>
10:45 am - Sunday May 22, 2022

የወያኔ መልክ ይጥፋ ....... (መስከረም አበራ)

የወያኔ መልክ ይጥፋ …….
መስከረም አበራ
ጭራሽ የፖሊስ መኮንን የሆኑ ሰውየ ያሰርናቸው ህገመንግስት ስለጣሱ ነው፤እነሱ ህገመንግስት ሲጥሱ እኛም ጥሰን አስረናቸዋል የሚል የመኪና ተራ መልስ ሰጥተዋል! ህግ የጣሰ ህግፊት የሚያቀርብ የህግ አካል የህገወጥነት ፉክክር ውስጥ የገባ የሚያስመስለው የክስ ምክንያት ስለሌለው ግን ደግሞ መንግስትነቱን ለማስረገጥ፣አንዱን እሹሩሩ ለማለት ሌላውን ማንገላታት ስላስፈለገ ነው!!!
አብይ ወደ ስልጣን ሲመጡ እስረኛ ፍቱልን ብለን የምንጮህበት ዘመን የተዘጋ መስሎኝ ነበር፡፡በበኩሌ ወያኔ ሰይጣን እስኪመስለኝ ድረስ የሚቀፈኝ ዜጎችን እያፈሰ በየእስርቤቱ ማጎሩ፣አጉሮም በእስርቤት የሚያደርገውን አረሜያዊነት ስሰማ ነው፡፡ ይህ ማለት ወያኔ ጥፋቱ ይህ ብቻ ነው ማለት አይደለም፡፡ሰዎችን በየእስርቤቱ የሚያንገላታው ሌላውን ብልግናውን ያለ ጠያቂ ለማስኬድ ነው፡፡ ወያኔ ሁለንተናዊ ብልግናው እንዳይስተጓጎል  ሰውን እስር ቤት አጉሮ ጥፍር ከመንቀል ታርዶ እንደሚገፈፍ እንስሳ ዘቅዝቆ ሰቅሎ የሰው ልጅ ፈርስ በአፉ እስኪመጣ ድረስ  የሚያደርገው ቃላት የማይገልፁት እርኩሰት ነው፡፡
ለወያኔ ይቅርታ የማይታሰብ የሆነው የሰውን ልጅ አስሮ የሰው ፍጡር ይችለዋል የማይባል እርኩሰት መፈፀሙን እንደ ጉብዝና ቆጥሮ መመፃደቁ ነው፡፡ በአንፃሩ የዶ/ር አብይን መንግስት ወያኔን በጠላንበት መጥላት ልክ የወደድነው የንፁሃን ወገኖቻችን (ሁሉንም ባይሆንም፤አሁንም በትግራይ እስርቤት የሚሰቃዩ ታሳሪዎች አሉና)የሃሰት የእስር ሰንሰለት በጥሶ ከዘመዶቻቸው ስላገናኘ ነው እንጅ ያቀረበው ርዕዮተ-ዓለም አማሎን አይደለም፡፡
 ይህን መንግስት እንደወደድነው እንድንሰነብት ሌላ የምንወድበት ምክንያቶች ሊጨመርልን ይገባል እንጅ ጭራሽ የወደድንበትን ምክንያት ራሱን  ማጣት የለብንም፡፡የጠ/ሚ አብይን መንግስት የወደድነው እስረኛ ስለፈታም ወደፊትም ያለ ተጨባጭ ምክንያት አላስርም ሲል ስለማለ ስለተገዘተ ነው፡፡ ይህን አምነን ነው ብዙ እየታዘብን እንኳን አፋችንን ይዘን ፋታ እንስጥ ብለን የተቀመጥነው፡፡ የተናገረው የአፉ ቃል ከጆሯችን ሳይርቅ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ያፍርድቤት ትዕዛዝ እያፈሱ ማሰር፣አሳሪም ዳኛም ሆኖ የልጆቹ ጥፋት በፍርድቤት ሳይረጋገጥ እንዲሁ ስልጠና ያስፈልጋቸዋል እና ወደ በረሃ ይውረዱ ብሎ ማጎር እጅግ አስቆጭ ጉዳይ ነው፡፡
የታሰሩት ልጆች በየትኛው ፍርድቤት ጥፋተኛ ተብለው ነው ያልታወቀ ቦታ ተወስደው የሚቀጡት? ወይስ መብትን ለማስከበር ግር ብሎ መበጥበጥ ያስፈልጋል? እንደ ግመል በአንድ ሰው ተነድቶ አለመበጥበጥ መልሱ የወንጀለኛ ጦስ ወስዶ መታሰር ነው ያለው ማን ነው? ይህ ነገር ማንን ለማስደሰት እንደተደረገ እናውቃለን፡፡ለግልፍተኛ ማብረጃ ንፁሃንን ማንገላታት ሁለቱንም የሚያሳጣ አጉልነት ነው! ስልጠና ካስፈለገ ማን ስልጠና እንደሚያስፈልገው አሳሪዎቹም አያጡትም፡፡
ጭራሽ የፖሊስ መኮንን የሆኑ ሰውየ ያሰርናቸው ህገመንግስት ስለጣሱ ነው፤እነሱ ህገመንግስት ሲጥሱ እኛም ጥሰን አስረናቸዋል የሚል የመኪና ተራ መልስ ሰጥተዋል! ህግ የጣሰ ህግ ፊት የሚያቀርብ የህግ አካል የህገ ወጥነት ፉክክር ውስጥ የገባ የሚያስመስለው የክስ ምክንያት ስለለለው ግን ደግሞ መንግስትነቱን ለማስረገጥ፣ አንዱን እሹሩሩ ለማለት ሌላውን ማንገላታት ስላስፈለገ ነው፡፡
ይህ የወያኔ መልክ ነው! የተንኮል እና ዘረኝነት ፖለቲካ ሰልችቶን ነው ቢቸግረን ከራሱ ከአረመኔው ኢህአዴግ መንደር እንኳን ለውጥ ይመጣ ይሆን ብለን ያማተርነው፡፡ በበኩሌ ይህን መቀበል እጅግ ፈተናየ ሆኖ ቆይቷል፤ እንዲህ ያሉ ነገሮች ደግሞ ተስፋ ማድረግን በተስፋ መቁረጥ የሚተካ ነው….. ቃል በተግባር ይፈተናል፤ ዝም ብለን አናስርም ያላችሁትን ቃላችሁን ስጋ ለብሶ እንየው፤ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ፍቱልን!
Filed in: Amharic