>

ይድረስ  ለጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ (አንጋፋው አርቲስት ጌታቸው አብዲ)

ይድረስ  ለጠቅላይ ሚ/ር አብይ አህመድ።

 

አንጋፋው አርቲስት ጌታቸው አብዲ

ይህን አጭር መልክት ወይንም አቤቱታ እማቀርብልዎ በታላቅ አክብሮትና ትህትና ነው።
ለአንድ ሰው በህይወት ዘመኑ ሀብታም ወይም ደሀ ፣ ታዋቂ ወይንም ተራ ዜጋ የመሆን ጉዳይ ሳይሆን “ሰብአዊ” ክብሩ ከምንም በላይ ቅድሚያ ማግኘት ያለበት የመሆኑ ጉዳይ ለጥያቄ የሚቅርብ አለመሆኑ ይጠፋዎታል አልልም።። በበትረ ስልጣንዎ የቆዩበት ጊዜ በርካታ ወራት በመሆን ደረጃ ላይ የደረሰ ባይሆንም በውስጤ ጥያቄ የጫሩብኝ ጉዳዮች ግን በዝምታ እንዳላልፍ ስላስገደዱኝ፣ እነሆ በአቤቱታ መልክ ላቀርብልዎ ወሰንኩ።ጥያቄዎችን ያነሳሁት እርስዎ ምንም አልሰሩም ለማለት ፈልጌ አይደለም።እንዲያውም እኔ በበኩሌ ተቀብሮ ቀረ የተባለውን ኢትዮጵያዊነት ከተቀበረበት ያነሱ ታላቅ ሰው መሆንዎንና ጥላቻን በፍቅር ቂምን በይቅርታ እንድንተገብር ለኢትዮጵያ ሕዝብ በግልፅ ያስተላለፋ መሪ መሆንዎትን በአክብሮት እናገራለሁ። ይህንን በማድረግዎ ብቻ በእጭር ጊዚያት የሕዝብ ተቀባይንት ያገኙ የሀገር መሪ መሆንዎ አይካድም። ይህ ሆኖ ሳለ ያለአግባብ በመናገሻ ከተማዎ የአዲስ አበባ ወጣቶች እየታፈሱ ታስረው ሲማቅቁ እየተሰማ የወሰዱት እርምጃ በይፋ የታየበት ሁኔታ ሲከሰት ግን አልታየም። እንቅልፍ ይዎስድዎ ይሆንን? ሰብእዊ ክብር እኮ ከነፃነት አይነጠልም። ይህ ለርስዎ ይጠፋዎታል ብየ አይደለም። በዚህ በእጭር ጊዜም ሁሉንም ባንድ ሌሊት አስተካክለው ይጨርሱ እያሉ እንደሚተችዎት እንዳንድ ስዎች እኔም ልተችዎ አይደለም። ይገባኛል። “ሮም በአንድ ሌሊት አልተገነባችም” ግን እኮ በአመራር ቅድሚያ ትኩረት የሚሰጠውና እንደ ህዝብ ጥያቄው አጣዳፊነት ውሳኔና ድርጊት የሚጠይቁ ክስተቶች ሊኖሩ እንደሚችሉ ለርስዎ አይነግሩም። እንበል አያድርስብንና፣ ነገ ሀገር ወራሪ ጠላት ድንበር ጥሶ ቢንቀሳቀስ ይህን የሀገር ጉዳይ ለመከላከል ሌላውን ሁሉ እርግፍ አድርገው መከላከያ ሀይልዎ ላይ አተኩረው ይንቀሳቀሳሉ እንጂ ፣ የለም የለም ቀደም ተብሎ ፕሮግራም የተያዘለት ጉብኝት አለብኝ ብለው ወደ ጉብኝትዎ ይሄዳሉን? አይመስለኝም ልበል። 


