>

በሕገ - ወጥ እስሩ መንግስት የፈፀማቸው ያልተገቡ ተግባራት መካከል ጥቂቶቹ :- (ጌታቸው አሰፋ)

በሕገ – ወጥ እስሩ መንግስት የፈፀማቸው ያልተገቡ ተግባራት መካከል ጥቂቶቹ :-
ጌታቸው አሰፋ
1) አድሎ ተሰርቷል:_ቄሮ ዋጋ ከፍሏል። ከሌሎች ጋር ሆኖ ለከፈለው ዋጋ ምስጋና ይገባዋል። ቄሮ ማለት ወጣት ነው። ቄሮን በየ አደባባዩ እያሞገሱ እና እያወደሱ የአዲስ አበባን ወጣት ማጎር ግን ግልፅ አድሎአዊነት ነው። በቡራዩ ለተፈፀመው በይፋ “ቄሮ አይደለም” ብሎ የተከላከለ መንግስት፣ የአዲስ አበባ ወጣቶችን ከተማ ውስጥ ይህ ነው የሚባል ሕገ ወጥ ነገር ሳይሰራ በጅምላ አስሯቸዋል።
2) ስም ማጥፋት ተፈፅሟል:_መንግስት ሲጋራ፣ መጠጥና ሺሻን አልከለከለም። በራሱ ቴሌቪዥን ትልቁን የማስታወቂያ ሰዓት የሚይዘው የመጣጥ ማስታወቂያ ነው። 5 ሚሊዮን ነፃ መጠጥ አለ እየተባለ በሚዲያ እየተለፈፈ መንግስት ስለ ሱስ ያገባኛል ቢል ምፀት ነው።  ይህን የሚያደርገው መንግስት ግን ለወጣቶች ማሰሪያ የፈለገው ሰበብ ሱስን ነው። በዚህም የወጣቶችን ስም አጉድፏል። በፖለቲካ ምክንያት የታሰሩትን ወጣቶች ስም አጉድፏል። የአዲስ አበባን ብቻ ሳይሆን ከጎንደር፣ ደሴና አርባምንጭ ድረስ መጥተው በሚል የሕዝብን ስም አጥፍቷል።
3) ለሕዝብ የሀሰት መረጃ አሰራጭቷል:_ መንግስት ለሕዝብ ግልፅና ታማኝ መሆን ነበረበት። ሆኖም በአዲስ አበባ ወጣቶች ጉዳይ መንግስት ለሕዝብ የሀሰት መረጃ ሰጥቷል። ወጣቶች የታሰሩት የአዲስ አበባን ፖለቲካ ለመቆጣጠር ሆኖ እያለ የሀሰት ምክንያት ሰጥቷል።
4) ቃሉን አጥፏል:_ የዶክተር አብይ አህመድ መንግስት እስረኞችን ሲፈታ “ከአሁን በኋላ አሳዳጅና ተሳዳጅ አንሆንም” ብሎ ነበር። ነገር ግን ወጣቶችን እያሳደደ አስሯል። የዶክተር አብይ አህመድ መንግስት “አጣርተን እናስራለን እንጅ አስረን አናጣራም” ብሎ ነበር። የሆነው ግን ተቃራኒው ነው። አስሮ በመቅጣት ላይ ነው።
5) ክህደት ፈፅሟል:_ የመደመሩ ፖለቲካ ሲጀምር፣ በይፋ “ተደምሬያለሁ” ያለው የአዲስ አበባ ሕዝብ ነው። የሰኔ 16 ፈንጅ ፍንዳታ ቀን ፈንጅ ቀልሞ ዶክተር አብይ አህመድን ያተረፈው አዲስ አበባ የነበረ ሕዝብና ወጣት ነው። የቆሰለው ሕዝብ ነው። ከፍንዳታው በኋላ ደም በመለገስና በሌሎቹም ጉዳዮች ከአብይ አህመድና መንግስቱ ጎን የቆመው የአዲስ አበባ ወጣት ነው። ይህ ወጣት ተግሳፅ እንኳ ባልተገባው። ላደረገው መልካም ነገር ሁሉ መልሱ አፈሳና ያልታወቀ ቦታ ማሰር የአዲስ አበባ ወጣትና ሕዝብ  ላይ የተፈፀመ ትልቅ ክህደት ነው!
6) ሕገ መንግስቱ በግልፅ ጥሷል:_ ዜጎች ከታሰሩም መታሰር ያለባቸው በፍርድ ቤት ትዕዛዝ ነው፣ ከታሰሩበት ጊዜ ጀምሮ በ48 ሰዓት ፍርድ ቤት መቅረብ ነበረባቸው፣ ከቤተሰቦቻቸው ጋር መገናኘት ነበረባቸው፣ ጠበቃ ማግኘት ነበረባቸው፣ በሕግ እውቅና ባለው ተቋም መታሰር ነበረባቸው።  ምቹ ባልሆነ እና የቅጣት ወታደራዊ ካምፕ ለአካላቸውና ለሕይወታቸው አደገኛ  በመሆነ ሁኔታ ይገኛሉ። ይህ ሁሉ ግልፅ ሕገመንግስታዊ ጥሰት ነው!
7) መንግስት በማያገባው ገብቷል:_ የአዲስ አበባ ወጣቶች ወንጀል ፈፅመው ቢሆን እንኳ ወታደራዊ ቅጣትና ስልጠና የመስጠት መብት የለውም። የአዲስ አበባ ወጣቶች በሱስ ምክንያት አልታሰሩም እንጅ ምክንያቱ  ሱስ ቢሆን መንግስት አስሮ ገርፎ ከሱስ ያላቅቃል የሚል ግዴታም መብትም አልተሰጠውም። ለፖለቲካዊ ምክንያቱ የአዲስ አበባን ወጣት አስሬ ከሱስ ነፃ አደርገዋለሁ የሚል የሀሰት መረጃ ሰጥቶ፣ የማያገባውን፣ ደግሞ ሕገ መንግስቱን የጣሰ ሕገ ወጥ ተግባር እየፈፀመ ይገኛል!
Filed in: Amharic