>

“የተወልደ ክለብ”፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የተዘረጋው የጭቆና ሰንሰለት! (ስዩም ተሾመ)

 

“የተወልደ ክለብ”፡ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ የተዘረጋው የጭቆና ሰንሰለት!

ስዩም ተሾመ

በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ በማንነት ላይ የተመሰረተ በደልና ጭቆና የሚፈፀመው በቀጥታ አይደለም። በእርግጥ የዘረኝነቱ ቁንጮ የመስሪያ ቤቱ ዋና ስራ አስኪያጅ አቶ ተወልደ ገብረማሪያም ነው። ነገር ግን አቶ ተወልደ በሰራተኞች ላይ በደልና ጭቆና እንዲፈፀም በቀጥታ ትዕዛዝ አይሰጥም። ከዚያ ይልቅ ይህን ተግባር የሚፈፅም የአቶ ተወልደ ክለብ (Tewolde’s Club) አለ። የዚህ ክለብ አባላት የተለያየ ብሔር ተወላጆች ናቸው። አንድ የሚያደርጋቸው ነገር ለአቶ ተወልደ ፍፁም አገልጋይና አጎብዳጅ መሆናቸው ነው። እሱ አድርጉ ያላቸውን ማንኛውም ነገር ያለ ማወላዳት ያደርጋሉ። ሕግና ደንብ የሚፃረርን ማንኛውም ተግባር ለምንና እንዴት ሳይሉ ይፈፅማሉ።

የተወልደ ክለብ አባላት በታማኝነትና አጎብዳጅነት ለሚሰጡት አገልግሎት የተወሰኑት በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ከሚፈፀመው ሙስና እና ዘረፋ ይቋደሳሉ፣ የተቀሩት ደግሞ የማይገባቸውን ስልጣንና ኃላፊነት ያገኛሉ። እነዚህ የጥቅምና ስልጣን ሱሰኞች በአቶ ተወልደ ወይም በክለቡ አባላት ላይ የሚሰነዘር ማንኛውም ዓይነት ጥቃትን በጋራ ይከላከላሉ። ምክንያቱም አቶ ተወልደ ከተነካ ወይም ክለቡ ከፈረሰ በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ያላቸው ህልውና ያከትማል። ስለዚህ ማንኛውንም ዓይነት ወንጀል በጋራ ይፈጽማሉ፣ ጥቃትም ሲመጣ በጋራ ይከላከላሉ። እዚህ ጋር ረዳት አብራሪ ዮሃንስ ተስፋየ በማንነቱ ላይ የተፈፀመበትን በደልን አስመልክቶ አንድ የተወልደ ክለብ አባል የሆኑ ሥራ አስኪያጅ የሰጡትን ምላሽ እንደ ማሳያ መጥቀስ ይቻላል።

ረዳት አብራሪ ዮሃንስ ተስፋየ ደረሰብኝ ያለውን በደል አስመልክቶ የሚሰጡት አስተያየቶች የተወልደ ክለብ አባላት በሚፈልጉት መንገድ ሲሆን የችግሩን ትክክለኛ ገፅታ በግልፅ አያሳይም። አንድ ሊሰመርበት የሚገባው ነገር የተወልደ ክለብ አንድን ሰራተኛ በማንነቱ ሊበድለውና ሊጨቁነው ይችላል። ነገር ግን በአማራነቱ ወይም በኦሮሞነቱ ምክንያት ከሥራው አያሰናብትም።

ነገሩን ይበልጣ ለማብራራት ያመች ዘንድ አንድ የማከብረው ወዳጄ የነገረኝን ገጠመኝ ልንግራችሁ። ይህ ወዳጄ ያሳደገው ልጅ አየር መንገድ ባወጣው የሥራ ማስታወቂያ ለመቀጠር ይወዳደራል። ወዳጄ ደግሞ አየር መንገድ ውስጥ የሚሰራ ጓደኛው ጋር ይደውልና “እባክህ ይሄ ልጅ እንዲቀጠር እርዳኝ?” በማለት ልጁ በአድልዎ እንዲቀጠርለት ይጠይቃል። የአየር መንገዱ ሰራተኛ በቅድሚያ የጠየቀው ነገር “ያሳደከው ልጅ ብሔሩ ምንድነው?” የሚል ነው። ወዳጄም “አማራ” እንደሆነ ሲናገር ጓደኛው በፍፁም እንደማይቻል ነገረው።

