>

‹‹ሐቡልቱ ዱቢ››   (ተፈሪ መኮንን)

‹‹ሐቡልቱ ዱቢ››

ተፈሪ መኮንን

 ፈረንሳዮች ‹‹አብዝቶ በተለወጠ መጠን፤ አብዝቶ ነባር መልኩን እንደያዘ ይቀጥላል›› የሚል ብሂል አላቸው፡፡ ይህ ብሂል ፈረንሳዮች፤ የኢትዮጵያን ፖለቲካ ከተመለከቱ በኋላ የቀመሩት ብሂል መሆኑን የሚነግረኝ ሰው ቢመጣ፤ ሳላንገራግር ልቀበለው ዝግጁ ነኝ፡፡ 

የኢትዮጵያ ፖለቲካ በጣም አሰልቺ ገጽታ አለው፡፡ ባለፉት 50 ዓመታት በኢትዮጵያ የፖለቲካ መድረክ ቋሚ አጀንዳ ሆነው እስከ ዛሬ የዘለቁ ሦስት ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህም፤ አንደኛ – የኤርትራ ጉዳይ፤ ሁለተኛ – የብሔር ብሔረሰብ መብት እና ሦስተኛ) የመገንጠል ጥያቄ ናቸው፡፡ ታዲያ አንዳንዴ ከመሰልቸት የተነሳ፤ ‹‹ዕድሜ ለኢህአዴግ! የኤርትራን ጉዳይ ከአጀንዳው መዘርዝር ሰረዘልኝ›› እል ነበር በጓዳ ጨዋታ፡፡ የመገንጠል ጥያቄ ከኤርትራ ባይሄድም፤ አረረም መረረ ዛሬ የኤርትራን ጉዳይ ሁላችንም ውሃ ልክ ይዘን፣ ለየት ባለ መንገድ ለማየት ችለናል፡፡ መሰልቸትን ለመከላከል ብቻ ሣይሆን የተደረገው ትንሽ ለውጥ፤ ትንሽ የመንፈስ፣ የልምድ፣ የአመለካከትና የእይታ ለውጥ ፈጥሮ ለዘላቂ መፍትሔ የሚበጅ አዲስ ምልከታ በመፍጠር ሊያግዘን ይችላል፡፡ ‹‹ሁሌ ከመደንገጥ፤ አንድ ጊዜ መሸጥ›› ይባል የለም፡፡

ያለፉት አምስት መቶ ዓመታት ያሳለፍነው ታሪከ አስረጂ እንደሚሆነው፤ ኢትዮጵያ በድህነትና በኋላ ቀርነት ግርግም ታስራ የቆየችው፤ በመጻዒው ዘመንም ከግርግሙ ለመውጣት የሚያስችል ጠባብ ዕድል የምታጣው፤ በእርስ በእርስ ጦርነት ወጥመድ ታስራ ከቀጠለች ነው፡፡ ‹‹ዕድሜ ለኢህአዴግ፤ የኤርትራን ጉዳይ ከአጀንዳው መዘርዝር ሰረዘልኝ›› የምለው የ30 ዓመት የእርስ በእርስ ጦርነት በምንም መንገድ እንዲቆም ስለምፈልግ ነው፡፡ ስለዚህ የኤርትራን መገንጠል (ወይም አቦ ዳውድ ከዋልታ ቴሌቭዥን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ምርጫቸው ባደረጉት አገላለጽ፤ ‹‹የኤርትራን ነጻነት››) የዘመድ ቄስ እያለቀሰ እንደሚፈታ፤ ቀፋፊውን እውነታ እያለቀሱም ቢሆን ተቀብሎ፤ ከአውዳሚ ጦርነት፤ መገላገል ይጠቅመናል፡፡

