>

ቅኝ ገዢዎቹ ትተውልን የሄዱት በጊዜ ሂደት የሚፈነዳ ደማሚትን ነው . . ! (አሰፋ ሀይሉ)

ቅኝ ገዢዎቹ ትተውልን የሄዱት በጊዜ ሂደት የሚፈነዳ ደማሚትን ነው . . !
አሰፋ ሀይሉ
እንደማይሆንላቸው ሲያውቁ የምቀኝነት ሤራቸውን ለእኛ አውርሰውን ሄዱ፡፡ እነርሱ አንድ ያረጉትን ዕድሜ ሰጥቶአቸው መግዛት ስላቃታቸው – እኛ አብሮነት እንዳይቻለን – ከፋፋይ ድንበርን አስምረውብን ሄዱ፡፡ የልዩነትን ግድግዳ ገንብተውብን ሄዱ፡፡
ፋሺስት ኢጣልያ እንደተመኘችው ተሣክቶላት እኛን ሁላችንን በቅኝ ለመግዛት ቢቻላት ኖሮ በቀጥታ ተግባራዊ የምታደርገው የታላቋ ኢጣልያ ንጉሠ ነገሥት መንግሥት አፍሪካዊ ግዛት ይሄን እንዲመስል ነበር ከ70 ዓመታት በላይ እንግሊዞችን ደጅ ስትጠና ጀምሮ ስታቅድ እና ስትቋምጥ የኖረችው፡፡
በእርግጥም በቤኒቶ ሙሶሊኒ የሚመሩት የኢጣልያ ፋሺስቶች በ1928 ዓ.ም. በኢትዮጵያ መሐል ምድር ላይ ከሰሜን በቀይ ባህር በኩል እና ከደቡብ በሶማሊያ በኩል በሁለት በኩል ጥቃት ከፍተው በመውረር – እውነትም – ለዘመናት የተመኙትን ምኞት ለጊዜው እውን ሊያደርጉት ተቃርበው ነበር፡፡
ያኔ – ምኞታቸው ባጭር ተቀጨ እንጂ – ለረዥም ጊዜ ዘልቆ ቢሰምርላቸው ኖሮ – ኤርትራን፣ ኢትዮጵያን እና ሶማሊያን – እንዲህ በካርታ እንደሚታየው አድርገው – ታላቋ የኢታሊያ የምሥራቅ አፍሪካ ቅኝ ግዛት በማለት – በካርታው የሚታዩትን ሁሉ ህዝቦችና ግዛቶች አንድ አድርገው ሊገዙ ይችሉ ነበር፡፡ ህልማቸውም ራዕያቸውም ያ ነበረ፡፡
በእርግጥም ስትራቴጂክም፣ ታሪካዊም፣ ነባራዊም አመክንዮ ያልተለየው ምኞት ነበር፡፡ እነዚያ አካባቢዎች በአንድ ቢጠቃለሉ የሚፈጠረው አመቺ የግብዓትና ምርት ድልድይ እጅጉን የሚያስመረቅን ነበረ – በኢጣልያኖች እግር ሆኖ ላሰበው ማንም የዘመኑ ሰው፡፡
ነገር ግን እጅግ በጣም፣ በጣም የሚገርመኝ – እነርሱ በትክክል ጠቃሚ ሊሆንላቸው እንደሚችሉት እኛን ሁላችንን አንድ ላይ አዋህደው፣ በአንድ ግዛት ሥር ለመግዛት እንደማይቻላቸው ሲያውቁት ግን – ለእኛ ትተውልን የሄዱት – ‹‹እኔ ከሞትኩ ሠርዶ አይብቀል›› ፍልስፍናቸውን ነው፡፡
እነርሱ እንደማይሆንላቸው ሲያውቁ የምቀኝነት ሤራቸውን ለእኛ አውርሰውን ሄዱ፡፡ እነርሱ አንድ ያረጉትን ዕድሜ ሰጥቶአቸው መግዛት ስላቃታቸው – እኛ አብሮነት እንዳይቻለን – ከፋፋይ ድንበርን አስምረውብን ሄዱ፡፡ የልዩነትን ግድግዳ ገንብተውብን ሄዱ፡፡
ቅኝ ገዢዎቹ ትተውልን የሄዱት ለራሳቸው የተመኙትን ሳይሆን – እንዳይሆንባቸው በፅኑ የተዋጉትን – ለራሳቸው እጅጉን የጠሉትን – በደምና በላብ ያስወገዱትን መነጣጠልን ነው፡፡ ክፍፍልን ነው ትተውልን የሄዱት፡፡ ትተውልን የሄዱት የእርስ በእርስ መጠፋፋትን ነው፡፡ ትተውልን የሄዱት አንዱ በሌላኛው ላይ መነሣትን ነው፡፡ ቀብረውልን የሄዱት የክፍፍልና የልዩነትን በጊዜ ሂደት የሚፈነዳ ደማሚትን ነው፡፡
እጅግ፣ እጅግ፣ እጅግ የሚያሣዝነው ደግሞ – እስከዛሬም ድረስ – ያን የቅኝ ገዢዎቹን ምኞት እና ምኞታቸው ሲመክን ጥለውብን የሄዱትን የማለያየትና የማጠፋፋት ተንኮል – እኛ ዛሬ በሥልጣኔ ዘመን የምንኖር አፍሪካውያን – እስካሁንም ድረስ አለመረዳታችን – እና ያን የእነርሱን አጀንዳ አንግበን የመገኘታችን አስለቃሽ እና አንገት አስደፊ እውነታ ነው፡፡
እንግዲህ … የታወረው ዓይናችን፣ የተሰለበው ልቦናችን፣ የዞረው ናላችን ወደ ትክክለኛ ጽሞናው ተመልሶ – ለእነርሱ ያውም በዚያ ዘመን የተገለጸላቸው ለእኛም ፋይዳው እስኪታየን ድረስ – ቀልባችን እስኪታረቀን ድረስ – እንዲሁ – የመለያየትንና የመጠፋፋትን አጀንዳ እንደትልቅ የሣይንስ ግኝት አድርገን የምንቆጥር – የጅል ደጃፍ ሆነን እንቀጥላለን፡፡
“አወይ ሰው መሆኔ…..!! አወይ ሰው መሆኔ…..!!” – ድምፃዊ አስቴር አወቀ፡፡
አምላክ የጥላቻንና የመለያየትን አጥር ከልባችን ውስጥ ምንጥርጥር አድርጎ ይንቀልልን፡፡ ኢትዮጵያዬ በልጆቿ ፍቅር ዓለምን የምታስቀናበትን ያን ዘመን አምላካችን እውን እንድናደርግ ይርዳን፡፡ ኢትዮጵያ – በልጆቿ ፍቅር እና አስተዋይነት ፀንታ – ለዘለዓለም ትኑር፡፡ መልካም ጊዜ፡፡
ካርታው፡– የሙሶሊኒ የኢትዮፒክ አፍሪካ ቅኝ ግዛት ካርታ – ከ1883 እስከ 1941 እ.ኤ.አ.፤ ምስል ማርቲን ካካፈለው፡፡
Filed in: Amharic