>
5:33 pm - Monday December 5, 5216

የጀኔራል ከማል ገልቹ  ሹመት፤ (ውብሸት ሙላት)

የጀኔራል ከማል ገልቹ  ሹመት፤
ውብሸት ሙላት
ጀኔራል ከማል ገልቹ የኦሮሚያ ክልል አስተዳደርና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ሆነው ተሹመዋል የሚል ዜና እየሰማን ነው፡፡ የእሳቸውን ሹመት በሚመለከት አስተያየቴን ላስቀምጥ፡፡
ጀኔራል ከማል ገልቹ አንድ ሻንበል ጦር ሠራዊት ገንጥሎ ኤርትራ ገባ፡፡ ወታደሮቹ ዉስጥ ከኦሮሞ በተጨማሪ አማራዎችም ነበሩ፡፡
የከማል ገልቹ ጦር ከኦነግ ጋር ተቀላቀለ፡፡ የተወሰነ ጊዜ ካየዉ በኋላ በአቶ ዳዉድ ኢብሳ የሚመራውን ኦነግ ጋር በዓላማም በግብም ባለመስማማታቸው የኦሮሞ ሕዝብ ዴሞክራሲያዊ ግንባርን (ኦሕዴግ) መሠረተ፡፡ አቶ ዳውድና ጀኔራል ከማል ገልቹ ፍጹም የማይስማሙ ናቸው፡፡
ጀኔራል ከማል ገልቹ ኦነግን በመተው የራሳቸውን ድርጅት መሥርተው ሲንቀሳቀሱ ከቆዩ በኋላ ከግንቦት 7 ጋር በጥምረት ለመታገል ተስማሙ፡፡ ይሁን እንጂ የግንቦት 7ም ሰማይ ላይ የተንጠለጠለ እና ሌሎች ችግሮችን ሲያስተውል ከማል ገልቹ ከግንቦት 7ም ተነጠለ፡፡
የከማል ገልቹ ወታደሮች በተለያዩ ጊዜያት አስቀድመዉ ወደ ኢትዮጵያ ተመልሰዋል፡፡ ጀኔራል ከማል ገልቹም አስመራ ላይ የተወሰነ ጊዜ ከቆዩ በኋላ ወደ ኡጋንዳ በመሔድ ራሳቸውን ሰወር አድርገው ወደ ሁለት ዓመታት ገደማ ቆዩ፡፡ ከዚያም በቅርቡ ኢትዮጵያ ገቡ፡፡
በነገራችን ላይ ከማል ገልቹ ባለፈው ሳምንት አማራ ክልል ዉስጥ ከሜሴና አካባቢው ባቲን ጨምሮ እዚያ እንደነበሩ ሰምተናል፡፡ እዚህ አካባቢ ላይ በከፍተኛ ሁኔታ የአቶ ዳውድ ኢብሳ ኦነግ እየተንቀሳቀሰ ነው፡፡  ጉብኝታቸው የዚህን አካባቢም ችግር ለመረዳት ይሆናል ብለን እንገምታለን፡፡
በመሆኑም ጀኔራል ከማል ገልቹ ሊታዩ ይገባል፡፡ ቢያንስ ቢያንስ አንድም ስለ ኦነግ፣ አንድም ስለ ግንቦት 7 ሲባል ይታዩ፡፡ ሹመቱ ተገቢ ነዉ።  ይበል።
(ይህን አስተያየት ከመጻፌ በፊት ጀኔራል ከማል ገልቹ ኤርትራ በነበሩባቸው ወቅት በቅርብ ከሚያውቋቸው የአማራ አርበኞች መረጃ በማሰባሰብ ነው፡፡)
Filed in: Amharic