በርግጥ ኢህአዴግ ‹‹ከመረገዙ በፊት የተወለደውን የኤርትራን ነጻነት›› (defacto ነጻነት ለማለት ነው)፤ መቀበሉን ከተራማጅና ከአርቆ አስተዋይ እርምጃ እንዳልቆጥረው የሚከለክሉኝ በርካታ ነገሮች አሉ፡፡ ለወጉም ቢሆን ‹‹በሽግግር መንግስት እንዲህ ዓይነት ነገር ለመወሰን አልችልም›› አለማለቱ፤ አንዳንድ የህግ ምሁራን ህጋዊ የመብት ጥያቄ አድርገው የሚመለከቱትን የመቶ ሚሊየን ህዝብ የወደብ ጉዳይ አለማንሳቱ፤ ሻእቢያ በጅ ባይልም ሪፈረንደሙ የጥሞና ጊዜ ተወስዶ (Cooling period) መካሄድ አለበት የሚል አቋም አለመያዙ፤ በጥሞና ጊዜው የመገንጠል አጀንዳ አራማጆች ብቻ ሳይሆኑ፤ አንድነት አስፈላጊ መሆኑን የሚያምኑ ወገኖችም፣ ሐሳባቸውን የማቅረብ ዕድል እንዲያገኙ ሁኔታዎች እንዲመቻቹ ጥረት አለማድረጉ፤ ሁለቱን ህዝቦች የሚያቀራርቡ ባህላዊና ስፖርታዊ ዝግጅቶች በተደጋጋሚ እንዲዘጋጁና የጦርነቱ ስሜት እንዲረግብ፤ የቆሰለው እንዲድን፤ የተጎዳው ተሐድሶ እንዲያገኝ፤ የፈረሰው እንዲገነባ፤ የተሰበረው እንዲጠገን ወዘተ ሳይደረግ መወሰኑ ትክክል አይመስለኝም፡፡ ይህን የምለው፤ ‹‹ስሙ እኩል፤ ሥራው ስንኩል›› እንዳይሆን፤ ኤርትራ እንዳትሄድ ለማንገራገር አይደለም፡፡

ህዝቡ በረጋ መንፈስ የመወሰን ችሎታ እንዲያገኝ ሁኔታዎች መመቻቸታቸው ይጠቅማል። ህዝቡ በጉልህ የጦርነት ትዕይንቶች ተከብቦ ህዝበ ውሳኔ ማድረጉና የሰዎች መንፈስ በምሬት ጢም ብሎ እንደ ተሞላ፣ ሪፈረንደም መካሄዱ፤ ‹‹ነጻነት እና ባርነት›› የሚል ምርጫ መቅረቡ፤ ከሁሉ በላይ ለዘመናት አብረው የኖሩ ህዝቦች መለያየት የሚያስደስት ትልቅ ሁነት ይመስል፤ ለኤርትራ ህጋዊ ዕውቅና ለመስጠት መሽቀዳደሙና የዓለም አቀፍ ድርጅቶችን መወትወቱ ከሚያስከፋ በቀር፤ ኤርትራን ከመሄድ ማስቀረት እንደማይችል አውቃለሁ፡፡

በተከታታይ መንግስታት የተበላሸ የፖለቲካ ጥያቄ የተነሳ ይበልጥ እየተወሳሰበና እየተካረረ የመጣው የኤርትራ ጉዳይ፤ በአግባቡ እልባት እንዲያገኝ፤ ለሠላሳ ዓመታት የዘለቀው ጦርነት እንዲገታና ደም መፋሰሱ እንዲቆም ለማድረግ መወሰኑ፤ በዚህም ለኢትዮጵያ ዕረፍት የሚነሳ የጥርስ ህመም ሆኖ ያስቸገራትን የኤርትራን ጉዳይ ከሐገራችን የፖለቲካ ተዋስዖ መድረክ እንዲወጣ ማድረጉን እንደ ትልቅ እርምጃ እቆጥረዋለሁ፡፡

