>
6:37 pm - Monday May 16, 2022

የለዘብተኛ ፖለቲካ አራማጁ የኦሮሞ ህዝብና ጥቂት አክራሪዎች ሊታረቅ የማይችል ልዩነት!!! (ፋሲል የኔአለም)

የለዘብተኛ ፖለቲካ አራማጁ የኦሮሞ ህዝብና ጥቂት አክራሪዎች ሊታረቅ የማይችል ልዩነት!!!
ፋሲል የኔአለም
ጫፍ ላይ የቆሙ ሃይሎች ምንጊዜም  ለዘብተኝነትን ( ሞደሬቲዝምን ) መጥላታቸው የሚጠበቅ ነው። ኢሳትም የ”ሞደሬት” ፖለቲካ አራማጅ እንደመሆኑ ጫፍ ላይ በቆሙ ሃይሎች መጠላቱ የሚገርም አይሆንም!!!
ጥቂት ሊህቃን ለመሳል እንደሚፈልጉት ሳይሆን፣ የኦሮሞ ህዝብ moderate (መሃልኛ) የፖለቲካ አስተሳሰብ መከተል የሚፈልግ ነው። እንኳንስ ህዝቡ፣ ጫፍ ላይ የቆሙት ሊህቃንም ቢሆኑ በአደባባይና በጓዳ የሚናገሯቸው ነገሮች የተለያዩ ናቸው። ብዙዎቹ በአደባባይ ጽንፈኛ፣ በጓዳ ደግሞ ለዘብተኞች ናቸው። አንዳንዶች እንዲያውም የስልጣን እና የጥቅም ጉዳይ ሆኖባቸው እንጂ፣ በአደባባይ የሚናገሩትን ሁሉ እንደማያምኑበት በጓዳ ስንጫወት የታዘብኩበት አጋጣሚ አለ፤ ከራሳቸው በላይ አክራሪ መስለው ለመታየት በሚሞክሩ ተከታዮቻቸው ሳይቀር ሲያሾፉ ( ሲያላግጡ) የሰሟሁዋቸው “መሪዎች” አሉ። የእነዚህ ሰዎች ትልቁ ችሎታ ተዋናይነታቸው ነው፤ ቀን ላይ ተከታዮቻቸውን በአንድ ብሄር አባል ላይ አዘምተው፣ ማታ ላይ የዚያን ብሄር አባል ሰው አቅፈው ለመተኛት የማይቸግራቸው ናቸው።
በኢትዮጵያ ብሄርን እንደ መስፈርት ሳይጠቀሙ፣ ከየትኛውም ህዝብ ጋር ጋብቻ ለመመስረት ችግር የሌለባቸውን ሁለት ብሄሮች ጥቀስ ብባል ኦሮሞና አማራን አስቀድማለሁ። የኦሮሞ ህዝብ የ”ሞደሬት” ፖለቲካን እንዲደግፍ የሚያደርገውም ይህ ዘመናዊ (modern) ባህሪው ይመስለኛል። እነዚህ ብሄሮች ከየትኛውም ብሄር ጋር ለመቀላለቀል አለመቸገራቸው፣ በኢትዮጵያ ውስጥ ቅይጥ ማንነት እንዲፈጠር ከፍተኛ አስተዋጽዖ አድርገዋል። አንድ ጓደኛዬ የነገረችኝ ታሪክ ትዝ አለኝ። እሱ ኦሮሞ ነው፤ እሷ አማራ ናት። እና በጣም ተዋደዱ። ሊጋቡ እየተዘጋጁ እያለ፣ እሱ ኦነግ ሆነ።” ለፖለቲካ ትግሌ አልተመቼኝም” አለና ከልጅቷ ጋር ተለያዬ።  እሷም፣ በጣም ብታዝንም፣ መልካሙን ሁሉ ተመኝታለት ተለያዩ። እሱም የብሄሩን ልጅ  መርጦ አገባ። ከተወሰኑ ጊዜያት በሁዋላ “አልፈልግሽም” ያላትን ልጅ አፈላልጎ አገኛትና ይቅርታ ካደረገችለት ሚስቱን ፈቶ ሊያገባት እንዳሰበ ነገራት። ፍቅሩ ብሄሩንም ፖለቲካውንም አሸነፈበት። የልጅቱ መልስ ግን ከሁለት ያጣ ጎመን አደረገው።
የኦሮሞን ህዝብ መሳል የምፈልገው በለማና በአብይ ስዕብና ነው፤ እነዚህ ሁለት ሰዎች ለዘብተኛ (moderate) የሆነውን የአብዛኛውን የኦሮሞ ህዝብ አስተሳሰብ ይወክላሉ። የዚህ ሰፊ ህዝብ የውበት ዳርቻ ናቸው ብል አሳንሼው እንደሆን እንጅ አላበዛሁትም። ቀኑን ሙሉ ልዩነትን ሲዘሩ የሚውሉ በጣም የተማሩ የኦሮሞ ልጆች፣ የዲግሪያቸው ብዛት  የወጡበትን ማህበረሰብ  ለመረዳት ባለማስቻሉ አዝንላቸዋለሁ።። Much learning doesn’t teach understanding የሚለው ወርቃማ አባባል ለእነዚህ ሰዎች ተስማሚ ይመስለኛል።
 ባልደረቦቼ ገላኔና በፈቃዱ ስራ ለቀቁ በሚል አንዳንድ የተማሩ የኦሮሞ ልጆች ሲደሰቱ አይቼ አዘንኩላቸው፤ ኦሮሞን ቢያውቁት ኑሮ ደስታቸው ወደ ሃዘን በተለወጠ ነበር።  ገላኔና በፈቃዱ እንደ  ለማና አብይ የሞደሬት አስተሳሰብ ወኪሎች ናቸው። እነዚህ ጀግኖች ጫፍ ላይ የቆሙ ሃይሎች የሚያወረውሩት  የቆሻሻ ክምር ሳያሰጥማቸው እስከዛሬ መዝለቃቸው፣ የጽናታቸውን ወሰን ያሳያል።  ጫፍ ላይ የቆሙ ሃይሎች ምንጊዜም  ለዘብተኝነትን ( ሞደሬቲዝምን ) መጥላታቸው የሚጠበቅ ነው። ኢሳትም የ”ሞደሬት” ፖለቲካ አራማጅ እንደመሆኑ ጫፍ ላይ በቆሙ ሃይሎች መጠላቱ የሚገርም አይሆንም። ያሉኝ መረጃዎች የሚያሳዩት አብዛኛው የኦሮሞ ህዝብ የሚሰማው ኢሳትን ነው፤ ለምን? “ሞደሬት” ህዝብ “ሞደሬት” ሚዲያን መስማቱ ተፈጥሮአዊ ስለሆነ። ኢሳት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ጣቢያዎችን ከፍቶ በብዙ ቋንቋዎች በማሰራጨት የሞደሬት ፖለቲካ አሸናፊ ሆኖ እንዲወጣ ትግሉን ይቀጥላል።
Filed in: Amharic