>
5:16 pm - Monday May 23, 4591

ዝርዝሩ!!! (በዳንኤል ክብረት)

ዝርዝሩ!!!

በዳንኤል ክብረት

አንድ ሞኝ አሽከር የነበረው ሰው ነበር አሉ፡፡ ይኼ አሽከር አድርግ የተባለውን ካልሆነ በቀር አስቦ፣ አውጥቶ እና አውርዶ፣ ብሎም አመዛዝኖ የሚሠራው ሥራ አልነበረም፡፡ ምን ጊዜም የሚጠብቀው የጌታውን ትእዛዝ ብቻ ነው፡፡

ለእርሱ ትክክል ነገር ማለት ጌታው ያዘዘው ሲሆን፣ ስሕተት ማለት ደግሞ እርሱ ያልነገረው ነገር ማለት ነው፡፡ ዓላማው ጥሩ ነገር መሥራት ወይንም አዲስ ነገር መሥራት ሳይሆን ጌታውን ማስደሰት ብቻ ነበር፡፡

ጌታው ከሳቀ ይስቃል፣ ካለቀሰ ያለቅሳል፣ ከተደሰተ ይደሰታል፣ ካዘነም ያዝናል፡፡ የወደደውን ይወድዳል የጠላው ይጠላል፡፡

ለርሱ የመደሰቱንም ሆነ የማዘኑን፣ የመሳቁንም ሆነ የማልቀሱን ምክንያት ማወቅ አይጠበቅበትም፡፡ ዋናው ነገር ጌታው መሳቁ ወይንም ማልቀሱ ነው፡፡

አንዳንዴ ሰዎች የሳቀበትን ምክንያት ሲጠይቁት «ጌታው ሳቁኮ! አላያችሁም?» ይላል፡፡ በዚህም የተነሣ ሰዎች «እንዳሉት»ብለው ይጠሩት ነበር፡፡
.
አንድ ቀን ጌታው እና እንዳሉት ወደ መንገድ ወጡ፡፡ እርሱ በእግሩ ከኋላ እየተከተለ፤ ጌታው ደግሞ በፈረስ ከፊት እየበረሩ፡፡ መንገድ ላይ ጌታው የገንዘብ ቦርሳቸውን ጣሉት፡፡

እንዳለውም ቦርሳውን አልፎት ሄደ፡፡ጌታው ያሰቡበት ከተማ ገብተው ኪሳቸውን እስኪቀደድ ቢበረብሩ ቦርሳቸውን ሊያገኙት አልቻሉም፡፡

በመጨረሻም ወደ እንዳሉት ተጠጉና «የገንዘብ ቦርሳ አላየህም» አሉት፡፡ እንዳሉት «አይቻለሁ፣ መንገድ ላይ ጥለውታል» አላቸው፡፡

ጌታው ደንግጠው እና ተናድደው «ታድያ ለምን አንሥተህ አልሰጠኸኝም» አሉት፡፡ እንዳሉት ደንግጦ አሰበ፣ አሰበ፣ አሰበ፡፡ ግን የተሰጠው መመርያ አልነበረም፡፡

ተከተለኝ ከማለት በቀር የነገሩት ነገር አልነበረም፡፡ «እንዴ እርስዎ የገንዘብ ቦርሳዬ ሲወድቅ አንሥተህ እንድትሰጠኝ መች አሉኝ» አላቸው፡፡

እርሳቸውም «በል ከዛሬ ጀምሮ እኔ በፈረስ ስሄድ የሚወድቅ ነገር ካየህ ሰብስበህ እንድትሰጠኝ» አሉት፡፡ ከእሺ በቀር ሌላ የማያውቀው እንዳሉት በጸጋ ተቀበለ፡፡
.
በቀጣዩ ጊዜ ጌታውን ተከትሎ መንገድ ጀመረ፡፡ መመርያው በልቡ ነበር፡፡ የሚያሳስበው የተነገረው ነገር ነው፡፡ በልቡ ውስጥም ከተነገረው ነገር በቀር ምንም ሌላ ነገር አልነበረም፡፡