የመገንጠሉ ተውኔት ከተጠናቀቀ በኋላ ኢህአዴግ የተከተለው የግንኙነት ፖሊሲም ብዙ ችግር እንደ ነበረው ባምንም፤ በድህረ ነጻነት ዘመን የታየውን የሆደ ሰፊነት ዝንባሌ ሙሉ በሙሉ አልቃወምም፡፡ ጥልቅ ለሆነው የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት አክብሮት እንዳለው የሚያመለክቱ አቋሞች አድርጌ በመውሰድ የተቀበልኳቸው የኢህአዴግ መንግስት አካሄዶች መኖራቸውን ሳልክድ፤ ለዚህ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ከህዝበ ውሳኔው በፊት ተገቢውን ግምት በመስጠት፤ በኢ-ዴሞክራሲያዊ መንግስታት የተበላሸ አካሄድ ሳቢያ በተፈጠረው ምሬትና ብሶት የህዝቦች ግንኙነት እንዳይጎዳ የሚፈልግ መሆኑን ሊያመለክት የሚችል ጥረት አለማድረጉ፤ በድህረ ነጻነት የታዩትን አስመስጋኝ ዝንባሌዎች ከድክመት እንጂ ከአስተዋይነት እንዳንቆጥራቸው ከማድረግ አልፎ፤ ‹‹የዓይናቸው ቀለም አላማረኝም›› ብሎ ግንኙነቱን የሚበጠስ እርምጃ ለመውሰድ የማያመነታ እንዳደሆነ ስናውቅ፤ በህግ ያልተገራው መረን የወጣ ግንኙነት፣ በተራ ፍላጎት የሚመራ እንጂ በላቀ ሞራላዊ መርህ የተመሠረተ ግንኙነት አለመሆኑን ለመረዳትና የ30 ዓመቱን ጦርነት የሚያስከነዳ ጉዳት ያስከተለው የ1990 አስከፊ ጦርነት እንዲፈጠር ያደረገ በመሆኑ ወቀሳ አይቀርለትም፡፡

በዚህም የተነሳ የኤርትራ ጉዳይ በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እንደ ቀድሞው የመሐል ባይሆንም ዛሬም የዳር ወንበር መያዙ አልቀረም፡፡ የኢትዮጵያ ፖለቲካ፤ ‹‹አብዝቶ በተለወጠ መጠን፤ አብዝቶ ነባር መልኩን እንደ ያዘ ይቀጥላል›› ማለት እንዲህ  ነው። ነገር ግን የኤርትራ ጉዳይ የሐገራችን የፖለቲካ ኃይሎች የተራማጅነትና የዴሞክራሲያዊነት የአቋም መለኪያ ‹‹ሊትመስ ፔፐር›› ሆኖ አልቀጠለም፡፡ ግን የኤርትራን ጉዳይ ለአንዴና ለመጨረሻ የተገላገልነው አልመሰለኝም፡፡ የኤርትራ ጉዳይ ሁለት ልደት ያለው ነው፡፡ አንድም በእንቁላል፤ አንድም በጫጩት ይመጣል፡፡

ስለዚህ ‹‹የራስን ዕድል በራስ የመወሰን መብት እስከ መገንጠል›› የሚለው ጥያቄ፤ ከሐገራችን የፖለቲካ አጀንዳዎች ዝርዝር አሁንም አልተሰረዘም፡፡ ስለዚህ ለ50 ዓመታት በጥይት ሆነ በሐቲት ተነጋግረን ከአንድ እልባት አልደረስንም፡፡ የፖለቲካ አገና (Political Settlement) መምታት አልቻልንም፡፡ ነገሩ ያሰለቻል፡፡ ኢትዮጵያ ከአናት ደርሶ ተመልሶ ቁልቁል የሚወርድ የፖለቲካ ቋጥኝ የሚገፋውን ሲዚፈስ ትመስላለች፡፡ ተመልሶ እንደሚወርድ እያወቀች፤ እርግማን በመሆኑ ቋጥኙን ወደ ተራራው አናት ለማውጣት ትገፋለች። ታሳዝናለች፡፡