1: በሀገራችን ሰሜናዊ ክፍለ ሀገር ውብና ታላቅ ታዋሽነት ያለው ህብረ ውህደቱ የኢትዮጵያ ጉራማይሌነትን የሚያረጋግጠው ጀግናው የራያ ህዝብ፣” ትህነግ” በተባለ ወራሪ ሽብርተኛ አካል፣ ህፃናት ሳይቀሩ ትግርኛ “” ብቻ”” ተናገሩ እየተባሉ ሲደበደቡ፣ሲታሰሩና እንደ እንስሳ እየታደነ ወጣቱ ሲገደል ሰምተው ዝምታን መረጡ እንዳልል የሚሠሩትን ወይም ያከናወኑትን አብይ እለታዊ ተግባራት ማወቂያ መንገድ ሁሉ ውሱን በመሆኑ በድፍረት አይንዎን ጨፈኑ ለማለት ባልደፍርም፣ ከላይ ስለጠቀስኩት እኩይ ፋሽስታዊ የትህነግ ተግባር
እንደመሪ ምርር ብለው እዝነው የወሰዱት አፋዊ እንኩዋን ማሳሰቢያ(አምልጦኝ ከሆነ ይቅርታ)
ባለመስማቴ አዝናለሁ። ተኝተው አድረውም ከሆነ የዋህ ልብ እንዳለው እረዳለሁኝ።


2: የኢትዬጵያ የክብር አርማ የሆነው “አየርመንገዳችን” ውስጥ ያለው አሳፋሪ፣አዋራጅና መላ ሀቀኛ ኢትዮጵያዊያንን ያስደመመው የካፒቴን ዮሀንስ ተስፋዬ እና መሰል የሥራ ባልደረቦቹ ከሥራ ገበታ መፈንቅል ጉዳይ ይታይዎታልን? ከፓይለትነት ወደ ግብርና መሄድ ምክንያቱ የሰብአዊ ክብር መደፈርና ወደባርነት ደረጃ ወርዶ የመረገጡ ታሪክ (በታላቅዎ ኢትዮጵያ ምድር) ምን ይሰማዎታል? አውቃለሁ ዶ/ር አብይ እነዚህና ሌሎችን ችግሮች ሁሉ እርስዎ ብቻዎን እንዲፈቱዋቸው በማለት አይደለም የማቀርበው ። እርስዎ አንድ ሰው ነዎት። መንግስትዎ ግን ስፊ የሀላፊነት የመወጣት /responsibility/ሥልጣን የተሽከሙ ተቅዋማት በእርስዎ ሥራ አከፋፋይነት ከታዘዙ እርስዎ በማእከልነት አየተቆጣጠሩ በርካታ ችግሮች ሊፈቱ እንደሚቻልዎ ያጡታል ብየ ሳይሆን እንደው ውስጤ የነደደበትን ላወሳልዎ ፈልጌ ነው።


3: ባለፈው ወቅት 


የጦር ሀይል አባላት ተሰብስበው ወደ ቤተመንግስት መጥተው ነበር ። ጥያቄ ለማቅረብ ወይም አቤቱታ ለማስማት በሚል። ይሁን መልካም። ነገር ግን የጦሩ አባላቱ የእዝ ሠንሰለት (chain of command)የላቸውምን? ገና ከካምፓቸው ዉስጥ ስብሰባ እያካሄዱ አስተባባሪያቸውን ሲመርጡ የርስዎ ደህንነት ምንም አያውቅም ነበርን?፣ ያም አልፎ በአደባባይ በገሀድ ቤተ መንግስትዎ ሲደርሱ ደህነትዎ አያምቀውም ነበርን? የወታደሮቹ አመጣጥ ህገ ወጥና ስርአትን የተከተለ አልነበረም ።
የርስዎ ሁኔታውን በዘዴና በጥበብ መወጣትዎ የማደንቀው መሆኑን እየገለጥኩልዎ ግና በሌላ
መልኩ አስቀድሞ የተዘጋጀ ድራማ ቢመድለኝም የሁኔታው አደገኛነት ሳይጠቅስ ማለፍ አይቻልም።
ይኸው ነው መልክቴ። ጉዳዩን ይመልከቱት ተመልክተውትም ተግባርዎ እንደሚቀጥልም ተስፋ አደርጋለሁ። እያልኩ ለርስዎ ያለኝን አክብሮት እየገለጥኩ እግዚአብሔር ለኢትዮጵያ መርጦታልና ይበርቱ!!!
ሌላ ምን ይባላል ። “አውቆ የተኛን ቢቀሰቅሱት አይሰማም ” ይላል ያገሬ ሰው” እግዚአብሔር ኢትዪጵያንና ሕዝብዋን ይባርክ!!!!


እርስዎንና መላ ቤተሰብዎንም ይባርክ ።
“ኢትዮጵያ እጆችዋን ወደ እግዚአብሔር ትዘረጋለች”
መዝሙረ ዳዊት ም 68 ቁ 31
እናምናለን እውንም ይሆናል።
ጌታቸው እብዲ

Filed in: Amharic