>
10:44 pm - Tuesday August 16, 2022

ኢህአዴጎች የተሰበሰቡበት አዳራሽ ውስጥ የሚጠጣ ሃይላንድ ላከፋፍል በገባሁበት ወቅት የተያዘ 'ሙድ ( በአሳየ ደርቤ)

ኢህአዴጎች የተሰበሰቡበት አዳራሽ ውስጥ የሚጠጣ ሃይላንድ ላከፋፍል በገባሁበት ወቅት የተያዘ ‘ሙድ

አሳየ ደርቤ

ከፊት ለፊት ከአቶ ደመቀ መኮንንና ዶክተር ደብረ-ጺዮን መሃከል ጠቅላይ-ሚኒስቴሩ ተቀምጧል፡፡

ዘግይቶ ወደ አዳራሹ የመጣው አቶ ለማ መገርሳ ከደጺ አጠገብ ያለውን ወንበር ክፍቱን ትቶ ዳር ላይ ሊቀመጥ ሲል ‹‹አክብሩኝ እንጂ ፍሩኝ ያልኩ ይመስል ምነው ሸሸኸኝ?›› በማለት ሲጠይቀው… አቶ ለማ ‹‹ወንበር ስለምትወድ አንዱ ብቻ አይበቃህም ብዬ ነው›› በማለት መለሰለት፡፡

ከአፍታ ቆይታ በኋላ ጠቅላይ ሚኒስቴሩ የመክፈቻ ንግግር ለማድረግ ወደ መድረክ ሲወጡ የብአዴንና የህውኃት ሊቀ-መናብርት በግላጭ ተፋጠጡ፡፡

በዚህ ጊዜም ደጺ ቀልጠፍ ብሎ ‹‹በክብር አሰናብቱኝ ካልክ በኋላ ለምን ተመለስክ?›› የሚል ጥያቄ ለአቶ ደመቀ ሰነዘረ፡፡

‹‹’ስምህ የጠፋበትን ለሱዳን የተሸጠ መሬትና የወልቃይትን ማንነት ሳታስመልስ ስልጣን አትለቅም’ በማለት ምክር ቤቱ ጥያቄዬን ሳይቀበለው ቀረ›› አለው፡፡ በደመቀ መልስ ደጺ ከመበሳጨቱ የተነሳ ንደቱን የሚገልጹ ቃላቶች ከትግረኛም ሆነ ከአማርኛ ቋንቋ ውስጥ በማጣቱ በዝምታ ውስጥ ሆኖ ከቆዬ በኋላ… የደህዴን ሊቀ-መንበር የሆነችው ወ/ሮ ሙፈሪያት ካሚል በፊታቸው ስታልፍ ጠብቆ ‹‹አዲሷ ምክትል ጠቅላይ ሚኒስቴራችን በጣም አምሮባታል›› በማለት ደመቀን ሊያናድደው ሞከረ፡፡

ደግነቱ የሁለቱ ሊቀ-መናብርት የቃላት ልውውጥ ወደ ቡጢ ከመሸጋገሩ በፊት መድረኩ ላይ የተሰየሙት ጠቅላይ-ሚኒስቴር መናገር ስለጀመሩ ሁለቱም ጸጥ ብለው መከታተል ያዙ፡፡

ሆኖም ግን ሰዎቹ በዝምታቸው የቆዩት ዶክተር አቢይ ‹‹ኢትዮጵያን ማንም ቢሆን ‘ብቻዬን ሰራሁ’ ማለት አይችልም›› ብለው እስኪናገሩ ድረስ ነበር፡፡ ደጺ ይችን አረፍተ ነገር ሲሰማ በደስታ ውስጥ ሆኖ አቶ ደመቀን እያዬ ‹‹ይሄ ሰውዬ ጥምድ አድርጎ የያዘህ ምን አድርገኸው ይሆን?›› በማለት ጠየቀው፡፡

