>

ሐረርና ድሬዳዋ (ነአምን ዘለቀ)

ሐረርና ድሬዳዋ
ነአምን ዘለቀ
* የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በገዛ ሀገሩ  የዜግነት ሙሉ መብቶች መከበርና መረጋገጥ ቀዳሚው ስራችን መሆን አለበት ስንል እያንዳንዱ አካባቢ የሰፈነውን ስር የሰደደና ዘግናኝ ኢፍትሃዊነት ማገለጥና መታገል የግድ ይላል!
_
 
ወደ ሃረርና ድሬዳዋ በሄድን  ጊዜ በሰማሁት በጣም አዝኛለሁ። የሀረሬ ክልል ባለስልጣኖች  “የደህንነት ስጋት”  እንደ ምክንያት በማቅረብ የአግ7  ህዝባዊ ስብሰባ   እንዳይደረግ  ቢከለክሉም  ድሬ ዳዋ ከተማ በመጨረሻው ሰአት ስብሰባ እንዲደረግ ከተፈቀደና ስባሰባውን ካደረግን በኋላ በነጋታው ከ አግ7 አመራሮችና ጓዶች ጋር በመሆን ወደ ሀረር ሄደናል።  ስለሀረር ችግሮች ረጅም ሰአታት የፈጀ ውይይት ከበርካታ ወጣቶችና የኮሌጅ መምህራን ጋር አድርገናል ። በሀረርና በድሬዳዋ የታዘብነው በዚያ አካባቢ ያለው ችግር እጅግ የገዘፈ የአፓርታይድ ደቡብ አፍሪካ መሰል ሁኔታ መኖሩን ነው ፣ ዜጎች የዜግነት መብቶቻቸው የተነፍጉበት፣ አንገታቸውን የደፉበት፣ በአገራቸው ባይተዋር ሆነው ለመኖር የተገደዱበት የተንሰራፋ አስከፊ ሁኔታ መኖሩን  ነው የተረዳነው።
ይህን እጅግ አሰክፊ  ሁኔታ በብዙ ደረጃ ለመታገልና ለመለወጥ መደራጀት ያስፈልጋል። የፓለቲካ፣ ህጋዊና፣ የሚዲያ ካምፕጌን ትግሎች መደረግ አለባቸው። የፓለቲካ ሰፊ ስራ ያስፈልገዋል። የመብት ተኮር ድርጅት እድቮካሲ ያስፈልገዋል፣ ችግሮቹን ለማጋለጥ ሀገር አቀፍና በአለም አቀፍ ሚዲያ ቅስቀሳ ያስፈልገዋል። አጋሮች ማሰባሰብ ያስፈልገዋል። ተዛማጅ በርካታ ስራዎች ያስፈልጉታል።
በቀዳሚነት ግን በሀረርና በድሬ ዳዋ  የሚገኘውን የዜጎች አስከፊና አሳዛኝ ሁኔታ በመረጃና በማስረጃ በአግባቡና  በተደራጀ ሁኔታ መቅረብ አለበት፡ ሃቁን፡ እውነቱን ይዘን ከተንቀሳቀስን እናሸንፋለን። ሀረርና ዴሬ ዳዋ በመላው አገሪቱ የመጣው ለውጥ አካል ማድረግ ይቻላል። ሀገር ውስጥ የተጀመረው ለውጥ ይህን ሁኔታ የሚፈቅድ ይሆናል የሚል ጽኑ እምነትና ተስፋ  አለኝ።
የተንሰራፋውን የጥቂቶች የበሰበሰ የለየለት  የዘረፋ አገዛዝ፣ የከረፋ ዘረኝነት፣ በዚሁም ሳቢያ የዜጎች በፓለቲካው የውክልና እጦት፣ የዜጎች ከፓለቲካ፣ ከአስተዳደር፣ ከደህነትና ሌሎችም  መስኮች ምንም ተሳትፎ እንዳይኖራቸው መገለል፣  መገፋትና አንገት መድፋት ወዘተ፣ወዘተ፣   በዝርዝር እሰከነመገለጫዎቻቸው ፣ በመረጃዎች፣ በማስረጃዎች አስደግፎ ሰፊ ስራዎች በመስራት  የለውጥ ሂደት ሊጀመር ይችላል። የእያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ በገዛ ሀገሩ  የዜግነት ሙሉ መብቶች መከበርና መረጋገጥ ቀዳሚው ስራችን መሆን አለበት ስንል እያንዳንዱ አካባቢ የሰፈነውን ስር የሰደደና ዘግናኝ ኢፍትሃዊነት ማገለጥና መታገል የግድ ይላል።  ይህን ከግብ ለማድረስ ደግሞ ድርጅት ወሳኝ ነው። የተደራጀ ትግልም በሀረርና በድሬዳዋ ማድረግ  እንደዚሁ።
Filed in: Amharic