>

አክቲቪስት ጅዋር እና የለማ መገርሳ ቡድን (ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ)

አክቲቪስት ጅዋር እና የለማ መገርሳ ቡድን

ዶ/ር በቃሉ አጥናፉ ታዬ

(ኮተቤ  ሜትሮፖሊታን  ዩኒቨርስቲ)

ተንሰራፍቶ የኖረውን የህወኃት አገዛዝ ለማንገዳገድ በርካታ ኢትዮጵያውያን ተሰደዋል፣ ተዋርደዋል፣ ሙተዋል፡፡ በባለፈው የሶስት ዓመታት የፖለቲካ ትግል እንን በአማራ፣ በኦሮሚያ፣ በደቡብ በርካታ ዜጎች ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ምንም እንኳን የአማራ ፋኖዎች፣ የኦሮሞ ቄሮዎች እና የጉራጌ ዘርማዎች አስፈላጊውን ትግል ቢያደርጉም፣ የእነሱ ትግል በብአዴን(አዴፓ) እና  በኦህዴድ(ኦዴፓ) የለውጥ ኃይሎች ባይታገዝ ኑሮ ለውጡ እውን ሊሆን አይችልም ነበር፡፡

ከአስተማማኝ ምንጭ ባገኘኋቸው መረጃዎች መሰረት በለውጡ የመጀመሪያው ጊዚያት በለማ መገርሳ ላይ በርካት የግድያ ሙከራዎች ታስበው  ነበር፡፡ ዳሩ ግን በርካታ ብርቅዬ ኢትዮጵያውያንን በጠራራ ፀሀይ የገደሉ የህወኋት ነፍሰ ገዳዮች በለማ መገርሳ ላይ እጃቸውን ማንሳት አልቻሉም፡፡ የለውጥን ኃይል በለማ አእምሮ ያስቀመጠው እግዚአብሔር፣ ለለማ መገርሳ አምባ መሸሸጊያ ሁኖ ጉዳዪ ከዚህ ደረሰ፡፡ ስለዚህ ምንም እንኳን የኢትዮጵያ ወጣቶች፣ ተቃዋሚዎች እና  የኢትዮጵያ ህዝብ ለለውጡ አስተዋጽኦ ቢኖራቸውም ያለ ለማ መገርሳ ቲም ሂደቱ ሊሳካ ባልቻለ ነበር፡፡ከሁሉም በላይ ግን ለውጡ እውን ለመሆኑ የእግዚአብሔር ፈቃድ ነበረበት፡፡ ለዚህም እግዚአብሔር ስሙ ይባረክ፡፡

እውነታው ይህ ሆኖ እያለ የለውጡ ምክንያቶች እኛ ነን ብሎ መናገር እና  መታበይ የለውጡን መነሻና እና መድረሻ ያለመረዳት ይመስለኛል፡፡ ይህ አልበቃ ብሎ ጃዋር  በናሁ ቴሌቪዥን ከበቀለ አመነ ጋር ባደረገው ዉይይት እንዲህ ሲል ሰማሁና አዘንሁ፡

”ኦሮምያን መገንጠል ብፈልግ ማን ከለከለኝ፤ አሁንም ማድረግ እንችላለን፡፡ አዲስ አበባን በቀለበት ዉስጥ አስገብተን በ24 ስአት ዉስጥ መቆጣጠር እንችላለን…” ሌላም…ሌላም…

ጃዋር ጥሩ ተናጋሪ፣ ፈጣና እና ብሩህ አዕምሮ ያለው አክቲቪስት ነው፤ ዳሩ ግን ስለ ራሱ ያለው ግንዛቤ የገዘፈ መሰለኝ፡፡ እነዚህ ሁሉ መፈክሮች መስዎት የከፈሉትን ሰዎች ዋጋ የሚያሳንሱ ብቻ ሳይሆኑ የአገሪቱን ሁኔታ በጥልቀት ካለመረዳት የመነጩ የግብዝ አስተሳሰቦች ናቸው፡፡ ኢትዮጲያን ማፍረስ መድረክ ላይ እንደማዉራት ቀላል አይደለም፡፡ ዶ/ር ዳኛቸው እንዳለው ኢትዮጲያን ቀብረናታል ያሉትን ሁሉ የምትቀብር አገር ነች፡፡ ይህን ለመረዳት ግን ነገረ ኢትዮጲያን ማወቅ ያስፈልጋል፡፡ ኢትዮጲያ በወሬ የምትፈርስ አገር አይደለችም፡፡ በተንኮልም ሊያፈርት የሞከሩትም አልቻሉም፤እነሱን ሁሉ በትናለች፣ ቀብራለች፡፡ ሚስጥሩ ታላቅ ነው፡፡

