>

ሸዋ የሌለበት ሴት የበዛበት አዲሱ ካቢኔ!!! (ያሬድ ጥበቡ)

ሸዋ የሌለበት ሴት የበዛበት አዲሱ ካቢኔ!!!
ያሬድ ጥበቡ
ዶክተር አቢይ አህመድ የኢትዮጵያን የሚኒስትሮች ምክርቤት በግማሹ በሴቶች በመሙላታቸው ደሰታውን የሚገልፀው ወንድ ብዙ ነው ። ለብዙ አስርተ ዓመታት ለሴቶች እኩልነት የተሟገትኩ በመሆኔና በትጥቅ ትግሉ ረጅም ዓመታትም የነበራቸውን የመንፈስም ሆነ የአካል ጥንካሬ ስላየሁ እንደብዙው የዓለም ወንድ በጉዳዩ ላይ ችግር የለኝም ። ዛሬ ግን ምስቅልቅል ስሜት ነው የተሰማኝ፣ የደስታም የስጋትም ።
ከዓለሙ ተለይተን እኛና ሩዋንዳ ብቻ ካቢኔዎቻችንን በሴቶች ማጋመሳችን፣ እውን የተሻለ ለሴቶች መብት ተቆርቋሪ በመሆናችን ነውን? ጡትመያዣቸውን ያቃጠሉ የሴት አርበኞች የሞሉባቸው የምእራብ ሃገራት በ200 ዓመታት የዴሞክራሲ ጉዞዋቸው ያላደረጉት ለምን ለኛ ቀለለን? ወይስ እንደ ክልል ፌዴራሊዝማችን ይሄኛውም ቤተሙከራ ይሆን?
አንድ ከአዲስአበባ ጉብኝቴ የታዘብኩት ነገር ቢኖር  የአቶ መለስ የመተካካት ፖሊሲ በሃገሩ ላይ ያረበበውን የወጣት ጊዜው የኛ ነው መንፈስ ነው ። ስለተማሩ፣ ስላጠኑ፣ ስለተዘጋጁ ወዘተ ሳይሆን ዝም ብሎ ወጣት በመሆናቸው ብቻ ሃገሩን ሊረከቡ የሚችሉ አይነት መዳፈር ነው ያየሁት ። የፌስቡክ መድረክም ላይ ይታያል። ሸበት ያለ ሰው ሁሉ በእድሜው ይዋረዳል፣ ይሰደባል ወዘተ። ይህ ፍፁም ውሸት የሆነ ስሜት ነው። የዛሬውም የሴቶች ሹመት እንደ ክልል ፌዴራሊዝሙና መተካካቱ የቤተሙከራ ጉዳይ እንዳይሆን ፍርሃት አለኝ ። አሁን ከሴትነቷ በላይ የመከላከያ ሚኒስትሯን ለዚህ ሹመት የሚያበቃት  ምን ይሆን? ያውም የከብት አርቢዎች እኩልነት በተንሰራፋበት የአፋር ባህል ያደገች ሴት፣ የሥልጣን ተዋረድና ሹመት የሞት ሽረት ጉዳይ የሆነበትን የሩብ ሚሊዮን የጦር ሃይል የሚያስተዳድሩትን ጄኔራሎች የሚመራ ተቋም እንዴት አድርጋ ልትመራው ይሆን? ወይስ ጠቅላይ ሚኒስትሩ “መከላከያውን እኔ ራሴ እመራዋለሁ፣ በደከመችበት አግዛታለሁ” ብለው አስበው ይሆን? ከሁሉም በላይ ግን ሌላው ዓለም ይህን ሴቶችን የሥልጣን ቁንጮ ላይ የማውጣት ጉዳይ ለምን ሳይደፍረው ቀረ? ትምክህተኛ ስለሆነ ነው ማለት በጣም ቀላል መልስ ነው። ከዚህ የበለጠ ምክንያት ይኖራቸው ይሆን?
አንዳንዴ፣ አንድ ውሳኔ ስናደርግ፣ በተቃራኒው ባለመወሰናችን የምናጣውን ማሰብ ተገቢ ይመስለኛል ። በታሪካችን የቆየውን የትምህርት፣ የሥልጠና፣ የዝግጅት፣ የሥራ ልምድ ወዘተ ታሳቢ ስናደርግ፣ ለእያንዳንዷ ተሿሚ ሚኒስትር፣ ለቦታው የሚመጥኗት እንዲያውም የሚበልጧት ሌሎች 200 ወንዶች ይኖራሉ ብለን ብናስብ፣ ኢትዮጵያችን የነዚያን ትጉሃን ወይም አዋቂ ወንዶች ችሎታ አጥታለች ማለት ነው ። ይህ ምን ያህል ተገቢ ነው? ያዋጣል? ያበላል?
የምንወዳቸው ጠቅላይ ሚኒስትራችን ከሁለት ሳምንታት በሁዋላ የጀርመኗን ቻንስለር አንገላ መርክልን እንደሚያገኙ እናውቃለን ። የመርክልን ድጋፍና ፍቅርም ያስገኝ ይሆናል ይህ ሹመት። የፈረንጅ መያዶችንም ፍቅርና ድጋፍ እንዲሁ ። ግን የኢትዮጵያ ህዝብስ? ካቢኔው በግማሽ በሴቶች ቢሞላስ ተብሎ መጠየቅ፣ ቢያንስ አስቀድሞ በነገሩ ላይ መጨቃጨቅ አልነበረበትም? ከበር ጀርባ በፈረንጅ አማካሪዎችና በአዋጅ የሚሠራ ነገር የሚበቃን መቼ ነው? መቼ ነው በሃገራችን ላይ ባለቤት የምንሆነው? ዶክተር አቢይ አስቀድመው ቢያማክሩን ምን ነበር የሚጎዳቸው? አንዳንዴ ሳያማክሩን የሚያደርጉት ነገር ሊጎዳን እንደሚችል ከኦነግ የትጥቅ ግርግር እንኳ መማር አልነበረባቸውም?
