>

ኤዲያ! (ፈላስፋው ጭሰኛ)

ኤዲያ!
ፈላስፋው ጭሰኛ
*“ክፋት- እሪሪሪሪሪ”
“እባክዎ ጌታዬ፤ ወደ ሐገር ከመግባትዎ በፊት ክፋትዎን ያውልቁ?” 
ክፋት- ውልቅ… ቁጭ – ልክ እንደ ጃኬት!
እለፍ ቀጣይ ተረኛ…
“ዘረኝነት- እሪሪሪሪሪሪ”
“እባክዎ ጌታዬ፤ ወደ ሐገር ከመግባትዎ በፊት ዘረኝነትዎን ያውልቁ?” 
ዘረኝነት ውልቅ… ቁጭ – ልክ እንደ ባርኔጣ!…
እንዲህ ቢሆንማ ኖሮ..
ድምፅሽ ያምራል” አላት።
“ያንተም ውብ ነው” አለችው።
“ምን እግር ጣለሽ?  ከየት መጣሽ ውዴ?” ጠየቃት።
“የእህል ውሃ ነገር፣ አንተን ሳታውቂው አትሙቺ ሲለኝ” ትመልሳለች፤ ሆድ በሚያባባ ድምጽዋ።
እንዲሁ አልጋ ላይ እየተንከባለሉ፣ የረባ ያልረባውን ሲጨዋወቱ ይዋደዳሉ። ፍቅር ይጠናል። አልፈው ተርፈው ቃል ይገባባሉ።
“እኔ እንደተፈለፈልኩ፣ አንተን ነው የማገባው” ትለዋለች፡፡
“እኔስ ካላንቺ ማን አለኝ!” ይላታል።
እንዲያውም ለጫጉላ ሽርሽር በሰዓታት በረራ ተጉዘው፣ አሰብና ምፅዋ ለመዝናናት ሁሉ ተመኝተዋል። (በረራው በክንፍ ይሁን በአውሮፕላን አንድዬ ይወቀው!)
በፍቅሩ ጥናትና ጊዜዋም ደርሶ ሴቷ ቀድማ እንቁላሏን በርቅሳ ወጣች – ርግብ ነበረች።
የውጪው አለም እንዴት እንደሚያምር …
ስለ ፀሐይ ድምቀት …ስለ ነፋሻው አየር…መብረር እንዴት ደስ እንደሚል– ሁሉንም እየተረከች ገና በቅርፊት ያለውን ወዳጇን አጓጓችው።
ቶሎ እንዲፈለፈልላት በላባዎቿ አቅፋ፣ ሙቀት በመስጠት ትዘምራለች… “የጓሮዬ አባሎ – አብብ ቶሎ
የጓሮዬ ጦስኝ – አብብልኝ” እያለች።
ውብ ዜማዋ ልቡን ሰውሮታል … ሙቀቷ የልብ ልብ ሰጥቶታል … ፍቅሯ ጉልበት ሆኖት፣ ቅርፊቱን ሰብሮ ተጠመጠመባት – እባብ ነበር።
“ዘመኑ ምናለኝ ዘመኑ ወርቅ ነው፤ ፍቅር ያለቀ ዕለት…”
እፈራለሁ…
በፍቅርና በይቅርታ፣ “ከእነ ቅርፊታቸው” የታቀፉት ሁሉ ሲፈለፈሉ፣ ርግብ ወይም ዶሮ ባይወጣቸውስ? እላለሁ።
እባብም ቢኖርስ?..
