>
5:13 pm - Thursday April 18, 6148

ኢሳያስ ለምንና ለማን መጣ? (ጌታቸው ሽፈራው)

ኢሳያስ ለምንና ለማን መጣ?
ጌታቸው ሽፈራው
ጀኔራል ከማል ገልቹ  እና ሌንጮ ለታ ተንከልክለው ሲገቡ ዳውድ  አስመራ ላይ ቀብረር ብሎ የቆየው እንዲሁ አይደለም። የኢሳያስ ድጋፍ ስላለው ነው። እነ ግንቦት ሰባት ያለ በቂ ድርድር የገቡት ነገ ኢሳያስ “ውጡ” ቢል አማራጭ ስለሌለ ነው። ዳውድ ግን ኢሳያስ እንደማይቆርጥበት ስላወቀ ለማ መገርሳን ኤርትራ ድረስ አከላትሞታል
___
 
ከእንቅልፌ ነቅቼ ወደ ፌስቡክ ሰፈር ሳቀና “ኢሱ! ኢሱ” የሚል የፌስቡክ ጩኸት ይሰማኛል። ኢሳያስ ወደ አዲስ አበባ መጣ ብለው የሚደሰቱ ወገኖችን ፅሁፍ አነበብኩ። ብዙዎቹ ኢሳያስ የሰላም ስምምነት ሊፈራረም እንደመጣ ይገልፃሉ። የአሰብም ጉዳይ አብሮ ይነሳል። ጥሩ ነበር።
 አብይ ወደኤርትራ ሁለት ጊዜ አቅንቷል። ኢሳያስ ከሁለት ወር በፊት ወደ ኢትዮጵያ መጥቶ ነበር። በመሃል ከአብይ ጋር መካከለኛው ምስራቅ ተገናኝተው ተነጋግረዋል። እንደእውነቱ መሪዎቹ ከአራት ጊዜ በላይ የተነጋገሩበትን ባለሙያዎች ይሰሩታል። ኢሳያስ ለስራ ጉብኝት ወደ አዲስ አበባ መጣ የሚባለው ለሰላም ስምምነቱ አይመስለኝም። በእርግጥ የሆነ ወረቀት ላይ ሊፈራረሙ ይችላሉ ይሆናል።
ኢሳያስ ወደ ኢትዮጵያ የመጣበት ዋናው  ምክንያት የሚሆነው የዳውድ ኢብሳ ጉዳይ ነው። በአሁኑ ወቅት ዳውድ ኢብሳ በእነ አብይ “አንደኛ ደረጃ በጥባጭ” ተብሎ ተፈርጇል።  ዳውድ ኢብሳ “ጦርነት ከፈለጉ” ሲላቸው እነ ዶክተር አብይ “የአፍ ወለምታ ይሆናል” ሲሉ የሰነበቱት ሰውየውን ስለፈሩት ነው። በዚህ ወቅት ቄሮን “ተነስ” ብለው እነ አብይን  ማስጨነቅ የሚችሉት ዳውድ እና ጃዋር ናቸው።  እነ ዳውድ ቄሮውን በለማ ላይ ዝመት ቢሉት ይዘምታል። ዳውድ ቄሮን ተማምኖ እንጅ ከ700  የማይበልጥ ጦሩ ሊያድነው አይደለም።
እነ አብይ አህመድ ዳውድን ሲለማመጡ ብዙ ድጋፋቸውን አጥተዋል። ኦዴፓ (ኦህዴድ) ኦሮሚያ ውስጥ አቅመ ቢስ ሆኗል። እነ አዲሱ አረጋ፣ እነ ታዬ ደንዳአ በኦሮምኛ ሲያባብሉ የሚውሉት ዳውድ ስላስቸገራቸው ነው።  በዚህ ሂደት እነ አብይ ከኦህዴድ ጀምሮ በኢትዮጵያ ሕዝብ ትዝብት ውስጥ ገብተዋል። ዳውድ እያቅራራባቸው እነሱ እየተለማመጡ ነው። ሌሎቹን ትጥቅ አስፈትተው ዳውድ ግን ከፈለጋችሁ ግጠሙኝ እያላቸው ነው።
