>
5:13 pm - Friday April 18, 4977

ጥቂት ነጥቦች ስለ ለውጥ ወቅት መሪዎችና ተከታዮች!!! (ዶ/ር ታደሰ ብሩ) 

ጥቂት ነጥቦች ስለ ለውጥ ወቅት መሪዎችና ተከታዮች!!!
ዶ/ር ታደሰ ብሩ 
አሁን አገራችን ፈጣን በሆነ  ለውጥ ውስጥ ትገኛለች።  በእንደዚህ ዓይነት ወቅት የሀገርም ሆነ የድርጅት መሪ መሆን በጣም አስቸጋሪ እና ከፍተኛ ብልሀትና ትዕግስት የሚጠይቅ ነው። በለውጥ ወቅት የሚፈፀም ትንሽ ስህተት አገርን ለብርቱ ጉዳት ሊዳርግ ስለሚችል የፓለቲካ ፓርቲዎች መሪዎችና ተከታዮች በከፍተኛ የኃላፊነት ስሜት መንቀሳቀስ ይኖርባቸዋል።
የሚከተሉት ሶስት ነጥቦች በለውጥ ውስጥ በምትገኝ ሀገራችን ውስጥ ያሉ ድርጅትን የሚመሩ ሰዎች ቢመለከቷቸው ይጠቅሙ ይሆናል።
 
1. ለውጥ እና ሥርዓት
በለውጥ  ወቅት ሀገርን ወይንም ድርጅትን የመምራት ኃላፊነት የወደቀባቸው ሰዎች ነባር ህጎችንና ልማዶችን ማፈራረስ ይጠበቅባቸዋል። ለውጥ ማፍረስን፤ በነባር ህጎችና ልማዶች ላይ ማመጽን ይጠይቃል። ለውጥ በስልጣን ላይ ያለውን አመራርን መቃወምን፤  አልታዘዝም ማለትን;፤  አመራሩ ከስልጣን እንዲወገድ ማስገደድን  ይጠይቃል። ይሁን እንጂ  አገርም ይሁን ድርጅት የስልጣንና  የህግ ክፍተቶች አይፈልጉም።  ህግ ከተሻረ አዲስ ህግ መውጣት አለበት። አመራር ከስልጣን ከለቀቀ ሌላ አመራር ኃላፊነት መውሰድ አለበት። ልማድ ከተሻረ በአዲስ ልማድ መተካት አለበት።  ይሁን እንጂ አዳዲስ ህጎች እስኪወጡ፤ አዲስ አመራር ስልጣን ላይ እስኪደላደል ጊዜ ሊወስድ ይችላል። አዳዲስ ልማዶች እስኪለመዱ በጣም ረዥም ጊዜ ሊወስድ ይችላል።
ተከታዮች ለውጥ ይፈልጋሉ፤ መረጋጋትንም ይሻሉ። ሁለቱን አብሮ ማስኬድ ግን ከባድ ፈተና ነው። ተከታዮች ረዥም ጊዜ የመጠበቅ ትዕግስት ላይኖራቸው ስለሚችል የለውጥ ወቅት መሪ የስልጣን እድሜ አጭር ሊሆን ይችላል።
የለውጥ ወቅት መሪዎች ስኬታማ እንዲሆኑ ከተከታዮች ብዙ ይጠበቃል። ነባር ሥርዓትን በማፍረስ መሪውን የተባበረ ተከታይ አዲስ ሥርዓት በመገንባትም ሊተባበር ይገባል። ይህም ማለት መሪዎች ብቻ ሳይሆኑ ተከታዮችም ከአማፂነት ወደ ሥርዓት አክባሪነትና አስከባሪነት መለወጥ ይኖርባቸዋል።
 
2. ተስፋ እና ተግባር
አብዛኛውን ጊዜ ለውጥ የሚጀምረው ከሀሳብ ነው። የለውጥ ሀሳብ ብሩህ ተስፋን ይሰጣል። ጥሩ የለውጥ መሪዎች የለውጥ ሀሳብ አመንጪዎችና ተስፈኞች ናቸው። ተከታዮች የመሪዎቻቸውን የለውጥ ሀሳብ ተረድተው የራሳቸው ማድረግ ይጠበቅባቸዋል። ተከታዮች የለውጡ ባለቤቶች መሆናቸው ሊሰማቸው፤ “ይህ ለውጥ የኛ ለውጥ ነው” ሉሉ ይገባል።  ይህ መሆን የሚችለው ግን የለውጡ ሀሳብ እና ለውጡ የሚሰጠው ተስፋ የተከታዮችን ልብና አዕምሮ መማረክ ሲችል ነው።
ይሁን እንጂ ሀሳብ ብቻውን ለውጥ አይሆንም። ሰው በተስፋ ብቻ ረዥም ጊዜ መቆየት አይችልም። ለውጥ ተግባር ይፈልጋል። በተግባር የሚታይ ነገር ከሌለ ተከታዮች በተስፋ ይዞ መቆየት አይቻልም። ተከታዮች ለውጡ በሕይወታቸው ውስጥ አዲስ ነገር ፈጥሮ ማየት ይፈልጋሉ።  በለውጥ ወቅት በተስፋ እና በተግባር መካከል ግጭት ሊፈጠር ይችላል።
በለውጥ ወቅት የተከታዮችን ተስፋ የመግራት ሥራ (expectation management) መሠራት አለበት። ተከታዮች ለውጡ ሊፈጥራቸው ከሚችላቸው ነገሮች በላይ እንዳይጠብቁ መደረግ ይኖርበታል። ልክ ከለውጡ ማግስት ጀምሮ  የአገሪቱ ችግሮች በሙሉ መፍትሄ ያገኛሉ የሚል የዋህ ግምት እንዳይፈጠር ጥንቃቄ  መደረግ አለበት።
 
3. መምራት እና መከተል
ለውጥ የጨለማ ጉዞ መሆን የለበትም፤ በተቻለ መጠን በጥሞና የታሰበበት መርሀ ግብር ሊኖረው ይገባል። የለውጥ ጊዜ መሪዎች ተከታዮቻቸውን ቀድመው የለውጡን የጉዞ መስመር ማሳየት አለባቸው።  የለውጥ መሪዎች የለውጥ ፍኖተ ካርታ ማዘጋጀት አለባቸው።  ይሁን እንጂ የለውጥ መሪዎች ፍኖተካርታ ከተከታዮች የለውጥ ተስፋ መቀዳት አለበት። የለውጡ ፍኖተ ካርታ ተከታዮች የሚመኙትን የሚያገኙ መሆኑን የሚያረጋግጥ ሊሆን ይገባል።
በዚህም ምክንያት የለውጥ ጊዜ መሪዎች ተከታዮቻቸውን ይመራሉ፤ ተከታዮቻቸውንም ይከተላሉ።  በአንድ ጊዜ መምራትና መከተልን ተግባራዊ ማድረግ ከባድ ነው፤ ሆኖም ግን ግድ ነው። በለውጡ ሂደት የተከታዮች ፍላጎት ሊለዋወጥ ስለሚችል አንዴ የወጣ ፍኖተ ካርታ ብዙም ሳይሠራበት መለወጥ ይኖርበት ይሆናል። በለውጥ ወቅት ብዙ ነገሮች ተለዋዋጭ መሆናቸው መረዳት ይገባል። ስለሆነ የለውጥ ወቅት እቅዶች ራሳቸው በለውጥ ሂደት ውስጥ ማለፍ አለባቸው።
Filed in: Amharic