ጃዋር የሚያወራውን ያህል ለለውጡ አስተዋፅኦ ቢኖረው ንሮ በዚህ መጠን ያወራል ብየ አልገምትም፤ ጃዋር ይህን ያህል ካወራ፣ የለዉጡ የማእዘን ድንጋይ የሆኑት እነ ለማ መገርሳ ምን ይበሉ? እነ ዶ/ር ዐብይ ምን ይበሉ? እነርሱ ግን በጠባቡ የፖለቲካ ሜዳ ላይ ሰፊዋን ኢትዮጵያን ያልማሉ፣  እነርሱ ግን በእሳት መሀል ሁነው ለነገዋ ኢትዮጵያ መስዋትነትን ለመክፈል በጅቦች መካከል ሁነው ማንነታቸውን ያሳዩን ጀግናዎቻችን ናቸው እንጅ ባህር ማዶ ሁነው የሚጮሁ ፅናፅል አይደሉም፡፡ እነርሱ ግን አላማቸው ሩቅ፣ አስተሳሰባቸው ረቂቅ ስለሆነ፣ በጥቃቅን ስኬቶች የሚረኩ ሰዎች ስላልሆኑ ማውራት ባህሪያቸው አይደለም፡፡ ከራሳቸው በላይ አርቀው በማያስቡ፣ በባለጌ መዳፍ እጅ የገባችውን ኢትዮጵያን፣ በመንፈስ ደክማ በስጋ የጎሰቆለችውን ኢትዮጵያን፣ በግፈች እጅ ተይዛ በደም የጨቀየችውን ኢትዮጵያን የታደት ለማ መገርሳ እና ዐብይ አህመድ ምን ያውሩ? ፊታቸው ማድያት እስከሚያወጣ እና ጉበት እስኪመስል ድረስ ስለ ኢትዮጵያ እና ስለ ህዝቦችዋ የሚቃትቱት እነርሱ ምን ይበሉ አንተ እንዲህ ካልህ ጅዋር?

ከአንድ የፖለቲካ አክቲቪስት የምንጠብቀው እንዲህ አልነበረም፤ የፖለቲካ አክቲቪስት ፍቅርን፣ አንድነትን፣ ሰላምን እየሰበከ፣ ለመሪዎች ግብአት የሚሆን የፖለቲካ ትንታኔ እያቀረበ ህዝቡን ያረጋጋል እንጅ ለሁሉም ጉዳይ አድራጊ ፈጣሪ እራሱን አድርጎ አይሰይምም፡፡ ለሚዲያ ቅርብ ስለሆንን ወይም ሚዲያ ስላለን እንዲሁ ዝም ብለን ማውራት ከፖለቲካ አክቲቪስት አይጠበቅም፡፡

አክቲቪስቶች እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች በትንሽ ስራ የመርካት ባህሪይ  አይታይባቸውም፡፡ አለም ዐቀፍ እውቅናን የተጎናፀፉት የሰብዕዊ መብት አቀንቃኞች (ማርቲን ሉተር ኪንግ፣ ጋንዲ፣ ማንዴላ…) ይቅርና አገራዊ የሆኑ የሰብአዊ መብት ተሟጋች እንን በሰሩት ስራ ሲኮፈሱ አይታዩም፡፡ ዘመን ተሻጋሪ ራዕይ ይዘው፣ ፍፁም ሰብአዊ አስተሳሰብ አንግበው፣ በጎጠኝነት ልክፍት ሳይማቅቁ፣ ሁሉን አቀፍ ስራ እየሰሩ በዚህ መጠን ሲያወሩ አላየሁም፣ አልሰማሁም፡፡  

ህወሀት በሰፋው ከጎሳ ፖለቲካ ጥብቆ ሳንወጣ፣  ዘመን ተሻጋሪ ራዕይ ሳንይዝ፣ ፍፁም ሰብአዊ አስተሳሰብ ሳናነግብ የተዋጣለት አክቲቪስት እና የሰብአዊ መብት ተሟጋች መሆን አይቻልም፡፡ ዳሩ ግን ወፍ እንደ አገርዋ ትጮሀለች ነውና ይህን መሆን ካልተቻለም ይህን ያህል ማዉራት ተገቢ አይደለም፡፡

Filed in: Amharic