>
5:14 pm - Monday April 20, 9643

ዘረኝነትን እናውግዝ ስልህ...!!! (ሞሀመድ አሊ መሀመድ)

ዘረኝነትን እናውግዝ ስልህ…!!!
ሞሀመድ አሊ መሀመድ
በሰዎች መካከል የዘር; የሃይማኖት; የፆታ … ልዩነትና አድሎ የማላደርግና እንዲደረግም የማልፈልግ አፍቃሬ-ፍትህ ይሉት ብጤ ነኝ:: ሰውን በሰውነቱ እቀበላለሁ; እወዳለሁ; እረዳዋለሁ; አምነዋለሁም።  ከዚያ በታች ወርጄ ከምገኝና ከዚሁ አንፃር ሰውን ከምመዝን ሞቴን እመርጣለሁ!!
 
እኔኮ ቀደም ብዬ ነግሬህ ነበር። አንተ ግን ዛሬም ሩቅ ይመስልሃል። ዘረኝነት ግን ላንተ ቅርብ ነው። እዚያው ጎረቤትህ ሆኖ ስትወጣ ስትገባ በጥላቻና ቂም-በቀልን ባረገዙ ዐይኖቹ ይከታተልሃል። ሚስትህንና የደረሰች ሴት ልጅህን ሊደፍር ይመኛል። አንተን; ወንድምህንና ወንድ ልጅህን እንደባብ ቀጥቅጦ ለመግደል (በልቡ) ያሴራል። ጥረህ ግረህ በላብህ ያፈራኸውን ሀብትና ንብረትህን ዘርፎ/ተቆጣጥሮ በድሎት ሲኖር ይታየዋል።
ይኸ ግን እንዴት ሊሆን ቻለ? ይኸ የእኛ ማንነትና ባህል መገለጫ ነው እንዴ? የክርስትናም ሆነ የእስልምና አስተምህሮቶች ዘረኝነትን የሚያበረታቱ አይደሉም። እንዳውም በግልፅ የሚያወግዙ ናቸው። ታላቁ ነብይ መሐመድ (ሰ.ዐ.ወ) “ዘረኝነት ጥንብ ነው” ማለታቸው በተደጋጋሚ ተወስቷል። ታዲያ የእስልምና ሃይማኖት ሊቃውንት የት ገቡ? የኦርቶዶክስ እምነት አባቶችስ ምን እየሠሩ ነው? የፕሮቴስታንት; የካቶሊክና ሌሎች ቤተ-እምነቶችስ ምን እያስተማሩ ነው? መቼም ዘረኝነትና ጥላቻን የሚሰብክ የእምነት ተቋም ይኖራል ተብሎ አይጠበቅም።
ምናልባትም ይኸ ጉዳይ የተጋነነ ሊመስል ይችላል። እንደ ክፉ ሟርትም ሊቆጠር ይችላል። ምክንያት እኛ መስማት የምንፈልገው እንዲነገር ነው የምንፈልገው። ካልደረሰብን በስተቀር መጥፎ ነገር መስማት ብቻ ሳይሆን እንዲወራም አንፈልግም። በእኛ ላይ ደርሶ ስናዬው ብቻ ነው አደጋውን የምናውቀው።
ዘረኝነት አስቀያሚ ነው። ልናወግዘውና በሩቅ ልንዋጋው ይገባል። ዘረኞች እንደፈለጉ ሲፈነጩ ዝም ብለን ቆመን ልናያቸው አይገባም። ልንቃወማቸውና ልንታገላቸው ይገባል። በዚህ ላይ ጥላቻችን ግልፅ መሆን አለበት። የምንጠላው ሰውን አይደለም። ፀባችን ከአስተሳሰቡ ጋር ነው። የምንፀየፈው ዘረኝነቱን ነው።
ምናልባትም እንዳንዶቻችን እንደሚመስለን ዘረኞች ሰፊ ማህበራዊ መሠረት የላቸውም። ማንኛውም ማህበረሰብ ቢሆን በተለይ በጥፋት ላይ ያነጣጠረ ዘረኝነትን የሚያስተናግድበት ባህላዊና ሥነ-ልቦናዊ ሊኖረው አይችልም። ይሁን እንጅ ዘረኞች ራሳቸውን ስለሚያደራጁና የጥፋት መረባቸውን (network) ስለሚዘረጉ የሚፈጥሩት ተፅዕኖ ቀላል አይሆንም። በተለይ ሌላው ወገን እጁን አጣጥፎ በተቀመጠበት ዘረኞች ሊያደርሱ የሚችሉት ጥፋት ከባድ ይሆናል። እነሱ ተደራጅተው ከመጡ በኋላ መደራጀት አስቸጋሪ ከመሆኑም በላይ ውጤታማ ቢሆን’ኳ ጥፋቱ ከደረሰ በኋላ ነው። ስለሆነም ዘረኝነትን ለመከላከል ቀድሞ መደራጀትና; ብሎም ሰብኣዊነትን ማስተማርና መከላከል ያስፈልጋል።
