>
11:08 am - Sunday May 22, 2022

ነገር መሸፋፈን መዘዙን ያወሳስበዋል! (ውብሸት ታዬ)

ነገር መሸፋፈን መዘዙን ያወሳስበዋል!
ውብሸት ታዬ
ብዙ አጠራጣሪ ነገሮች አሉ። በአንድ በኩል የኦሮሞ ነፃነት ግንባር መሪ ሠራዊታቸው ትጥቅ እንደማይፈታ ይፋ አድርገዋል። ይህ ሠራዊት በኦሮሚያ የተለያዩ አከባቢዎች የመንግስት ተቋማትን ተቆጣጥሮ ውሳኔዎች እየሰጠ ይገኛል ተብሏል። መንግስት በበኩሉ የኦነግ አመራር ሠራዊቱን ትጥቅ እንዲያስፈታ ጥሪ ያቀረበ ሲሆን ካልሆነ ግን የፌዴራል ሃይል እርምጃ እንደሚወስድ አሳስቧል።
  ነገሩ የትጥቅ ፍታ አትፍታ ነገር ብቻ አይደለም። በተለይ ለ40 ዓመታት ያህል በትጥቅ ትግል ላይ ከቆየ ድርጅት ጋር ድርድር ሲካሄድ ስለትጥቅ መፍታት ጉዳይ በግልጽ የተነሳ ነገር አልነበረም ማለት ማንንም ካለማሳመኑም በላይ ለምን እና እንዴት የሚሉ ጥያቄዎች ማስነሳቱ አይቀርም።
   የነገሮቹ መሸፋፈንን ያህል መዘዞቹም የተወሳሰቡ መሆናቸው የሚጠበቅ ይሆናል። በተለይ ከትጥቅ መፍታት ጋር በተያያዘ በአስቸኳይ አንድ ስምምነት ላይ ካልተደረሰና መንግስት ወደሃይል እርምጃ የሚገባ ከሆነ በሚያስቆጭ ሁኔታ ተስፋ ያደረግንበትን የዴሞክራሲ ፋና ያዳምንበታል። ምክንያቱም ኦነግ አንዳንድ ወገኖች (ከመረጃ ማነስ ይመስለኛል) በማሕበራዊ ሚዲያ  እንደሚሉት አንድ ጥይት ሳይተኩስ ኖሮ በተደረገለት ጥሪ የገባ ሳይሆን ለረዥም ዓመታት ትክክል ነው ብሎ ለተነሳለት ዓላማ ብዙ የተፋለመ፣ ሠራዊቱ፣ ደጋፊዎቹም ሆነ ሕዝቡ ሁለንተናዊ መስዋዕትነት የከፈሉ፣ ሰፊ ሕዝባዊ ድጋፍ ያለውና አሁን ለመጣው ለውጥ የራሱ ድርሻ ያለው ነው። ይህን እውነታ በመካድ ወይም በማጣጣል ምንም በጎ መፍትሔ አይመጣም።
   ይህ ማለት ግን ለነፃነት ሲፋለሙ የቆዩ ታጣቂ ድርጅቶች ከነትጥቃቸው አገር ውስጥ ገብተው ሊንቀሳቀሱ ይገባል ማለት ፍጹም መርሐዊ  አይደለም። በእንደዚህ አይነት አጋጣሚዎች በየትኛውም ዓለም የሚሰራባቸው አሠራሮች አሉ። አንደኛው አማጽያኑን ተሃድሶ በመስጠት እንደየአቅማቸውና ሙያቸው በአገሪቱ የመከላከያ፣ የፖሊስና የጸጥታ ክፍል እንዲሁም ሌሎች የሲቪል ተቋማት ውስጥ መመደብ ነው። (‘ተሃድሶ’ ለሚለው ቃል ከተፈጠረው አዲስ ነባራዊ ሁኔታ ጋር የማዛመድ ተግባር ሊባል ይችላል።)
መንግስትም ለሕዝቡ ሰላምና ደህንነት መከታ መሆኑን በማሳየት(እንደ ጅግጅጋው በብዙ መቶ ሺዎች ግፍ ሲወርድባቸው ቆሞ ባለማየት) ሌላ ታጣቂ ሃይል እንደማያስፈልግ ማረጋገጥ አለበት!
