አበበ ቶላ
“ኦሮሞ አትመስይም የሚሉኝ አሉ ኦሮሞ ምንድነው የሚመስለው…?” ስትል አንድ እህታችን በቁጭት ስትናገር OMN አሳየን…
ኦሮሞ የራሱ መገለጫ የሆነ ባህል አለው ብለሽ እየተከራከርሽ… ኦሮሞ ምንድነው የሚመስለው? ብሎ ሰውን ሆድ ማስባስ እና ራስም ቁጭት ውስጥ መግባት ቁጭትን ማባከን ነው… ፀጉርሽን የትግሬ ሹሩባ ወይም ደግሜ ፍሬንች ተሰርተሽ ኦሮሞ ነኝ ስትዩ “ኦሮሞ አትመስይም” መባልሽ ምንም አይገርምም።
ችግሩ ግን ባለፉት ግዜያት ፖለቲከኞቻችን ሁሉ ሃይላቸውን ለማደራጀት ሲሉ ይንቁናል ይገፉናል… ከዛም ላቅ ሲል በባርነት ሸጠውናል እያሉ ብሶት እየሸጡ ፖለቲካቸውን ሲያደልቡብን በመኖራቸው እያንዳንዷን አስተያየት ስንሰማ በመናቅ እና በመጠላት የተነገረን ይመስለናል። ለዚህ ያበቁን አክራሪ ብሄርተኞች ናቸው… (እግዚአብሄር የስራቸውን ይስጣቸው)
ኦቦሌቲ ቲያ እውነት እልሻለሁ ከፍ ያልሽ ነሽ እና የበታችነት ስሜት አይሰማሽ… ኦሮሞ አትመስይም… ስትባይ “እንዴ ለዛውም የሰላሌ… ለዛውም የወለጋ ለዛውም…” እያልሽ እያቆላመጥሽ ኮራ ብለሽ መናገር ስትችይ ስለምን ሆድ ባሰሽ… (ባንቺ አልፈርድም…)
ለምሳሌ እኔ እምኖርበት እንግሊዝ ውስጥ ብዙ ሰዎች “ኢትዮጵያዊ አትመስልም…” ብለውኝ ያውቃሉ። አንድም ቀን ኢትዮጵያዊ ምንድነው የሚመስለው? ብዬ ተሸማቅቄ አላውቅም ኮራ ብዬ ለዛውም ኩሩ ኢትዮጵያዊ ነኛ… ብዬ ነው የምመልስላቸው። “ኦሮሞ አትመስለኝም ነበርኮ…” ተብዬም አውቃለሁ ለዛውም “ኢጆሌ ሰላሌ ነኛ… አቡነ ጵጥሮስ የፈለቁበት፣ ትግራይ ድረስ ዘምቶ ጣሊያን እና ባንዳ ላይ ታላቅ ጀብድ የፈፀመው ህፃኑ አብቹ የፈለቀበት…” እያልኩ ሳስረዳ በኩራት እንጂ አንድም ቀን የበታችነት ስሜት ወይም ቁጭት አድሮብኝ አያውቅም። ምክንያቱም ስሰማ ያደኩት ሰላሌነትም ኦሮሞነትም ኢትዮጵያዊነትም ሰፈር ስትመጪ ራሱ የሽሮሜዳ ልጅነት ኩራት እንደሆነ እየተነገረኝ ነው ያደኩት።
ስለ አዲሳባ ስናስብ አዲሳባ ከቀን ቀን የራሷን ባህል እያዳበረች የመጣች ከተማ ናት።(ይሄ የየትኛውም ከተማ ባህርይ ነው)
ከዛ በመለስ ግን በተለይ ባለፉት ግዜያት የክፍለ ሃገር ልጆች አዲሳባ ሲመጡ በአነጋገራቸው በስማቸው በአለባበስ እና አመጋገብ ዘይቤያቸው ሳይቀር “ሙድ ይያዝባቸዋል” ብዙውን ግዜ የኦሮሞ ፖለቲከኞች ይሄንን የአዲሳቤ ሌሎችን የማግለል መጥፎ ባህል በኦሮሞ ላይ ብቻ እንደሚፈፀም በደል አድርገው እየቀሰቀሱ ቁጭት እና ብሶት እየዘሩ አባል እና ደጋፊ ሲሰበስቡ ኖረዋል። ይሄ አይነቱ ግራ ቀኙን ያላገናዘበ የብሶት ቅስቀሳ የኋላ የኋላ ውጤቱ አያምርም። ኦሮሞን ብቻ ለይቶ የሚያጠቃ ጠላት እንዳለ በመስበክ የምናገኘው ትርፍ የበታችነት ስሜትን በትውልዱ ውስጥ ማዳበር ነው!
እርግጥ ነው በተቃራኒው ደግሞ ኦሮምኛ ሙዚቃ ስትሰማ እንኳን ሲያገኝህ… “አንተ ለካ ዘረኛ ነህ…? ” የሚል ሸውራራ አመለካከት ያለው ሰው ይገጥማል ያሰው ስለ ዘረኝነት ያልገባው ምስኪን ከመሆን በዘለለ ለመገለል ስሜት የሚዳርግ መሆን የለበትም።
ባጠቃላይ ችግር አለ፤ ችግሩን ለመረዳትም ችግር አለ፤ ችግሩን ለመቅረፍ የምንሄድበት መንገድ ላይም ችግር አለ!
ነገሮችን በአንድ አቅጣጫ ብቻ ማየት መከራችንን ያረዝመዋል… እንትን የሆነው እንትን ስለሆነ ይሆናል፣ እንትን ስለሆነም ሊሆን ይችላል፣ እንትንንም መጠርጠር አይከፋም… እያሉ በተለያየ አቅጣጫ ማገናዘብ ይጠቅመናል!