>

የህወሓት ሙከራ ከሽፏል!!! (ሀብታሙ አያሌው)

የህወሓት ሙከራ ከሽፏል!!!
ሀብታሙ አያሌው
ዶ/ር አብይ አህመድ እና አቶ ደመቀ መኮንን  በድጋሚ ተመርጠዋል።  ወይዘሮ ሞፎርያት ካሚል ድምፃቸውን ለአቶ ደመቀ በመስጠት ባለፈው ምርጫ አቶ ደመቀ ለዶክተር አብይ ቅድሚያ በመስጠት ያሳዩትን ይበል የሚያሰኝ ውሳኔ ደግመዋል።  ምርጫው ከመካሄዱ በፊት በቲም ለማ ኮር አመራር መካከል ተፈጥሮ የነበረው  ከፍ ዝቅ እረግቦ መግባባት ላይ ተደርሷል  የለውጥ አደናቃፊው ቡድን ሴራ ግን እንደቀጠለ ነው የሚለውን ማስረጃ ማድረሴ ይታወቃል። ወይዘሮ ሞፎርያት ካሚል ከልብ ለወሰደችው በሳል ውሳኔ ምስጋና ይገባታል።
ኢህአዴግ እንደ ድርጅት ይህ ነው የሚባል የአገሪቷን ችግር ሊፈታ የሚችል የውሳኔ  አቅጣጫ ያላስቀመጠ በዚያው በአብዬታዊ ዲሞክርሲው ርዕዬት አለም ውጥንቅጥ እና በግንባሩ አባል ድርጅቶች መካከል በተፈጠረ አለመተማመን እና መሰረታዊ የአቋም ልዩነት ዳርና ዳር ቆሞ አለባብሶ ለመጓዝ እየሞከረ ያለ ድርጅት መሆኑ ግልፅ ነው። ይሁን እንጂ በትግል ሂደት ለውጥ አመጣለሁ ብሎ ቃል በመግባት በርካታ ተግባራት ያከናወነው የእነ ዶክተር አብይ ቲም ችግር ላይ ወድቆ አክራሪ ብሔርተኛው ቡድን ወደፊት እንዳይመጣ ሰፊ እርብርብ አድርገናል። ቸር ተመኝተናል፣ እናም ለጊዜው የተመኘነው ቸር ሰምሯል የለውጥ ሃይሉ ሌላ እድል አግኝቷል።
ዶ/ር ደብረጽዮ ከድርጅታቸው 29 ድምጽ ሲነፈጉ በአንጻሩ አቶ ደመቀ ከህወሀት 15 ድምጽ አገኙ!!
ፋሲል የኔአለም

ከ15 ያላነሱ የህወሃት የማዕከላዊ ኮሚቴ አባላት ከደብረጺዮን ይልቅ ደመቀ መኮንን መምረጣቸው፣ በክልሉ ለውጥ የሚፈልጉ አመራሮች መኖራቸውን የሚያሳይ ነው። ደመቀ መኮንን የ3ቱን ድርጅቶች ድምጽ ቢያገኙ ሊያገኙ የሚችሉት አጠቃላይ ድምጽ 135 ነው።  14 ድምጾችን ከህወሃት ካላገኙ በስተቀር 149 ድምጽ ሊያገኙ አይችሉም። ደብረጺዮን ደግሞ ( ጌታቸው ሲቀነስ) ቢያንስ 44 ድምጽ ማግኘት ነበረባቸው። ያገኙት ግን 15 ብቻ ነው። ድርጅታቸው 29 ድምጾችን ነፍጓቸዋል። ከነዚህ ድምጾች ተቀንሶም ለደመቀ ለመሰጠቱ ተጨማሪ ማሳያ ነው።  ህወሃት ለአብይ ሙሉ ድምጿን መስጠቷ “ስማርት” ፖለቲካ ለመጫወት እንዳሰበች ያስታውቃል። እንደማታሸንፍ ካወክ የሚያሸንፈውን ደግፈህ ከቆምክ ጠላትን ትቀንሳለህ። ለማንኛውም እነዛ ባለ 14 ድምጾች ለለውጡ ፍጥነትም ሆነ ለሰሜኑ ክፍል መረጋጋት ሊጠቅሙ ይችላሉና ታውቀው ቢበረታቱ መልካም ነበር።

Filed in: Amharic