በእርግጥ አየር መንገድ ውስጥ አንድ የአማራ ተወላጅ በአድልዎ ከማስቀጠር አስር የትግራይ ተወላጅን ማስቀጠር ይቀላል። የዚህ መሰረታዊ ምክንያቱ የተወልደ ክለብ ነው። አንድ የትግራይ ተወላጅ በማንኛውም መንገድ ሄዶ ከተወልደ ወይም የትግራይ ተወላጅ ከሆኑ የክለቡ አባላት ጋር ከተነካካ በመስሪያ ቤቱ ይቀጠራል፣ እድገት ያገኛል፣ የማይገባ ጥቅም ያጋብሳል፣ …ወዘተ። ምክንያቱም በአቶ ተወልደ በኩል የመጣን ሰው ማገልገል የተወልደ ክለብ አባላት ድርሻና ኃላፊነት ነው።

በሌላ በኩል የአማራ ወይም የኦሮሞ ተወላጅ በአቶ ተወልደ በኩል የመምጣት እድል ስለሌላቸው በዚህ አድሏዊ አሰራር እንደ ትግራይ ተወላጆች ተጠቃሚ አይደሉም። በእርግጥ የአማራ፥ ኦሮሞ ወይም ሌላ ብሔር ተወላጅ በአድሏዊ አሰራር ወይም በማንነቱ ተጠቃሚ መሆን የለበትም። ነገር ግን እንደ አቶ ተወልደ ዓይነት ዘረኛ አመለካከት ያለው ግለሰብ በሚመራው መስሪያ ቤት ውስጥ በማንነት ላይ የተመሰረተ ጥቅም ብቻ ሳይሆን በደልና ጭቆና ይኖራል።

ከላይ በተጠቀሰው መልኩ በአድልዎ የተቀጠረ የትግራይ ተወላጅ በመስሪያ ቤቱ የተቀጠረው አስፈላጊው ብቃትና ክህሎት ስላለው ሳይሆን በብሔር ማንነቱ አማካኝነት በፈጠረው ግንኙነት ነው። በመሆኑም በብሔር ማንነቱ ያገኘውን ጥቅምና ተጠቃሚነት በማንኛውም አግባብ ለሌላ ተላልፎ መሰጠት እንደሌለበት ያምናል። ለዚህ ደግሞ፤ አንደኛ፡- ለአቶ ተወልደ ክለብ ፍፁም ታማኝ አገልጋይ ይሆናል፣ ሁለተኛ፡- ከክለቡ አመራርና አባላት የተለየ አቋምና አመለካከት ያላቸው፣ ከራሱ ከሰራተኛው እስከ አቶ ተወልደ ድረስ ለተዘረጋው ያልተገባ የጥቅም ትስስርና የሙስና ተግባር አደጋ ሊሆኑ የሚችሉ ሰራተኞችን ይከታተላል፥ ይጠቁማል፥ ያስፈራራል፥ ይጨቁናል፥… ወዘተ።

የተወልደ ክለብ በዘረጋው አድሏዊ አሰራር ተጠቃሚ የሆነው ሰራተኛ በሂደት የክለቡ መረጃ አቀባይ፣ ተላላኪ፣ አስፈፃሚ፣… ወዘተ እያለ በመጨረሻ የክለቡ አባል ይሆናል። ስለዚህ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ሰራተኞች ላይ በደልና ጭቆና የሚፈጽሙት የተወልደ ክለብ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው። በዚህ መልኩ የሚፈፀም በደልና ጭቆና ሰለባ የሆኑ በጣም ብዙ ሰራተኞች አሉ። ከእነዚህ ውስጥ አንዱ ረዳት አብራሪ ዮሃንስ ተስፋየ ነው። በእርግጥ እንደ ዩሃንስ ተስፋየ አስከፊ በደልና ጭቆና የደረሰባቸው፣ አሁንም እየደረሰባቸው ያሉ ሰራተኞች በጣም ብዙ ናቸው። ሰሞኑን “አስተዳደራዊ በደልና ጭቆና የተፈፀመባቸው በብሔር ማንነታቸው ነው?” የሚለው በማህበራዊ ሚዲያዎች ላይ አነጋጋሪ ሆኖ ሰንብቷል። ይህን ጥያቄ በአግባቡ ለመመለስ ከላይ የተገለጸውን የመስሪያ ቤቱን ነባራዊ እውነታ ከግንዛቤ ማስገባት ያስፈልጋል።

