>

በፖለቲካ ፍቅር አታወራም ፖሊሲ ነው የምታወራው!!! (ዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያት - ኢትዮጵስ)

በፖለቲካ ፍቅር አታወራም ፖሊሲ ነው የምታወራው!!!
ዶ/ር ታዬ ወ/ሰማያት
* ቧንቧ ውስጥ ቤንዚን ፈሰሰበት፣ ዲዲቲም ፈሰሰበት፣ ውሃም ፈሰሰበት ያንን መስመር ይዞ ነው የሚሄደው። እነዚህ ሰዎች ቧንቧው ውስጥ እየፈሰሱ ነው። ቧንቧውን አልለወጡትም። ቧንቧው ነው መለወጥ ያለበት። ርዕዮቱ ነው መለወጥ ያለበት!!!
——-
ኢትዮጵስ በዚህ ሳምንት እትሟ ታዋቂውን ምሁር ዶክተር ታዬ ወ/ሰማያትን አነጋግራ የሚከተለውን ይዛ ወጥታለች!
—–
ኢትዮጵስ ጋዜጣ፣ መስከረም 27/2011 ዓ.ም
ኢትዮጵስ፦ ወደ ወቅታዊው የሀገራችን ሁኔታ እንግባና፣ በዶ/ር አብይ የመደመር ስሌት፣ እርሰዎ የትኛው ዛቢያ ላይ ነዎት? የዶ/ር አብይን አመራር ያምኑበታል?
ዶ/ር ታዬ፦ ጥርጣሬ አለኝ። ፊት ለፊት እናገራለሁ። ይሄን ሁለተኛው ምዕራፍ ነው የምለው። አንደኛው ምዕራፍ፣ አሜሪካኖች ወያኔን ያስገቡበት ድራማ ነው። በሁለተኛው ምዕራፍ፣ የወያኔ ስርዓት በወጣቱ ትግል ሲወድቅ፣ አዲስ ነፍስ ዘርቶ እንዲቀጥል እየተደረገ ነው። ዶ/ር አብይ የወጡት ከኢህአዴግ ውስጥ ነው። እኔ ቲዎሪ አለኝ። ኤጀንት እና ኮዝ የምለው። በኮዝ እና ኤጀንት መካከል ልዩነት አለ። ለምሳሌ ወባ ምንድነው ሲባል ብዙዎች ቢንቢ ነች ይላሉ። ቢንቢ ግን መልዕክተኛ ነች። አንድ ሰው ወባ ካለው፣ ያንን ደም መጥጣ እኔ ጋር የምታመጣ መልዕክተኛ ነች። ምግብ ፍለጋ የምትዞር ነች። ኮዙ ግን ሌላ ነው። ደሙ ውስጥ ያለ ነው። ለእኔ ተቋሙ እና ሥርዓቱ ነው ዋናው ኮዝ እንጂ ኤጀንቶች አይደሉም። አብይ ኤጀንቱ ነው። ዋናው ኮዙ፣ ማለትም ሥርዓቱ፣ እንዳለ ነው። አልተነካም። እንዲቀጥል ነው እየተደረገ ያለው።
ኢትዮጵስ፦ እነዚህ ሰዎች (እነ ዶ/ር አብይ) የህዝቡን ትግል የተቀላቀሉ እና ለለውጥ የተዘጋጁ አይደሉም?
ዶ/ር ታዬ፦ ሥርዓቱ እና ተቋማቱ እንዳሉ ናቸው። የችግራችን ኮዝ ደግሞ እነሱ ናቸው። የኤጀንቶቹ መለዋወጥ ትርጉም የለውም።
ኢትዮጵስ፦ ተቋማቱን ቀስ እያሉ ማመንመን አይችሉም?
ዶ/ር ታዬ፦ ቧንቧ ውስጥ ቤንዚን ፈሰሰበት፣ ዲዲቲም ፈሰሰበት፣ ውሃም ፈሰሰበት ያንን መስመር ይዞ ነው የሚሄደው። እነዚህ ሰዎች ቧንቧው ውስጥ እየፈሰሱ ነው። ቧንቧውን አልለወጡትም። ቧንቧው ነው መለወጥ ያለበት። ርዕዮቱ ነው መለወጥ ያለበት።
ኢትዮጵስ፦ ህገ መንግሥቱ ሙሉ በሙሉ መቀየር አለበት ብለው ያስባሉ?
ዶ/ር ታዬ፦ አዎ። ኮዙ እሱ ነውና። ለውጥ ለማምጣት ሰዎቹን ብቻ አይደለም የምትለውጠው። የአሰራር ስርዓቱን ነው የምትለውጠው። በዚያ መንገድ ግን እየሄድን አይደለም። እሳቸው (ጠ/ሚ/ር አብይ) ምስጢረኛ አይደሉም። ተናግረዋል። “የኢህአዴግ መሰረቱ አይለወጥም፣ ባለው ላይ ነው የምትደመሩት” ብለዋል።
በነበረው ላይ ነው የምትደመረው፣ በነበረው ላይ ነው የምትጨምረው። ለምሳሌ፣ የሹመት አሰጣጡን እንኳን ብንመለከት፣ ከተቃራኒው ጎራ፣ ከተቃዋሚው ለአንድ ሰው እንኳን ሹመት አልተሰጠም። ገንዘብ ያለበት ቦታ ላይ የመለስ ባለቤት ናቸው የተሾሙት። ያለውን ነገር ነው ያጠናከሩት። በፖለቲካ ፍቅር አታወራም። ፖሊሲ ነው የምታወራው። የትኛውን ህዝብ፣ የትኛው ፖሊሲ ይጠቅማል? ነው የምትለው። እስካሁን ያለፉትን ሂደቶች የሚሽር አንድም ፖሊሲ የለም። የትምህርት ፖሊሲው ትውልድ ገዳይ እንደሆነ እያወቁ እንኳን እንሰርዘዋለን አላሉም። እንዴውም የትምህርት ጥራቱን ችግር “…ከፖሊሲ የማስፈፀም ችግር እንዲሁም ተራ የፍትሃዊነት ትርክት ጋር ተሳሰረ እንጂ የትምህርት ፖሊሲ ካለ ባህሉ፣ ካለ ርዕዮቱ፣ ካለ ፍልስፍናው ብቻውን ፖሊሲ ሊሆን አይችልም ። ..ፖሊሲው የድሮው የትምህርት ስርዓት ከመተግበር እና ቋንቋን መሰረት ያደረገ የፖለቲካ ፍላጎትን ከመተግበር የዘለለ አይደለም። እሱም ቢሆን ለትምህርት ፍኖተ ካርታው ግባት የሆነው ጥናት የተጀመረው ከሶስት አመት በፊት ስለሆነ ከወያኔ ኢህአዴግ ቅኝት የተላቀቀ አይደለም”
Filed in: Amharic