>

ህወሃትስ ይህንን አይደል ሲፈጽም የቆየው? ያሳፍራል!?! (ፋሲል የኔአለም)

ህወሃትስ ይህንን አይደል ሲፈጽም የቆየው? ያሳፍራል!?!
ፋሲል የኔአለም
የሃረሪ ክልል ለአርበኞች ግንቦት7 መሪዎች የጸጥታ ዋስትና እንደማይሰጥ በመግለጽ ስብሰባ መከልከሉን ሰምተናል። ክልሉ የኦህዴድና የሃረሪ ሊግ (ሃብሊ) መፋለሚያ ቦታ በመሆኑ ውሳኔው ብዙም ላያስገርመን ይችላል።
ሃብሊ እስካሁን በስልጣን ላይ ያለው በ”ኦዴፓ” ምህረት እንጅ በራሱ ህዝብ ጥንካሬ አይደለም። ውሳኔውም የተላለፈው ከኦዴፓ የክልሉ አመራሮች እንጅ ከሃብሊ ባለስልጣናት እንዳልሆነ አምናለሁ። ለምን ቢባል በቅርቡ በእነዚህ ሰዎች ተጽዕኖ፣ ለኦ ኤም ኤን ክልሉ በሚሊዮን የሚቆጠር የመንግስትን ገንዘብ ሰጥቷል። የክልሉ ፕሬዚዳንትም በፍርሃት ገንዘብ ለዚሁ ሚዲያ ለግሷል። ይህ ሁሉ በክልሉ ምክር ቤት ያሉ የኦዴፓ መሪዎችን ለማባበል ተብሎ የተደረገ  አሳፋሪ ድርጊት ነው።
ገንዘቡን የተቀበሉት ደግሞ ትናንት ህወሃትን በተመሳሳይ መንገድ ሲወቅሱ የነበሩ “ነጻ አውጭዎች” መሆናቸው  ሌላው አሳፋሪ ነገር ነው። ለማ የሚመራው ኦዴፓ በሃረሪ ክልል ያለው ተጽዕኖ አነስተኛ ነው፤ ከለማ ኦዴፓ ይልቅ፣ ኦነግን የሚደግፉ የኦዴፓ ባለስልጣኖች  በክልሉ ውስጥ ከፍተኛ ተጽዕኖ አላቸው።
ይህን ውሳኔ ያስተላለፉት እነዚህ በሙስና የቆሸሹ በኦዴፓ ስም የሚነግዱ ኦነጎች ናቸው።  ውሳኔው የመሸነፍ ምልክት ነው፤ በራስ ያለመተማመን ውጤት ነው፤ የፍርሃት ማሳያም ነው። ከምንም በላይ ሁዋላ ቀርነት ነው። በ21ኛው ክፍለ ዘመን “በእኔ ክልል መጥተህ ስብሰባ እንዳትጠራ” ብሎ መከልከልን የመሰለ ሁዋላ ቀርነት ሊኖር አይችልም።
 ምንም ይሁን ምን ህዝብ በተለያዩ መንገዶች መደራጀቱ አይቀርም፤ አደገኛውና ለቁጥጥር የሚያስቸገረውም እንዲህ አይነቱ “ በተከለከልኩ” ስሜት የሚፈጠረው አደረጃጀት ነው። ህዝቡ እልህ ውስጥ ሲገባ የተለያዩ አማራጮችን ሊጠቀም እንደሚችል ከቅርቡ ታሪካችን ካልተማሩ መቼም አይማሩም።
እንዲህ አይነት ውሳኔ በየትኛውም ቦታ በማንም ድርጅት ላይ ተፈጻሚ ቢሆን፣ ዲሞክራሲያዊ ስርዓት እንዲፈጠር የሚታገሉ ሃይሎች ሁሉ ሊያወግዙት ይገባል። ህወሃትስ ይህንን አይደለም ሲፈጽም የቆየው? ያሳፍራል።
Filed in: Amharic