>

እባቡ ቆዳ ገፈፈ እንጂ አልሞተም!!! (ታምሩ ተመስገን)

እባቡ ቆዳ ገፈፈ እንጂ አልሞተም!!!
ታምሩ ተመስገን
ኢህአዴግ ቆዳ ገፈፈ እንጂ ከነመርዙ አልሞተም፡፡
“ፖለቲካ ላይ ቋሚ ጥቅም እንጂ ቋሚ ጠላት የለም” ትናንት ወዳጄ የነበረ ዛሬ ጥቅሜን የማያስከብርልኝ ከሆነ ጠላቴ የማይሆንበት ምንም ምክንያት የለም፡፡ መደመሬ ኪሳራው ካመዘነም ተግበስብሼ አልደመርም መንገዴን እለያለሁ እንጂ፡፡ መንቃት ባለብኝ ሰዓት ነቅቻለሁ፡፡
.
በጣና ላይ ከሚነሱ ትኩሳቶች መካከል ቀዳሚውን ድርሻ የሚይዘው “ማዕከላዊ መንግስት እስካሁን ድረስ ለምንድን ነው ጣናን የማይታደው? ጣና እኮ የኢትዮጲያ ብቻ ሳይሆን የአለም ሁሉ ሀብት ነው ሲባል በዩኔስኮ ተመዝገቧል፡፡ ማዕከላዊ መንግስት ለምን ዝምታን መረጠ?”
.
እኔ ግን እንዲህ እላለሁ እንኳን ለጣና ዛሬ ለታመመው ጎንደር ላይ ለሀበሻ አንድነት ትናንት ለወደቀው መይሳው ካሳ መቅደላ ላይ የተደረገለት እንክብካቤ ከቁራጭ ቆርቆሮ መቼ ተሻገረና፡፡ ሊያውም “አፄ ቴዎድሮስ ራሳቸውን ያጠፉበት ቦታ” በሚል ታሪክ ጎራጅ አጉራሽን ነካሽ ፁሁፍ፡፡
ማዕከላው መንግስት ለምን ጣና ላይ ዝምታን እንዳበዛ አንዲት ብቻ ማሳያ ልጥቀስ፡፡ የኢህድሪ ኢትዮጵያ ሕዝባዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፑብሊክ  ጠቅላይ ሚኒስትር የነበሩት ፍቅረሥላሴ ወግደረስ የጣና በለስ ፕሮጀክትን አስመልክተው ‘እኛና አብዮቱ በፍቅረሥላሴ ወግደረስ ነጻነት’ በሚለው መፅሀፋቸው የፃፉትን ከዚህ ዝቅ ብየ ላስነብባችሁ…
.
“የግብፆችን ጠላትነትና ተቃውሞ በማጤን የጣና በለስ ስራ በጣና ኃይቅ ዙሪያ (ከፍተኛው የዓባይ ወንዝ መነሻ) የዓባይን ወንዝ ገድቦ የኃይቁን ውሃ ከፍ በማድረግና ውሃውን በቦይ እንዲያልፍና ተሽከርካሪዎች ተጠቅሞ የሚወርደውን ውሃ ለመስኖ እርሻ መጠቀም ነበር። እቅዱ ሙሉ ስራ ላይ ሲውል በዚህ አካባቢ ብቻ አንድ ሚሊዮን ሄክታር መሬት ለመስኖ እርሻ ለማዋል ነበር። የጣና በለስ “በአስደሳች ሁኔታ ተጀመረ። ከጣልያን አገር አግሮኖሚስቶች (የእርሻ ባለሞያዎች)፤ የተለያዩ የቴክኒክ እውቀት ያላቸው በለሞያዎች መጡ። ኢትዮጵያውያን የእርሻ ባለሞያዎችና በሺህ የሚቆጠሩ ሠራተኞች ከጣልያኖች ጋር ተቀናጅተው እንዲሰሩ ተደረገ። የአፈር ምርመራ፤ የመስኖ መሥመር ዝርጋታ፤ የሙከራ ጣቢያዎች ግንባታ፤ የውሃ፤የኤሌክትሪክና የቴሌፎን ዝርጋታ ስራ ተጀመረ። የእርሻው አካባቢ ተቀየሰ። ወደፊት ከተማ ሊሆኑ የሚችሉ ጣቢያዎች ተቆረቆሩ። የመንገድ ግንባታ በየአቅጣጫው ተጀመረ። ከድህነትና ከረሃብ የመገላገል ተስፋችን ለመለመ። ኢትዮጵያ የምስራቅ አፍሪካ የውሃ ምንጭ እየተባለች በመስኖ መጠቀም ተስኗት ለዘመናት በረሃብ መጠበሷ ያከትማል የሚል ተስፋ አደረብን።” አስደናቂ ዘመናዊና የተያያዘ የልማት ስራ መካሄድ ጀመረ ማለት ነው። በአፄ ኃይለ ሥላሴ ዘመነ መንግሥት ይኼን የሚመስሉ እቅዶችና ጅምሮች