ሥልጣን በመስጠት የዜጎችን በሀገሪቱ በነጻ የመዘዋወር፣ ኑሮን የመመሥረትና ሀብት ንብረትን የማፍራት መብት ይሽረዋል፣ ይጥሰዋል፣ ያስቀረዋል፡፡ ምክንያቱም አንድ ዜጋ ያለ ክልሉ ቢሔድ የዚያ ክልል ባለቤቶች ከተባሉት ከባለክልሎቹ ጋር ዕኩል የመስተናገድ መብት የለውምና ነው ከጅሎቹ የአማራ ክልል በስተቀር፡፡
የኢትዮጵያ ሕዝብ ሆይ! አገዛዙ ከላይ አስቀድሜ የገለጽኩትን የመፍትሔ እርምጃ ለመውሰድ የማይፈቅድና የማይፈልግ ከሆነ እሱ ባመጣው ቀውስ እርስ በእርስ ተፋጅተህ ከመጥፋትህ በፊት አገዛዙን አጥፍተህ እራስህን ከመታደግ ውጭ ሌላ አማራጭ የለህም!!! እንደምታየው ደግሞ አንድነት ኢትዮጵያ ምንትስ እያሉ ሲያጃጅሉን ከርመው እንደገና ወደኋላ እያሉ ያሉበት ሁኔታ ነውና ያለው ብትነሣ ነው የሚሻልህ ተነሥ!!! ጊዜ አታጥፋ!!!
ድል ለኢትዮጵያ ሕዝብ!!! ኢትዮጵያ ለዘለዓለም ትኑር!!!
Filed in: Amharic