ኦዴፓ በዳውድ ላይ ብዙ ሰው አዝምቷል። የቀድሞው የኦነግ መሪ  ሌንጮ ለታ በይፋ በሚዲያ ተችቶታል። ለሌንጮ ኦዴፓ ዋስትና ስለሚሆነው እንጅ ሌላ መጠጊያ የለውም። ጀኔራል ከማል ገልቹ ከዳውድ አንፃር ሲታይ ለዘብተኛ ብሄርተኛ ነው። የኦነግ አንደኛው መሪ ከማል ነበር። ሌንጮ፣ ዳውድና ከማል ኦነግን ለሶስት ሸንሽነውት ነበር። ሶስቱ መሪዎች አይንና ናጫ ከሆኑ ቆይተዋል። ከማል የኦሮሚያ ክልል ፀጥታ ጉዳይ ኃላፊ ተደርጎ መሾሙ ተገልፆአል። ይህም ሌላ በዳውድ ላይ የተደረገ ዘመቻ ነው። ይህም ግን ዳውድን አላንበረከከውም። ቄሮ ማንን በደንብ እንደተቀበለ እና እንደሚቀበል ሁሉም ገብቷቸዋል። በተለይ ዳውድ ተማምኖበታል። እነ አብይም ዳውድን ደፍረው መናገር አልቻሉም። ዳውድን ደፍሮ መናገር የሚችለው አንድ ሰው ብቻ ነው። ኢሳያስ አፈወርቂ!
ዳውድ ኢብሳ ለረዥም ጊዜ አስመራ ውስጥ ኖሯል። ዳውድ ባለው ጠርዝ የያዘ አመለካከት ከኢሳያስ ጋር ጥሩ ግንኙነት እንደነበራቸው ይነገራል።  ከሶስቱ የኦነግ መሪዎች አስመራ በቅንጦት ይኖር የነበረው ዳውድ ነበር። በኢሳያስ የተመረጠው ዳውድ ኢብሳ ነው። ጀኔራል ከማል ገልቹ  እና ሌንጮ ለታ ተንከልክለው ሲገቡ ዳውድ  አስመራ ላይ ቀብረር ብሎ የቆየው እንዲሁ አይደለም። የኢሳያስ ድጋፍ ስላለው ነው። እነ ግንቦት ሰባት ያለ በቂ ድርድር የገቡት ነገ ኢሳያስ “ውጡ” ቢል አማራጭ ስለሌለ ነው። ዳውድ ግን ኢሳያስ እንደማይቆርጥበት ስላወቀ ለማ መገርሳን ኤርትራ ድረስ አከላትሞታል። አቅሙንም ለማሳየት ጭምር ነው። መለማመጡ በከፋ ሁኔታ የጀመረው ያኔ ነው።
ዋናው ከኢሳያስ ጋር ፍቅር መሆናቸው ብቻ አይደለም። ዳውድ ኢሳያስን መስማቱ ብቻ አይደለም። ኤርትራ ውስጥ ሲኖር የቤተሰብና ሌሎች መረጃዎቹ ሳይቀር ከኤርትራ ደሕንነቶች እይታ አያመልጡም። ኢሳያስ በቀድሞው ጊዜ ቢወደው፣ በጣም ሲተብት “አርፈህ ተቀመጥ” የሚያሰኝ  መረጃ አለው። ለሁለት አስርት አመት ኤርትራ ውስጥ የነበር ሸማቂ ጦሩ ተራራ ወጥቶ፣ ወርዶ (ስልጠና) ተኝቶ ከመዋል ውጭ “ኦፕሬሽን” የሚያደርገው ከስንት አንድ ጊዜ ነው። ቀሪው ጊዜ የእረፍት ነው። በተለይ ለመሪዎች ሰፊ ጊዜ ነበራቸው። በዚህ የእረፍት ጊዜ እነ ዳውድ  ንግድን ጨምሮ ብዙ እንቅስቃሴዎች ውስጥ ሊገቡ እንደሚችሉ ግልፅ ነው። በአንዳንዶቹ ላይ መረጃዎች አሉ። ከዚህ የከፉም መረጃዎች ይኖራሉ። ይነገራሉም። ይህ ለኢሳያስ አቅም ነው። ኢሳያስ ወደ አዲስ አበባ የመጣው “እባክህ ዳውድን ተቆጣው” ተብሎ ይመስላል። እነ አብይ ትግስታቸው እያለቀ ይመስላል። ችግር ከመፈጠሩ በፊት፣ ኦሮሚያ ውስጥ ችግር ከመፍጠሩ በፊት አንድ በልልን ተብሎ ነው።
በእርግጠኝነት ለማስመሰል የሆነች ወረቀት ላይ ውል እየተዋዋሉ ያሳዩናል።  በሚዲያም የስምምነት ዝርዝር ይነግሩን ይሆናል። የሰላም ስምምነት ሊሏትም ይችላሉ። ምን አልባት ለዳወድ ጉዳይ መጥቶ ጨርሶት የሚሄድ ጉዳይም ሊኖረው ይችላል። ተዋዋልን ቢሉ እንኳ በውስጥ ቀስ እያሉ የሚጨርሷት ጉዳይ ትኖራለች እንጅ ቅድሚያው ዳውድ ኢብሳ ነው!
Filed in: Amharic