ሰውነት – ወረድ ሲል ኢትዮጵያዊነት – ከዚያ በታች መውረድ ግን. …
እኔ ሰው ነኝ:: ሰብኣዊ ባህሪያትን የተላበስኩ ምክንያታዊ; ቅን አሳቢና ማህበራዊ ፍጡር ነኝ:: በሰዎች መካከል የዘር; የሃይማኖት; የፆታ … ልዩነትና አድሎ የማላደርግና እንዲደረግም የማልፈልግ አፍቃሬ-ፍትህ ይሉት ብጤ ነኝ:: ሰውን በሰውነቱ እቀበላለሁ; እወዳለሁ; እረዳዋለሁ; አምነዋለሁም።  ከዚያ በታች ወርጄ ከምገኝና ከዚሁ አንፃር ሰውን ከምመዝን ሞቴን እመርጣለሁ።
ዘረኝነት ፀያፍና የሰብዕና ውርደት/ዝቅጠት ነው። ጠባብ ብሔርተኝነትም ያው ነው። እስካሁን ድረስ በዓለም ላይ ዘረኝነትን አቀንቅኖ ያተረፈ መኖሩን አላውቅም። አውሮፓ ተሻግረን የነሂትለርን አነሳስና አወዳደቅ መመርመር እንችላለን። የነሱ ታሪክ ጀርመኖችን አንገት እንዳስደፋቸው ነው። ጦሱ እስካሁን አለቀቃቸውም። እዚሁ አህጉረ-አፍሪካ የነሩዋንዳን ተሞክሮ ወስዶ ማዬት ይቻላል። በሁትሲና ቱትሲ ጎሳዎች መካከል የተቀነቀነው ዘረኝነት ውጤቱ ምን እንደሆነ ሊነግሩን የሚችሉት በከፍተኛ ቁጭትና ፀፀት ተሞልተው መሆን አለበት።
ወዲህ ወደ ሀገራችን ስንመጣስ ጠባብ ብሔርተኝነትን/ዘረኝነትን ያቀነቀኑ ወገኖች ምን አተረፉ? ትናንት በድል አድራጊነት ስሜትና በእብሪት ተሞልተው ዘረኝነትን በሰበኩባት ምድር ዛሬ ላይ አንገታቸውን ቀና አድርገው መንቀሳቀስ የማይችሉበት ሁኔታ እየተፈጠረ ነው። ዘረኝነት አስነዋሪ; አሳፋሪና አንገት የሚያስደፋ ወራዳ ተግባር ነው።
እኔ ዘረኝነትን እፀየፋለሁ። ራሴን ከዚያ በላይ አድርጌ ማየትና ሰው ሆኜ መገኜት እፈልጋለሁ። ይህን ሰብዕና ይዤ ኢትዮያዊ ዜጋ በመሆኔም እኮራለሁ:: ኢትዮጵያዊነት የጀግንነት; የአልበገርም ባይነት; የአሸናፊነት; የነፃነትና የፅናት መገለጫ እንጅ ሌላ አይደለም:: ኢትዮጵያዊነት የአብሮነት መገለጫ እንጅ ሰው ወገኑን እንደ አውሬ አሳድዶና ቀጥቅጦ የሚገድልበት የጭካኔን ዳርቻ ማሳያ አይደለም።
ኢትዮጵያዊነት በፈሪሃ-እግዚአብሔር/አላህ የተገነባ ደግነትና  ርህራኄ የሰፈነበት ምድር እንጅ የሰው-አውሬዎችና አረመኔዎች መናገሻ አይደለም; ሊሆንም አይገባም።  ኢትዮጵያዊነት አካታች እንጅ ሰዎችን በዘራቸው; በሐይማኖታቸውና በሌላ ማንነታቸው የሚያገልና የሚያሳቅቅ አይደለም; ሊሆንም አይገባም። ይህ ስሜት በሚሊዮኖች ውስጥ እንዳለም አምናለሁ:: ኢትዮጵያዊነት ዛሬ በተለያዩ ተፅዕኖዎች ሥር ቢሆንም “የተዳፈነ ረመጥ” መሆኑን እገነዘባለሁ:: ረመጡን ቢረግጡት ይፋጃል:: ሊቀጣጠልም ይችላል:: ለሚወዱት ግን ብርሃንን ይፈነጥቃል።
ኢትዮጵያዊነት ይለምልም!!!
Filed in: Amharic