የርሱ ልብ አዲስ ነገር አያመነጭም፤ አዲስ ነገር ማመንጨት የሚችሉት የርሱ ጌታ ብቻ ናቸው፡፡

የርሱ ሥራ ያለ ጥርጥር ሲጠሩት አቤት፣ ሲልኩት ወዴት ማለት ብቻ ነው፡፡ ለምን? ማለት አያውቅም፡፡

ለምን? ማለት ከጀመረማ አሽከር አይሆንማ፡፡ አሽከር ደግሞ ይጠይቃል? የታዘዘው ትእዛዝ ብቻ ነበር ትዝ የሚለው፡፡ «እኔ በፈረስ ስሄድ የሚወድቅ ነገር ካገኘህ ሰብስበህ እንድትሰጠኝ» የሚለው፡፡

ይህ ትእዛዝ ይፈጸም ዘንድ አንዳች ነገር እንዲወድቅ ተመኘ፡፡ ያለበለዚያማ ትእዛዝ ፈጻሚ ላይሆን ነው፡፡ የሚወድቅ ነገር ከሌለማ እርሱ የወደቀን ሰብሳቢ መሆኑ እንዴት ይታወቃል?

ስለዚህ ለመሰብሰብ ሲባል ብቻ መጣል አለበት፡፡ ጥቂት እንደተጓዙ አንዳች ነገር መውደቅ ጀመረ፡፡

እርሱም እያነሣ በቀረጢት ከተተ፡፡ ሲወድቅ ሲያነሣ፣ ሲወድቅ ሲያነሣ፣ ሲወድቅ ሲያነሣ በመጨረሻ ያሰቡበት ቦታ ደረሱ፡፡ ጌታውም «እህሳ፣ ዛሬስ የወደቀ ነገር የለም?» አሉት፡፡ «አለ እንጂ» አላቸው፡፡

ደንግጠው ኪሳቸውን ዳበሱት፡፡ ቦርሳቸው ከነ ገንዘቡ እንዳለ ነው፡፡ «ምንድን ነው የወደቀው?» አሉት ጌታው፡፡ እንዳሉት ግን ቀረጢቱን ይዞ መጣ፡፡ ሲከፍተው የፈረሱ ፋንድያ ነበር፡፡

«ይህንን ምን ሊጠቅምህ ሰበሰብከው?» አሉት ጌታው፡፡ «እኔ በፈረስ ስሄድ የሚወድቅ ነገር ካገኘህ ሰብስብ ብለውኛላ» አላቸው፡፡ እውነቱን ነው፡፡

አሽከር አንድ ነገር ይጠቅማል፣ አይጠቅምም፤ ያስፈልጋል፣ አያስፈልግም ብሎ እንዲወስን ማን ፈቀደለት? አሽከር ማለት የታዘዘውን ብቻ የሚፈጽም ማለት ነው፡፡

አሽከር ከአንገት በታች እንጂ ከአንገት በላይ አለው እንዴ? «በል» አሉት ጌታው፡፡

«ከዛሬ ጀምሮ የምታነሣው ቦርሳዬ፣ ካባዬ፣ ባርኔጣዬ፣ ጅራፌ፣ ገንዘቤ፣ እንዲሁም ከፈረስ ዕቃዬ አንዱ ነገር ከወደቀ ብቻ ነው»፡፡ እንዳሉት በፈገግታ ተቀበለ፡፡ ግን ፈራ፡፡ ይህንን ዝርዝር ቢረሳውስ፡፡

ቁጭ ብሎ በአንድ ወረቀት ላይ ጻፈው፡፡ መጻፍ ብቻ አይደለም እንደ ውዳሴ ማርያም ደጋገመው፡፡
.
ለሦስተኛ ጊዜ መንገድ ተጓዙ፡፡ እንዳሉት እና ጌታው፡፡ በሄደበት መንገድ ሁሉ የሚጓዝበትን አካባቢ፣ ዛፎቹን እና እንስሳቱን፣ መንደሩን እና መስኩን አያይም፡፡

እየደጋገመ የሚያየው ዝርዝሩን ነው፡፡ አንዴ ዝርዝሩን፣ አንዴም መንገዱን ያያል፡፡ ከዝርዝሩ መካከል መሬት የወደቀ እንዳለ ብሎ፡፡ እርሱም ዝርዝሩን እንዳየ ጌታውም እንደሸመጠጡ ያሰቡበት ቦታ ደረሱ፡፡