ነበሩ። የጣናን ኃይቅና የዓባይን ወንዝ በጥናትና አግባብ ባለው እቅድ በስፋት ሲሰራ የመጀመሪያው መሆኑ ነው። ከዚያስ ምን ተከተለ? “እኛ እንደሰት እንጅ ጠላቶቻችን (ግብፆች፤ ሻቢያ፤ ህወሓት) በጣና በለስ ፕሮጀክት ቅሬታ ተሰምቷቸዋል። በዚህም የተነሳ ህወሓት አካባቢውን በያዘበት ጊዜ እንዳልሆነ አድርጎ ፕሮጀክቱን አፈራረሰ። ለፕሮጀክቱ ስራ ይጠቅማሉ ተብለው የመጡትን የግንባታና የእርሻ መሣሪያዎች በሙሉ እየጫኑ ወደሚፈልጉበት አካባቢ አጓጓዙ። ጠቃሚ መስሎ የታየውን ማንኛውንም እቃ እየነቀለ ወሰደ። ዘመናዊ የሕክምና መሣሪያዎች ተደራጅቶ የተቋቋመውን ሆስፒታል አፈራረሰ። የኤክስሬይና ዘመናዊ የምርመራ መሠራሪያዎችን ነቃቅሎ አጓጓዘ። የተዘርጉ ቧንቧዎች ሳይቀሩ ተነቃቅለው ተወሰዱ።
..
በህወሀት የሚመራው ኢህአዴግ መንግስት ጣና በለስን ካፈራረሰና ከ 15 ዓመት በኋላ ግን “የጣና በለስ ኤሌክትሪክ ኃይል ግድብን” ለመገንባት እንቅስቃሴ መጀመሩን አስታወቀ፡፡ ይሄው ግድብ የቀድሞው የጣና በለስ የተቀናጀ ፕሮጀክት አንድ አካል ነበር:: የኤሌክትሪክ ኃይል ማመንጫ መሰራቱ ይበል የሚያሰኝ ቢሆንም ከግድቡ የሚወጣውን ውሃ ማልማት በሚል ምክንያት ጣና በለስ ሸለቆ አርሷአደር ላይ ሌላ መከራ አመጣ:: ይሄውም ይህ የጣናበለስ እቅድ እንደቀድሞው አርሷደሩን ተጠቃሚ መሰረትና ማዕከል ባደረገ ሁኔታ ሳይሆን አርሷደሩን አንስቶ በ75 ሺህ ሄክታር መሬት ላይ መንግስት የስኳር እርሻና ፋብሪካ በመትከትል አካባቢውን ለስኳር እንደሚፈልገው በማሳወቅ በሺዎች የሚቆጠሩ አርሷደሮችን ለዘመናት ከኖሩበት ቦታ ማፈናቀሉን ቀጠለ:: በተለይም እንደፈንድቃ ከተማ ያሉ አርሷደሮች ሙሉ ለሙሉ በሚባል ሁኔታ ለዘመናት ከኖሩበት የአያት ቅድመአያቶቻቸው ርስት ተነቅለው ፣ ትርፍ አምራች የነበሩት አርሶአደሮች አገዳ ቆራጭ እንዲሆኑ ተደርገዋል:: ይሄው ፕሮጀክትም ወደ አለፋና መተማ አድማሱን በማስፋት ከአለፋ በርካታ ቀበሌዎች ውስጥ ያሉ አርሷደሮች እየተነሱ ነው::
ይበልጥ የሚያስዝነው ግን አንዱን አንስቶ ሌላውን ለመትከል የሚደረገው ሩጫ ነው:: እንደ ፈንድቃ ከተማ ላይ ይኖሩ የነበሩ አርሷደሮች ከተነሱ በኋላ የስኳር ፕሮጀቱን ሊሰራ ነው የተባለው ሜቴክ እጅግ በሚገርም ሁኔታ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎችን ከትግራይ አምጥቶ ማፍሰሱ ነው:: በመሰረቱ ኢትዮጵያ የእትዮጵያውያን ናት:: ማንኛውም ኢትዮጵያዊ የትም ሄዶ ሰርቶ መኖር አለበት::  ነገር ግን ለዘመናት የኖረውን አርሷደር በልማት ተነሺ ስም አፈናቅሎ ከሌላ ቦታ ሌሎች አርሷደሮችን አምጥቶ ማስፈር ግን ምን ማለት ነው? ማንም ሄዶ ማረጋገጥ በሚችለው መልኩ አሁን ጣና በለስ ላይ ያለው ሁኔታ ነባሩን አርሷደር በልማት ስም አንስቶ በሌላ የመተካትና የአካባቢውን ማህበረሰባዊ ገፅታ (demography) የመቀየር ከፍተኛ ስራ እየተካሄደ ነው፡፡
ይላል የመፅሀፉ ግንጣይ…
.