የኢትዮጵያ ፖለቲካ ‹‹አብዝቶ በተለወጠ መጠን፤ አብዝቶ ነባር መልኩን እንደያዘ የሚቀጥል›› በመሆኑ፤ ለግማሽ ምዕተ ዓመታት በሦስቱ አጅንዳዎች ተነታረክን፣ ተታኮስን፣ ተከፋፈልን፣ ተዛዝተን ነገሩን ዛሬም አልጨረስነውም፡፡ አሁንም ወደፊትም መጨቃጨቃችንን አንቀጥላለን፡፡ የሐገራችን የፖለቲካ ልሂቃን አሁንም እንቅርታቸው እስኪፈርጥ እየጮኹ ይከራከራሉ፡፡ ኢትዮጵያን በሲዚፈስ መርገም ያደክሟታል፡፡ እኒህ ልሂቃን፤ አዕምሯቸው ዝግ ነው፡፡ የሽንብራ አፍንጫ የምታክል፤ የሰናፍጭ ቅንጣት መጠን ያላት ትንሽ የፈጠራ ብቃት የሌላቸው እና አንድ ዘፈን ከፍተው እስከ ምጽአት ለማዳመጥ የማይሰለቹ ይመስሉኛል። መስማማት ሆነ መፋረስ አልሆነላቸውም፡፡ ግማሽ ምዕተ ዓመት ሙሉ በተመሳሳይ ትርክቶች የሚደገፉ እና በተመሳሳይ ሰዎች የሚቀርቡ ተመሳሳይ ጥያቄዎች እና ለጥያቄዎች የሚሰጡ ተመሳሳይ ምላሾችን ወይም ክርክሮች እየሰማን ለመኖር ተፈርዶብናል፡፡ ለሐገራዊ አንድነት እና ለብሔር ብሔረሰብ መብት መከበር እንታገላለን በሚሉ ቡድኖች መካከል የሚደረገው ጦርነት እና የፖለቲካ ግብግብ እረፍት እንደነሳን እንኖራለን። ውይይታቸው መስማት በተሳናቸው ሰዎች መካከል የሚደረግ ውይይት በመሆኑ መፍትሔ የሚያመጣ አይደለም ብለን እንድናስብ እያደረገን ነው፡፡ ሁለቱም ትንታኔአቸውን በተጨባጭ እውነታና ንባብ ሊገሩት ሲሞክሩ አናይም፡፡ ስለዚህ በክርክራቸውና በሐሳባቸው አንዳችም ለውጥ አናይም፡፡ ስለዚህ ያሰለቻል፡፡ ከመሰላቸቴ የተነሳ፤ የዚህ ረጅም እና አስልቺ ተውኔት ሴራ በአንድ መንገድ ልቀት አግኝቶ መጋረጃው እንዲዘጋ ከመመኘት ደርሻለሁ፡፡
በአፍሪካ ሁለት ሺህ ገደማ ቋንቋዎች ይገኛሉ ይላሉ፡፡ ከእነዚህ ቋንቋዎች ከ70 እስከ 80 በመቶዎቹ ተከማችተው የሚገኙት አንዳንድ ምሁራን ‹‹Fragmentation Belt›› ሲሉ በሚጠሩት ኢትዮጵያን በሚይዘው የአህጉራችን ክፍል ነው። በዚህ ‹‹የመበታተን መቀነት›› ውስጥ የሚገኙ ሐገሮች አንዳች ህብረት የሚፈጥር ፖለቲካ መፍጠር ተስኗቸው፤ የብሔር እና የቋንቋ አለመመሳሰላቸውን በማየት ልዩነታቸውን ካጠናከሩ ይቸገራሉ፡፡ ልዩነትን በማክበር ህብረትን ለመፍጠር መስራት ይገባቸዋል፡፡ ከዚህ አልፎ በመገንጠል የሚከበር መብት ይኖራል ብዬ አላምንም፡፡