አቶ ደመቀም ‹‹ኢትዮጵያ ስትሰራ አብረን ሰርተናል እንጂ ብቻችን ሰርተናል ስላላልኩ ንግግሩ እኔን የሚመለከት አይደለም›› ብሎት ከጠቅላያችን አፍ አጸፋውን የሚመልስበት ሽሙጥ ሲጠባበቅ ከቆዬ በኋላ….. ‹ሌብነትን ኪራይ ሰብሳቢ በሚል የዳቦ ስም በማንቆለጳጰሰ ፈንታ ሌባ ብለን በትክክለኛ ስሙ ልንጠራው ይገባል›› ባሉበት ቅጽበት ወደ ደጺ ጆሮ በመጠጋት ‹‹በቢክ እስኪብርቶ ጻፈው እንጂ›› ከሚል ትዕዛዝ ጋር የሚያናድድ ሳቅ ስቆበት ፊቱን አዞረ፡፡
.
ለተሰብሳቢው የማከፋፍለውን ደርዘን ውሃ ተሸክሜ ወደ ኋለኛው ረድፍ ሳመራ… ከእስረኛነት ወደ ስራ-አስፈጻሚነት የተሸጋገረው አቶ መላኩ ፈንታ ከሆነ ኮፊያና መነጽር ካደረገ ሰው ጎን ተቀምጦ አየሁት፡፡ እናም ለአቶ መላኩና አብሮት ላለው ሰውዬ ውሃ ስሰጣቸው…. ባለኮፊያው የኮዳውን አስተሸሸግ ባግባቡ ሲመረምር ከቆዬ በኋላ ‹‹ቀይርልኝ›› አለኝ፡፡
‹‹እሱ ምን ሆነብህ? ስለው ‹‹ገመድ የተንጠለጠለበት ሃይላንድ ፈልጎ ነው›› በማለት አቶ መላኩ ፈንታ መለሰልኝ፡፡
በእውነቱ አቶ መላኩ የሰጡኝ መልስ የሰውዬውን ፍላጎት ብቻ ሳይሆን የሰውዬውን ማንነትም ጭምር ገልጾልኝ ስለነበር… በብርሃን ፍጥነት የዘር ፍሬዬን ጨብጬ ከአጠገባቸው ሸሸሁ፡፡
.
ወደ ስብሰባ አዳራሹ አርፍዶ የመጣው አቶ አያሌው ጫሚሶ በር ላይ ቆሞ የጸጥታ ሐይሎች ጋር ይጨቃጨቃል፡፡ ወታደሮቹ ‹‹ከተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ዝርዝር ውስጥ ስምህ የለም›› ሲሉት ‹‹ቅንጅት ውስጥ ካጣችሁት ህውኃት ውስጥ ፈልጉት›› ይላቸዋል፡፡ ከትንሽ ፍለጋ በኋላም የጠቀሰው ድርጅት ውስጥ ስሙ ተገኘለት መሰል… ወደ አዳራሹ ገብቶ ከዶክተር ብርሐኑ ነጋ ጎን እየተቀመጠ ‹‹አበል ወሰዳችሁ እንዴ?›› ይለው ጀመር፡፡
ከጠቅላያችን አንደበት ‹‹እንቁላል ከውስጥ ሲሰበር ሕይወት፣ ከውጭ ሲሰበር ግን ሞት ነው›› የሚል አባባል ሲፈልቅ…. ደጺ ይሄን ንግግር እንደ ተረት በመቁጠር…. ወደ ለማ መገርሳ ተጠግቶ ‹‹የዚህ ሰውዬ የዘር ሃረግ ውስጥ የአማራ ደም ያልተገኘ እንደሁ ከምላሴ ላይ ፂም ይነጭ!›› አለው፡፡
ሆኖም ግን ለዶ/ር ደጺ መላምት መልስ የሰጠው አቶ ለማ ሳይሆን ከኋላቸው የተቀመጠው አቶ ገዱ ሲሆን… መልሱም ‹‹ስለ ሰው የዘር ሐረግ ከማውራትህ በፊት ከምላስህ ላይ ቀርቶ ከጉንጭህ ላይ የሚነጭ ጺም አለመኖሩን ማወቅ ነበረብህ›› የሚል ነበረ፡፡
እነ ደመቀን ችላ ብዬ በስተግራ ወዳለው ጫፍ ቀልቤን ስልከው… ከሞንጆሪኖ ጎን ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ተቀምጦ አየሁት፡፡ የዶክተሩ ስሜት በጠቅላይ ሚኒስቴሩ ንግግር መነካቱን የሚገልጹ የእንባ ዘለላዎች ዐይኑ ሽፋሽፊት ላይ ተንቀርዝዘዋል፡፡
እናም ይሄ ሆዴ-ባሻ ሚኒስቴር ወደ ሞንጆሪኖ ጠጋ ብሎ ‹‹ሶፍት የለሽም?›› በማለት ሲጠይቃት ‹‹አይሻልህም እንባ-ጠባቂ ተቋም›› ብላው ቦርሳዋን ትበረብር ያዘች፡፡
ይሄን ታዝቤ ስመለስ… ከለማ መገርሳ ጀርባ የተቀመጠው ጌታቸው ረዳ የማዛጋት ድምጽ ሲያሰማ… አቶ ለማ ፊቱን አዙሮ ‹‹የድራፍት ሱስ ነው?›› በማለት ሲጠይቀው ጌቾ ማዛጋቱን ሳይጨርስ እንዲህ የሚል መልስ ሰጠ፡፡
‹‹አይ የድራፍት ሳይሆን የኢትዮጵያዊነት ሱስ ነው››
ይቀጥላል….

Filed in: Amharic