ፍቅር ባያልቅ እንኳ፣ እንደ አስራ ሦስት ወር ፀጋ፣ ከአመት አመት የአገራችን ሰማይ በፍቅር ቢሸፈን እንኳ … አብሮ የማያዛልቅ ስንት አይነት ማንነት አለ?… “በእንቁላሉ ጊዜ…”ንም ለመተረት’ኮ፣ ከመነደፍ መትረፍና መሰንበት ያስፈልጋል፤ ወገኖቼ።
..እንዲህ አምናለሁ…
ሁሉም እጅ ተዘርግቶ አይታቀፍም። አገር በፓስተር አብይ በገራገር የእንደመር ፈሊጣዊ ፈገግታ ብቻ አትመራም። በኮስታራ ግንባርና በአርጩሜም ጭምር እንጂ። በየመድረኩ እየተቃቀፉ መሳሳቁን ለበላቸው ግርማ ተውለት- እስቲ ‘ጊነስ ወርልድ ቡክ ኦፍ ሪከርድስ’ ላይ ይመዝገብበት። በሰው እንጀራ አትግቡ። ፈገግታ ጥሩ ነው፤ ከበሽታ ይከላከላል፣ ረዥም ዕድሜንም ያጎናፅፋል … በሰዎች ዘንድ ተቀባይነትንም ይቸራል … (ይላሉ ተመራማሪዎቹ)፡፡
ዝም በል! ሱፍ ገበርዲን ለብሶ …. ሱፉን ግጥም አርጎ፣ ፀጉሩን ተከረክሞ– የመጣው ሁሉ “መልዓክ” መስሎ ከታየን፣ (አይ ያለው ማማሩ¡) አስቴር አወቀን መሆናችን ነውና፣ ድምፃችንን ሞርደን፣ ከአዝማሪው ቴዲ አፍሮ ቀጥሎ ባለው ሳምንት ኮንሰርት ብናዘጋጅስ?
አብሮ ለመቀጠል፣ አብሮ ለመሰንበት ግን “ከሱፉ ስር ማነው?” ነው ጥያቄው። ኧረ የምን ሱፍ፣ ከቆዳው ስር ራሱ ማነው?
እንደ አንድዬ ልብንና ኩላሊትን መመርመር ባይሆንል፣ “ጊዜው ደርሶ እንቁላሉ ሲፈለፈል ምን ይወጣል?” ብንል ደግ ነው። “አስኳሉ ጤነኛ ነው ወይ?” ማለትም አይከፋም ።
መፈልፈሉ ይቅር … ለመብልነት እንኳ ስንገዛ፣ በአውራ ጣታችንና በሌባ ጣታችን መሐል ይዘን ፤ አንድ አይናችንን ጨፍነን ፤ ወደ ፀሐይ አንጋጠን፤ በአንድ አይናችን አጮልቀን አይተን አይደል እንቁላል የምንገዛው? ውስጡ ቢጫ ፣ብርሐን ፣ ንፁህ መሆኑን ፈትሸን…!
አንዳንድ ሰው አለ፤ ልክ እንደ እንቁላል ወገቡን ይዛችሁ፣ ወደ ፀሐይ በአናቱ በኩል ቀና አድርጋችሁ ስትፈትሹት፣ በተረከዙ በኩል ፀሐይዋን ካላያችሁ የማትቀበሉት፣ የማታምኑት፣ የማታቅፉት።
ለምግብነትም ለዘርም፣ ለምንም የማይሆን ደደብ…!
..እንዲህ እመኛለሁ…
ያ በየኤርፖርቱና በየሆቴሉ ደጃፍ ያደፈጠው ማሽን፤ ጫማና ጃኬት ሳይቀር አስወልቀው የሚፈትሹበት ግድግዳ አልባ፣ መዝጊያ አልባ፣ የብረት ጉበን … ለአምስት ሳንቲምና ለፀጉር ማስያዣ ቢም እንደዚያ “እሪሪሪሪሪ” ከሚል፣ ምነው የየሰውን አመል እየጮኸ ቢያጋልጥ…!
አለ አይደል…
“ክፋት- እሪሪሪሪሪ”
“እባክዎ ጌታዬ፤ ወደ ሐገር ከመግባትዎ በፊት ክፋትዎን ያውልቁ?”
ክፋት- ውልቅ… ቁጭ – ልክ እንደ ጃኬት!
እለፍ ቀጣይ ተረኛ…
“ዘረኝነት- እሪሪሪሪሪሪ”
“እባክዎ ጌታዬ፤ ወደ ሐገር ከመግባትዎ በፊት ዘረኝነትዎን ያውልቁ?”
ዘረኝነት ውልቅ… ቁጭ – ልክ እንደ ባርኔጣ!…
እንዲህ ቢሆንማ ኖሮ..
ቅርፊቱ፣ ሱፉ፣ ቦዲው ካራሶሪያው … ምናምኑ እያማለለን፣ የመጣውን ሁሉ ተንሰፍስፈን ባላቀፍን! አይ ሀባሻ።
Filed in: Amharic