>

የ"ሱሪ" ነገር (ብርሀኑ ተክለያሬድ)

የ”ሱሪ” ነገር
ብርሀኑ ተክለያሬድ
በነገራችን ላይ ኦቦ ዳውድ ኢብሳ የታጠቁ ካልፈቱ ትጥቅ አልፈታም ያሉት ሱሪያችንን ይጨምራል???
 
በልጅነቴ የቅድመ አያቴን ስም ለሰዎች ከመናገሬ በፊት የሚስቁብኝ እኩዮቼ በአጠገቤ መኖራቸውን ገልመጥ ብዬ እመለከታለሁ እኩዮቼ አጠገቤ ካሉ ዘር ቆጠራዬ አያቴ ላይ ይቆማል አልያም የቅድመ አያቴን ስም በሌላ እቀይራለሁ እነሱ ከሌሉ ደግሞ ብርሀኑ-ተክለ ያሬድ-አሰፋ-ሱሪ ብዬ በኩራት እናገራለሁ ይህን የማደርገው “ሱሪ ብሎ ስም” “ቀጥሎስ ቁምጣ ነው?”የሚለውን የእኩዮቼን ብሽሽቅ በመፍራት ነበር
  በአንዱ ቀን ግን አባቴን የቅድመ አያቴ ስም ለምን እንዲያ እንደተባለ ጠየቅኩት እናም ፈገግ እያለ እንዲህ መለሰልኝ “እኔ በተወለድኩበት ሚዳ መራኛ መሀል ሜዳ ወዘተ አካባቢዎች ሱሪ ማለት እንዲህ ከተማ ላይ ለገላ መሸፈኛና ለቄንጥ እንደሚደረገው አይነት ትርጉም አይሰጠውም ከልብስነት የዘለለ ትርጉም አለው “ሱሪ” ማለት ወንድነት ነው አልታረም ያለ ትእቢተኛን ለማስታገስ “ሱሪ” ያስፈልጋል  ጠንካራ ገበሬ ሆኖ ሀገር ለመመገብም ሆነ ጀግና ወታደር ሆኖ ለጠላት አልቀመስ ለማለት “ሱሪ” አስፈላጊ ነው
ደግሞም “ሱሪ”ማለት ወኔ ነው ትጥቅ ከመታጠቅ በፊት ሱሪ መታጠቅ ያስፈልጋል ሱሪ ያልታጠቀ ሰው አርባ ክላሽ ቢታጠቅ ሸክም ነው ትርፉ ትጥቅ ቢያሳምሩ “ሱሪይት” ከሌለች እንኳን ጠላት ላይ የጥምቀት ንግስ ላይ መተኮስ ይቸግራል በሀገራችን ሱሪውን ፈቶ የተቀመጠ ጠላት እንኳን ቢሆን ጥቃት አይሰነዘርበትም ሱሪ የወኔ ምልክት ነዋ ወኔ ቢሱንና ራሱን መከላከል የማይችለውን አጥቅቶ ማን ሊሞገስ?
ደግሞም “ሱሪ”የጀግንነት ምልክት ነው ጀግና ሲፎክር በብዙሀን ሱሪ ለባሾች መሀል ቆሞ “ሱሪ የለበሰ ካለ ይሞክራታ”ይላል ጀግና ነኝ ባይ ወዲህ ና ማለቱ ነው ታዲያ ጀግና አቅመ ደካሞችን ህፃናትንና አረጋውያንን ቢተናኮሉት እንኳን አያጠቃም ይህ ያልተፃፈ “የባለሱሪዎች” ህግ ነው ይህን አርጎ የተገኘ አሁን እሱ ሱሪ ለብሷል? ተብሎ በማህበረሰሰቡ ዘንድ ይወገዛል አየሀት የሱሪን ጥቅም?”አለኝ የአባቴን ሱሪያዊ ትንተና ከሰማሁበት ቀን ጀምሮ ትጥቅ አልባው ግን ሱሪ ታጣቂው አዲስ አበቤ መሀል ተቀምጬ አንድ ሰው እንዲህና እንዲያ አደረገ ስባል “ይቺ የትጥቅ ናት የሱሪ?” የምትለዋን ጥያቄ አስቀድማለሁ ሴት ደፋሪዎች ህፃናትና አረጋውያን ገዳዮች በንፁሀን ላይ ተኳሾች ሁሉ ሱሪ አልታጠቁም ለካ!
በነገራችን ላይ ኦቦ ዳውድ ኢብሳ የታጠቁ ካልፈቱ ትጥቅ አልፈታም ያሉት ሱሪያችንን ይጨምራል?
Filed in: Amharic