ርግጥ ነው፤ በአንዳንድ ሁኔታዎች የመገንጠል መብትን ማክበር መፍትሔ ሊሆን ይችላል፡፡ ነገር ግን አሁንም ከመነሻው ጥያቄው በአግባቡ ሳይያዝ ቀርቶ፤ በሽታው ወደ ጋንግሪን በመሸጋገሩ፤ አካልን ከመቁረጥ በቀር ሌላ የመዳኛ መንገድ ባለመኖሩ ከሚወሰድ የችግር እርምጃ ውጭ አድርጌ አልመለከተውም፡፡ እንደ መብትም አልቆጥረውም። ግን የጨነቀው እርጉዝ ያገባል ብዬ እቀበለዋለሁ። የኤርትራ ጉዳይ ከዚህ ዓይነት ችግር ሊመደብ የሚችል ነው፡፡ 30 ዓመታት በእርስ በእርስ ጦርነት ውስጥ ተዘፍቆ፤ የመልማት ዕድልን ከማበላሸት በሰላም መለያየትን እመርጣለሁ፡፡ ነገር ግን የችግሩ ምንጭ የዴሞክራሲያዊ ስርዓት አለ መኖር እንጂ፤ ከሌሎች ህዝቦች ጋር አብሮ ከመኖር የመነጨ ችግር አይደለም፡፡

የአጼ ኃይለ ስላሴም ሆነ የደርግ መንግስት ዴሞክራሲያዊ መንግስታት አልነበሩም፡፡ በእነዚህ ስርዓቶች የኤርትራ ህዝብ ብቻ ሳይሆን የኢትዮጵያም ህዝብ መብት አልተከበረም፡፡ በህዝቡ ላይ የደረሰው በደል ምንጭ፤ የዴሞክራሲ ስርዓት ካለመኖር ጋር የሚያዝዝ ነው፡፡ በደሉ ሊቀር የሚችለውም ዴሞክራሲን በማስፈን ብቻ ነው፡፡ ታዲያ አንዳንዴ በሐገር አቀፍ ደረጃ ለውጥ ለማምጣት የሚያስችል ትግል የማድረግ አቅም የሌለው የፖለቲካ ኃይል፣ መገንጠልን እንደ አማራጭ የሚመለከት ቢሆን አይገርመኝም። ችግሩ ከሌሎች ጋር አብሮ መኖር ባይሆንም፤ ቀሪው የሐገሪቱ ክፍል በአንድ ምክንያት ለትግል ዝግጁ የሚያደርግ ህሊናዊና ነባራዊ ሁኔታ የሌለው መሆኑን የተረዳ የፖለቲካ ኃይል የመገንጠል ጥያቄ ሊያነሳ ይችላል፡፡ የኤርትራ ህዝብ ትግል ደርግ ሲወድቅ፣ ዴሞክራሲያዊ ስርዓት የመመስረት ዕድል መፈጠሩን በመመልከት ኢትየጵያን ለሁሉም ዜጎች ምቹ እንድትሆን ለማድረግ ከቀሪው የኢትየጵያ ህዝብ ጋር ተባብሮ የተሻለች ሐገር ለመመስረት ቢታገል ትክክለኛ ይሆን ነበር፡፡