እና ዛሬም ጣናን ማዕከላዊ መንግስት ካልታደገልን እንል ይሆን? በእውነቱ አሁን ያለው መንግስት ላሊበላ ጧት አስቀድሰን ከሰዓት ፍርስራሽ ቢሆን የሚደንቀው ከመሰለን ተሳስተናል፡፡ የሚገደው ከሆነ የታለ? ዛሬም እንቅልፍ ላይ ነን ወገን? ይልቁንስ የክልሉ መንግስትና ምሁራኑ ተደራጅተው መፍትሄ እንዲያበጁ መመካከሩ ይሻላል ባይ ነኝ፡፡  ጣናን ለመታደግ ጥቅምት 16 2017 BBC በዶክተር ሰለሞን የተጠናውንና በገፁ ላይ ያስነበበው መተግበር እንደአንድ መፍትሄ ይመስለኛል፡፡
ለማሳያ የጣናን ጉዳይ አነሳሁ እንጂ አጠቃላይ መንግስት አካሄዱ እየተንሸዋረረ ነው፡፡ ለምሳሌ
1. ቅርሶቻችን ምልክቶቻችን ታሪኮቻችን ሲጠፉ እያየ ዝምታን የመረጠ መንግስት አለን
2. የአዲስ አበባ ወጣት ታፍሶ ወደ ጦላይ ሲጋዝ አበጃችሁ ያለ መንግስት አለን
3. የራያ ወጣት በትህነግ ሲሰቃይ እያየ እየሰማ ጆሮ ዳባ ልበስ ያለ መንግስት አለን
4. በመደመር ቁማር የሚፈልገው ቦታ በፈለገው መንገድ ራሱን እያደላደለ ያለ መንግስት አለን
5. አንድ ቦታ የቤት ስራ በጥንቃቄና በከፍተኛ ትኩረት እየተሰራ እንደሚገኝ እየሸተተኝ ነው
6. በምኒስትር ሹመት ላይ እንኳን ግልፅ ሿሿ ተሰርቷል
እንግዲህ አካሄዳቸው እንደዚህ ከሆነ፤ አቋማቸው ሲሾም ያልበላ ሲሻር ይቆጨዋል ከሆነ ኢህአዴግ እንደ እባብ ቆዳውን ገፈፈ እንጂ ከነመርዙ አልሞተም ለማለት እገደዳለሁ፡፡ መልክ ቀየረ እንጂ ልብ አልቀየረም፡፡
መታወቅ ያለበት አንኳር ጉዳይ እኛም ፍቅር አንድነት ብለን እንጅ እኛ እምንለው፣ መመከቻ ሰፊ ትክሻ ያለው ጎጥ አጠን አይደለም፡፡ መምረጣችንን ግድ ካደረጋችሁብን ግን እናስብበታለን፡፡
.
ይህን ስለፃፍኩ መደራጀት ለማጥቃት ብቻ የሚመስልህ ካለህ መንገዱን ጨርቅ ያድርግልህ፡፡ መደራጀት ለመከላከለም ይሆናል፡፡ ወንድማለም የአዲስ አበባ ወጣት ስላልተደራጀ መቀለጃ እንደሆነ አትርሳ፡፡
Filed in: Amharic