ሀብታሙ አያሌው
እራሳቸውን ኦነግ እያሉ ከሚጠሩት አምስት ድርጅቶች አንዱ የሆነው በቅርቡ አዲስ አበባ የገባው የኦነግ ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ ከዋልታ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ “ትጥቅ ለመፍታት አልተደራደርንም ትጥቅ ፈቺ እና አስፈቺ የለም” ሲሉ አቋማቸውን ገልፀዋል። ድርድሩ የተካሄደው በአስመራ ሲሆን ከመንግስት በኩል የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ለማ መገርሳና የውጭ ጉዳይ ኃላፊ ሚኒስትሩ ወርቅነህ ገበየሁ ተደራዳሪ እንደ ነበሩ ይታወቃል። ዶክተር አብይም ጉዳዩን በቅርበት ሲመራ እና ሲከታተል ቆይቷል።
ድርድሩ ምን ነበር ? ኦነግ ትጥቅ ሳይፈታ እንዴት ሊገባ ቻለ፤ ትጥቅ ሳይፈታ ያሁሉ ያቀባበል ሽርጉድ እንዴት ተሰናዳ ? የአገር መከላከያ የታጠቀ ኃይል ወደ አገር ውስጥ ገብቶ ግድያ ሲፈፅም ለምን ዝምታ መረጠ? የአዲስ አበባን ወጣት በአፈሳ አስሮ ጦላይ ለመጫን፣ ግንቦት ሰባትን ትጥቅ ለማስፈታት አቅም ያላጣው የዶክተር አብይ መንግስት እንዴት ኦነግን ከነ ትጥቁ አስገብቶ ህፃናት እየመለመለ በባሌና በወለጋ ጫካዎች እንዲያሰለጥን ፈቀደ ? የኦሮሚያ ክልል የገጠር ፖለቲካ ኃላፊ አቶ አዲሱ አረጋ ቂጤሳ ኦነግ ትጥቅ እንዲፈታ ለመማፀን የበቁት እንዴት ነው ?