«እህሳ ዛሬስ የወደቀ ነገር አለ?» አሉት፡፡ «የለም፤ ከዝርዝሩ ውስጥ የወደቀ ነገር የለም» አላቸው፡፡

ለእርሱ ዋናው የሚጠቅም ነገር ወድቋል? የሚለው አይደለም፤ ከዝርዝሩ መካከል፤ ከታዘዘው መካከል ወድቋል ወይ? የሚለው ነው፡፡

ከዝርዝሩ ውጭ ምን ነገር አለ? ማንኛውም ነገር ያለው በዝርዝሩ ውስጥ ብቻ ነው፡፡ ከዝርዝሩ ውጭ ያለ ነገር አንድም እንዳለ አይቆጠርም፤ ያለበለዚያም የማይጠቅም ነገር ነው፡፡ ዋናው ዝርዝሩ ነው፡፡

ለርሱ ዝርዝሩ ቁጥሩ ከወንጌል፣ አንዳንዴም ከወንጌል በላይ ነው፡፡ ደስ አለው፡፡ ከዝርዝሩ መካከል የነጠበ ነገር የለምና፡፡
.
ከብዙ ጊዜ በኋላ እንዳሉት እና ጌታው ለአራተኛው ጉዟቸው ተነሡ፡፡ እርሳቸውም ፈረሳቸውን እርሱም ዝርዝሩን አዘጋጁ፡፡ ሄዱ፡፡ ሸመጠጡ፡፡

እርሳቸው ፊት ፊታቸውን፣ እርሱም ዝርዝሩን እያዩ፡፡ ዋናው ዝርዝሩ ነው፡፡ ሲሄዱ፣ ሲሄዱ፣ ሲሄዱ መንገድ ላይ ፈረሱ አደናቀፈውና ጌታውን ይዟቸው ወደቀ፡፡ ፈረሱም የሲቃ ድምጽ አሰማ፡፡ ጌታውም ጮኹ፡፡

«አንሣኝ አንሣኝ» እያሉ ጮኹ ጌታው፡፡ እንዳሉት ዝቅ ብሎ በእጁ ያለውን ዝርዝር አየ፡፡ ጌታው ሲወድቁ እንዲያነሣ የሚያዝ በዝርዝሩ ውስጥ የለም፡፡ «አላነሣዎትም» አላቸው፡፡

«ለምን ለምን፤ ኧረ ተላላጥኩልህ አንሣኝ» አሉት በልመናም በትእዛዝም፡፡ «የለም ጌታው በዝርዝሩ ውስጥ እርስዎ የሉም» በመካከል ፈረሱ ተነሣ፡፡

ጌታው ግን ሰውነታቸው ተላልጦ እየደማ እዚያው ያቃስቱ ጀመር፡፡ ፈረሱ መንገዱን ይዞ ሸመጠጠ፡፡

ጌታው እጃቸውን እያርገበገቡ «እባክህ ስለ ፈጠረህ አምላክ አንሣኝ» እያሉ እንዳሉትን ለመኑት፡፡

እርሳቸው ያንን ዝርዘር ሲሰጡት ቃላቸውን ለማስጠበቅ እና ከቃላቸው እንዳ ይወጣ እንጂ እርሳቸው ሊወድቁ እንደሚችሉ መች ገመቱ፡፡ ደግሞስ ጌታ እወድቃለሁ ብሎ እንዴት ይገምታል፡፡

አሁንም እጃቸውን እያርገበገቡ ለመኑት «አንሣኝ አንሣኝ እባክህ» እንዳሉት ግን ፈረሱን ተከትሎ አሁንም ዝርዝሩን እያየ ትቷቸው ሮጠ፡፡

ብቻውን «እንዴ እዚህ ዝርዝር ውስጥ የሌሉትን እንዴት ብዬ ላንሣቸው፡፡ በኋላ ደግሞ ከዝርዝሩ ውጭ አነሣህ ብለው ራሳቸው ቢቆጡኝስ፡፡

እኔ ካዘዙኝ ውጭ ሠርቼ ዐውቃለሁ? አሁን ማንን ክፉ ለማድረግ ነው» እያለ ያጉረመርም ነበር፡፡

*እንደዚህ አሽከር የተሰጠንን ትዕዛዝ ከመፈጸማችን በፊት ለምን? እንዴት? ብለን እንጠይቅ።
*ሁልጊዜም ስንራመድ በማስተዋል ቢሆን ለእኛ መልካም ነው!

Filed in: Amharic