  ለመጨመር ያህል … ሃይል ሕዝብ ነው። በቅርቡ ከኢትዮጵያ ሕዝብ ጫንቃ ላይ የወረደውን የጭቆና ቡድን ያሸነፈው በባዶ እጁ እምቢ ያለው የሕዝብ ልጅ ነው። አያይዘንም አንድ ክስተት ዳሰስ አድርገን እንቋጭ።
  ስለትናንትናው የ240 የመከላከያ ሰራዊቱ የ4 ኪሎ ቤተ መንግስት ‘ውሎ’ም ጥርጣሬዎች አሉ። እንደተባለው ሰራዊቱ ያቀናው ለደመወዝና ጥቅማ ጥቅም (የመብት)ጥያቄዎች ነውን? የዚህ አይነቱ ጥያቄ ከ1966ቱ የሠራዊት የደመወዝ ጭማሬ ጥያቄ በኋላ የመጀመርያው ይመስላል። የ1966ቱ ጥያቄ በአዝጋሚ የመፈንቅለ መንግስት እርምጃ መቋጨቱም ይታወሳል።
   ዋናው ነገር ለሰላም ማስከበር ግዳጅ የመጣ ሠራዊት እንዴት በአጭር ጊዜ የዚህ አይነት ጥያቄ ይዞ ከነሙሉ ትጥቁ ወደቤተ መንግስት ተመመ? የዚህ አይነት የመብት ጥያቄዎች የሚቀርቡበት ወታደራዊ የእዝ ጠገግ አልነበረም ወይ? አገራችን ካለችበት ተጨባጭ ሁኔታ አንጻር ይህን አጋጣሚ ሊጠቀሙበት የፈለጉት ወገኖች እነማን ናቸው? በእርግጥ በሚዲያ እንደተገለጸልን ጥያቄው የመብት ከነበረ ድርጊቱ ለምን በድንገት ተፈጸመ?(የአንድን አገር ጠ/ሚ/ር ቀጠሮ ሳያስይዙና ቦታ ሳይዘጋጅ!) ለምን ሁኔታው ስጋት በሚያጭሩ ግልጽ እንቅስቃሴዎች ታጀበ? ወደ ኢቲቪ የተጓዘው ሃይልስ ምን ነበር? ወዘተ…
 ሌላው የፌዴራል ፖሊስ ኮሚሽነሩ ጄኔራል ዘይኑ አንዴ ከሃዋሳ ወደ ቡራዩ መጥተው የነበሩ የሠራዊቱ አባላት ወደ ምድብ ጦርሰፈራቸው ሲመለሱ ወደ ቤተመንግስት ጎራ ማለት ስለፈለጉ ነው፣ ሌላ ጊዜ ደግሞ ከጦርሃይሉ የተውጣጡ አባላት ጥያቄያቸውን ለማቅረብ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ለመወየየት ቤተመንግስት ሄደው ነው በሚል የተሰጡት እርስ በርሳቸው የሚቃረኑ የመንግስት መግለጫዎች፣ መንግስትን በአፈላማ የሚያስጠረጥሩና ተአማኒነቱን የሚያጎድሉ በመሆናቸው በቶሎ ሊታረሙ ይገባል ።
 ህዝብ መንግስትን መጠራጠር ከጀመረ ለመረጋጋቱ አደጋ ነው ። የዶክተር አቢይ አስተዳደር ከትናንትናው መዝረክረኩ ብዙ ሊማር ይገባዋል ። ሂሳዊ ደጋፊዎቹም ወይም በስዩሜ አጠራር የሰይጣን ጠበቃዎቹም ጭፍን ድጋፍ ከመስጠት ይልቅ፣ ድክመቱን በማሳየት ነው እንዲሻሻል ልንረዳው የምንችለው ። አለበለዚያ ተያይዞ መውደቅ ነው ያለው አማራጭ ። ያ ደግሞ አማራጭ ሊሆን አይችልም!
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ያስብ፤ ሕዝቧን ይባርክ!
Filed in: Amharic