የኦነግስ ይሁን የውስጥ ጉዳይ ነው፣ ለመሆኑ ከኤርትራ ጋር ያለን ስምምነት ምንድን ነው? መካከለኛው ምሥራቅ ውስጥ ውይይት መጀመሩን ሰምተን ነበር። የአረብ አደራዳሪዎች የሚያውቁት ለእኛ ለባለቤቶቹ ባእድ መሆን ይገባዋል? ሃሳባችንስ መጠየቅ የለበትም? ከጀርባችንና የታሪክ ምሁራኖቻችን፣ የህግ አዋቂዎቻችን፣ የፖለቲካ ሳይንስ ጠበብቶቻችን ሳይሳተፉበት የሚደረግ ውል የአልጀርስ ስምምነት ላይ በባዶ እጅ አስጨብጭቦ እንዳስቀረን የትናንት ትዝታ አይደለምን? አበው ከአንድ ብርቱ ሁለት መድሃኒቱ ያሉት ለዚህ መስሎኝ! አሁንስ ሆድ ሊብሰኝ ነው መሰለኝ ። የሚወዱትን ጠቅላይ ሚኒስትር እንዴት ነው የሚተቹት? ይጨክኑበታል? ወይስ ራርተው ይሸፋፍኑለታል? ለዚህ አበው መልስ አላቸው ፣ “አለባብሰው ቢያርሱ በአረም ይመለሱ” ብለው። ወይስ በአረሙ መመለስ ይሻል ይሆን? የጨነቀ ነገር ነው ይላል የጎንደር ሰው ።
ዶክተር አቢይ የሹመኞቹን የትውልድ ቦታ ሲጠሩ ባዳምጥ ባዳምጥ ከሸዋ ተሿሚ አጣሁ ። መቼም አዲስአበባ ሸዋን አይወክልም ። አዲስአበባ ሸገር ነው፣ ራሱን የቻለ። ባስበው ባስበው የሸዋ መገለል የአቢይ ሳይሆን የአዴፓ/ብአዴን ችግር ነው። የብአዴን ችግር ደግሞ ከወያኔ የሸዋ ጥላቻ የተቀዳ ነው። ህወሓት ብአዴን ላይ የበላይነት በነበረው  ዓመታት የሸዋ ምሁር መመልመል አይችልም ነበር ፣ በተፃፈ ህግ ሳይሆን ባልተፃፈ መግባባት። አሁንም አዴፓ አስቀድሞ ያላዘጋጀውን ከየት ያምጣው? ለሚኒስትር ሹመት የሚበቁ አቅርብ ሲባል እነዚያኑ የጎጃምና ወሎ መንደርተኞቹን ሊስት ነው የሚያቀርበው። ሆኖም ብአዴን ማቅረብ ባይችልም፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ራሰቸው “እስከመቼ ሸዋን አግልለን እንዘልቃለን” ብለው፣ ከብአዴን ውጪም ለቦታው የሚመጥኑ ሰዎችን መሾም ነበረባቸው ። ለወደፊቱ ይማሩበታል ብዬ አስባለሁ ።
በተረፈ፣ በመካከለኛ እርከን ክፍት የሥራ ቦታ በተገኘ ቁጥር በኦሮሞዎች ይሞላሉ የሚለው ቅሬታ እየጨመረ የ26 ዓመት ወጣት ኢንደስትሪያል ፓርኮችን ሁሉ ለሚመራው ተቋም ሲኢኦነት ሲመድቡ ሳይ ተሳቅቄ ስለነበርና፣ “ጊዜው የኛ ነው” የሚለውም የኦሮሞ ብሄርተኞች ተፅእኖ ከፍተኛ መሆኑን ስለማውቅ፣ አዲሱን ካቢኔ ሲያቋቁሙ ወደ ኦሮሞው ያዘነብሉና ከሂሳዊ ደጋፊነት ወደተቃዋሚነት ይገፉን ይሆን የሚል ፍርሃት ነበረኝ ። ያ ፍርሃቴ በመምከኑ ደስ ተሰኝቻለሁ ። ጠቅላይ ሚኒስትራችንንም ማመስገን እወዳለሁ ። የሴቶቹን ሹመት ግን ደግመው ቢያሰላስሉት ደስ ይለኛል። ሌላው ዓለም ትምክህተኛ ሰለሆነ አይመስለኝም እኛ ያደረግነውን ማድረግ ያቀተው ። በአዋጅ ስለማይሠራ ይመስለኛል። ኢትዮጵያችንም ከዝግ በርና ከአዋጅ አሠራር፣ ከፈረንጆችና ከመያዶች ምክር ወጥታ፣ በልጆቿ ሁሉ ፍፁም ባለቤትነት የምትተዳደርበትን ቀን በመመኘት ሂሳዊ ድጋፌን በዚህ ለቋጭ ። በሌላ ሂሳዊ ድጋፍ ትችት እስክንገናኝ፣ መልካሙን እመኝላችኋለሁ!
Filed in: Amharic