ቀደም ሲል ለመግለጽ እንደተሞከረው አየር መንገድ ውስጥ በሰራተኞች ላይ አስተዳደራዊ በደልና ጭቆና የሚፈፅሙት የተወልደ ክለብ አባላትና ደጋፊዎች ናቸው። በዚህ መሰረት፤ አንደኛ፡- አቶ ተወልደ የትግራይ ተወላጅ ከመሆኑም በላይ የህወሓትን ዘረኝነትና ጥላቻ በማስፈጸም ረገድ ባሳየው ብቃትና ችሎታ ለሹመት የበቃ፣ ከህወሓት ካድሬዎችና ጄኔራሎች ጋር በዘረፋና ሙስና ተግባር የተዘፈቀ ነው፣ ሁለተኛ፡- የክለቡ አባላት የአቶ ተወልደ ፍላጎት ማስፈጸሚያ፣ ፍፁም አጎብዳጅና አገልጋይ የሆኑ የተለያዩ ብሔር ተወላጆች ናቸው፣ ሦስተኛ፡- አብዛኞቹ የተወልደ ክለብ አባላትና ደጋፊዎች በብሔር ማንነታቸው አማካኝነት በፈጠሩት ያልተገባ ግንኙነት በመስሪያ ቤቱ የተቀጠሩ፣ የሥራ እድገትና ኃላፊነት ያገኙ ሰዎች በአብዛኛው የትግራይ ተወላጆች ናቸው።

አሁን የአቶ ተወልደ ክለብ የጨዋታ ስልትን እና አሰላለፍን በግልፅ ለይቶ ማስቀመጥ ይቻላል። ከፊት አቶ ተወልደ፣ መሃል የክለቡ አባላት፣ ከኋላ ደግሞ የክለቡ ደጋፊዎች አሉ። በማንኛውም አግባብ አቶ ተወልደን፣ የህወሓት ካድሬና ጄኔራሎችን፣ የክለቡ አባላት የሚፈፅሙትን ግፍና በደል ወይም በመስሪያ ቤቱ ውስጥ ያለውን አድሏዊ አሰራርና ሙስና የመቃወም፥ የመተቸት፣ የመጋፈጥ፣… አዝማሚያ ያሳየ፣ ሙያዊ ስነ-ምግባርና የመስሪያ ቤቱን ደንብ በአግባቡ ለመተግበር ወይም መብትና ነፃነቱን ለማስከበር የሚውተረተር ሰራተኛ አስተዳደራዊ በደልና ጭቆና ይደርስበታል።

ለምሳሌ እንደ ረዳት አብራሪ ዩሃንስ ተስፋየ ያለ ሙያቂ ብቃትና ክህሎት እንዳለው ተረጋግጦ በመስሪያ ቤቱ የተቀጠረና ከ1000 ሰዓት በላይ አውሮፕላን ያበረረ ሰራተኛ በተወልደ ክለብ ደጋፊዎች የሚደረግበትን ክትትልና ትንኮሳ፣ እንዲሁም በማንነቱ ላይ የሚደርስበትን ዘረኝነትና ጥላቻ በራሱ ለመቋቋምና ሰብዓዊ ክብሩን ለማስከበር ጥረት ያደርጋል። ግጭትና አለመግባባቱ እየከረረ ሲሄድ የተወልደ ክለብ ደጋፊዎች ረዳት አብራሪ ዮሃነስ በሥራና በባህሪው ያሳያቸው ክፍተቶችና ድክመቶችን እየተከታተሉ መረጃ በማጠናቀር ወደ በአመራርነት ደረጃ ወዳሉት የክለቡ አባላት መላክ ይጀምራሉ።