ሆኖም ሻእቢያ የያዘው የትግል ግብ የመገንጠል እንጂ ዴሞክራሲያዊ መብቶችና ነጻነቶች የሚከበርበት ስርዓት መፍጠር ባለመሆኑ፤ የኤርትራ ህዝብ በተገነጠለ ማግስት የእርሱን ቋንቋ በሚናገር አዲስ ገዢ መደብ አገዛዝ ሥር ወድቆ  ሲሰቃይ አይተናል፡፡ አንዳንዴም ከቀድሞው የባሰ መከራ ይመስላል፡፡ በኤርትራ የተመለከትነው እንዲህ ያለ ችግር ነው፡፡ ቀድሞም ችግሩ ከሌሎች ጋር አብሮ ከመኖር የመነጨ ችግር አይደለም። ስለዚህ በመገንጠል የሚመጣ መፍትሔ አይኖርም፡፡ በአንድ መንግስት ውስጥ በሚኖሩ የሁለት ብሔር አባላት መካከል ያለ ግንኙትን (ወይም የመንግስት እና ዜጎች ግንኙነትን) የተሻለ ሊያደርገው የሚችለው በዴሞክራሲያዊ ስርዓት እሴቶች ላይ የተመሰረተ የማህበራዊ ስርዓት መኖር እንጂ፤ የአንድ ቋንቋ ተናጋሪዎች ከሌሎች ብሔሮች ተገንጥለው መንግስት መመስረት የሚችሉበት ዕድል ማግኘታቸው አይደለም፡፡ ለዚህ ነው፤ መገንጠል መፍትሔ የማይሆነው፡፡ አሁን ከፋም ለማም አብዛኛው ብሔር ብሔረሰብ፤ ራሱን በራሱ እያስተዳደረ (ለማስተዳደር እየሞከረ) ቢሆንም፤ በሁሉም ክልል፣ ብሔረሰባዊ ልዩ ዞን እና ወረዳ መልካም አስተዳደር ማስፈን አልተቻለም። ዴሞክራሲያዊ አስተዳደር በማስፈን ረገድ ሁሉም በፈተናው አላለፈም፡፡ ሙስና እና ብልሹ አስተዳደርም አልተወገደም፡፡ ስለዚህ የህዝቡ እንባ አልደረቀም፡፡

ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የገባንበት እና አሁን የምንገኝበት ሁኔታ ለወሬ የሚመች አይደለም፡፡ በአምባገነን ሥርዓት ውስጥ እንኳን ሊገኝ የሚችለው ሰላም ውሎ መግባት፤ በፈለጉት የሐገሪቱ ክፍል እንደ ልብ መንቀሳቀስ፤ ማንነትን መሠረት ካደረገ ጥቃትና ከመኖሪያ ቀዬ በመቶ ሺዎች ከሚያፈናቅል አደጋ መጠበቅ ብርቅ ሊሆንብን ጀምሯል፡፡ የዩኒቨርስቲ ተማሪዎች ከክልላቸው ወጥተው ለትምህርት ወደ ሌላ ክልል መሄድ የሚፈሩበት ሁኔታ ተፈጥሯል። ከዚህ ችግር መውጣት የሚቻለው ባለፉት 27 ዓመታት የተገኙትን በጎ ነገሮች በማጠናከር፤ በመጣንበት መንገድ የፈጸምናቸውን ስህተቶች ደግሞ ተመካክሮ በማረም እንጂ የሚጋጩ ፍላጎቶችን በመጋለብ አይደለም፡፡

ዶ/ር መረራ ጉዲና በቅርቡ ከአንድ የመገናኛ ብዙሃን ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ፤ ‹‹ሟርተኛ እንዳትሉኝ እንጂ በእጃችን ላይ ሊፈነዱ የሚችሉ በርካታ ፈንጂዎች አሉ፡፡ የሚጋጩ ህልሞች ያላቸው ወገኖች፤ የየራሳቸውን ፈረሶች እየጋለቡ ነው፡፡ ሐገሪቱ ከአደጋ መዳን የምትችለው በኢትዮጵያ አንድነትና በዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የጋራ አመለካከት ይዘን፣ በመከባበርና በመቻቻል መሥራት ከቻልን ብቻ ነው›› ብለው ነበር፡፡ መፍትሔው ይኸው ነው፡፡

