>

የወታደሩ አድማ እውነት ከሆነ… (ፋሲል የኔአለም)

የወታደሩ አድማ እውነት ከሆነ…
ፋሲል የኔአለም
ሃዋሳ ላይ አብይ አዲስ የጸጥታ ሃይል እየተዋቀረ መሆኑን ሲናገር አልተመቸኝም ነበር። ይህ ጊዜ እንዳይመጣ በመስጋት ” ምነው ባይናገረው  እያልኩ” አስብ ነበር። እንዲህ አይነት ቁልፍ ጉዳዮች በሚስጢር ተይዘው ተግባራዊ የሚደረጉ እንጅ በየአደባባዩ የሚነገሩ አልነበሩም። ሙያ በልብ ነው። የቤተመንግስቱን ወታደር ያስጨነቀው የደሞዝ ወይም የአበል ጥያቄ አይመስለኝም።  የሚቀነሱ ወታደሮች እንደሚኖሩ መነገሩ የፈጠረው ድንጋጤ ደሞዝን ሰበብ አድርጎ የወጣ ይመስለኛል።  ጥያቄውን ቀለል አድርጎ ማየት ተገቢ አይደለም። ወታደሮች ላነሱት ጥያቄ አወንታዊ መልስ ቢሰጥ፣ በየካምፑ ያሉት ወታደሮች በተመሳሳይ አድማ ጥያቄያቸውን ማቅረብ ይቀጥላሉ፤ መልስ ባይሰጥ ደግሞ ጠባቂዎቹ ሌላ ችግር ሊፈጥሩ ይችላሉ። አጋጣሚውን ተጠቅሞ ስልጣን መንጠቅ የሚፈልግ ወታደር፣ እንደነ መንጌ በየካምፑ ያለውን ወታደር ቀስቅሶ እድሉን ከመሞከር ወደ ሁዋላ አይልም። በዚህ መሃል አንድ መፍትሄ ይታየኛል።  በ66ቱ አብዮት ወታደሩ ሊሳካለት የቻለው ህዝቡን፣ በተለይ ተማሪውን፣ ፊት አሰልፎ ለስልጣን ስለታገለ ነው። ህዝቡ  ራሱን ከፊት ወታደሩን  ደግሞ ከሁዋላ አሰልፎ ቢታገልም፣ በመጨረሻው ሰዓት ላይ ግን ወታደሩን ፊት፣ ራሱን ደግሞ ከሁዋላ አግኝቶታል። ዛሬም ተመሳሳይ ነገር እንዳይፈጠር ማድረግ ይገባል።  ለውጡን የሚደግፈው ህዝብ የወታደሩን ድርጊት ተቃውሞ ሰልፍ መውጣት ወይም በተለያዩ መንገዶች ተቃውሞውን መግለጽ አለበት። አገራችን ከእንግዲህ በወታደር እንደማትገዛ ግልጽ ማድረግ ይኖርብናል። ወታደር መግቢያ ቀዳዳ የሚያገኘው ህዝብ ሲከፋፈልና መንግስት የተደካመ ሲመስለው ብቻ ነው። ስለዚህ ህዝብ ድርጊቱን ነቅቶ በመከታተልና ሙከራው ሲከሽፍም የወታደሩን ድርጊት በተከታታይ በማውገዝ፣ ወታደሩ ከእንግዲህ እንዲህ አይነት ድርጊት እንዳይፈጽም ማሸማቀቅ ይገባል። ጥያቄውን በአድማ ሳይሆን በሰላማዊ መንገድ ብቻ መቅረብ እንዳለበት ሊማር ይገባዋል።
የወታደሮች ጥያቄ በሰላም መጠናቀቁ ደስ ብሎኛል። ድርጊቱ ግን የሚወገዝ መሆኑን መርሳት የለብንም። 240 መምህራን እንዲህ በቡድን ቢመጡ፣ ቤተመንግስት እንዲገቡ አይፈቀድላቸውም፤ ጠ/ሚኒስትሩንም ያለቀጠሮ ማነጋገር የሚችሉ አይመስለኝም። ሃሳብ ሳይሆን ጠመንጃ ስለያዙ ነው የተፈሩት፤ ጠመንጃ የማይፈራበት ማህበረሰብ እስኪፈጠር እንዲህ አይነቱ ድርጊት ሊቀጥል ይችላል። በሁለት ምክንያቶች፣ ድርጊቱ አደገኛ መልዕክት አስተላልፎ መጠናቀቁን መካድ አይቻልም- setting a precedent.   አንደኛ፣ ወደ አዲስ አበባ የሚመጡ ወታደሮች፣ ለእውነተኛ ጥያቄም ይሁን ለፎቶ መነሳት፣ ቤተመንግስት ካልገባን እያሉ ሊያስቸግሩ ይችላሉ። ቤተ-መንግስትን መላመድ ደግሞ ቤተ-መንግስትን መናቅ በሂደትም ልቆጣጠር ማለት ሊያመጣ ይችላል። ቤተመንግስትን ቀድመው የሚደፍሩት የቤተመንግስት ጠባቂዎች መሆናቸውን መርሳት አይገባም። ሁለተኛ፣ አንዳንዶች ድርጊቱን አካባቢውን ለማጥናት ( testing the waters) ተጠቅመውበትም ሊሆን ይችላል- የጥበቃውን ጥንካሬ፣ የባለስልጣናቱን በራስ መተማመን፣ የህዝቡን ምላሽ ወዘተ። ለዚህ ነው ፍጥጫው በሰላም መጠናቀቁ ደስ ቢለንም፣ ድርጊቱን ከማውገዝ ማፈግፈግ የለብንም የምለው።
ማህበራዊ ሚዲያው፣ በተለይም አንዳንድ የፌስቡክ ተጠቃሚዎች፣ ያልሆኑ መረጃዎችን በማሰራጨታቸው፣ አውቀውም ይሁን ሳያውቁት አለመረጋጋት ቢፈጥሩም፣ አብዛኛው ፌስቡከኛ ግን፣ ለውጡ እንዳይቀለበስ ትኩረት ሰጥቶ መከታተሉ ሊያስመሰግነው እንደሚገባ ለኢቲቪ ጋዜጠኞች ማስታወስ ይገባል። ወታደሩ ወደ ሌላ እርምጃ ቢሄድ ኖሮ፣ ለተቃውሞ ጥሪ የሚያቀርበው ፌስቡከኛው መሆኑን መዘንጋት አይገባም። በዚህ አጋጣሚ ግን ሁላችንም አንደኛ ለመባል መረጃ ሳናጣራ ማውጣታችን የሁዋላ ሁዋላ ተዓማኒነታችን ሊጎዳ እንደሚችል መማር ይገባናል። የጋዜጠኝነት አለም ያስተማረኝ ትልቁ ትምህርት ይህ ነው።
ለማንኛውም መንግስት የሚሰጠውን መግለጫ በአንክሮ እንከታተል።
Filed in: Amharic