ዮሃንስ በሚደረግበት ክትትልና ጫና እየተበሳጨ፣ ለሥራው ያለው ፍላጎት እየቀነሰ፣ ከባልደረቦቹ ጋር ያለው ግንኙነት እየሻከረ በሄደ ቁጥር በተደጋጋሚ ይሳሳታል፣ ክፍተቶችም ይመዘገቡበታል። በዚህ መሰረት ከተወሰነ ግዜ በኋላ ረዳት አብራሪ ዮሃነስን ከስራ ለማባረር ወይም ከደረጃው ዝቅ ለማድረግ የሚያስችል መረጃ ይሰበሰባል። በአመራርነት ደረጃ ያሉት የክለቡ አባላት እነዚህን መረጃዎች በማጠናቀር ውሳኔ እንዲሰጥበት ወደ ተወልደ ይመራሉ። አቶ ተወልደ ደግሞ ይህን መሰረት አድርጎ የውሳኔ እርምጃ ይሰጣል ወይም የቀረበው የውሳኔ ሃሳብ ተግባራዊ እንዲሆን ይፈቅዳል።

የተወልደ ክለብ በኢትዮጵያ አየር መንገድ ውስጥ ለሚፈፀመው ዘረኝነትና ጥላቻ፣ አስተዳደራዊ በደልና ጭቆና፣ እንዲሁም አድሏዊ አሰራርና ሙስና ዋና ምክንያት ከመሆኑ በተጨማሪ ተጠያቂነትን ለማስወገድ ታስቦ ተደርጎ የተዋቀረ ነው። ከላይ ለመግለፅ እንደተሞከረው የክለቡ መሪ አቶ ተወልደ እና አብዛኞቹ የክለቡ ደጋፊዎች የትግራይ ተወላጆች ሲሆኑ የክለቡ አባላት ግን የተለያየ ብሔር ተወላጆች ናቸው። በመስሪያ ቤቱ የሚፈፀመው ግፍና በደል ገፈት የሚቀምሱት የሌላ ብሔር ተወላጆች ናቸው። ነገር ግን ግፍና በደል የፈጸሙት የክለቡ ደጋፊዎች ሆኑ የችግሩ ቁንጮ የሆነው አቶ ተወልደ ተጠያቂ አይሆኑም።

አቶ ተወልደ በመሪነት፣ ደጋፊዎቹ ደግሞ በተግባር የፈጸሙትን ቢሆንም ይህን ተግባር አስፈፃሚ የሚመስሉትና በኋላ ላይ ፊት ለፊት ወጥተው የሚከላከሉት ግን የተበዳዬ ብሔር ተወላጅ የሆኑ የክለቡ አባላት ናቸው። ለምሳሌ እንደ ረዳት አብራሪ ዮሃንስ ተስፋየን ጉዳይ የሚከላከለው የአማራ ተወላጅ የሆነ የተወልደ ክለብ አባል ነው። ልክ ዛሬ በአማራ ቴሌቪዥን ላይ እንደተመለከትነው አንድ የተወልደ ክለብ አባል ቀርቦ “ረዳት አብራሪ ዮሃንስ ተስፋየ በአማራነቱ በሚደርስበት በደል ከስራ አልተሰናበተም። እኔ የሰጠሁትን ትዕዛዝ ተቀብሎ ተግባራዊ ለማድረግ ፍቃደኛ ባለመሆኑ ስራውን ለቅቆ ሄዷል። ‘በአማራነቴ በደልና ጭቆና ተፈጸመብኝ’ የሚለው ስህተት ነው። ምክንያቱም እኔ ራሴ አማራ ነኝ” ብሏል። የክለቡ ደጋፊዎች በረዳት አብራሪ ዮሃንስ ተስፋየ የሸረቡት የበደል ሴራ በዚህ ሰውዬ በኩል እንዲቋጭ የተፈለገው ዛሬ በቴሌቪዥን ቀርቦ የተናገረው እንዲናገር ታሳቢ ተደርጎ ነው። ይህ ስልት በአየር መንገድ ውስጥ የተንሰራፋውን አስተዳደራዊ በደል፣ ዘረኝነት፣ አድልዎና ሙስናን ለመከላከል ታቅዶ የተነደፈ ነው። የተወልደ ክለብ ፈርሶ፤ የክለቡ መሪ፥ አባላትና ደጋፊዎች ከዚያ መስሪያ ቤት ተጠራርገው እስካልወጡ ድረስ የተባረሩ ሰራተኞችን በመመለስ የኢትዮጵያ አየር መንገድ አይስተካከልም። Seyoum Teshome |

Filed in: Amharic