መገንጠልን ማስፈራሪያና የኢትዮጵያ አንድነት ይጠቅመናል የሚሉ ሰዎች መግረፊያ አለንጋ ማድረግ አይቻልም፡፡ የኢትዮጵያ አንድነት የሁላችንም ህልውና የተንጠለጠበት ወሳኝ አጀንዳ እንጂ የተወሰኑ የህዝብ ክፍሎች የተለየ ጥቅም ማስጠበቂያ መፈክር አይደለም፡፡ የሐገራዊ አንድነት ጉዳይ ዘላቂ የብሔር-ብሔረሰቦችን ጥቅምን በማረጋገጥ ስሌት የሚታይ የሁላችንም ጉዳይ እንጂ ‹‹ያለፈው ስርዓት ናፋቂዎች፣ የአማራ ገዢ መደቦችና የትምክህተኞች›› የፖለቲካ መፈክር አድርገን ከወሰድነው እንሳሳታለን፡፡ አሁን ብዙ ነገሮች ተለውጠዋል፡፡ የክልሎች የአስተዳደር ወሰንን እንደ ድንበር የመመልከት ዝንባሌ መጠናከሩን ልብ ማለት አለብን፡፡ ‹‹እኔ ብፈልግ ዛሬ ኦሮሚያን ማስገንጠል እችላለሁ›› የሚሉን ሰዎች፤ የመገንጠልን ጥያቄ ከህዝቡ መብት መከበር አንጻር ሳይሆን ከእነሱ መፈለግ – አለመፈለግ አንጻር የሚመለከቱት መሆኑንም ያረጋግጥልናል፡፡ የህገ መንግስቱን ስርዓት ተከትሎ ሊስተናገድ የሚገባው ጥያቄ መሆኑን አለመቀበላቸው ሳይሆን፤ ህዝቡ እንደ ጠረጴዛ ሰዓት በፈለጉት ጊዜ ሊያስጮሁት የሚችሉት ግዑዝ ነገር እንጂ ከጥቅሙ ተነስቶ ለመወሰን የሚችል አስተዋይ አካል አድርገው አለማየታቸው ቅር ያሰኛል፡፡

የኦሮሞ ህዝብ እንኳን ሐገራዊ ጉዳይን ያህል ትልቅ ነገር ቀርቶ ጠንከር ያለ የቤተሰብ ጉዳይ ሲገጥመው፤ ‹‹ሐቡልቱ ዱቢ›› (ነገር ይደር) ብሎ መክሮ እና በደንብ አስተውሎ የመወሰን ድንቅ ባህል ያለው ህዝብ ነው፡፡

እነዚህ ሰዎች በፖለቲካዊ ትክክኛነት ስሌት ‹‹ይህን መወሰን የሚችለው ህዝቡ ነው፡፡ እኔ ህዝቡን ተክቼ ለመወሰን አልችልም›› የሚል ተራ ጥንቃቄ ማድረግ የቸገራቸው ለምን እንደሆነ ባላውቅም፤ ‹‹እኔ ብፈልግ ዛሬ ኦሮሚያን ማስገንጠል እችላለሁ›› የሚለው ንግግራቸው፤ ከሮማው ንጉሥ ከኔሮ ዝነኛ አባባሎች መዝገብ ሊገባ የሚችል ብሂል ነው።  የዳኒሽ ፈላስፋ ሶረን ኬርኬጋርድ፤ ‹‹የሞኝነት መንገድ ሁለት ነው፡፡ አንድም፤ ውሸት የሆነውን ነገር ማመን፤ አንድም እውነት የሆነውን ነገር አምኖ ለመቀበል አለመፍቀድ ነው›› (There are two ways to be fooled፡፡ One is to believe what is isn’t true. The other is to refuse to believe what is true)፡፡ እንዲያ እንጂ ነው። የመገንጠል ጥያቄ በሶማሌ ክልል ከተጠያቂነት መሸሻ ሲደረግም አይተናል፡፡ ካለፉት ዓመታት ልምዳችን ብዙ ተምረናል፡፡ ‹‹ሐቡልቱ ዱቢ›› ብዬ የተውኩት ነገር አለኝ፡፡ የሣምንት ሰው ይበለን፡፡

Filed in: Amharic